የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች

የኤሌክትሮኒክ ግብይት ልማትና ተጠቃሚነት ላይ የመሪነቱን ድርሻ የግሉ ዘርፍ ነው ተብሎ ቢታመንም መንግሥትም መሠረት በመጣል የንግድ ተቋማትን በማበረታታት ረገድ የራሱን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል። “የኤሌክትሮኒክ ግብይትን እና ዲጅታል ኢኮኖሚን” ለማጠናከር የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መካከል የአሥር ዓመቱ የልማት እቅድ፣ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ፣ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ፣ ብሔራዊ የዲጅታል ክፍያ ስትራቴጂ፣ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ስትራቴጂ እና ሌሎች ይገኙበታል።

የኤሌክትሮኒክ ግብይትን እና ዲጅታል ኢኮኖሚውን ጅምር በሚባል ደረጃ የሚገኝ ቢሆንም በሂደቱ ላይ በርካታ ተግዳሮቶች ተያይዘው ይነሳሉ። ይህንን አስመልክቶ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ የንግድ ማህበራት ምክር ቤትና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ ‹‹ኢኮሜርስ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ጉዳይ የመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ አዘጋጅተው እንደነበር የሚታወስ ነበር። በምክክር መድረኩም ኢኮሜርስ በተመለከተ ጥናታዊ ጹሑፍ ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ በጥናታዊ ጽሑፉ የተገለጹ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ምላሽ የሰጠበት መድረክ ነበር። የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው ሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ያዘጋጀውን ዳሰሳ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።

በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንዳሉት፤ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስ አሠራር ማስፋፋት ተግዳሮት የሆኑ ዋና ዋና ችግሮች ለይቶ በደረጃ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ አስቀምጧል። ስትራቴጂው አጠቃላይ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ ንግዱ የሚመራበት የአሠራር ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል መፍትሔ የሚያመላክት ነው። ከእነዚህ በተጨማሪም ኢ-ኮሜርስን በማንቀሳቀስ ረገድ ቁልፍ ሚና ያላቸው የንግድ ዘርፎች እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ እና ዘርፉ እንደ አንድ ወሳኝ ዘርፍ እንዲታይ ለማስቻል እቅድ ተይዞ ሲሰራ ነበር።

“በስትራቴጂ እቅዱ የተያዙት ዋና ዋና ጉዳዮችን ተግባራዊ ለማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል” የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከእነዚህ ውስጥ የኢኮሜርስ ኤሌክትሮኒስ አሠራርና ሌሎችም ግንኙነቶች የሕግ መሠረት እንዲኖራቸው የሚያደርገው ‘የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን’ አዋጅ እንዲቋቋም በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። ኢኮሜርስና ሌሎች ለኢኮሜርስ ወሳኝ የሆኑ ዘርፎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ውስጥ እንዲካተቱም መደረጉንም አንስተዋል። ለ-ኢኮሜርስ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የዲጅታል ንግድ ሥርዓቶች እንዲስፋፉ ተደርጓል። የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተነድፎ ሥራ ላይ ውሏል። ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የኢኮሜርስ መስፋፋት የሚያግዙ የሙከራ ፕሮጀክቶች ለጀማሪ ኢኮሜርስ ካምፓኒ፣ ለፋይናንስ ኤጀንቶችንና የኢ-ኮሜርስን የሚመለከቱ ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ የማስፋፊያ ፕሮግራሞች ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉንም አብራርተዋል። በዘርፉ በርካታ የንግድ ተቋማት በኢኮሜርስ ሥራቸውን እያስፋፉ እና ህብረተሰቡ የኢኮሜርስ አሠራር እየተለማመድ ይገኛል በማለትም ተናግረዋል።

‹‹ኢኮሜርስ በቀጣይ የሚደረጉ ማንኛውም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። የኢኮሜርስ እድገት ለማፋጠንና የሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በርካታ ሥራዎች የሚጠበቁ በመሆኑ በመንግሥት ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን የግሉ ዘርፍም የሚሠራው ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዘበዋል። የኢኮሜርስ እድገት ለጤናማ ንግድ ውድድር መጠቀም ያለበት ሆኖ ሳለ የዘርፉን እድገት ሊጎዱ የሚችሉ አካሄዶችንና አሠራሮችን ህብረተሰቡ እና ሀገር ሊጎዱ እንዲሁም የዘርፉ እድገት ሊያቀጭጩ የሚችሉ በመሆናቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ የኢኮሜርስ እድገት በዋናነት ከተማውንና የገጠሩን ህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የግሉ ዘርፍ አማካሪ አቶ ብሩህ ገመዳ በበኩላቸው < ኢኮሜርስ በኢትዮጵያ> በሚል ርዕስ ጥናት ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናታዊ ጽሑፍ በኢኮሜርስ ዘርፍ የሚጋጥሙ ተግዳሮቶች በስፋት ለመዳሰስ ሞክረዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢኮሜርስ የኢንተርኔት፣ የዲሊቨሪ (ቤት ለቤት የማድረስ)፣ የክፍያ አገልግሎቶች እና መደበኛው ግብይት በኤሌክትሪክ ግብይት ዘዴዎች ተጠቅሞ ማሳለጥን የሚያስችል ነው። መደበኛ የንግድ እቃዎች ብቻ ሳይሆን ዲጅታል የሆኑ የማይዳሰሱ እቃዎችን ግብይትም የሚመለከት ነው። ኢ-ኮሜርስ በሁለቱም ንግድ ላይ የተሰማሩ ማህበረሰቦች ወይም ቢዝነሶች ያካተተ ነው።

በኢትዮጵያ ዲጅታል ኢኮኖሚው ለውጥ ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብሩህ ፤ ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንፃር ብዙ እንደሚቀር ይናገራሉ። በጥቅሉ በዚህ ዘርፍ ገና ጀማሪ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሆንን አብራርተዋል። ኢ-ኮሜርስ ላይ የውጭ ሀገራት ተሞክሮ በዋናነት ኢኮኖሚውን የሚመሩ ዘርፎች እንዴት አድርጎ በዲጅታላይዘሽን መደገፍ እንደሚቻል ትኩረት አድርገው ይሰራሉ ብለው፤ በዚህም ሀገር “ኢ-ኮሜርስን እንዴት መደገፍ ይቻላል” የሚለው ጉዳይ ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

አቶ ብሩህ፤ ወደፊት ከሁሉም ዘርፎች በላይ ትልቁን የሰው ኃይል ሊይዙ የሚችለው (ወጣቱን ወጣቱን በስፋት የሚያሳትፍ) አገልግሎት ዘርፍ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ዋነኞቹ ኢ-ኮሜርስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና መሰል የቴክኖሎጂ አይነቶች መሆናቸውን ይናገራሉ። ከዚህ አንጻር ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና ማበልጸግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። የኢ-ኮሜርስ ዘርፍ በአንድ መሥሪያ ቤት የሚሰራ ሳይሆን የሁሉም ዘርፎችን ድጋፍ እና ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

በኢ-ኮሜርስ የታዩ ቁልፍ ተግዳሮቶች በጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ የዳሰሱት አቶ ብሩህ፤ አነስተኛ ኢንቪስትመንት እና ፋይናንስ አለመኖር፣ የመንግሥት ድጋፍ አነስተኛ መሆን፣ የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት ጥምረት አለመኖረ፣ ስለ ኢ-ኮሜርስ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና አመኔታ ማጣት፣ የፖስታ አገልግሎትና የአድራሻ ሥርዓት ደካማነት እንዲሁም አለመጠናከር፣ የመሠረተ ልማት አለማሟላት፣ የዲጅታል ቴክኖሎጂ እውቀት አነስተኛ መሆን፣ የግለሰብ መረጃ (ዳታ) ደህንነት ጥበቃ አለመኖር፣ የሳይበር ደህንነት እና የመሳሰሉት እንደ ምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ አነስተኛ መኖር፣

አቶ ብሩህ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ኢ-ኮሜርስ ዘርፍ ላይ ለመሥራት የሚፈልጉ አነስተኛ ካፒታል ሀሳብና እውቀትን ይዘው ለሚነሱ ወጣቶች አዳጋች መሆኑን ይናገራሉ። የፋይናንስ እጥረት በተለይ ደግሞ በአብዛኛውን ውስን ሀብት ላላቸውና ስኬታማ ለመሆን ሰፊ ኢንቨስትመንት ለሚፈልጉት ፈታኝ ሊሆን የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ሆነ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት ከባንኮች ብድር ለማግኘት ይቸገራሉ ብለዋል።

ኢኮሜርስ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ለተወሰነ ዓመታት ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ቢደረግ እና የውጭ ኢንቨስትመንቶች ለመሳብ የሚደረገውን አይነት ማበረታቻ ቢሰጣቸው ሊበረታቱ እንደሚችሉ አመላክተዋል እንደ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት ጥምረት አለመኖር፣

አቶ ብሩህ በጥናታቸው ላይ የክፍያ ሥርዓቶችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲሆን ማድረግና እነዚህ መንገዶች በአንድ አጣምሮ መሄድ ላይ እጥረት መኖሩን ያነሳሉ። ነገር ግን የዲጅታል የክፍያ ሥርዓቱን አንድ ላይ አጣምሮ መሥራት የሚያስችል ሥራን ለመሥራት አቅም እንዳለ አንስተዋል። ለምሳሌ እንደ “ኢትስዊች” አይነቶች የዲጅታል ክፍያን በአንድ አጣምሮ የያዝ አሠራር ሁሉንም የባንክ አገልግሎት በአንድ ላይ በማጣመር በአንድ “ኤቲ ኤም ካርድ” ሁሉም የባንክ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ነው። “ከሞባይል ባንኪንግ ወደ ዋሌት፤ ከዋሌት ወደ ሞባይል ባንኪንግ የሚደረጉ አሠራሮች እና፤ ማህበራዊ ሚዲያውን ሆነ የክፍያ ሥርዓቱን በአንድ ላይ ማጣምር ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂው አለ፤ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የሚችሉ ተቋማት ስላሉ ሊጠናከር ይገባል” በማለትም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የዲጅታል መሠረት ልማት እጥረት

ሌላው አቶ ብሩህ ያነሱት የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማከናወኛ በቂ የዲጅታል መሠረት ልማትና ቴክኖሎጂ አለመኖሩን ነው። አሁን ያለውም መሠረት ልማት የኤሌክትሮኒክ ግብይት ለማካሄድ የንግድ ተቋማትን እና የደንበኞች ግንኙነት የሚገድብ ብሎም ሸማቾች በኢንተርኔት አማካይነት ግዢዎችን እንዳይፈጽሙ እንቅፋት የሚፈጥር እንደሆነ ነው የጠቆሙት።

የዲጅታል ቴክኖሎጂ እውቀት አነስተኛ መሆንና አመኔታ ማጣት

“በንግድ ተቋማት ሆነ በፖሊሲ አውጪዎች የዲጅታል ንግድ ጠቀሜታዎችን በተመለከተ የግንዛቤና የእውቀት ማነስ ይስተዋላል” በማለት በጥናታቸው የጠቆሙት አቶ ብሩህ በሌላ በኩል ደንበኞች በኤሌክትሮኒክ የንግድ ግብይት ላይ አመኔታ እንደሌላቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙ አንስተዋል።

ደንበኞች ቴክኖሎጂው አምነው አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትኛውን አዲስ ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ግንዛቤ መፈጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። የኢ-ኮሜርስ ግብይቱ የክፍያ ሥርዓቱ ፈጣን በሆነ መንገድ ወዲያውኑ እንዲከናወኑ በማድረግ ክፍያውን ወዲያው ከፍለው አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። አለበለዚያ ከፍዬ አገልግሎቱን ባላገኝስ የሚል ስጋትን ስለሚያሳድር አመኔታው መቀነሱን እንደ ምክንያት አስቀምጠዋል።

የፖስታ (ዴሊቨሪ) አገልግሎት እና የአድራሻ ሥርዓት ደካማ መሆኑ

በኢትዮጵያ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ግንኙነት የምናደርግበት መንገድ ቢኖርም፤ አሁንም ድረስ የቁሳቁሶችና የሽቀጦች ላይ የተመሰረተ ሰነዶች በመላው ዓለም የሚጓጓዙበት አሠራሮች አልቀሩም። ለዚህም የሚሆን የኢንተርኔት መገበያያ መድረኮች እና ዲጅታል የክፍያ ሥርዓቶች እድገት ቢኖርም ፤ ቁሳቁሶችን ግን የግድ ለደንበኞች ካሉበት ቦታ መድረስ የሚያስችል ቀልጣፋና ፈጣን የፖስታ አገልግሎት ሊኖር እንደሚገባ ይናገራሉ። የፖስታ አገልግሎት ማሻሻልና የከተሞችን እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶችን የአድራሻ ሥርዓቶች የማዘመን ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዳልተሰጠው ይናገራሉ።

“የፖስታ መልዕክት (ዲሊቨሪ) አገልግሎት ከሌለ ዲጅታል ቴክኖሎጂን ኢ-ኮሜርስን ማሰብ አይቻልም” የሚሉት አቶ ብሩህ፤ ሌላው ሀገር ተሞክሮ እንዲሚያሳየው ማንኛውም የመንግሥት ከዜጎች ጋር የሚደረግ የሰነድ ግንኙነቶች እና ኮሙኒኬሽን በፖስታ በኩል መሆኑን ያነሳሉ። የፖስታ አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋት ስለሚያስፈልግ እያንዳንዱ የአዲስ አበባ የመንገድ አሠራር ላይ እንዲገቡ ማድረግና የቴክኖሎጂ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ይገባል ይላሉ።

የሳይበር ደህንነት

አቶ ብሩህ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ የሀገሪቱ የሳይበር ደህንነት አቅም ማሳደግ ለዲጅታል ኢኮኖሚው እድገት እንዲሁም እስካሁን ድረስ በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን አስጠብቆ ለመቀጠል እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ። ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ጊዜ የግሉም ሆነ የመንግሥት ዘርፉ የሳይበር ጥቃት የሚያደርሰውን ጉዳት በጥልቀት በመገንዘብ ረገድ ያላቸው ግንዛቤ አነሰተኛ መሆን አንሰተዋል።

የግል መረጃ ጥበቃ አለመኖር

አቶ ብሩህ ገመዳ በማጠቃለያ ሀሳባቸው ላይ ድንበር ተሻጋሪ የመረጃ ፍሰትን የሚቆጣጠር አዋጅ አለመኖር፣ ከሀገር ውስጥ መረጃ ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ ወይም ፖሊሲም አለመኖር በእጥረት የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል።

እነዚህ በጥናት ላይ የቀረቡትን ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ውይይት ከተደረገ በኋላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በተነሱት ሀሳቦች ላይ ማጠቃለያ ሰጥተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 በግልጽ እንዳስቀመጠው ዘርፉ በግል ተዋንያን እንደሚመራው የሚያሳይ ነው። ይህንን በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ለግል ዘርፉም ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለበት። እነዚህ በኢ-ኮሜርስ ዙሪያ የተነሱ ተግዳሮቶች ለመፈታት መንግሥትና የግል ዘርፉ ተቀራርቦ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል። የግል ዘርፉ ለኛ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

“እንደ ሀገር የአሥር ዓመት የዲጅታል የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ ተነድፎ ሥራዎች እየተሠሩ ነው” የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በዚህ ትኩረት ተሰጥቶቸው ከሚሰሩ አምስት ዘርፎች አንዱ የአይሲቲ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል። የአብዛኛዎቻችን ሕይወት ወደ ዲጅታል እየተቀየረ ባለበት( የትምህርት፣ የጤና እና የመሳሰሉ ብዙ ዘርፎችም) በዚህ ዘመን እንደ ሀገር ከዓለም ጋር መራመድ ስላለብን የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የነበሩ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ነው። የመሠረተ ልማት ችግሮች፣ የዲጅታል አሠራርን የዲጅታል መታወቂያ፣ የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት፣ የሳይበር ደህንነት በተመለከተ የሚያስፈልጉ ፕላትፎርሞችን በመሆናቸው ለእነዚህ ሁሉ አስፈላጊ የሆኑ ምቹ ከባቢ ተዘርግቶ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *