ቤዛ ለሴቶችከኢትዮጵያውያን ጎን የመቆም ትልም

 የተቸገረን በመደገፍ፣ የወደቀን በማቅናትና በደግነት ምግባራቸው የሚታወቁ ሰዎች አንድ አባባል አላቸው “በጎነት መልሶ ይከፍላል” የሚል። ደግ መዋል በክፉ ቀን ለተደረሰለት ሰው ብቻ ሳይሆን ውለታ ለዋለው “አለሁ ባይ” በራሱ የሕሊና እርካታን የሚሰጥ እና ሌሎች አያሌ በረከቶች እንዳሉትም ጭምር ይታመናል።

ለዚህም ነው ከራሳችን የግል ጩኸትና ውጣ ውረድ አልፈን ከወደቁበት መነሳት ላቃታቸው፣ በተተበተበ ችግር ውስጥ ሆነው መውጫው ለጠፋቸው፣ በማኅበረሰቡ አመለካከት ምክንያት ወደ ዳር ተገፍተው ኑሮ እንደ ቋጥኝ ለከበዳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ድምፅ መሆን እና የችግራቸውን መውጫ መሰላል ለማበጀት መትጋት የሚጠበቅብን።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ልቦናዊ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአቅማቸውን በማድረግ፣ ከራሳቸው አልፈው ብዙኃንን በማስተባበር ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦች በርካታ ናቸው። ከግል ጥረታቸው ባለፈም አጀንዳ በመቅረፅ፣ በቡድን፣ በማኅበር፣ በግብረ ሠናይ ድርጅት እና በሌሎችም መሰል አደረጃጀቶች ተሰባስበው አቅም በመፍጠር የመፍትሔ አካል ለመሆን ይሞክራሉ።

በኢትዮጵያ መሰል ድጋፍ ከሚሹ እና ልዩ ትኩረትን ከሚፈልጉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ቀዳሚ ናቸው። ከላይ በስፋት እንደጠቀስነው ይህንን ጉዳይ አጢነው በሴቶች ላይ የሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃትና ማኅበራዊ ጫናዎች እንዲሻሻሉ የሚሠሩ ቡድኖችና ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በርካቶች ናቸው። የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው ሀገርኛ አምድ ላይ የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች የሚደርስባቸውን ችግሮች ተገንዝበው በጎ ምግባር ላይ ከተሰማሩ ሀገር በቀል ግብረ ሠናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን “ቤዛ ለሴቶች የማኅበረሰብ አቀፍ የልማት ድርጅትን” የዓመታት ተሞክሮ ከዚህ እንደሚከተለው ለመዳሰስ ወድደናል።

ሀኒያ መሐመድ ትባላለች። መቀመጫውን በደሴ ከተማ ወሎ ባሕል አምባ ግቢ ያደረገው የቤዛ ለሴቶች የማኅበረሰብ አቀፍ የልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ነች። በሴቶች ባሕላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ለመቀነስ ግብ ይዞ የተነሳው ሀገር በቀል ድርጅት የዛሬ 20 ዓመት በ25 ሴቶች በጎ ፍቃድ “በሴቶች ክበብ” እንደተቋቋመ ትናገራለች።

በወቅቱ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን፣ ፆታን መሠረት አድርጎ የሚሰነዘር ጥቃትን፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር ተያይዞ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስና ለመከላከል በማሰብ ክበቡን እንዳቋቋሙት ትገልፃለች። በጊዜው እነርሱ ይኖሩበት በነበረው ደሴ ከተማ እና በዙሪያው መሰል በሴቶች ላይ የሚደርስ ጫና መኖሩን ገልፃ፤ ያንን ችግር ለመጋፈጥ በማሰብና የችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ለመደገፍ በሚል እሳቤ ወደ ምሥረታውና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደገቡ ትናገራለች።

“ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ለሴቶች የሚሠራ ክበብ መሥርተን ወደ ሥራ ስንገባ የነበረው ፈተና እጅግ በጣም ከባድ ነበር” የምትለው ዳይሬክተሯ፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረውን የአመለካከት ክፍተት፣ ለሴቶች ያለውን ግንዛቤ እና ውጣ ውረድን ለማለፍ ተቸግረው እንደነበር ታነሳለች። በተለይ ሥራቸውን ዝቅ የሚያደርግና ሞራላቸውን የሚገድል አስተያየቶች ይደርሳቸው እንደነበር ታስታውሳለች።

ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ ጋሬጣዎች ተጋፍጠው ሴቶች ላይ ስለሚደርስ አስገድዶ መድፈር፣ ግርዛትን ጨምሮ ስለሚከሰት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት፣ በሴቶች ላይ ስለሚደርስ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን የተመለከቱ ግንዛቤን የሚፈጥሩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን በድራማና በልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎች በማቅረብ ማስተማር ጀመሩ። ይህ ተግባራቸው ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክል የራሱን አሻራ ከመጣል ባለፈ ሴቶች በራሳቸው የሚደርስባቸውን ጫና እንዲቋቋሙ የሚያስችል ሥነ ልቦናን ይፈጥርላቸው እንደነበር ትገልፃለች።

“የቆምንለት ዓላማ መሳካትና ተስፋ ሰጪ ድጋፍ ማግኘት የጀመርነው ማኅበረሰቡ የእኛን ጥንካሬና ብርታት ማየት ከጀመረ ወዲህ ነው” የምትለው የቤዛ ለሴቶች ዳይሬክተር ሀኒያ፤ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ማግኘት ሲጀምሩ የአማራ ክልል መንግሥት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትኩረት እየሰጧቸው እንደመጡ ትገልፃለች። በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚያነሱት አጀንዳዎች እንዲሳኩ የፋይናንስና የሞራል ማበረታቻ እያገኙ መምጣታቸውን ትገልፃለች። ይህንን አቅም በመጠቀም ሴቶች የሚደርሱባቸውን ጫናዎች ለመቀነስ ልዩ ልዩ ዘዴዎችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ስኬት ማስመዝገብ እንደጀመሩ ትናገራለች።

በደሴ ከተማና ዙሪያ ቤዛ ለሴቶች ክበብ ሥራውን ሲጀምር ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ፣ ግርዛትና ሌሎችም በሴቶች ላይ ጫና የሚፈጥሩ ልማዶች እንደነበሩ የምትናገረው ዳይሬክተሯ፤ ይህንን ለመስበር የጉዳቱ ተጋላጭ የሆኑ ሴት ወገኖቻቸውን ከችግሩ እንዲላቀቁ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ ሕክምናና ወሳኝ መረጃዎችን በመስጠት ለወገኖቻቸው መድረስ እንደጀመሩ ትገልፃለች። በተለይ የሴቶች ግርዛትን በሚያበረታቱና ድርጊቱን እንደ ገቢ ምንጭ ያደረጉ አካላትን በማስተማር፣ እንዲሁም አማራጭ የሥራ እድልና የገቢ ምንጭ በመፍጠር ረገድ የተሳካ ሥራ መሥራታቸውን ታስረዳለች። ይህ ጥረታቸው ለሴቶች ያለው አመለካከትና የሚደርስባቸውን ጫና ከመረዳትም ባሻገር “ሴቶች እድልና ድጋፍ ከተደረገላቸው መሥራት እንደሚችሉ” እያስገነዘበ መምጣቱ ትገልፃለች።

ቤዛ ለሴቶች ክበብ ለዓመታት በሠራቸው ተግባራት ተቀባይነት እያገኘና ለማኅበረሰቡ እሴት እየሆነ መጣ። ለ12 ዓመታት በዚህ አደረጃጀት ከቆየ በኋላ ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ሴቶች የሚደርስባቸውን ማኅበራዊ ጫናዎች ለመቀነስ በሚል ተደራሽነቱን ማስፋቱ ተገቢ እንደሆነ አምኖ ወደ ማኅበረሰብ አቀፍ ልማት ድርጅትነት ማደጉን ዳይሬክተሯ ሀኒያ ትገልፃለች። ከደሴ ከተማ የጀመረው ይህ ድርጅት በአራት ክልሎችና በከተማ አስተዳደር (አማራ፣አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና አዲስ አበባን) ላይ ለመሥራት ዓላማና ግባችን አስፍቶ ሥራ መጀመሩን ትናገራለች።

“ከደሴ ተነስተን ክልሎችን ከማዳረስ ባሻገር ሴቶችና ሰላምን በተመለከተ የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና በመወከል እየሠራን ነው” የምትለው ዳይሬክተሯ፤ በዚህ ተግባራቸው ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው የሥራ ፈጠራና የንግድ ባለቤት እንዲሆኑ፣ በገጠራማ አካባቢዎች ጫና የሚቀንስላቸው የውሃ ፕሮጀክቶች፣ የጤና ጣቢያ፣ የሥልጠና አገልግሎት እና ሌሎችም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆኑን ታነሳለች።

በሀገር በቀል ግብረ ሠናይ ድርጅትነት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በመሥራት ውጤታማ እንደሆኑ ነው የምትናገረው። በተለይ ግንዛቤ ከመፍጠር የዘለለ ተግባር ላይ መሰማራት የጀመሩት ግብረ ሠናይ ድርጅት ከሆኑ ወዲህ መሆኑን ገልፃ፤ ከዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪዎች ጋር በመቀናጀት ፍቺ የፈፀሙ፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸውና ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ ያልቻሉ እናቶችን መደገፍና የትምህርት ቤት ግንባታን በማከናወን እድል እንዲያገኙ ማድረግ እንደቻሉ ትገልፃለች። በዚህ ሳይገደቡ ሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ በቀላሉ እንዲያገኙ፣ ወጣት ሴቶች የነፃ የትምህርት እድል (ስኮላር) እድል እያመቻቸ እንደሚገኝ ገልፃለች።

“አሁን ከኢትዮጵያ አልፈን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን እያገኘንና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ችግሮችን የሚቀንሱ ፕሮጀክቶች ላይ ሀገር ወክለን እየሠራን ነው” የምትለው ዳይሬክተሯ፤ በዲጂታል ፕላት ፎርም ጭምር ሴቶችና ወጣቶች ስለ ሥርዓተ ፆታና መሰል ጉዳዮች መረጃና ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮጀክቶችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽኖች ጋር በቅንጅት እያመቻቹ መሆኑን ታስረዳለች። እንደ ሀገር ፍላጎቱ ብዙ በመሆኑና ከዓላማቸው አንፃር በርካታ ተግባራት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም እቅድና ፍላጎታቸውን እያሳኩ እንደሚገኙ ትናገራለች።

በደሴ የጀመረው በጎ ምግባር ሰፍቶና አድጎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች ሕይወት ላይ ተፅዕኖ ያሳረፈ ውጤታማ ተግባር ማከናወናቸውን የምትናገረው የቤዛ ለሴቶች ማኅበረሰብ አቀፍ የልማት ድርጅት ዳይሬክተር ሀኒያ፤ በውሃ ግንባታ፣ በግንዛቤ፣ በልጅገረዶች ትምህርት ጎጂ ልማድ በማስቀረትና የሥራ እድል በመፍጠር ስኬታማ አፈፃፀም ማሳየት እንደቻሉ ታስረዳለች። በደብረብርሃን፣ ደሴ እና ወልዲያ “መላ ኔትን” የተሰኘውን በሬዲዮ የሚሰጥ ትምህርትን በመጠቀም በመገናኛ ብዙኃን ስለ ሥርዓተ ፆታ፣ የሴቶች ጫናን ከመቀነስና ማኅበራዊ እረፍት እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር ግንዛቤ የሚፈጥሩ ዝግጅቶችን እያሰናዱ እንደሚያቀርብ ያስረዳሉ።

“በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እናትና ልጅ ተደፍረው ድርጅታችን አግኝቷቸው ነበር” የምትለው ሀኒያ፤ በተለይ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልጅ ትምህርቷን መቀጠል ተቸግራ እንደነበር ትናገራለች። ይህንን ከባድ ስነልቦናዊ ቀውስ መሰል ጉዳት ከደረሰባቸው ታዳጊዎች ጋር በባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ወደ ቀድሞው በራስ መተማመኗ እንድትመለስ ትምህርቷን እንድትቀጥልና ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም እንዳደረጉ በምሳሌነት ታነሳለች።

ይህን መሰል ጉዳት ደርሶባቸው ከማኅበረሰቡ የተገለሉና መፍትሔ ያጡ ወጣት ሴቶች፣ እናቶችን በባለሙያዎች የመደገፍና የሚያግዛቸውና የሚረዳቸው ወገን እንዳለ እንዲገነዘቡ ማድረግ የድርጅታቸው ተቀዳሚ ሥራ መሆኑንም አስረድታለች። በተለይ ሴቶች እራሳቸውን እንዲችሉ ሥራ እድል ማመቻቸትና ገንዘብ መስጠት አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ግን ከሥነ ልቦናዊ ጫና እንዲላቀቁ ማድረግ እንደሆነ አንስታ፤ በዚሀ ዙሪያ ልዩ ትኩረት አድርጎ ድርጅታቸው እንደሚሠራ ነው የገለፀችው። ይህንን ለማሳካትም ከበጎ ፍቃደኞችና የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በማመቻቸት እንደሚሠሩ ተናግራለች።

በሴቶች ዙሪያ በርካታ ድጋፎችን በማድረግ ራዕያቸውን ለማሳካት እየሠሩ መሆኑን የምትናገረው ሀኒያ፤ እነርሱ ብቻቸውን ግን ሁሉንም መሸፈን እንደማይችሉ ትገልፃለች። በተለይ ፍላጎቱ ከመብዛቱና ያላቸው አቅም ውስን ከመሆኑ አኳያ የኢትዮጵያ ሴቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊና መሰል ጫናዎችን በሚፈለገው ልክ ለመቀነስ እክል እየሆነባቸው እንዳለ ታስረዳለች።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እያጋጠማት ካለው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ችግሮች አንፃር “በምን መልኩ መደጋገፍና ከፈተናዎቹ በጋራ መውጣት ይቻላል?” የሚለው ጉዳይ ጋር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መፍትሔ ጠቋሚ ሀሳቦች ላይ እየተመካከሩ እንደሆነ ታነሳለች። እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ግን ድርጅታቸው የበለጠ ለመፍትሔው እንዲተጋና ውጤት እንዲያስመዘግብ እያደረገው መሆኑን ነው አልሸሸገችም።

“ሴት ሆኖ ሴቶችን ለማንቃትና ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት በሚደረገው ሂደት ላይ ጎታች የሆኑ አካላት በስፋት አሉ” የምትለው ዳይሬክተሯ፤ እነርሱ ግን ሴቶች እኩል እድል፣ ድጋፍና ማበረታቻ ማግኘት ይገባቸዋል የሚል ቁርጠኛ አቋም ይዘው ለራዕያቸው መሳካት እየተጉ መሆኑን አንስታለች። ይህንን ግብ ለመምታት እንዲችሉ ግን የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ትገልፃለች።

ግብረ ሠናይ ድርጅቶች መንግሥት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ክፍተቶቹን ለመድፈንና ከማኅበረሰቡ ጎን ለመቆም እየሠሩ በመሆኑ የመንግሥት ተቋማትም ይህንኑ ዓላማ መደገፍና በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብላለች። ከዚሁ ጎን ለጎን መገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ በመፍጠር እና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ረገድ ያላቸውን ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ተጠቅመው ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርባለች።

 ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *