ሀምበሪቾ ዱራሜ እግር ኳስ ክለብ በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከተቀላቀሉት ሦስት ክለቦች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ክለቡ በተመሰረተ በስምንተኛ ዓመቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን መቀላቀል ችሏል። ይህንን ተከትሎም በ2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ጠንካራ ቡድን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ሀምበሪቾ የወንዶች እግር ኳስ ክለብ የተመሰረተው በ2007 ዓ.ም ሲሆን፤ የሴቶቹ ደግሞ በ2014 ዓ.ም ተመስርቶ በተለያዩ የእግር ኳስ ደረጃዎች ሲወዳደር ቆይቶ በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት በሁለቱም ጾታ የኢትዮጵያ የወንዶችና ሴቶች ፕሪሚየር ሊግን ተቀላቅሏል። በወንዶች ምድብ የከፍተኛ ሊግ ቆይታው በምድብ ‹‹ሐ›› ተደልድሎ ሲወዳደር የነበረ ሲሆን፤ ጠንካራ እና ፈታኝ በሆነው የውድድር መድረክ በአስደናቂ ሁኔታ ከፍተኛ ነጥብ በመሰብሰብ በበላይነት አጠናቆ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን እንደተቀላቀለ ይታወሳል።
ክለቡ ከተመሰርተ በኋላ ውድድሩን በክልል ክለቦች ቻምፒዮና ተሳትፎ በመጀመር እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በአንደኛ ሊግ ቆይታ አድርጓል። ቆይታውን በበላይነት በመፈጸም ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችሏል። ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ሲወዳደር ቆይቶም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከነበረበት ምድብ የላቀ ውጤትን አስመዝግቦ ሦስተኛው የፕሪሚየር ሊጉ አዳጊ ክለብ መሆኑን አረጋግጧል። የክለቡ የከፍተኛ ሊግ ቆይታ ፈታኝ መሆኑን፣ በተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ጥረትም ማደጉ እውን መሆኑን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳግም ማርቆስ ለአዲስ ዘመን በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል።
ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ ቆይታ በ2013 ዓ.ም 2ኛ፣ 2014 ዓ.ም 3ኛ እንዲሁም ዘንድሮ አንደኛ ደረጃን በመያዝ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ሊቀላቀል ችሏል። በዚህም የክለቡ ደጋፊዎች ቡድኑ በተጓዘበት የውጤት መንገድ ያለምንም መሰልቸት ድጋፋቸውን በመስጠታቸው የእነሱ ጥረት ከፍተኛ ነበር። ስለሆነም ይህንን የውጤት ሰንሰለት ማስቀጠልና ለፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ቡድን ይዞ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
መቀመጫውን በደቡብ ክልል ከምባታ ዞን፣ ስያሜውን ደግሞ በዞኑ ውስጥ በሚገኝ ተራራ አድርጎ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግን መቀላቀል የቻለው ሀምበሪቾ ዱራሜ፤ በሊጉ ቀላል የሚባል ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ አይታሰብም። ክለቡ በሊጉ ከውጤት ባሻገር ሊገጥሙት የሚችሉትን ተግዳሮቶች አሸንፎ ለመቆየትና ተፎካካሪ ቡድን ይዞ ለመቅረብ እንደተዘጋጀም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
ክለቡ በመንግሥት በጀት የሚደገፍ እንደመሆኑ ህዝባዊ መሰረትን በማስያዝ ጠንካራ ቡድን ለመገንባት ታቅዷል። ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በዝውውር መስኮቱ ውላቸውን የሚያድሱትን ተጫዋቾች ጨምሮ አዳዲስ ወጣትና ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች በማስፈረም ጠንካራ የእግር ኳስ ክለብ እንደሚሰራም ሥራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ። ክለቡ በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎን እያደረገ አይገኝም ለሚለው ጥያቄ ጊዜው ገና መሆኑንና ክለቡን የማጠናከር ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለመደውና ብዙዎችን ከማነጋገር አልፎ ክለቦቹን ውዝግብ ውስጥ ሲከት የቆየው የፋይናንስ ጉዳይ ክለቡን እንዳይገጥመውና በፋይናንስ ጠንካራ እንዲሆን ሰፊ ሥራ መሰራት እንደሚኖርበትም እምነታቸው ነው። ህዝባዊ መሰረት ያልያዘ ክለብ ሁሌም ችግር እንደሚገጥመው የጠቆሙት አቶ ዳግም፤ እንደ መንግሥት የበጀት እጥረት፣ የደመወዝና ሌሎች ችግሮች በመኖራቸው በመንግሥት ፋይናንስ መካተታቸው ግዴታ ቢሮክራሲውን እንዲጠብቁ አስገድዷቸዋል። በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍና ክለቡን ህዝባዊ መሰረት በማስያዝ ጠንካራ የደጋፊ ማህበር ተቋቁሞ የክለቡን የገቢ ምንጭ በማሳደግ ቢያንስ ደመወዙን በአግባቡ የሚከፍል በትንሽ ብር ጠንካራ እግር ኳስ ክለብ የመገንባት ውጥን እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ሀምበሪቾን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያሳደገው አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ከክለቡ ጋር ለመቀጠል ስምምነት የፈጸመ ሲሆን፤ በውሉ መሰረትም ለአንድ ዓመት ከክለቡ ጋር የሚቆይ ይሆናል። አሰልጠኙ በአንድ ዓመት ቆይታው ክለቡን በሊጉ ጠንካራና ተፎካካሪ የማድረግና በሚመዘገበው ውጤት መሰረት ቆይታውን በመነጋገር እንደሚወሰንም ተጠቅሷል። በቀጣይ በክለቡ የሚቆዩትና ክለቡን የሚቀላቀሉት ተጫዋቾች ከታወቁ በኋላ አሰልጣኙ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት ክለቡ በአጭር ጊዜ ዝግጅት እንደሚጀምሩም ታውቋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2015