ሰንኮፍ በማለዳ
ስለዛሬው ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ እንግዳ ያወጋኝ ባጋጣሚ ያወኩትና አብሮት የሚማር የኋላ እሸት ተስፋው የሚባል ጓደኛው ነው። የኋላ እሸት ስለዚህ ሰው ሲነግረኝ ብርቱና ፍላጎቱ የላቀ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ ነበር። ዕድሜውን ሙሉ በሕይወት ፈተናዎች መሀል ስለማለፉ ሲያጫውተኝ ደግሞ ይበልጥ ትኩረቴን ሳበው። ጊዜ አልወሰድኩም። የዚህ ሳምንት እንግዳዬ እንዲሆን ወዳሰቡት ረመዳን ዘንድ ፈጥኜ ደወልኩ።
በቀጠሯችን መሠረት አራት ኪሎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በር ላይ ልቀበለው ወጣሁ። ለረመዳን ከሕንፃው በር ጀምሮ በዊልቸር ለመግባት አመቺ አልሆነም፤ ደረጃዎቹም ቢሆኑ እሱን ለማሳለፍ ዝግጁ አልነበሩም። ምርጫ አልነበረንም። ከግቢው አጸድ አረፍ ብለን ወጋችንን ጀመርን።
ረመዳን ናስር ይባላል። በ1978 ዓ.ም ነው የተወለደው። ከአባቱ ጋር 22 በሚባል ሰፈር ለዓመታት ቆይቷል። አሁን ደግሞ አውቶቡስ ተራ አካባቢ እየኖረ ነው። ቀድሞ ከነበረበት ስፍራ አሁን ወዳለበት የመምጣቱ ምክንያት እሱና አባቱ ኑሮ ስለከበዳቸውና ዘመድ ዘንድ ለመጠጋት ነበር። የረመዳን ወላጅ እናት ገጠር ውስጥ ይኖራሉ። አባቱም ከተማ ከመጡ ወዲህ ኑሮ ቀላል አልሆነላቸውም። ለረመዳን ደግሞ ሕይወት ከዚህም በላይ ከባድ ነበር።
ረመዳን ከአንዲት ሴት ቤት በጥገኝነት ተዳብሎ ዓመታትን አሳልፏል። ወይዘሮ ኑሪቱ ይባላሉ። ረመዳን ስለ ወይዘሮዋ አውርቶ አይጠግብም። እኝህን ሴት ሲያስብ ሁሌም መልካም ሰዎች በምድር ላይ ይሞሉ ዘንድ ይፀልያል፤ በእሳቸው ብዙ ችግሮቹን አልፏልና።
ረመዳን በተወለደ በሁለት ዓመቱ እንደ እኩዮቹ ቆሞ ያለመሄዱ ለቤተሰቦቹ ሃሳብ ሆነ። እስከዚህ ዕድሜው ድረስ ግን ችግሩ ምን እንደሆነ የተረዳው አልነበረም። አካባቢው ገጠር መሆኑና ጤና ጣቢያ ያለመኖሩ ለችግሩ መላ ማጣት ምክንያት ሆኖ ቆየ። ቤተሰቦቹ ግን ይህንንኑ ሰበብ አድርገው ዝም አላሉም። ወደ ባህላዊ ህክምና ወሰደው የአቅማቸውን ሞከሩ። በወቅቱ የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም ዘላቂ መፍትሄ አልተገኘም።
አራት ዓመት እንደሞላው አባቱ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ አመጡት። ጥቂት ቆይቶም አጎቱ በወቅቱ በኤርትራ አሰብ ግዛት ይሰሩ ስለነበር ወደዚያው ይዘውት ሄዱ። ይህን ማድረጋቸው በአካባቢው ሙቀት ይሻለዋል በሚል ተስፋ ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን ረመዳን እንደታሰበው ሊሻለው አልቻለም።
10 ዓመት እንደሞላው ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ከአባቱ ጋር ሆኖም አስቸጋሪውን ሕይወት ይገፋ ጀመር። በእግር ቆሞ የመሄድ ህልሙ አልተሳካም። ከዊልቸር ላይ ተቀምጦ ለመንቀሳቀስ ተገደደ።
ረመዳንና ሥራ
በተቻለው አቅም ሁሉ ሰርቶ ማደርን ይሻል፤ ምንጊዜም ከሰው ባይጠብቅ ይመርጣል። እስከዛሬ በዊልቸር እየተንቀሳቀሰ ብዙ ነገሮችን ሰርቷል። ‹‹ጀብሎ›› በአንገቱ ይዞ እያዞረ ሲሰራ ቆይቷል። በፈለገው መጠን መንቀሳቀስ ያለመቻሉ ከባድ ፈተና ሆኖበት ሥራውን ሊያቆም ተገደደ።
ለእሱ በእንዲህ ዓይነቱ ውሎ መሰማራት እጅግ ያሰለቻል። አንዳንዴም እጁ እየዛለ የሚሰራው ይጠፋዋል። ወደ ትምህርት ቤት ሲመጣና ሲሄድ በዊልቸር ስለሚጠቀም ዳገታማ ቦታዎች ሲደርስ ይደክመዋል። ብዙ ነገሮች ቢታክቱትም ለመኖር ሲል ውጣ ውረዶችን መጋፈጥ ነበረበት።
‹‹ትምህርት ከረፈደ››
ረመዳን በልጅነቱ ትምህርት አልጀመረም። እሱና ቀለም የተዋወቁት በ18 ዓመቱ ነበር። በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ከ9 እስከ 12 ክፍል ተምሯል። በ2004 ዓ.ም ደግሞ የማትሪከ ውጤት አምጥቶ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አካውቲንግ ዲፓርትመንትን ተቀላቀለ።
በወቅቱ እሱን የሚያግዘው ከጎኑ አልነበረም። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖም ቀድሞ ያመው የነበረ እግሩ ክፉኛ ባሰበት። ባህርዳር ሲደርስ ህመሙን መቋቋም አልቻለም። ትምህርቱን አቋርጦ ከመመለስ ሌላ ምርጫ አልነበረውም። በጊዜው ሁኔታውን የማስረዳትና የድጋፍ ደብዳቤ የማጻፍ ዕድል አላገኘም።
በባህርዳር ሦስት ዓመታት ቆይቶ አዲስ አበባ ሲመለስ፡ ስለነገሮች ደጋግሞ አሰበ። ያለፈበት መንገድ፣ የወደፊት ሕይወቱና አሁን ያለበት አቋም ዕንቅልፍ የሚያስተኛው አልሆነም።
ከቀናት በአንዱ ቀን ግን ከአንድ መልካም ሰው ጋር ተገናኘ። እርሳቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙሉ ወጪውን እንደሚሸፍኑለት ቃላቸውን ሰጡት። ረመዳን ለዓመታት ከተራራቀው ትምህርት ጋር ዳግም ሊገናኝ ሆነ።
አግዙኝ
በዩኒቨርሲቲው ግቢ አብዛኞቹ ይንከባ ከቡታል። አንዳንድ መምህራንም አስተማሪዎቹም ምግብና ገንዘብ በማገዝ ያበረታቱታል። ሕንፃዎቹ ለአካል ጉዳተኛ ምቹ አለመሆናቸው ደረጃ ወጥቶና ወርዶ እንዲማር አላደርገውም። ችግሩን የተረዱ መምህራን ግን እሱ ባለበት የታችኛው ወለል በመምጣት ሊስተምሩት ይፈቅዳሉ። እንዲህ በመሆኑ ሁሌም ደስተኛ ነው።
ለረመዳን ከስድስት ኪሎ መርካቶ በዊልቸር መመላለስ ከባድ ነው። ለዚህም ማደሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ። ምላሹ ግን እንደጠበቀው አልሆነም። ‹‹ዶርም›› መስጠት እንደማይቻል ተነገረው። ጠዋትና ማታ በመመላለስ መጠየቁ አሰልቺ ነበር። ለአካል ጉዳተኛ ምቹ ባልሆነው ግቢ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ምቹ ባልሆነው አሠራር ሊፈተን ተገደደ።
ረመዳን ሌሎች አማራጮችን ፈለገ። ጎተራ፣ መርካቶ እና የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙና ለአካል ጉዳተኞች የሚረዱ ባለሞተር ዊልቸርና ሞተር ሳይክል እንዲሰጡት ቢጠይቅም ዕድለኛ አልሆነም። ሁሌም ስልኩን ተቀብለው፤ ድምጻቸውን ያጠፋሉ።
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 4ተኛ ዓመት ማናጅመንት ተማሪ ሲሆን ሊመረቅ እየተቃረበ ነው። አሁንም ግን በትምህርቱ ላይ ብዙ እክሎች አሉበት። በተደጋጋሚ እየረፈደበት በሰዓቱ መድረስ አልቻለም። በአንድ አጋጣሚ ጨረር ዓይኑ ላይ በማረፉም ህመም ጀምሮታል። ወደ ጤና ጣቢያ ሄዶ መነጽር ቢሰጠውም ለውጡ እምብዛም ያለመሆኑ ያሳስበዋል። በችግሮቹ ላይ ሌሎች ችግሮች ቢደረቡም ረመዳን በፈተና ወድቆ አልቀረም። ዛሬም በጥንካሬው በርትቶ ከኑሮ ጋር ግብግብ ገጥሟል።
ገጠመኝ
ረመዳን እስከዛሬ ባለፈባቸው በርካታ ገጠመኞች ይገረማል፣ ይናደዳል፣ ይተክዛል። አልፎ አልፎም ከልቡ ይስቃል። አንዳንድ ጊዜ እርሱ በፍጥነት ለመሄድ ዊልቸሩን ሲገፋ ብዙዎች ከፊት ወደ ኋላ ስለማይመለከቱት ዞር በሉልኝ ብሎ እስከ መናገር ይደርሳል።
አልፎ አልፎ ደግሞ አንዳንዶች «እንርዳህ» ይሉትና ዊልቸሩን መግፋት ዳገት ይሆንባቸዋል። በተለይ ደግሞ በአባጣ ጎርባጣ መንገዶች ላይ ሲሆን ፍዳውን ያያል። ብዙዎችን አጋጣሚዎች ታዲያ በትካዜና በቀልድ አዋዝቶ ያልፋቸዋል።
በአንዱ ቀን የገጠመውን ግን ረመዳን መቼውንም አይዘነጋውም። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለምዶ አምስተኛ በር በሚባለው በር የምሽት ትምህርቱን አጠናቆ ከግቢ ይወጣል። ይሁን እንጂ ታክሲም ሆነ አውቶቡስ ሊያገኝ አልቻለም።በሰዓቱ ያሰበውን ቢያገኝ እንኳን ግፊያውን ስለማይችለው በቀላሉ አይዳፈርም። ለመሄድ ቢሳካለትም የመጓጓዣ አቅም ስለሚያጥረው ይሸማቀቃል።የዚያን ዕለትም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ከክፍል ወጥቶ ዊልቸሩን እየገፋ ወደ ሰፈሩ ያመራል።
«አፍንጮ በር» አካባቢ ሲደርስ ግን ያልታሰበ ኃይለኛ ዶፍ ይወርድበት ጀመር። በዕለቱ ደብተሩን ጨምሮ በርካታ ሰነዶች ይዞ ስለነበር እንዳይሆን ተበላሹበት። በመንገዱ ከባድ ጎርፍ መኖሩ ደግሞ ዊልቸሩን እያንሳፈፈ ለመውሰድ አንገዳገደው።ዛሬ ላይ ያቺን ቀን ሲያስታውሰ «በፈጣሪ እርዳታ አለፍኳት» ይላል።
ነገ ያስጨንቀኛል
ረመዳን ስለ ነገ ብዙ ነገሮችን ያልማል። የመጀመሪያ ዲግሪውን ለመያዝ በርካታ ዓመታትን ተጉዟል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የቅርብ አጋዥ ማጣቱ ነው። ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑና እነርሱን ብቻ ያማከለ ትምህርት ቤት ያለመኖሩ በወቅቱ ትምህርት ለመጀመር አልታደለም። ግና በ18 ዓመቱ ‹‹ሀ›› ብሎና ከፊደል ተዋውቆ ዲግሪውን ለመያዝ ሲንደረደር እንሆ! 37ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል ።
በእነዚህ ውጣ ውረዶች መሀል አልፎና የጤና እክሉን ተቋቁሞ ራሱን ለማሸነፍና ከጥገኝነት ለመውጣት ሁሌም እንዳሰበ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ነገ ሲያስብ ብዙ ነገሮች ያጨንቁታል። ሥራ ለማግኘት ካለው ውጣ ውረድ ጋር በየቦታው ዞሮ ማስታወቂያን ለማንበብ ሲያስብ ከአሁኑ ይደክመዋል። እንግልቱም ይታየዋል። በርካታ ተቋማት አሳንሳር ‹‹ሊፍት›› የሚጠቀሙ ናቸው። ለእርሱ ግን ደረጃዎችን ለመውጣትና ለመውረድ የሚወስደውን ጊዜ ያስባል።
ለአካል ጉዳተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በሰፊው አለመገ ኘታቸው፣ ማህበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው ንቃተ ህሊና ያለማደጉ፣ በመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ውስጥ አካል ጉዳተኞች በቂ ትኩረት ያለማግኘታቸው ሁሉ ያሳስበዋል።
አሁን ባለው የሕዝብ መጨናነቅና ትራንስፖርት እጥረት ብሎም አመቺ ጎዳናዎች አለመኖር ነገን ለመኖር ሲያስብ ይጨነቃል። ሆኖም ግን ውጣ ውረዶችን ለማለፍ የተጓዘባቸውን ርቀቶች ከወዲሁ እያሰበ በፅናት እንደሚወጣው ተስፋ ያደርጋል። ወዲህ ደግሞ ምናልባትም በዚህ አምድ ስለ እኔ ችግርና ሕይወት አንብበው «አይዞህ» ሲሉ የሚመጡ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል የሚል እምነት አለው።
ረመዳን ከሌሎች ብዙ እገዛ አይፈልግም። ግን ደግሞ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ብቻውን ማሳካት የማይችላቸውን ነገሮችን ሲያስብ ድጋፋቸውን ይሻል። ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ወደ አገር ቤት ሄዶ ዘመዶቹን አላየም። የመንገዱን አመቺ አለመሆንና አቅም ማነስ ከዚህ አግዶታል። ግን አንድን ነገር ተስፋ ያደርጋል። ነገ ጥሩ ሥራ አግኝቶ ድሃ እናቱን ለማገዝ። ወደ ጉራጌ ምድር ሄዶ ዘመዶቹን ለማየትና እትብቱ የተቀበረበትን ቀዬ አየር ማጣጣም። «ሰፈሬ ሆይ እንዴት ነሽልኝ» ሊላት ይጓጓል።
ረመዳን ነገን ሲያስብ ብዙ ነገሮች እንደሚያስጨንቀው ሁሉ ብዙ ነገሮችን ተስፋ ያደርጋል። ዛሬ ብቻውን ማለፍ ቢከብደውም፤ መልካም ኢትዮጵያውያን በመኖራቸው በፈጣሪ ፈቃድና በመልካም ሰዎች ድጋፍ የማይፈነቅለው ቋጥኝ፣ የማያልፈው ጊዜ እንደማይኖር ተስፋ ያደርጋል።
ባለፈው ዓመት የቀበሌ ቤት ተሰጥቶታል። በሴፍትኔት መርሐ ግብር ታቅፎ በየወሩ 400 ብር ያገኛል። በጉልበት ሥራ የሚተዳደረውና ከአጠገቡ ያለው አንድ ወንድሙ የተገኘውን እንደ ፍጥርጥሩ እየከወነ በጋራ ይቃመሳሉ። አባቱም የቀን ሥራ እየሠሩ ሕይወታቸውን ይገፋሉ። ትዳር የያዙ እህቶቹም እየመጡ ልብስ ያጥቡለታል። ግን ከራሳቸው ተርፎ እሱን ለማገዝ ይከብዳቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የረመዳን አማካይ ውጤቱ 2ነጥብ5 ነው። ከዚህም በላይ ከፍ ለማድረግ ይጥራል። ሆኖም እስካሁን በጤና መታወክ ሳቢያ ሦስት ኮርሶችን አላጠናቀቀም። እነዚህንም ማጠናቀቅ ግድ ይለዋል። ረመዳን ግን አንድ ነገር ዛሬ ካልተሳካ ነገም ሌላ ቀን ነው የሚል ተስፋ አለው።«የማይቻሉ ነገሮችን እየቻልኩ ማለፌ አይቀርም። ሰው ከጠነከረ የማያልፈው ነገር የለምና» ይላል ጠንካራው ረመዳን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በ ክፍለዮሐንስ አንበርብር