ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ካልተለመዱ ስፖርቶች መካከል አንዱ ክብደት ማንሳት ነው፡፡ ክብደት ማንሳት ለሌሎች ስፖርቶች መሠረት ነው፤ በመሆኑም ስፖርተኞችም ሆኑ ለጤንነታቸው ጂምናዚየሞችን የሚጎበኙ ሰዎች እንደየአቅማቸው በሚመጥናቸው መልክ ያዘወትሩታል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህም በዚህ ስፖርቱ በጥቂቱም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ ውድድሮችም እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ስፖርት ውስጥ ረጅም ጊዜ ካሳለፉና ስፖርቱን ለማሳደግ እየተጉ ካሉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ዮናስ መኮንን ነው፡፡ የስፖርቱ ፍቅር ገና በለጋ ዕድሜው ቢሰርጽበትም ቤተሰቦቹ ይከለክሉት ስለነበር ከትምህርት ቤት መልስ ከሽሮሜዳ መርካቶ ድረስ እየተመላለሰ ለመሥራት ይገደድ ነበር፡፡ ዮናስ ለስፖርቱ ካለው ፍቅር የተነሳ በታዳጊነት ዕድሜው ‹ሚስተር ኦሊምፒያ› በተባለው ውድድር የሰባት ጊዜ አሸናፊና አንድ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው ዝነኛው አሜሪካዊ የፊልም አክተር አርኖልድ ሸዋዚንገር ደብዳቤ ይፅፍ ነበር፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል የላከው ደብዳቤም አድናቂው እንደሆነ እና እንዴት ትልቅ የቅርጽ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል የሚጠይቅ ነበር፡፡ ከሦስት ወር በኋላ በደረሰው ምላሽም ‹‹በቅርብ ሆኜ እንዳላግዝህ ሩቅ ነው ያለኸው በየወሩ በሚወጣው ፊለክስ መጽሔት ስለምጽፍ በዚያው ተከታተለኝ›› ብሎ መልስ እንደሰጠው ዮናስ ይናገራል፡፡
ከዓመት በኋላ ግን አሜሪካ በምትኖረው እናቱ አማካኝነት ዮናስ ወደዚያው የመሄድ ትልቅ አጋጣሚ ተፈጠረለት። ይህም አዲስ አበባ ሆኖ እንደልቡ የሚወደውን ስፖርት እንዳይሠራ እንቅፋት የሆነበትን የቤተሰብ ቁጥጥር አስቀረለት፡፡ ዮናስ በባህሪው ጽናትና ትጋትን በሚፈልገው የክብደት ማንሳት ስፖርትም ላለፉት 26 ዓመታት ቆይቷል። አንድ ሰው የተሻለ የሰውነት አቋም እንዲኖረው ቢያንስ አምስት ዓመት በጽናት መሥራት አለበትም ይላል። በረጅም ዓመት የስፖርተኝነት ሕይወቱም በሳምንቱ መጨረሻ የረፍት ቀን ካልሆነ በቀር ከጂምናዚየም የቀረው ሳምንት ጊዜ ብቻ መሆኑን ያስታውሳል፡፡ በየዕለቱም ቢያንስ ከአርባ ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ለሚሆን ጊዜ ስፖርቱን ይሠራል፡፡
ዮናስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰውነት ቅርጽ ውድድር ያደረገው በአሜሪካ ይኖርበት ከነበረው ግዛት አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ እየተጓዘ በወቅቱ በብዛት የሰውነት ቅርጽ ውድድር በሚካሄድበት ባልትሞር ነበር፡፡ በውድድሩ ከእሱ ጋር አሥራአምስት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው። በሳምንቱ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት ትምህርት ቤት በተዘጋጀው ውድድር ተካፈለ፤ ከመጀመሪያው ውድድር የሚበዙ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም ዮናስ ሁለተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። ከዚህ ውድድር በኋላም ስድስት ውድድሮችን ለማድረግ በቅቷል።
ዮናስ ሁሉንም ዓይነት የቅርጽ ውድድሮች ያደረገው በአሜሪካ ሲሆን በተወዳደረባቸው ውድድሮች ሁሉ የኢትዮጵያን ስም አስጠርቷል። ለመጨረሻ ጊዜ ያደረገው ውድድር በከባድ ሚዛን ሲሆን ትውልደ ኢትዮጵያዊ በመባል ሀገሩን ከፍ አድርጓል። እአአ በ2019 ግን ጉዳት አጋጥሞት ቀዶ ጥገና ለማድረግ በመገደዱ የውድድር ዝግጅቱን አቆመ፡፡ ከቀዶ ጥገናው በኋላ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ውስጥ ወደ ውድድር መመለስ ቢቻልም ዮናስ ያለፉትን ዓመታት ልምዱን ለወጣቶች ለማካፈል አንበሳ ፊትነስ የሚል መጽሐፍ አሳትሟል። ለጀማሪዎች ስፖርቱን ከየት መጀመር እንዳለባቸው፣ መጽሐፉም በዘርፉ ለቆዩት ደግሞ ድጋፍና ምክርን ያካተተ ነው። ስፖርተኞች ከስፖርት ሊከተሉት የሚገባውን አመጋገብ ጨምሮ ዝርዝር ምክረ ሃሳቦችንም የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡
በዚህ ብቻ ያልተገደበው ዮናስ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርቱን እንዴት ማስፋፋት እችላለሁ›› ብሎ በማሰብ እአአ በ2010 ኢትዮጵያ ውስጥ የክብደት ማንሳት ውድድርን ለማስጀመር እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ጉዳዮች ስለዘገየ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በ2019 ዓለም አቀፍ የውድድር መስፈርቶችን ያሟላ የመጀመሪያው አንበሳ ፊትነስ ውድድር ለማካሄድ በቃ።
ከኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ስፖርት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበርም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ሚስተር ኢትዮጵያ›› እና ‹‹ሚስስ ኢትዮጵያ›› በሚሉ ዘርፎች ባለፈው ዓመት ውድድር አድርጓል። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከየሀገራቱ የተውጣጡ ‹‹ሚስተር›› እና ‹‹ሚስስ›› ውድድር አሸናፊዎች የሚካፈሉበት ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች እንዲኖሩ ሂደቶችን ጨርሶ በዚህ ዓመት የይሁንታ ደብዳቤ አግኝቷል።
በዚህ ዓመትም በካፒታል ሆቴል በተደረገው ውድድር ከሁለት መቶ በላይ ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው ከ160 በላይ ተወዳዳሪዎች ማጣሪያውን አልፈው በውድድሩ ተካፍለዋል።
በወንዶች አጭር የሰውነት ምድብ፣ ረጅም የሰውነት ምድብ እና በከባድ ሚዛን ምድቦች፤ በሴቶች ደግሞ ‹‹ቢኪኒ›› በተሰኘ ምድብ ውድድር ተደርጓል። የዚህን ዓመት ውድድር ካለፉት ለየት የሚያደርገውም በሴቶች ‹‹ሚስስ ኢትዮጵያ›› አሸናፊ እና በወንዶች ‹‹ሚስተር ኢትዮጵያ›› አሸናፊዎች ኢትዮጵያን ወክለው ዘንድሮ በሚዘጋጀው የዓለም አቀፍ የሰውነት ግንባታ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ውድድር መካፈላቸው ነው፡፡
ከውድድሩ ባሻገርም በዚህ ዓመት ለሁለት ሳምንት አስራ አንድ የሰውነት ግንባታ ውድድር ዳኞችን አሰልጥኖ ብቁ ማድረግ ችሏል፡፡ እንዲሁም አርባ የግል አሰልጣኞች እና የብቃት አሰልጣኞችን አሰልጥኗል።
ማህሌት ጋሻው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015