የማር ሀብታችን፡-እያጋጠሙ ያሉት ተግዳሮቶችና ተስፋዎች

በኢትዮጵያ የንብ ቀፎን በዛፍ ላይ ሰቅሎ ማር መጠበቅ፣ በማር ቆረጣ ወቅትም ጭስ መጠቀም፣ ማርን ከነሰፈፉ ለገበያ ማቅረብ በኢትዮጵያ የተለመዱ የማር ልማት ሂደቶች ናቸው። ይሁን እንጂ ምርታማነትን ለመጨመር ንቦች የሚቀስሙትን እጽዋት ከማዘጋጀት ጀምሮ በተሻሻሉ ቀፎዎች ንብ የማነብ ሥራን በማከናወንና በማር ቆረጣ ወቅትም አልባሳትን በመጠቀም ባህላዊውን በዘመናዊ የአመራረት ዘዴ በመተካት አጣርቶ መግለጫ ጽሑፍ ባለው ዕቃ አሽጎ ማር ለገበያ ማቅረብ ወደ ዘመናዊ ሽግግር የሚደረግ ሂደት ነው። በዚህ በኩል አሁን አሁን እየታዩ ያሉ ጥረቶች አበረታች ናቸው።

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ፣ ከባእድ ነገር ነፃ የሆነ ተፈጥሯዊ(ኦርጋኒክ)ማር ለገበያ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረትም እንዲሁ ሌላ በዘርፉ ላይ እየታየ ያለ ለውጥ መሆኑ እየተገለጸ ነው። በማር ልማት እንዲህ አበረታች ነገሮች እየታዩ ቢሆንም በጥራትና በመጠን ተወዳዳሪ ሆኖ የዓለም ገበያን ሰብሮ በመግባት በተሻለ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ ግን ሰፊ ሥራዎች ይጠይቃል። የተወዳዳሪነት አቅም ለመፍጠርም ቅንጅታዊ ሥራ ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም የዘርፉ ምሁራን ምክረ ሀሳብ እየቀረቡ ነው።

የተፈጥሮ (ኦርጋኒክ) ማር ወደ ተለያዩ ሀገራት ለገበያ በማቅረብ ከ2010ዓ.ም ጀምሮ በልማቱ ላይ የሚገኘው ግሪን ፌስ ኩባንያ በአጭር ጊዜ የሥራ ቆይታው የዓለም ገበያ የሚፈልገውን ለማወቅ ዕድል አገኝቷል። እንደሀገር የዓለም ገበያን ሰብሮ ለመግባት ገና አቅም እንዳልተፈጠረም ተገንዝቧል።

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ጆኒ ግርማ እንደሚገልጹት፤ በዚህ ወቅት የሚያስፈልገው በተናጠል መንቀሳቀስ ሳይሆን በስልጠና ክህሎት በማስጨበጥ ወጣቶችን አደራጅተው ወደ ልማቱ እንዲገቡ ከሚያደርጉት ተቋማት ጀምሮ በላኪነትና በተለያየ ሥራ በዘርፉ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ተሰባስበው በሀሳብና በተለያየ መንገድ አቅም ፈጥረው ክፍተቱን መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።

አቶ ጆኒ የኢትዮጵያ የማር ምርት በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ኢኮኖሚውን እንዳይመራ ካደረጉት ምክንያቶች ብለው ካነሷቸው መካከል፤ ጥራቱ የተረጋገጠ የተፈጥሮ(ኦርጋኒክ)ማር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስፈልግ ሂደትን ማለፍ ላይ ክፍተት መኖር አንዱ ሲሆን፣ ጥራት ጉድለትን ከሚያስከትሉት ደግሞ ለተለያየ ሰብል ልማት ጥቅም ላይ የሚውሉ ፀረ ተባይና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ይጠቀሳል።የማር ልማቱ ከዚህ አካባቢ የራቀ መሆን ይኖርበታል። እንደ ስኳር ያሉ ባዕድን ነገሮችን መቀላቀልም ለጥራት መጓደል ሌላው ምክንያት ነው።

ዘርፉ የሚፈልገውን ክህሎት ተላብሶ በጥራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለው ጥረት አናሳ ሆኖ መገኘት ገበያው የሚፈልገውን ያህል ማቅረብ እየተቻለ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ጆኒ፣ ዘርፉን የሚመራው አካልም ልማቱ የግለሰብን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ በሀገር ምጣኔ ዕድገት ላይ ያለውን ፋይዳ መሠረት አድርጎ ለመንቀሳቀስ የቁርጠኝነት ማነስ ይስተዋላል ብለዋል።

ለክትትልና ለቁጥጥር ምቹ ያልሆነ የገበያ ሰንሰለት ባለመፈጠሩ አምራቹ ለላኪው የሚያስረክብበት የዋጋ መጠን ከፍተኛና የተለያየ መሆን ለዓለም አቀፍ ገበያ የመሸጫ ዋጋ ላይም ተጽእኖ ማሳረፉን ጠቅሰዋል። ዘርፉ ከባንኮች ብድር ማግኘት አለመቻሉም ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ጠቁመዋል። የማር ጥራትን የሚያረጋግጥ ቤተሙከራ በሀገር ውስጥ አለመደራጀቱም ላኪዎች ለናሙና ፍተሻ ወደተለያዩ ሀገራት ለመላክ መገደዳቸውንና ለወጪም መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የዓለም ገበያው ምርቱ ስለሚከናወንበት አካባቢ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የአምራቾችን ነባራዊ ሁኔታ የሚቃኝ ታሪክ የያዘ መረጃ ጭምር የማወቅ ፍላጎት እንዳለው ኩባንያቸው ተደራሽ በሆነባቸው ገበያዎች የተገነዘበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጆኒ እንዳስረዱት፤ ኩባንያቸውም የዓለም ገበያ የሚፈልገውን መሠረት በማድረግ ንብ አንቢዎችን በማደራጀትና በስልጠና ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ፣ንቦቹ የሚቀስሙትንም እጽዋት በጥንቃቄ በማልማት፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኢሉባቦር ላይ ልማቱ እንዲከናወን በማድረግ ከአምራቾቹ የሚረከበውን የማር ምርት አጣርቶና አሽጎ፣ የምርቱን አጠቃላይ ታሪክ በያዘ መግለጫ እየላከ ይገኛል።

ኩባንያቸው እንደሚያደርገው ላኪዎች የማምረት ሥራ ውስጥ መግባት የለባቸውም። በምርት ሂደት ወቅት ከፀረ አረምና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የፀዳ እንዲሁም ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት የማር ምርት ከአምራቹ ማግኘት ባለመቻሉ ነው ወደ ልማቱ የገባው። የገበያውን ፍላጎት ለማሳየት የሚረዳ ተሞክሮ ለማካፈል እንጂ አንድ ኩባንያ አምራችም ላኪም ሆኖ ሀገራዊ ገጽታ ላይ ለውጥ ያመጣል ከሚል እሳቤ አይደለም። በሌሎች ሀገሮች አምራቾች መጋዘናቸው ድረስ ምርቱን በመውሰድ ነው ትስስሩን የሚፈጥሩት።

ኩባንያው የዓለም ገበያን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የጀመረው ሥራ ሞዴል እንጂ ከፍተኛ መጠን ያለው ማር ለማምረት የሚያስችል እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ጆኒ፤ እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት በመጠንም በጥራትም በማምረት ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላኪዎችም በምርቱ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ነው ያለው።በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበትና የልማቱ ሥራ በሚከናወንበት ሥፍራ ያሉት የቀበሌ አመራሮች ድጋፍና ክትትል ቢጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዘርፉ ተግዳሮት የሆኑትን መፍትሔ በመስጠት መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ነው የተናገሩት።

መፍትሔ ብለው ባነሱት ሀሳብም ወጣቶችን አደራጅቶ በክህሎት በማብቃት በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው። በማር ልማት የሥራ ዕድል የተፈጠረለት አንድ ወጣት በአመት አንድ ቶን ማር እንዲያመርት በማድረግ ምርቱን መጨመር ይቻላል።ማር ለማምረት ብዙ ቦታ አይጠይቅም።ወጪን ለመቀነስም እንደ ቀርከሃ(ባምቡ) ያሉ አካባቢ ላይ በሚገኝ ግብዓት ቀፎ ማዘጋጀት ይቻላል። አንዴ የንብ ቀፎውን ካዘጋጀ በኋላም የሚያደርገው እንክብካቤ አድካሚ አይደለም። ድርሻው የሚሆነው የንግሥቷ ንብ ነው። አንድ ሰው በዚህ መልኩ ተዘጋጅቶ እስከ 60 ቀፎዎች ይዞ ቢሰራ በትንሹ በአመት አንድ ቶን ማምረት ይችላል። ንብን ምቹ ወደ ሆነ አካባቢ በማዟዟርም ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል።

ገበያውንም ቢሆን አምራቹ ከብዛት ለመጠቀም ነው ጥረት ማድረግ ያለበት። አንድ ኪሎ ማር በሁለት መቶ ብር ሂሳብ ለገበያ ቢያቀርብ ይህ ሰው በወር የ16ሺ ብር ደመወዝተኛ መሆን ይችላል። ንብ ማነብ ተጓዳኝ የግብርና ሥራን ለማከናወንም ምቹ በመሆኑ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እድል ይፈጥርለታል።የአምራቹን ተጠቃሚነት በዚህ መንገድ ማሳየት ከተቻለ ምርታማነትን መጨመር ያስችላል።

ትንሽ አምርቶ በከፍተኛ ዋጋ ሸጦ ተጠቃሚ ለመሆን መሞከር የግለሰቡንም ሆነ የሀገርን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ አያስችልም።በተወዳዳሪነት ላይ የሚስተዋለውንም ክፍተት አይቀርፍም። ትንሽ አምርቶ በውድ ዋጋ መሸጥ የሚለው አስተሳሰብ ግን እድገትን የሚገታ እንደሆነ ጠቁመዋል።በብዛት አምርቶ ለላኪዎች ቢያቀርብ ግን አስተማማኝ ገበያ በማግኘት እድገቱን ሊያስቀጥል ይችላል።አምራቾች በራሳቸው ተደራጅተውም ለውጭ ገበያ ለማቅረብም ይነሳሳሉ።ሰፋ አድርጎ ማሰብ ካልተቻለ ችግሮች እየተንከባለሉ ይሄዳሉ እንጂ አይቀረፉም።

ከመንግሥት የሚጠበቀውንም ድርሻ በተመለከተ እንደገለጹት፤ ለማር ምርት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ለዘርፉ የማዋል ተግባር ቢከናወን (ስፔሻላይዝ) ቢደረግ ዘርፉ ልዩ ስለሚያገኝ በምርታማነት ላይም ሆነ በጥራት ላይ የሚነሳውን ክፍተት መቅረፍ ይቻላል። በዘርፉ ላይ የተካነ አምራችም መፍጠር ያስችላል። እንደ ሀገር የተያዘውን የሌማት ቱሩፋት ማሳካት የሚቻለውም ተቀናጅቶና ተናብቦ በመሥራት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በገበያ ላይም ተወዳዳሪ በመሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አቶ ጆኒ እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ያላት የአየር ፀባይና ሥነ ምህዳር ለማር ምርት ምቹ ነው። በሰው ኃይልም ወጣት አምራቾች አሏት። በተለይ ደግሞ ከአራት አመታት በፊት መተግበር የጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የማር ልማቱን ምርታማነት ለመጨመር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው።

ንብ የሚቀስመውን ነገር ማግኘት ከቻለ ጊዜና ወቅትን የሚከተል እጽዋት መጠበቅ ግድ አይሆንም። በሌማት ትሩፋት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትም እንዲሁ ዘርፉን ለማነቃቃት ያግዛል። እነዚህን እድሎች በመጠቀም በዘርፉ ላይ መሥራት ከተቻለ በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት አመታት ጊዜ ታሪክ በመሥራት ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻላል። በተለይም በአመት የማምረት አቅም ወደ 129ሺ ቶን አድጓል ተብሎ በግብርና ሚኒስቴር በቁጥር የተገለጸው ገበያው ላይ ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል።

በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ ገበያ በመፈለግ ዘርፉ ሊታገዝ እንደሚገባና ለዚህም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ እንደሆነ ሀሳባቸውን የሰጡን ደግሞ በዓለም አቀፍ የሥነ- ነፍሳት ሳይንስ ሥነ-ምህዳር ማዕከል (ኢሲፔ) የሞይሽ ፕሮግራም ከፍተኛ አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ ሙላቱ ናቸው። የማር ልማቱ በሀገር ምጣኔ እድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ሥራ እንደሚፈልግ በመጠቆም ስኬት ላይ ለመድረስ የብዙ ተዋናዮች ድምር ውጤት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉት ክፍተቶች መነሻቸው የሚሆነው በአምራቹም ሆነ በላኪዎች ወይንም በግሉ ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ የአቅም ውስኑነቶች እንደሚሆኑ የጠቆሙት አቶ ኢሳያስ፤ ክፍተቶችን ለይቶ የጋራ መፍትሄ በመፈለግ ዘርፉ ከችግር ወጥቶ ለስኬት እንዲበቃ ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚመካከሩበት መድረክ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ኢሳያስ እንዳሉት፤ በአምራቹና በላኪው እንዲሁም በአቀነባባሪው መካከል ደህንነቱና ዘላቂነቱ አስተማማኝ በሆነ ገበያ ውስጥ ግብይቱ እንዲከናወን ማስቻል እንዲሁም አምራቾች በአካባቢያቸው ላይ አቀነባብረው ምርት ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። አሁን ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ባለው ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙም ሥርዓት መዘርጋት ለገበያ ተወዳዳሪነት ዕድል ይፈጥራል። በዚህ ረገድ ኢሲፔ በማር ልማት ላይ አንዱ ባለድርሻ በመሆኑ የገበያው ችግር በዚህ መንገድ እንዲፈታ በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች እገዛ እያደረገ ይገኛል።

በስልጠናና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በስድስት ክልሎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ነው። ኢስፔ አሁን ላይ እያደረገ ያለው ድጋፍ መሠረት የሚጥል እንጂ ዘርፉን በማስቀጠል ረገድ ተዋናይ መሆን ያለባቸው አምራቾችና ከላኪዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በአመት ግማሽ ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማር የማምረት አቅም እያላት ነገር ግን ቀደም ባሉት አመታት ሲመረት የነበረው ከ50ሺ ሜትሪክ ቶን የበለጠ እንዳልነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። የቅርብ ጊዜ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ደግሞ 129ሺ ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም መፈጠሩን ነው።

 ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *