አዳማ፤ ህብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ ለፍትሀዊ ተጠቃሚነት እየሰሩ መሆኑን የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው የማህበራቱንና ኢንዱስትሪ ግብዓት ትስስርን አስመልክቶ በአዳማ ሪፍት ቫሊ ሆቴል ትናንት በተካሄደው የውይይት ላይ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ እንዳሉት የህብረት ሥራ ማህበራት ከአምራቹ ጋር ባላቸው ቀጥተኛ ግንኙነት ግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚነቱን በማረጋገጥ ላይ ናቸው።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ መንግሥት ህብረት ሥራ ማህበራቱን ገበያ መዳረሻዎች በማስፋት ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው፡፡በተለይ የህብረት ሥራ ማህበራት በከተሞች ከሚገኙ የሸማቾች ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠራቸው ህብረተሰቡ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እያደረጉ ናቸው።
ማህበራቱ የግብርና ምርት በስፋት ከሚጠቀሙ መንግሥታዊ ተቋማት ማለትም ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት ጋርም የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አብዲ ገለጻ፣ ማህበራቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የምርት መጠንና ጥራት ማሳደግ አለባቸው።እንዲሁም በመንግሥት በኩል ደግሞ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት፣ የእውቀትና ክህሎት ክፍተታቸውን መሙላት ያስፈልጋል።
በፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ከፍተኛ የግብይት ባለሙያ የሆኑት አቶ መኳንንት አዱኛ ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ህብረት ሥራ ማህበራት በምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂ ፣ በምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችና ሌሎች ዘርፎች በመሰማራታቸው ከ 22 ነጥብ 9ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት ችለዋል፡፡ ህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻርም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በአሁኑ ወቅትም 85 ሺ 496 መሰረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት፤ 388 ህብረት ሥራ ዩኒኖች እንዲሁም ሦስት ህብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች መኖራቸውን ጠቅሰው አብዛኞቹም ግብርና ምርቶችን ወደ ተጠቃሚው በማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ የግብይት ዳይሬክተር አቶ ሙሉሸዋ በቀለ በበኩላቸው ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በተደራጁት የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የኅብረተሰቡ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ለማለት ባይቻልም አምራችና ሸማቹን በማገናኘት በኩል ሚናቸው ቀላል አለመሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
በእፀገነት አክሊሉ