ትንሿ ኢትዮጵያ በላስቬጋስ

ከአርባ ሺህ በላይ ኢትዮጵዊያን እና ኤርትራዊያን በሚኖሩባት በላስቬጋሷ ክላርክ ካውንቲ ትንሿ ኢትዮጵያ ሊትል ኢትዮጵያ። በመባል በቅርቡ አንድ ወረዳ ተሰይሟል።

ይህ በኢትዮጵያ ስም የተሰየመው አካባቢ የሚገኘው በአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት ላስቬጋስ ውስጥ በምትገኘው ክላርክ ካውንቲ ውስጥ ነው። ይህ ስያሜ እንዲሰየም የተጀመረው ጥረት ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም በአራት አመቱ ሊሳካ ችሏል።

በአሜሪካ አንድ አካባቢ በኢትዮጵያ ሲሰየም ይህ የመጀመሪያ ቢሆንም፤ ከዚህ በፊት የአሜሪካ ከተሞች በሆኑት በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎሳንጀለስ እና በካናዳ ቫንኮቨር መንገዶች ተሰይመዋል። በተጨማሪም በ2010 ዓ.ም በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን ቀን ተብሎ መሰየሙ አይዘነጋም።

አካባቢው በኢትዮጵያ መሰየሙ የሀገሪቱን ታሪክ በማስተዋወቅ፤ ገጽታን ከመገንባት እና በአካባቢው የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵዊያን የሀገራቸውን ታሪክ እና ባህል በማስተዋወቅ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ያግዛል ተብሎ ታምኖበታል።

በአሜሪካ በኔቫዳ ግዛት ላስቬጋስ ክላርክ ውስጥ በኢትዮጵያ ስም አካባቢ መሰየሙ የኢትዮጵን ገጽታ ለመገንባት ሚናው ጉልህ እንደሆነ እና ይህም ሕዝቡ ውስጥ የሚፈጥረው ተጽእኖ ትልቅ እንደሆነ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪና መምህር አቶ ሱራፌል ጌታሁን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ከፈረንጆቹ 1903 ጀምሮ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ሱራፌል፣ በእነዚህ ጊዚያት ሁለቱ ሀገራት በተለያየ ዘርፍ እርስ በርስ ሲደጋገፉ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።

አሜሪካ የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆና በንጉሱ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከ1945 እስከ 1960ዎቹ አምስት ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ የተማሩበት ሁኔታ እንደተፈጠረም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በርካታ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ ሀገር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት እውቀት እና አቅማቸውን እያወጡ የሚገኙ ሲሆን፣ ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አንጻር ከተሞች፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች መሰየማቸው ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያጠናክረዋል ሲሉ ተመራማሪው ገልጸዋል። በተጨማሪም ከዲፕሎማሲ አንጻር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት እንደሚያጎለብት አስረድተዋል።

አካባቢው በኢትዮጵያ መሰየሙ በአካባቢው ለሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊያኖች በሀገራቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው እና በራስ የመተማመን ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግም ያብራራሉ።

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ አንድነት በለጠ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን ለረጀም ዘመናት በአሜሪካን ሀገር እንደሚኖሩ በማስታወስ፣ ይህም አካባቢ በኢትዮጵያ መሰየሙ የእርስ በእርስ ግንኙነቱን በላቀ ደረጃ ያጠናክረዋል ይላሉ።

አቶ አንድነት እንደተናገሩት፤ አካባቢው ትንሿ ኢትዮጵያ ተብሎ መሰየሙ ሀገር በቀል የሆነውን የኢትዮጵያን ባህል ኢትዮጵያን ማወቅ ለሚፈልጉ ለሌላ ሀገር ዜጎች ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥራል።

በኔቫዳ ግዛት ውስጥ በኢትዮጵያ ስም በተሰየመችው አካባቢ ክላርክ ካውንቲ ውስጥ 17 የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ከ50 በላይ የኢትዮጵያውያን የንግድ ተቋማት እንደሚገኙ ቢቢሲ የላስቬጋሱን ሪቪው ጆርናል ጠቅሶ ዘግቧል።

የላስቬጋስ ከተማ ክላርክ ወረዳ ኮሚሽን ተሰብስቦ ውሳኔውን ያሳለፈ ሲሆን፣ በከተማዋ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም መጽደቁና ሥራ ላይ መዋሉ ታውቋል። ይህንንም በላስቬጋስ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ንኡስ ኮሚቴ አባላት በይፋ አሳውቀዋል። በዚሁ ወቅት የኮሚቴው አስተባባሪ እና ሊቀ መንበር አቶ ግርማ ዘይድ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮሚቴው ይህን ስያሜ ለማጸደቅ፣ ያለፋቸው ብዙ ውጣ ውረዶች እልህ አስጨራሽ እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የስያሜው መጽደቅ፣ በከተማዋ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎች ላቅ ያለ ጠቀሜታ እንደሚሰጥና የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቁ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው፣ በንግድ እና በመሳሰሉት ሥራዎች ላይ የተሠማሩት የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለፁም ቢቢሲ በዘገባው አካቷል።

ስያሜው በተሰጠው ሥፍራ፣ አዲስ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ተቋማት ለማሳደግ ዕቅድ እንዳለም፣ በንኡስ ኮሚቴው ማብራሪያ ተጠቁሟል።

እንደ አቶ ግርማ የቢቢሲ ማብራሪያ፣ ምንም እንኳን በዘልማድ አንድ የሀገር ዜጎች በብዛት የሚኖሩበት እና የሚሠሩበት አካባቢ የመጡበትን ሀገር መጠሪያ ቢያገኝም በሀገረ ገዢ ደረጃ አዋጅ ወጥቶለት ሲጸድቅ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ይህንን ስያሜ ለማግኘት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ40 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ባሉበት ከተማ እንዴት አንድ የባህል ማሳያ አካባቢ አይሰየምም በሚል መነሻ ነበር። ሐሳቡን የጀመሩትም በላስቬጋስ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሴንተር ሰብሳቢ አሌክሳንደር አሰፋ እንደነበሩ ተጠቁሟል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሌሎች ተግዳሮቶች የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጓትቶ የቆየ ሲሆን፣ አቶ ግርማ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሴንተር ቦርድ ዳሬክተሮች ጋር በመነጋገር ነበር ፕሮጀክቱ እንደገና መንቀሳቀስ የጀመረው።

እኤአ ከየካቲት 2022 ጀምሮም አቶ ግርማ የንዑስ ኮሚቴው ሊቀመንበር ሆነው ፕሮጀክቱን ሲመሩ መቆየታቸውን ተጠቅሷል። የዓለም ቱሪስቶች መዳረሻ በሆነችው ላስቬጋስ የትንሿ ኢትዮጵያ መመሥረት ኢትዮጵያን ለሰፊው ዓለም ማስተዋወቅ ዋነኛው ዓላማ መሆኑም ተገልጿል።

 ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 27/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *