ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በራባት ዳይመንድ ሊግ ለአሸናፊነት ይጠበቃሉ

የ2024 ዳይመንድ ሊግ አራተኛ መዳረሻ እና በአህጉረ አፍሪካ ብኛዋ አዘጋጅ የሆነችው የሞሮኮዋ ራባት ከነገ በስቲያ የአትሌቲክሱ ዓለም ከዋክብት ለአሸናፊነት የሚያደርጉትን ፍልሚያ ታስተናግዳለች፡፡ አስቀድሞ ውድድር ይደረግበት የነበረው የልኡል አብደላ ስታዲየም በእድሳት ላይ በመሆኑ የዘንድሮው ውድድር 45ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው በታላቁ የማራካሽ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡

በትራክ(መም) እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ድንቅ ብቃታቸውን በማሳየት ለዳይመንድ ዋንጫው እንዲሁም ለመጪው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ራሳቸውን የሚያዘጋጁ አትሌቶችም ከመላው ዓለም በዚህ ፉክክር ይሰባሰባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊያን ስመ ጥር አትሌቶችም በተለያዩ ርቀቶች ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ፡፡

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ 1ሺ 500 ሜትር የወንዶች ውድድር ነው፡፡ በተለይ በ3ሺ ሜትር የሚታወቀውና በቤት ውስጥ እንዲሁም ከቤት ውጪ የዓለም ክብረወሰንን የጨበጠው ወጣቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ ደግሞ የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ትኩረት ያረፈበት ነው፡፡ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ስኬታማ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ለሜቻ የዳይመንድ ሊጉ መጀመሪያ በሆነው ዚመን 5ሺ ሜትር መሮጡ የሚታወስ ነው፡፡ ፈጣኑ አትሌት ቀጣይ መዳረሻውን ራባት ላይ በሌላ ርቀት አድርጓል፡፡ አብረውት ከሚሮጡ አትሌቶች ካላቸው ፈጣን ሰዓት አንጻር ለሜቻ ያለው የ3 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ ከ51 ማይክሮ ሰከንድ ፈጣኑ ሲሆን፤ ብቸኛው በ25 ማይክሮ ሰከንድ የሚበልጠው ፈረንሳዊው አትሌት ሃብዝ አዘዲን ነው፡፡ ይህም በአትሌቶቹ መካከል ጠንካራ ፉክክር እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ ሌላኛው የውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ኢትዮጵያዊው ታደሰ ለሚ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ሞሮኳዊውን የኦሊምፒክ ቻምፒዮን አል ባካሊን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተፎካካሪ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ርቀት ለዓመታት የበላይነቱን ይዞ የቆየው የሞሮኳዊያን ኩራት የሆነው አትሌት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያዊው ወጣት አትሌት ለሜቻ ግርማ ፈታኝ ፉክክር ሲያስተናግድ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ 7 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ ከ68 ማይክሮሰከንድ የሆነ ፈጣን ሰዓት ያለው አትሌቱ ባለፈው ዓመት በዚህ ውድድር ላይ ባይካፈልም የዘንድሮውን ዳይመንድ ሊግ ግን ከሀገሩ የሚጀምር ይሆናል፡፡ በጉጉት በሚጠብቁት የሀገሩ ልጆች ፊት በለመደው የአየር ሁኔታ መሮጡ አትሌቱን ለአሸናፊነት ሊረዳው እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡

ይሁንና አንጋፋውን አትሌት በእጅጉ ሊፈትኑ የሚችሉ ወጣት አትሌቶች ከኢትዮጵያ በኩል በውድድሩ እንደሚካፈሉ መረጋገጡ ውድድሩን ሌላ መልክ ሊያስይዘው እንደሚችል ይታመናል፡፡ በተለይ ከቀናት በፊት በኳታሯ ዶሃ በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ በአስደናቂ ብቃት አሸናፊ የነበረውና ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ሳሙኤል ፍሬው ከፍተኛ የአሸናፊነት ቅድመ ግምትን አግኝቷል፡፡ በርቀቱ በኢትዮጵያ እየታዩ ካሉ ተስፈኛ አትሌቶች መካከል ቀዳሚው የሆነው ወጣቱ አትሌት በግሉ ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት 8 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ ከ25 ማይክሮሰከንድ ቢሆንም በዚህ ውድድር በድጋሚ በማሻሻል የዳይመንን ሊጉን እና የፓሪስ ኦሊምፒክ ተስፋውን ያጠናክራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በውድድር ዓመቱ ጥሩ ብቃት በማሳየት ላይ የሚገኘውና ዶሃ ላይ የሮጠው ጌትነት ዋለ እንዲሁም በጋናዋ አክራ አዘጋጅነት በተደረገው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሀገሩን የወከለው አብርሃም ስሜም ራባት ላይ በጠንካራ ተፎካካሪነታቸው ቀላል ግምት የማይሰጣቸው አትሌቶች ናቸው፡፡

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከሚካፈሉባቸውን አሸናፊ የመሆን እድላቸውም ከፍተኛ እንደሚሆን ከሚጠበቁ ርቀቶች መካከል አንዱ በሴቶች የሚደረገው የ5ሺ ሜትር ውድድር ነው፡፡ ዶሃ ላይ አስደናቂ ብቃቷን ያስመሰከረችው መዲና ኢሳ ራባት ላይ በድጋሚ ስትሮጥ፤ ፍሬህይወት ገሰሰም ከዚመን መልስ ሁለተኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች፡፡ መልክናት ውዱ፣ ፎተን ተስፋዬ፣ ልቅና አምባው፣ ገላ ሃምቤሴ፣ ጥጋብ በርሄ እና አልጋነሽ በርሄ ሌሎች በርቀቱ እንደሚካፈሉ ያረጋገጡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You