ፓን አፍሪካኒዝም መላውን የዓለም ጥቁር ሕዝብ እንደአንድ አፍሪካዊ ቤተሰብ የሚመለከት አስተሳሰብ ወይም ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው በዋነኝነት የቅኝ ግዛት መስፋፋትንና የነጭ የበላይነትን ለመዋጋት፤ አፍሪካዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለመ ነበር። ፓን አፍሪካኒዝም በፖለቲካ፣ በሥነጽሑፍና ሥነጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በባሕል እና በመሳሰሉት ዘርፎች የተቃኘ ሰፊ ንቅናቄ ነበር።
ይህ ንቅናቄ መሠረቱን በሀገረ አሜሪካ ያድርግ እንጂ የንቅናቄው መንፈስ እና ብርታት ኢትዮጵያ ነበረች። በዚህም ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኃይልና ኩራት ተደርጋ ትወሰዳለች። የእዚህ አስተሳሰብ እና እምነት ገፊ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ በማንኛውም ቅኝ ገዢ ኃይል ያልተንበረከከች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ነው።
ወጣት ስንታየሁ ተፈሪ ይባላል። የሥነጥበብ ባለሙያ እና ፓን አፍሪካኒስት አርቲስት ነው። ወጣት ስንታየሁ ወደ ስዕል ሥራ እንዴት እንደገባ ሲናገር፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ለሥነጥበበዊ ሥራዎች በጣም ልዩ ፍላጎት ነበረው። የወዳደቁ ዕቃዎችን መጠጋገን እንደሚወድ በተረት መጽሐፍ ላይ ተረቶችን ካነበበ በኋላ ስዕሎችን በማየት መልሶ በመሳል፣ በትምህርት ቤትም የሚሰጡ የስዕል ሥራዎች በመሥራት፣ በበዓላት ደግሞ አበባ እና መሰል ስዕሎችን ይሠራ እንደነበረ ይናገራል።
የገና በዓል በሚከበርበት ወቅት በተለያዩ ካርዶች ላይ የተሳሉ ስዕሎችን እንደሚመለከት የሚናገረው ወጣቱ፤ ለብዙ የሥነጥበብ ሰዎች አርዓያ ተደርጎ የሚወሰደውን የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን ሥራዎች በፖስት ካርድ መልክ ኮፒ አድርጎ ይሸጥ እንደነበረ ይገልፃል። ‹‹ የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎችን መልዓክ እንጂ ሰው የሠራቸው አይመስሉኝም ነበር። በዚህ ደረጃም ሰዓሊ መሆን እንደሚቻል አላውቅም ነበር።›› ብሎ የልጅነት ጊዜውን ወደኋላ ተመልሶ ያስታውሳል።
በተጨማሪ የተለያዩ ፈጠራዎችን በመጠቀም ቤቶችን የማስዋብ ሥራ ይሠራ እንደነበረ እና ከስዕሉ በዘለለ ግጥም፣ ሙዚቃ እና ትያትር ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ በተለየ ይስቡት እንደነበር ይገልፃል። እነርሱን በመሞከር ሙያዊ ወደ ሆነ የሥነጥበብ መስመር ውስጥ ለመግባት መቻሉን እና በዚህ ሂደት ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ የተለያዩ ሥራዎችን ስለመሥራቱ እና በልጅነት የሠራቸው ሥራዎች ለዛሬ ሙያው በር እንደከፈቱለት ያስረዳል።
ከአቻ ጓደኞቹ በተለየ ለፎቶ ግራፍ፣ ለስዕል ልዩ ፍቅር እንደነበረው የሚናገረው ወጣት ስንታየሁ፤ ከምንም በላይ ደግሞ ለ (storytelling) አንድን ነገር በስዕል መንገር ቀልቡን ይገዛው እንደነበረም ይናገራል። የስዕል ባለሙያ ሆኖ ለመቀጠል ሲያስብ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጅ ሁሉ በጣም የበዙ የተለያዩ ጫናዎች ይኖራሉ የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ ምንም አይነት መሰናክል ቢኖር ለዓላማው ያለው ፅናት ከፍ ያለ ከሆነ ማንም ወደሚፈለገው ለመድረስ እንደሚችል እና እርሱም ላጋጠሙት ተግዳሮቶች እጅ ሳይሰጥ ዛሬ ላይ ስለመድረሱ ይናገራል።
ሙያውን ለማሳደግ በሚፈልግበት ጊዜ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የሥነጥበብ ትምህርት ቤት አንድ ብቻ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያለው የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ነው። ይህም እንዳለም መገንዘብ የቻለው ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደሆነ ይገልፃል። ወደ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ለመግባት ደግሞ እራሱን የቻለ ውጣ ውረድ አለው የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ ቤተሰብ ውጤት እስከሚያይ ድረስ ይህ የስዕል ሥራ የሙያ መንገድ ነው ብሎ ለመቀበል የሚከብደው ቢሆንም ግን በጥንካሬ በመጓዝ ፈተናዎችን ወደ ጎን በመተው ያመነበትን በመሥራት በመልካም ሥነምግባር እና በፅናት እያንዳንዱን በፕሮጀክት በመያዝ ኤግዚቢሽኖች ማቅረብ ሲጀምር ተቀባይነቱ እየጨመረ እንደሄደ ይናገራል።
በመጀመሪያ አካባቢ ባሉ ደረጃዎች ላይ ከፍተኛ ፈተና አለው የሚለው ወጣቱ፤ የሥነጥበብ (ስዕል) ሀገርን የሚያሳድግ የሥራ ዕድል የሚከፍት እንደሆነ ብዙ ሰው አይረዳውም፤ እንደ ሀገርም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። የግለሰቡ ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ ማኅበረሰብ እና መንግሥት የራሳቸውን ኃላፊነት በተለያየ መልኩ መወጣት አለባቸው ይላል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በውድድር ተቀላቅሎ በሥነጥበብ የመጀመሪያ ዲግሪ ማግኘት ችሏል። ስዕል እና ማኅበረሰብ በእጅጉ ቁርኝት ስላለው ማኅበረሰቡን ለመረዳት እንደሚያግዘው በማመን ከቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርስቲ በሶሾሎጂ በዲግሪ ተመርቋል። ከሥነጥበብ የመጀመሪያ ዲግሪው በኋላ ወዲያውኑ ትምህርቱን በመቀጠል በአፍሪካ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪውን ማግኘት ችሏል።
ወጣት ስንታየሁ የስዕል ሥራዎቹን በአፍሪካ ኅብረት፣ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በጣሊያን ባሕል ኢንስቲትዩት፣ በእንጦጦ ሙዚየም፣ በአሌ የሥነጥበብ እና ዲዛይን፣ በቪላ ቬርዴ አዲስ አበባ፣ በአቶሞስፌር አርት ጋለሪ፣ በፈንዲቃ የባሕል ማዕከል፣ በሒልተን ሆቴል እና በሌሎችም ቦታዎች አዲስ አበባ ላይ በግሉና ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በመሆን የስዕል ሥራውን ማቅረብ ችሏል።
ወጣቱ እንደሚገልፀው፤ ፓን አፍሪካኒዝም ሁሉም አፍሪካውያን ለማንነታቸው ላላቸው ባሕል እና ቀደም ብሎ የነበራቸውን ሥልጣኔ እና ያላቸውን የማንነት መገለጫ በመጠቀም፤ የቅኝ ግዛት ደባዎችን በመቃወም፤ አፍሪካውያን ድር ቢያብር አንበሳን ያስር እንደሚባለው ሁሉም ወደ አንድ አቅጣጫ በመምጣት የተባበረች አፍሪካን የመፍጠር ትልምን የያዘ ነው።
ይህ ሰፊ ሀሳብ ወደ ሥነጥበብ ሲመጣ ደግሞ ከቀለማት ጀምሮ ፓን አፍሪካኒዝም የእራስ ባሕልን መጠቀም፣ በእራስ ባሕል መመካት እና በእራስ ማንነት መገለጥን ያበረታታል ይላል። የፓን አፍሪካ ሥነጥበብ በአፍሪካ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉትን ነገሮች በጥበብ ሲገልፅ፤ ‹‹አንድ ከሆንን ጠንካራ እንሆናለን፤ ከተከፋፈልን ደግሞ እንወድቃለን›› ይባላልና አንድነት የሁሉም ነገር መሠረት ስለሆነ ይህንን የሚያንፀባርቁ የስዕል ሥራዎች ላይ እንደሚያተኩር ይናገራል።
በቀለም ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ የነፃነት ፋና ወጊ ናት የሚለው ወጣቱ፤ በርካታ ሀገሮች ከባንዲራ ጀምሮ የሚጠቀሙት ከኢትዮጵያ ቀለማት ነው። ይህ እንደመነሻ የሚወሰድ ነው። በዚህ ስለ አንድነት አስፈላጊነት መስበክ ይቻላል፤ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ችግሮች ረሀብ፣ ድህነትና መጎሳቆል፣ ውጣውረድ በስዕሎቹ እንደሚያንፀባርቅ ይገልፃል።
የኢትዮጵያውያን የሥነጥበብ ሰዎች ለአፍሪካዊነት ያበረከቱትን አስተዋፅዖን አስመልክቶ ሲናገር፣ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ላይ የአፍሪካን አንድነት የሚገለፅ ሥራ ከጨለማ ወደ ብርሃን በሚል የሠሩት ትልቅ ሥራ አለ። በተጨማሪም እስክንድር ቦጎስያን የሚባሉ ኢትዮጵያዊ አርቲስት አሜሪካን ሀገር የአፍሪካን ማንነት እውነት በሥነጥበብ ያንፀባረቁ ሰው ናቸው፤ ሌሎችም አፍሪካዊነትን ያቀነቀኑ ሰዎች እንዳሉ ይናገራል። እነርሱም የፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤዎችን በስዕሎቻቸው እንደሚያንፀባርቅ ይገልፃል።
የአፍሪካዊነትን የውበት ሀሳቦችን በማንገብ የአፍሪካዊነትን ጭብጥ መነሻ አድርጌ እሠራለሁ የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ አፍሪካ ውስጥ ዕለት ከዕለት ስለሚከናወኑ የማኅበረሰብ አኗኗር ባህል ሙዚቃ፣ ትያትር፣ ወግ ላይ በመንተራስ የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን አከናውናለሁ ይላል።
አፍሪካ ውስጥ ያሉ ዕውቀቶችን ማውጣት እና አፍሪካዊነትን የሚሸቱ ነገሮችን መግለጽ መቻል በራሱ ፓን አፍሪካኒዝም ነው የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ በሥነጥበብ ደግሞ የተሻለ ማንነትን ለመናገር ምቹ ስለሆነ፤ ሀሳብን ለመግለጽ የሚመረጥ መንገድ ነው ይላል። ከአንድ ሺህ ቃል አንድ ስዕል እንደሚባለው ስዕል ከቃላት በላይ መልዕክት ለማስተላለፍ ጉልበት እንዳለው የሚናገረው ወጣት ስንታየሁ፤ በጥበብ ሥራዎች በአፍሪካውያን መካከል አንድነትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይገልፃል።
አፍሪካ መድብለ ባሕላዊነት የሚንሸራሸርባት ምድር ነች የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ አፍሪካ ጥንታዊ ባሕላዊ እሴቶች እና ልዩ የሆነ ማኅበራዊ መዋቅር ያላት አህጉር በመሆኗ፤ በዚህ ረገድ ለዓለም የምታቀርበው ብዙ ነገር ያላት ቢሆንም፤ ነገር ግን አሁንም በአካባቢው ክፍተት እንዳለ ይናገራል። አፍሪካ ለታሪኳ እና ለሀገር በቀል እውቀቷ ዋጋ መስጠት አለባት የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ የአፍሪካ ወጣቶችን በእውነተኛ ማንነት ማሳደግ፤ የሁሉም ምሑር ኃላፊነት ነው። ካልሆነ አዲሱ ትውልድ ለሌሎች የባሕል ባሪያ የመሆን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ይናገራል።
የአፍሪካ አንድነትን በሚመለከት የሚናገረው ወጣት ስንታየሁ “አፍሪካ ልዩ ልዩ የሆኑ ባሕላዊ እሴቶች ያላት ትልቅ አህጉር ነች። የተለያዩ የአልባሳት ዓይነቶች፣ የፀጉር አበጣጠር፣ ጥበቦች እና ዕደ ጥበባት፣ ሙዚቃዎች እና የክብረ በዓሎች እና መሰል ሀብቶች የአፍሪካውያንን ልዩነት የሚያሳዩ እና ማንነታቸውን እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ ወይም እንደ ሀገር የሚያንፀባርቁ ናቸው። በዚህ ውስጥ ልዩነት ቢኖርም፤ በአፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነት አለ። የአፍሪካውያን የተባበሩ እጆች እና በውስጣቸው ድንበር ተሻጋሪ የባሕል ልውውጥ አህጉሪቱን በአንድነት ያቆያታል። አንዱ በሌለበት ሌላው ሊኖር አይችልም። ማንኛውም የአፍሪካ ሀገር የጎረቤቱ ጠባቂ መሆን እንዳለበት እና የሌላውን ባሕል ማክበር እንደሚገባው ይገልፃል።
አርቲስት ስንታየሁ ‘ፋኖሱ እና ብርጭቆው’ በሚል ርዕስ ስላከናወነው አንድ የፈጠራ ጥበብ ሥራ (ስዕል) ሲናገር፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የአብሮነት አስፈላጊነት ፋኖስና ብርጭቆን በመወከል ለማሳየት እንደሞከረ እና የሁለቱም (መብራቱና መስታወቱ) በሰላም አብሮ መኖር አማራጭ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ አንዱ ለሌለው ሕልውና አስፈላጊ መሆኑን የገለፅበት መሆኑን ይናገራል።
እንደወጣቱ ገለፃ፤ በአህጉሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት የሀገሪቱን ሃብትና የልጆቿን ሕይወት ዋጋ እያስከፈለ ነው። ጠንካራ ወንድማማችነት ግንኙነትን መፍጠር እና የፓን አፍሪካኒዝምን መንፈስ ማሳደግ የአፍሪካን አንድነት ያረጋግጣል። ለዚህም የሥነጥበብ የራሱን ሚና መወጣት ይኖርበታል። የስዕል ሙያ ያለው ሰው በፋሽን ዲዛይን በቤት ውስጥ ውበት፣ በፊልም ፕሮዳክሽን ላይ አሻራውን ማኖር ይችላል የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በገቢ ደረጃም የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እየተሻሻለ መጥቷል፤ ጥሩ ሥራዎች ከተሠሩ ሰዎች የስዕል ሥራዎችን የመጎብኘት፣ የመግዛት ልምድ እያዳበሩ ነው።
‹‹በስዕል ብቻ ደግሞ እራሴን አልገድብም›› የሚለው ወጣት ስንታየሁ፤ ከስዕሉ በተጨማሪ ፎቶግራፈር እንደሆነ እና የተለያዩ ዲዛይኖችን በመውጣት ቦርሳዎችን እንደሚሠራ እንዲሁም የቤት ውስጥ ዲዛይን በመሥራት እራሱን በገቢ እንደሚደግፍ ይገልፃል። ዘመኑ ሁሉንም ነገር በቀላሉ በእጅ ማግኘት የሚቻልበት የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ተሰጥዖ እና ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች የግድ ትምህርት ቤት ሄደው መማር ሳይጠበቅባቸው የፈለጉትን የሥነጥበብ አይነት ማወቅ እና ማየት ይችላሉ።
በዚህም ጥበቡን በእርሳቸው መንገድ በመቀየር ተሰጥዖዋቸውን ወደፊት ማምጣት እና ማሳደግ እንደሚችሉ ሰፊ ዕድል መኖሩን የሚጠቁመው ወጣት ስንታየሁ፤ ሕይወት ፈተናዋ ብዙ ቢሆንም ዓላማ እስካለ ድረስ ወጣቶች ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል እንዳለባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም