የትኛውም ማህበረሰብ ነገዎቹን ብሩህ አድርጎ ለማሰብ ሆነ ተስፋ ያደረጋቸውን ነገዎች እውን ሆነው ለማየት፤ ከሁሉም በላይ ሰላም ሊኖረው ይገባል። ለሰላም ደግሞ፤ ለሰላም የተገዛ የአስተሳሰብ መሰረት መገንባት፤ በመሰረቱ ላይ የሰላም ጡቦችን /እሴቶችን/ መደርደር ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ በነገዎች ላይ ተስፈኛ ሆኖ ለመቆመ አይቻልም፤ እንደሚቻል ማሰብም ጥፋቱ የከፋ እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ አይደለም።
ለዚህ ደግሞ የራሳችንን የትናንት የጦርነት እና የግጭት ታሪኮች ወደኋላ መለስ ብሎ ማየቱ በራሱ በቂ እና ከበቂ በላይ ትምህርት ነው። እንደ አንድ ትልቅ ማህበረሰብ ትናንት ከነበርንበት ትልቅነት ወርደን አሁን ወዳለንበት ሁኔታ የደረስነው በአንድም ይሁን በሌላ ለሰላማችን የነበረን አመለካከት የተዛባ ስለነበር ነው። በተለያዩ ወቅቶች በእጃችን የገቡ ሰላምና የሰላም አማራጮችን መጠበቅ የሚያስችል ዝግጁነት በማጣታችን ነው።
በርግጥ ህዝባችን ሰላምን የሚሸከሙና የሚያጸኑ ሰፊ ማህበራዊ እሴቶች ባለቤት ነው። ተናግረው የሚሰሙ የሀገር ሽማግሌዎች ያሉበት፤ ገዝተውና ገስፀው የጥፋት ጉዞዎችን ማቋረጥና ማስቆም የሚችሉ ካህናትና ቀሳውስቶች፤ ሼሆችና ኡስታዞች ያሉባት ሀገር ነች። ወቅታዊ ችግሮችን ለዘለቄታው በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ ብዙ ሀገር በቀል እውቀትና ጥበቦች ባለቤት የሆነ ነው።
እንደ ህዝብ ነገዎችን ተስፋ በማድረግ ለረጅም ዘመናት ዋጋ ሲከፍል የኖረና በከፈለው ዋጋ መጠን ተስፋ ያደረጋቸውን ነገዎች የራሱ ማድረግና ማጣጣም ያልቻለ ነው። ዛሬም ቢሆን ነገዎቹን ለራሱና ለመጪው ትውልድ የተሻለ ለማድረግ ብዙ ዋጋ እየከፈለ ያለ፤ እየከፈለ ካለውም በላይ ለመክፈል ሁለንተናዊ ዝግጁነት የፈጠረ ነው።
በየወቅቱ ከሰላም እጦት ጋር ከከፈለው እና እየከፈለው ካለው ያልተገባ ዋጋ አንጻር፤ ለሰላም ከፍ ያለ ቀናኢነት ያለው፤ ይህንንም ግጭቶችንና ጦርነቶች በማውገዝ በየወቅቱ ሲገልጽ የቆየ ነው። ይህንንም በተለይ የለውጥ ኃይሉ የሽግግር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የቀደሙ ችግሮችን በይቅርታ/በሰላም ለማለፍ የደረሰበትን ውሳኔ አደባባይ በመውጣት በከፍተኛ ደስታ መቀበሉ የዚህ እውነታ አንዱ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ይህም ሆኖ ግን ከህዝቡ የመሆን መሻት ተስፋ የተወለደን የሰላም ሀዋሪያነት የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች በየዘመኑ ተፈጥረው፤ ህዝቡን እንደ ህዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል። የቀደሙት ታሪኮቻችን ተናግረው የሚሰሙ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ገዝተውና ገስፀው የጥፋት ጉዞዎችን ማስቆም የሚችሉ ካህናትና ቀሳውስቶች፤ ሼሆችና ኡስታዞች ባሉበት የጦርነትና የግጭት ለመሆን ተገድደዋል።
ዛሬም ቢሆን እነዚህ የህዝባችንን የሰላም መሻቶች የሚገዳደሩ ተግዳሮቶች፤ ሀገርን እንደ ሀገር ፈተና ውስጥ ሲከቱ ማየት የእለት ተእለት ሕይወታችን አካል ከሆነ ውሎ አድሯል። ችግሩ ሀገርና ህዝብን እያስከፈለ ያለው ዋጋም ከፍያለ ስለመሆኑ ነጋሪ የሚፈልግ ጉዳይ አይደለም። ሀገርን እንደሀገር የህልውና አደጋ ውስጥ ከትቶ እንደነበርም አይረሳም።
ከዚህ ሀገራዊ የግጭት አዙሪት ወጥቶ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችም፤ ጽንፈኛ በሆኑ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦቹ በሚወልዷቸው ያልተገቡ ድርጊቶች እየተፈተኑ ነው። ለዚህ ደግሞ ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶች እና ከግጭቶቹ በስተጀርባ ያሉ እና የነበሩ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በአግባቡ ማጤን ተገቢ ነው።
ከነዚህ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በስተጀርባ ያሉት ግለሰቦችና ቡድኖች እንጂ ህዝብ አይደለም፤ አስተሳሰቦቹ በወለዷቸው ሁከት፤ ግጭትና ጦርነት ዋንኛው ተጠቂ የነበረው ግን ህዝቡ ነው። በነዚህ አስተሳሰቦች ተስፋውን የተነጠቀው፤ ለከፋ ስቃይና መከራ፤ ለሞት እና ለአካል ጉድለት፤ ለስደት እና ለልመና የተዳረገው፤ ነገዎቹ የጠቆሩበት ህዝቡ ነው።
ዛሬም በአማራ ክልል የሚታየው ከዚህ የተለየ አይደለም። የአማራ ህዝብ ተናግረው የሚሰሙ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ገዝተው የጥፋት ጉዞዎችን ማቋረጥና ማስቆም የሚችሉ ካህናትና ቀሳውስቶች፤ ሼሆችና ኡዝታዞች፤ ወቅታዊ ችግሮችን ለዘለቄታው በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ ብዙ ሀገር በቀል እውቀትና ጥበቦች ባለቤት ሆኖ ሳለ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በሚወልዷቸው የጥፋት ድርጊቶች ሰላሙን እያጣ ይገኛል።
የጽንፍና የግጭት መንገድ የህዝቡን ፍትሀዊ ጥያቄዎች መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ፣ ያለውን የሚያሳጣ፣ እና በዘላቂነት ሊፈቱ የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ ነው። የአማራን ህዝብ ለመገዳደር በየአቅጣጫው፣ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ለተሰለፉ ኃይሎች አቅም የሚፈጥር፣ የአማራን ህዝብ ክብር የሚጎዳ እና ለአደጋ ተጋላጭነቱን የሚያሰፋ ነው።
ለአማራ ህዝብ ነገዎች ዘላቂ ዋስትና የሚሆነው የጽንፍና የግጭት መንገድ ሳይሆን የተሟላ የህግ የበላይነት ማስፈን ነው። ለዚህ ደግሞ መላው የክልሉ ህዝብ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስፈን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ለሚደረገው ጥረት ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮና ተናቦ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ።
በክልሉ ብረት አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ቢሆኑ፣ በእርግጥ ለአማራ ህዝብ፣ ከዛም ባለፈ ለሀገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ እና ዘላቂ ተጠቃሚነት አሳቢ ከሆኑ እየሄዱበት ካለው፣ ሀገርና ህዝብን ለቀደሙት ስድስት አስርት ዓመታት ዋጋ ሲያስከፍል ከነበረ፣ ጊዜ ያለፈበት የግጭት መንገድ ወጥተው በሀሳብ የበላይነት ልእልና ወደሚያገኙበት ዘመናዊ የፖለቲካ መንገድ ሊመጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም