ሀገራችን በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ረጅም ዘመናትን ማሳለፏን ተከትሎ፤ በዲፕሎማቲክ ዘርፉ ያላት ተሞክሮም በተመሳሳይ መልኩ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። በተለያዩ ዘመናት የነበሩ የሀገሪቱ ነገሥታቶች ባህር የተሻገሩ ግንኙነቶችን ከመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ እና እስያ ካሉ ሀገራት ነገሥታት ጋር ፈጥረው እንደነበርም የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉ።
በተለይም ሀገሪቱ ገናና በነበረችባችው በ4ኛው እና 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ኢዛና፣ እና ካሌብ ዘመነ መንግሥት ጠንካራ የውጭ ግንኙነቶች ታደርግ እንደነበር፣ የባዛንታይን ኢምፓየር እና የእስልምና ተከታዮች ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ከሁለቱም እምነት ተከታዮች ጋር መልካም የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንደነበራትም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአክሱም ዘመነ መንግሥት የነበሩ ረጃጅም የንግድ መስመሮች እና ይካሄዱ የነበሩ ንግዶች ሀገሪቱ ከተቀረው ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት የቱን ያህል ከፍ ያለ ደረጃ ደርሶ እንደነበር በተጨባጭ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ዘመናዊው ዲፕሎማሲ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሩ በፊት በሸዋ፣ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በሐረር እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የአካባቢ ገዥዎች ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝ እና ከሌሎች ሀገራት መልዕክተኞች ጋር የንግድ እና የወንድማማችነት ስምምነቶችን ያደርጉ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዓድዋውን ድል ተከትሎ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ ተጀምሯል፤ የመጀመሪያውን ቆንስላ ጽህፈት ቤትም በጀርመን ተከፍቷል። የዓድዋን ድል ተከትሎ የተጀመረው የሀገሪቱ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። እንደ ሀገርም ሀገሪቱን የረጅም የዲፕሎማሲ ታሪክ ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል።
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመው ትልቁ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ተቋም የሊግ ኦፍ ኔሽን መስራችና አባል ሆናም ሰርታለች። በአፍሪካውያን የነጻነት ትግል ማግስት የተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች በመሆንም አፍሪካውያን ለነጻነታቸው ያደርጉት የነበረው ትግል ስኬታማ እንዲሆን ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን በማድረግ ተጠቃሽ ነች።
ይህ በረጅም ታሪክ የታጀበው የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በየዘመኑ፤ ዓለም ከምታስተናግዳቸው የዲፕሎማሲ እሳቤዎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፈተናዎችን ለማስተናገድ የተገደደበት ጊዜያት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ፈተናዎቹን ተሻግሮ ለማለፍ እንደ ሀገር የተጓዝንባቸው ውጣ ውረዶች፤ እና ያስከፈሉን ዋጋም በቀላሉ የሚሰላ አይደለም።
ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ የተፈጠረው የለውጥ መነሳሳት ስጋት የፈጠረባቸው ኃይሎች በሀገሪቱ ላይ ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ጫና በመፍጠር፤ ፍላጎታቸውን በአስገዳጅ ሁኔታ ለመጫን ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። በዚህም ሀገርን እንደሀገር ችግር ውስጥ የሚከቱ ያልተገቡ ተግባራትን አከናውነዋል።
ይህንን ጫና ተቋቁሞ ለመሻገር መንግሥት፣ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ እና መላው ሕዝብ በጋራ በመሆን ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር መንፈስ እና ቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም ጫናዎቹን መቀልበስ፤ የሀገር ህልውናን ከስጋት መታደግ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች የነበራትን ተደማጭነት መመለስ ተችሏል።
በተለይም ሀገሪቱ ቀደም ሲል የነበራትን የዲፕሎማሲ ተደማጭነት በማቀጨጭ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ድምጿ እንዳይሰማ፤ ከዚያ ይልቅ በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል/በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት / ተጽእኖ በመፍጠር የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቀልበስ የተደረጉ ጥረቶች መክነዋል።
ይህን ተከትሎ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ አቅም እለት ተእለት እየጎለበተ፤ የሀገርንና የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም ማስከበር የሚችልበት ስትራቴጂክ አቅም እየተላበሰ ይገኛል። ይህ በዘርፉ እየተስተዋለ ያለው ስኬት እንደ ሀገር ለተጀመረው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሀገራዊ ጥረት አቅም የሚሆንበትን ደረጃ እየደረሰ ነው።
ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ወር ብቻ በተለያየ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ ለመገኘት ፈረንሳይ፣ በግብጽ፣ በጣሊያን እና በሩሲያ ያደረጓቸው ጉብኝቶች እና ጉብኝቱን ተከትሎ የተፈራረሟቸው ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሁለትዮሽ ዘርፈ ብዙ ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህም ጎን ለጎንም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖሊት ቢሮ አባል እና የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክተር፤ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን፣ ጨምሮ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በሀገሪቱ ያደረጉት ጉብኝትና ከሀገራቱና ከተቋማቱ ጋር የተደረሱ ስምምነቶች የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በስኬታማ መንገድ መጓዙን ስለመቀጠሉ ተጨባጭ ማሳያ ናቸው!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2015