አበረታች ውጤት ያስመዘገበውና ብርቱ ሥራ የሚጠብቀው የሲዳማ ኢንቨስትመንት

ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነው የሲዳማ ክልል ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች ያሉት ክልል ነው። ክልሉ ያለው ሀብት ሀገርን የሚያኮራ፣ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መልካም አጋጣሚና ፀጋ ነው።

የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ ምርቶች መገኛ ነው። ከፍተኛ የቡናና ሌሎች ሀብቶችን የያዘው ይህ ክልል፤ ሀብቱ ከክልሉ አልፎ ለሀገርም የሚተርፍ ፀጋ ነው። የክልሉ ሁለንተናዊ ሀብትና አቅም የባለሀብቶችን ትኩረት የሚስብ ነው። በርካታ የኢንቨስትመንት አቅሞች ያሉት ሲዳማ ክልል፣ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶች ይመረቱበታል። ብዙ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፣ የቡና፣ የወተት፣ የዶሮ፣ የማር፣ የስጋና ሌሎች ሀብቶች አሉት። ክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከግብርናው በተጨማሪ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ዕድል የሚፈጥር ነው።

የሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በክልሉ ከ17 በላይ የማዕድን ዓይነቶች ይገኛሉ። ክልሉ በኢንቨስተሮች ተመራጭ እንዲሆን ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል እምቅ ሀብት ባለቤት መሆኑ፣ ሥራ ፈላጊ ወጣት የሰው ኃይል መኖሩ፣ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ የሚዘልቀው መንገድ የክልሉን ዋና ከተማ ሐዋሳን አቋርጦ ማለፉ እና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት መኖር ይጠቀሳሉ።

ክልሉን ከሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ የኢንቨስትመንት ልማት ሥራዎች ሲናወኑ ቆይተዋል። በክልሉ የኢንዱስትሪ ክላስተር ዞኖችን በማደራጀት የክልሉን ሀብት ለኢንቨስተሮች የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል። የክልሉን የኢንቨትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታዎችን ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል። በተሠሩ የንቅናቄ ተግባራትም አማካኝነት ብዙ ባለሀብቶች በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ማወቅ ተችሏል። ክልሉ ትኩረት ከሰጣቸው የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ነው። ሲዳማ ክልል በቡና ሀብት ትልቅ አቅም ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። ለተከታታይ ዓመታት የጥራት ውድድር (Cup of Excellence) ላይ ቀርቦ አሸናፊ የሆነው የሲዳማ ቡና ነው።

የሲዳማ ክልል በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት አበረታች የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ማስመዝገቡን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ፈቃድና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ሮባ ይገልጻሉ። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት በክልሉ 99 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል። ባለሀብቶቹ ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን፤ በኮንስትራክሽን (31)፣ በአገልግሎት (29)፣ በማምረቻ (22) እና በግብርና (17) ዘርፎች እንደሚሰማሩ ይጠበቃል። ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። በበጀት ዓመቱ በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ለ17ሺ 800 ዜጎች (1896 ቋሚ እና ጊዜያዊ) የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።

አቶ ታሪኩ እንደሚሉት፣ በሲዳማ ክልል ሦስት የኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫዎች አሉ። እነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች የኢንቨስትመንት አቅም ጥናትና የመሬት ዝግጅት፣ ፕሮሞሽን እና ፈቃድና ክትትል ናቸው። በኢንቨስትመንት ዘርፎች ረገድ ከማምረቻ ዘርፍ በተጨማሪ ክልሉ በአገልግሎት ዘርፍም በሐዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ትልልቅ ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን በመገንባት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ ዙሪያ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ። የሐዋሳ ሐይቅ እና ታቦር ተራራን ጨምሮ በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ለማልማት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች የመሬት ዝግጅትና ሌሎች ግብዓቶች በፍጥነት እንዲሟሉላቸው ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም ክልሉ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ፣ የበርካታ አዕዋፋትና እንስሳት እንዲሁም የተፈጥሮ ገፅታዎች እና የብዙ ባህላዊ የሽምግልና ስፍራዎች መገኛ በመሆኑ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንትም ተመራጭ የመሆን አቅም አለው። የክልሉን የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የክልሉ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ከክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በጋራ የሚሠሩበት ቅንጅታዊ የአሠራር ሥርዓት መዘጋጀቱ ይጠቀሳል።

በክልሉ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑና በዘርፉ አቅም ያላቸው አካባቢዎች በጥናት ተለይተዋል። ለአብነት ያህል የሐዋሳ ሐይቅ፣ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ እና በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የባህላዊ የሽምግልና ስፍራዎች ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው። ዘርፉን ለማሳደግ በእነዚህ አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችንና ሎጅዎችን መገንባት ያስፈልጋል። ብዙ አካባቢዎች ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ እንደሆኑና በዘርፉ ክልሉን ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል አቅም እንዳላቸው ቢታወቅም፣ የባለሀብቶች ፍሰት በሚፈለገው ልክ አይደለም፤ ክልሉ ካለው ሀብት አንፃር ሲመዘን የዘርፉ አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው። ስለሆነም ባለሀብቶች በቱሪዝም ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎች ይከናወናሉ።

በግብርናው ዘርፍ ደግሞ፣ አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ አብቃዮች በመሆናቸው በእነዚህ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ለክልሉ ኢንቨስትመንት፣ በተለይም ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች፣ እድገት ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ዕድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱ ከሐዋሳ ከተማ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሆነ አቶ ታሪኩ ያስረዳሉ።

የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ከታመነባቸው እና የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለምርት የሚያገለግለውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱን የሚያገኘው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ነው። የአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል። አርሶ አደሮቹ የፓርኩ መጋቢ በሆኑ ሦስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት (በንሳ ዳዬ፣ አለታ ወንዶ እና ሞሮቾ አካባቢዎች የሚገኙ) እና በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የአቮካዶ፣ የማር፣ የወተት፣ የቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በፓርኩ ውስጥ ለተሰማሩ ለአልሚዎች እያቀረቡ ነው። የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማር እንዲሁም የወተት ምርት የሚያቀርቡ ማኅበራት ግብዓቶችን የሚሰበስቡት በገጠር የሽግግር ማዕከላቱ በኩል ነው። ፓርኩ ግብአቶችን በማቅረብ የገበያ ትስስርና የገቢ ምንጭ ከፈጠረላቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ በየአመቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ይህ ተግባር የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የማስቀረትና ገቢ ምርቶችን የመተካት ድርብርብ ዓላማዎች አሉት።

ከሦስት ዓመታት በፊት ትልቅ ገበያ ያልነበረው የአቮካዶ ምርት በአሁኑ ወቅት ደረጃ ወጥቶለት አርሶ አደሩ ምርት በስፋት እያቀረበ፣ ገቢ እያገኘና አዳዲስ ዝርያዎችን እያለማ ነው። ፓርኩ አርሶ አደሩ ጥሬ ዕቃን በብዛትና በጥራት እንዲያቀርብ ዕድል እየፈጠረ ነው። ይህም የግብርና ምርታማነት እንዲጨምርና የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል እያደረገ ነው።

አቶ ታሪኩ እንደሚናገሩት፣ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለግብርና ኢንቨስትመንት እድገት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። በፓርኩ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ለፓርኩ ግብዓት የማቅረብ አቅም ያላቸው በመሆኑ፣ በፓርኩ ውስጥ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስርም ሆነ የሥራ ዕድል በመፍጠር የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው። ስለሆነም ባለሀብቶች ወደ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው እንዲያለሙ የሚከናወኑት የፕሮሞሽን፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የክትትል ተግባራት በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ ይሆናሉ። ከይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ ግዙፉ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም በክልሉ በማምረቻ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ትልቅ ዕድልን የሚፈጥር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ክልሉ በፋርማሲቲካል፣ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶችም ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ ባለሀብቶችን እየጠበቀ ይገኛል።

የሲዳማ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች ሆነው ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የመንገድ፣ የኃይል እና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች ይገኙበታል። አቶ ታሪኩ ‹‹ከዘርፉ መሰናክሎች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት ችግር (የኃይል አቅም ማነስና መቆራረጥ) ነው። የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ የገቡ ባለሀብቶችም ቅሬታ የሚያቀርቡበት የመሠረተ ልማት ዘርፍ ነው። በተለይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የኃይል አቅርቦት እንዲስተካከልላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። በፋይናንስ አቅርቦት ረገድም የኢንቨስትመንት ፕሮፖዛሎችን ገምግሞ ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት ችግር ይስተዋላል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ችግሮቹን ለማቃለል ጥረት እያደረግን ነው። ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻልም እንዲቃለሉ ተደርጓል›› ይላሉ።

በክትትልና ድጋፍ ረገድ ደግሞ ‹‹የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች የሥራ ውላቸውን አክብረው እንዲሠሩ ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ውላቸውን አክብረው የማይሠሩ ባለሀብቶች ምክርና ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፤ በመቀጠልም ውላቸውን የማቋረጥ እርምጃ ይወሰድባቸዋል። በዚህ መሠረት ዝቅተኛ አፈፃፀም በማሳየታቸው እርምጃ የሚወሰድባቸው 339 ፕሮጀክቶች ተለይተዋል። ለኢንቨስትመንት አቅም ጥናትና የመሬት ዝግጅት፣ የፕሮሞሽን እና የፈቃድና ክትትል ሥራዎች ትኩረት የመስጠቱ ተግባር በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል›› በማለት ይገልፃሉ።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው። በዚህ ረገድ በሲዳማ ክልል የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ኅብረተሰብ በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙ አቶ ታሪኩ ይገልፃሉ።

ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ሲሰማሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከሚያደርጉባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ከሥራ ዕድል በተጨማሪ የክልሉ ሕዝብ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ ዕድልም ተጠቃሚ ሆኗል።

እንደአቶ ታሪኩ ገለፃ፣ በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት 480 የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቴክኖሎጂ ሽግግር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። ዜጎች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ከሆኑባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ግብርና ነው። በግብርና ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የምርት ዘዴዎችንና ግብዓቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። ለአብነት ያህል በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አርሶ አደሮች ዘመናዊ የዶሮ እርባታ ስልት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸው እንዲሁም በንብ እርባታ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮች በነፃ ማቅረባቸውና ስለአጠቃቀሙም ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረጋቸው የዚህ ተሳትፎ ማሳያ ተደርገው የሚጠቀሱ ናቸው።

ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን በሚሠሩባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ በዚህ ተግባር በኩል በርካታ የክልሉ ሕዝብ ተጠቃሚ ሆኗል። በክልሉ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና የትምህርት ግብዓቶችን በማቅረብ ለአገልግሎት አብቅተዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 27/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *