በመም እጥረት እየተፈተነ የሚገኘው የዓለም ቻምፒዮናው ቡድን

 ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚካሄደውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅታቸውን በማጠቃለል ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንም በሦስተኛ ሳምንት የዝግጅት ምዕራፉ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያን በዓለም ቻምፒዮናው የሚወክሉ ከዋክብት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከክረምቱ ዝናብ ጋር ግብግብ ገጥመው ዘወትር ጠንካራ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። በአካዳሚው የሚገኘው ጠባብ የመሮጫ ትራክ(መም) ጉዳይ ግን እየተፈራረቁና እየተጠባበቁ በጥንቃቄ ልምምድ እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል።

እነዚህ ከዋክብት ጥቂት ጊዜ ለቀረው ቻምፒዮና መም እንደልብ አለማግኘታቸው ዝግጅታቸውን ማወኩ አልቀረም። ይህም በቻምፒዮናው ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ስጋት ፈጥራል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያዎች የተገነቡ ቢሆንም የኢትዮጵያን ስም ባገነነው አትሌቲክስ ስፖርት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚመጥን የመለማመጃ መም እንደልብ አለመኖሩ በአትሌቶችም ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ ነው።

የኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ቻምፒዮኑ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፤ የማዘውተሪያ ጉዳይ ሁሌም ቅሬታ የሚነሳበት ነገር ግን ሰሚ ያጣ መሆኑን ይናገራል። የአካዳሚው መምም ቢሆን የዓለም ቻምፒዮና በመኖሩ እንጂ አትሌቶች በግላቸው እንዲዘጋጁበት አይፈቀድላቸውም። እሱና ሌሎች አትሌቶች ከዚህ ቀደም ፈቃድ አጥተው የተመለሱበትን አጋጣሚ እንዳለም ያስታውሳል። የቡድኑን ዝግጅት ተከትሎም በርካታ አትሌቶች መሙን ስለሚጠቀሙ በመገፋፋትና በመጠባበቅ ተገቢውን ዝግጅት ለማድረግ እንደተቸሩ የሚናገረው ሰለሞን፣ ከመም ባለፈ በጎዳና ላይ የሚደረጉ ዝግጅቶችም አትሌቶችን ለመኪና አደጋም ጭምር እየዳረገ በመሆኑ በኮሮኮንች ላይ ልምምድ ለመሥራት እንደተገደዱ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት የምትታወቅ ሀገር ሆና ሳለ ከማዘውተሪያ ስፍራ ጋር በተያያዘ እንቁ አትሌቶቿ ይህንን ችግር መጋፈጣቸው ሁሌም ግራ አጋቢ መሆኑንም የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ይናገራል። የ3ሺ ሜትር መሰናክል አሰልጣኝ ተሾመ ከበደም በዚህ የውድድር ዝግጅት ላይ ፈተና የሆነው መም እንደሆነ ይጠቁማሉ። በዚህ ችግር የተነሳም አሰልጣኞች አትሌቶችን ከፋፍለው የሚያሠሩ ሲሆን፤ በመሰናክል ልምምድ ለማድረግ ደግሞ ሌሎች ርቀቶች ላይ ያሉ አትሌቶች ዝግጅታቸውን እስኪጨርሱ መጠበቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ። ኦሊምፒክም እየተቃረበ እንደመሆኑ ችግሩ እስካልተቃለለ ድረስ ብሔራዊ ቡድኑ በመሰል ሁኔታ እንዳይቀጥል ያላቸውን ስጋትም ገልፀዋል። ብሔራዊ ቡድኑ እየተዘጋጀ ያለበት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም ባለው ሁኔታ ጫና እየበዛበት በመሆኑ እየተጎዳ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵ እና ቻምፒዮናውን በምታስተናግደው ሃንጋሪ መካከል ያለው የወቅቱ የአየር ሁኔታ ፍጹም የተለያየ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ ስፍራዎች ነው። በጥቂቱም ቢሆን ሞቃት አየር ለማግኘት ቡድኑ ወደ ቃሊቲ የሚሄድ ቢሆንም ባለው የመንገድ መጨናነቅ ምክንያት ለተጨማሪ እንግልት መዳረጋቸው አልቀረም። ‹‹ቶኪዮ ኦሊምፒክ ሊያስተምረን ይገባል›› የሚሉት አሰልጣኝ ተሾመ በተለይ በማራቶን በርካታ አትሌቶች ውድድር የማቋረጣቸው ምክንያት የአየር ሁኔታው እንደነበር ያስታውሳሉ። በመሆኑም ለሁለቱም ጉዳዮች መፍትሔ ይሆናል የሚሉት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ባሉ ስፍራዎች ዝግጅት ማድረግን ነው። ውድድሩ ከሚካሄድበት ሀገር ጋር የሚጠጋ የአየር ሁኔታ ወዳላቸው ክልሎች በመሄድ ዝግጅት ማድረግም አማራጭ ነው ይላሉ። ይህንንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጥናት ላይ ተመስርቶ አሊያም በቁርጠኛ ውሳኔ ሊሞክረው የሚገባ ነው ባይ ናቸው። ከማዘውተሪያ አንጻርም ክልሎች ከአዲስ አበባ የተሻሉ ናቸው የሚሉት አሰልጣኙ፤ ፌዴሬሽኑ ይህንን ደፍሮ ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ።

በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር አሰልጣኝ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ፤ ዝግጅት የሚደረግበት ብቸኛው መም የአካዳሚው በመሆኑና ሁሉም አትሌት ልምምድ ያድርግ ቢባል ስለማይበቃ አትሌቶችን በመከፋፈል እንዲሁም ለሌሎች ርቀቶች ጋር እየተጠባበቁ ሥልጠናውን እየሰጡ መሆኑን ይጠቁማሉ። እንደ ኬንያ ባሉ ሀገራት የጥርጊያ መንገድን ጨምሮ ለዝግጅት የሚሆኑ ስፍራዎች በመንግሥት ይዘጋጃሉ። በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደ እንጦጦ እና ሰንዳፋ ባሉ ስፍራዎች የሚሠሩ ቢሆንም፤ በሂደት እሱም የማይሞከር እየሆነ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የመንገዱ ሁኔታ ነው። ስለዚህም በመንግሥት በኩል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዓለም ቻምፒዮናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስተባባሪ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱም ችግሩ ስለመኖሩ ይናገራሉ። የቀድሞው ኦሊምፒያን ቶሎሳ ቆቱ እንደሚናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቻምፒዮናን ጨምሮ ሌሎች ውድድሮች እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን ዝግጅቶች በብቸኛው የአካዳሚው መም ላይ ይደረጋል። ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ ያሉ ስፍራዎች ለመጓዝም ባለው የመንገድ መጨናነቅ ሰዓት ይባክናል። አትሌቶችም በዚህ ዓይነት እንግልትና ድካም ውስጥ እያለፉ ነው ሀገርን የሚያስጠሩት። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ የፌዴሬሽኑ አቅም አይፈቅድም በመሆኑም መንግሥት እንደ አዲስ አበባ ስታዲየም ያሉትን መሞች በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይገባል ይላሉ።

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 26/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *