የአዲስ አበባ የ2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ይካሄዳል

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሳተፉበት ስፖርታዊ ውድድር ከመጪው ቅዳሜ አንስቶ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። ውድድሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በድምቀት የሚጀመር ሲሆን፤ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ ሜዳዎች ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡

የወጣትና ተተኪ ስፖርተኞች ምንጭ ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮም ከከተማዋ ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እርስ በእርሳቸው የሚፎካከሩበትን የውድድር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ በመጪው ቅዳሜ ግንቦት 10/2016 ዓ.ም የሚጀምረው ውድድር ዓላማ ትምህርት ቤቶች የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ እንዲሆኑ፣ በአካልና አእምሮ የዳበረ እና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ መፍጠር፣ እምቅ አቅምን የያዙ ተማሪዎች በክለቦችና ቡድኖች የመታየት ዕድልን እንዲያገኙ እንዲሁም የኦሊምፒክ ችቦን ባማረና በደመቀ መልኩ ለመቀበል እና ወደ ኦሊምፒክ የሚሄዱ ስፖርተኞችም የሚሸኙበት መድረክ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ውድድሩ በተሳካና ባማረ መልኩ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አዘጋጅ ተቋማቱ ከትናንት በስቲያ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ በስፖርት አማካኝነት ተማሪዎችን ማቀራረብ፣ ማህበረሰቡ ዘንድ የስፖርት ንቅናቄን መፍጠር፣ ተማሪዎች ትርፍ ጊዜያቸውን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማሳለፍ አላስፈላጊ ቦታ እንዳይውሉ እና ልዩ ተሰጥኦና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች በክለቦች እይታ ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እንደሚካሄድም ተጠቅሷል፡፡

‹‹የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለሁለንተናዊ ብልጽግና›› በሚል መሪ ሃሳብ በከተማዋ በሚገኙ የተመረጡ የ2ኛ ደረጃ ትምርህርት ቤቶች ውስጥ በሚገኙ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ይካሄዳል። በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከ18 ሺ በላይ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ደጋፊዎች በስድስት የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቮሊቮል እና ጠረጴዛ ቴኒስ ደግሞ ውድድር የሚደረግባቸው የስፖርት ዓይነቶች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት እና በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ውድድር ለአስራ አምስት ቀናት ተማሪዎችን በተለያዩ ስፖርታዊ ሁነቶች የሚያፎካክር ሲሆን፣ የውድድሩን የመክፈቻ ሥነሥርዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ለማካሄድም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ ስፖርትና ትምህርት ተያያዥ፣ ተደጋጋፊ፣ ተወዳዳሪ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ያለው ትውልድ በመገንባት ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተክለ ሰውነቱ የደረጀና ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ ትውልድ በመገንባት ረገድም አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን የማዘውተሪያ ስፍራዎች በአግባቡ በማስተካከል ተማሪዎች በስፖርታዊ ጨዋነት ታንጸው ጤናማና ሰላማዊ የሆነ የውድድር መንፈስን በመላበስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ያጠናክራል ሲሉ አክለዋል፡፡ ውድድሩ በተሟላ እና በተቀናጀ መልኩ እንዲካሄድ ከከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን ሁሉም ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡

በውድድሩ የሚያሸንፉ ስፖርተኞችን ለማበረታታትና ለቀጣይ ውድድሮች መነሳሳትን እንዲፈጥር በማሰብ መጠኑ ባይገለጽም አቅም በፈቀደው ልክ እና ውድድሩን በሚመጥን መልኩ ለመሸለም ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በሁለቱ ቢሮዎች ቅንጅት ውድድሩን በበላይነት ለሚመሩትና ለሚያስተባብሩት የሰውነት ማጎልመሻ መምህራን ክህሎትን ለማሳደግ ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን የአቅም ግንባታ ስልጣናዎችን በመስጠት ዝግጁ ማድረግ ተችሏል። በቀጣይ ስፖርቱ በትምህርት ቤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የመምህራን ወድድር እንደሚካሄድም ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በከተማው ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስምምነት በማድረግ አብረው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸው፤ ከነዚህም ውስጥ ትምህርት ቢሮ አንዱ እንደሆነና ምርጥና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረትም በግንባር ቀደምትነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የተማሪዎች ውድድር ዋና ዓላማው ትምህርት ቤቶች ተተኪ እና ምርጥ ስፖርተኛን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ማሰልጠኛ ማዕከላትን እና ፕሮጀክቶችን በማስፋት እና ታዳጊ ወጣቶች በየእድሜ እርከናቸው የስልጠና እና ውድድር ተጠቃሚ ለማድረግም ነው፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You