ለሰብሎች እድገት ወደ 18 የሚደርሱ ንጥረ ነገሮች እንደሚያስፈልጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ሶስት ያህሉ ንጥረ ነገሮች ከውሃና አየር (Carbon, hydrogen and oxygen) ውስጥ የሚያገኙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ግን ከአፈር ውስጥ ነው የሚያገኙት።
የአፈሩ ፒ ኤች (የአፈር ጣዕም) ይዘት ዝቅተኛ በሚሆንበት ወቅት በአፈር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ወደ ሌላ ውህድ የሚቀየሩበት አጋጣሚ ሁኔታ ይፈጠራል። በተለይም ሃይድሮጂን የሚባለው ንጥረ ነገር እየበዛ ሲመጣ የአሉሙኒየምና የአይረን ንጥረ ነገር ውህዶችም በዚያው ልክ ይበዛሉ።
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት የአፈር አሲዳማነት ችግሮች በሀገራችን የሰብል ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል።
እንዲህ ማብራሪያ የሰጡን በግብርና ሚኒስቴር በአፈር ሃብት መሪ ሥራ አስፈጻሚ የአፈር ጤንነትና ለምነት ዴስክ ኃላፊ አቶ ፋኖሴ መኮንን ናቸው። እንደ አቶ ፋኖሴ ማብራሪያ አሲዳማ አፈር ማለት የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ወይም ፒ ኤች (pH) ከ7 በታች ሲሆን እና የሃይድሮጅን (H+) እና አልሙኒየም (Al+3) ንጥረ ነገሮች በአፈር ውስጥ ሲበዙ ነው። ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሩ ወይም ፒ ኤች ከስድስት በታች እየወረደ ሲሄድ አፈሩ አሲዳማ ይሆናል።
ለአፈር አሲዳማነት መከሰት መንስኤ የሚሆኑት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠንና የአሲድ መሠረት ያላቸው ተፈጥሯዊ አለቶች መኖር ነው። በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ተጎጂ የሆኑ አካባቢዎችም ተለይተዋል። አሲዳማ የሆነ አፈር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰብሎችን ስለሚያጠቃ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል።
በዚህ ወቅት ለሰብል ጠቃሚ የሆኑ እንደ ማግኒዥየም፣ ካልሽየም፣ ፖታሺየም ያሉ ንጥረ ነገሮች በውሃ ታጥበው ወደ ከርሰ ምድር በመስረግ እጽዋቶች እንዳይጠቀሙባቸው ይሆናሉ። በሌላ መልኩ ፎስፈረስ የተባለው ንጥረ ነገር በአፈር አሲዳማነት የተነሳ ከአልሙኒየምና አይረን ጋር በመዋሀድ ወደ አልሙኒየም ፎስፌት ይቀየራል። ይህን ንጥረ ነገር ሰብሎች ስለማይወስዱት በሰብሎች ላይ የፎስፈረስ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል።
በሌላ መልኩ የሃይድሮጂን፣ አይረንና አልሙኒየም ንጥረ ነገሮች በአሲዳማ አፈር ውስጥ ከመጠን በላይ ስለሚከማቹ የእጽዋቶችን ሥር በመመረዝ እጽዋቶች የሚያስፈልጓቸውን ንጥረ ነገሮች እና ውሃ እንዳይወስዱ ያደርጋቸዋል።
አቶ ፋኖሴ የአፈር አሲዳማነትን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ይገልጻሉ። ለከፍተኛ ዝናብ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን በመትከል፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃን በስፋት በማከናወን እርከን በመሥራት፣ መሬቱን ከመሸርሸር መከላከል እንዲሁም ተዳፋት መሬቶችን ለእርሻ ሥራ ባለመዋል ችግሩን መቀነስ ይቻላል እንደሚቻል ነው ያብራሩት።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ካልሼም ካርቦኔት፣ ካልሼም ኦክሳይድ፣ ማግኒዥየም ካርቦኔት የተባሉ የተለያዩ የግብርና ኖራ የማከሚያ ውህዶችን ጥቅም ላይ በማዋል አፈሩን በማከም ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። የማከሙ ሥራም በማሳው ላይ የግብርና ኖራ በመጨመር የሚከናወን ሲሆን፣ የግብርና ኖራ የአጠቃቀም መጠኑም እንደ አፈሩ፣ ሰብሉና ስነምህዳሩ አይነት ይለያያል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በአማካይ በሄክታር እስከ 30 ኩንታል የግብርና ኖራ በመጠቀም ማከም ይቻላል። የአሲድ መጠኑ ከፍተኛ ሆኖ ሲገኝ ግን በሄክታር ከ30 ኩንታል በላይም ሊያስፈልግ ይችላል።
በሌላ በኩልም ማግኒዥየምና ካልሽየም ኦክሳይድ የሚባል ንጥረ ነገርን በማዳበሪያ መልክም ጥቅም ላይ በማዋል የማከሙን ሥራ ማከናወን እንደሚቻልም ኃላፊው ይጠቁማሉ። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ አሲዳማነትን የሚቋቋሙ እንደ ቡና፣ የሻይ ቅጠል ያሉ ተክሎች፣ በምርምር የሚወጡ የስንዴና የገብስ እንዲሁም የመኖ ዝርያዎች መርጦ ማልማት ይቻላል ነው የሚሉት። አሲዳማነትን ለመከላከል የተለያዩ አማራጭ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚቻልም ይገልጻሉ።
በሀገሪቱ ከሚታረሰው መሬት ወደ 43 በመቶ የሚሆነው ወይንም ወደ ሰባት ሚሊየን ሄክታር የሚሆን መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ እንደሆነ አቶ ፋኖሴ ይጠቁማሉ። ጉዳቱም ጠንካራና መካከለኛ በሚባል ደረጃ እንደሚገለጽ ጠቅሰው፣ በአሲዳማነት ከተጠቃው ውስጥም ወደ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሆነው ጠንካራ በሚባል አሲዳማነት መጠቃቱን አመልክተዋል። በመካከለኛ ደረጃ የተጠቃው ሳይታከም ምርት ሊመረትበት የሚችል ቢሆንም፣ የመከላከል ሥራ ካልተሰራ ወደ ጠንካራ አሲዳማነት ሊቀየር ይችላል ሲሉም ያስገነዝባሉ። በጠንካራ አሲዳማነት ደረጃ የተጠቃው ወደ አራት ሚሊየን ሄክታር መሬት የሚሆነው ግን በግብርና ኖራ መታከም እንዳለበት ነው የገለጹት።
በአሁኑ ጊዜም በከፍተኛ ሁኔታ በአፈር አሲዳማነት የተጠቁት አካባቢዎች ከፍተኛ የዝናብ ሥርጭት ያለባቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል። እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ከፍተኛ አምራች የሚባሉና ለሰብል ምርትና ምርታማነት ጥሩ ሥነ ምህዳር የሚገኝባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ አካባቢዎቹም ደጋና ወይናደጋ ሲሆኑ፣ ለአብነትም በአማራ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን እና በደቡብ ጎንደር፤ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ አርሲና ባሌ፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጨንቻ፣ ወላይታ፤ የጉራጌ ዞን ደጋማ ቦታዎች፤ ሲዳማ ክልል፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአጠቃላይ ከፍተኛ የዝናብ ሥርጭት ባለባቸው ስድስት ክልሎች የአሲዳማነት ችግር በስፋት ይስተዋላል።
በጠንካራና በመካከለኛ ሁኔታ በአሲዳማነት በተጠቁት በእነዚህ አካባቢዎች አሁን ላይ ስላለው የልማት ሁኔታም አቶ ፋኖሴ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በከፍተኛ አሲዳማነት ከተለዩት ወደ አራት ሚሊየን ሄክታር ከሚሆነው መሬት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት የሚሆነው ከምርት ውጭ በመሆን ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል። በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደግሞ ምርት እየሰጡ ቢሆንም ምርታማነታቸው ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት። በተለይም የአፈር አሲዳማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ በታየባቸው አካባቢዎች በዚሁ ከቀጠለ በሂደት ምርት እየቀነሰ እንደሚሄድ ኃላፊው አመልክተዋል።
ችግሩ በዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ቀድሞ የመከላከሉም ሆነ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም ቢሆን ለማከም ለምን ጥረት እንዳልተደረገም በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ፋኖሴ በሰጡት ምላሽ፤ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ሳይሆን መቀነስ ነው የሚቻለው ብለዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ አንዱ ክፍተት ችግሩን ለመቀነስ ሥራዎች ቢሰሩም ሥራዎቹ ተከታታይ አለመሆናቸው ነው። በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ግብርና ቢሮ ሥር ሆነው የግብርና ኖራ አምርተው የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች በመለዋወጫ ዕቃ ችግርና በተለያየ ምክንያት በሙሉ አቅማቸው አምርተው ማቅረብ አለመቻላቸውም ሌላው ክፍተት ነው። ለአብነት ባለፉት አመታት የግብርና ኖራን ከግል አምራቾች ገዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ደግሞ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ከፋብሪካ አንዱ ኩንታል እስከ 250 ብር የሚሸጥ ቢሆንም የማጓጓዣ ዋጋ መጨመር የአንዱን ኩንታል ዋጋ 700 ብርና ከዚያ በላይ አደርሶታል። ርቀት ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 1200 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ይህም በተደራሽነቱ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።
በዚህ ወቅት የጉዳዩ አሳሳቢነት ግንዛቤ በማግኘቱ ሰፊ ርብርብና እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ፋኖሴ፣ በአሁኑ ጊዜም በአሲዳማነት የተጠቃ በአመት እስከ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በማከም በሶስት አመት ውስጥ ችግሩ ያለባቸውን አካባቢዎች መፍትሄ ለመስጠት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አፈሩን የማከሙ ሥራ አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች የግብርና ኖራውን በመግዛት እንዲሳተፉ፣ አቅም የሌላቸው ደግሞ በብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የጋራ ግንዛቤ ይዞ አለመነሳትም ክፍተት እንደሆነ ቀደም ሲል ከነበረው ተሞክሮ ትምህርት መወሰዱን የጠቀሱት አቶ ፋኖሴ፤ አርሶ አደሩ መሬቱ ምርት አልሰጥ አለ ብሎ መሬቱን ለቆ የመሄድ ሁኔታ እንጂ ችግሩን ተገንዝቦ ለመፍትሔ የመንቀሳቀሱ ሁኔታ እንዳልነበር አስታውቀዋል። አሁን ላይ ግን እንዲህ ያለው አስተሳሰብ መለወጡንና ለችግሩ የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ በአርሶ አደሩ በኩል ፍላጎት መኖሩን ነው የገለጹት። በተለይም አቅሙ ያላቸው አርሶ አደሮች መሬቱ ቢታከም ምርታማነቱ እንደሚጨምርና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግንዛቤ መያዛቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህ አርሶ አደሮች የግብርና ኖራን ገዝተው በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
የነበረውን የግብርና ኖራ አቅርቦት ውስኑነትም ሆነ ለተያያዥ ጉዳዮች መፍትሔ በመስጠት አሲዳማ አፈርን ለማከም በተለይ በ2016 በጀት አመት ሰፊ ንቅናቄ በመፍጠር ችግሩን በጋራ ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉንም አቶ ፋኖሴ አስታውቀዋል። የግብርና ኖራን ሲሚንቶ ፋብሪካዎችም የሚያመርቱበት ሁኔታ መኖሩንና በግል የተቋቋሙ አምራቾችም ተጨምረው በሚያከናውኑት የማምረት ሥራ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንደሚፈታ እምነት እንዳላቸው።
ሌላው ችግር ሊሆን የሚችለው የማጓጓዣ ዋጋ መናር እንደሆነም ጠቅሰው፣ ይህንንም በመረባረብ መፍታት እንደሚገባ ነው የገለጹት። በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የተለያየ የሰብል ምርት በተለያየ መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል የሚጠቀሙ እንደ ሆቴሎች፣ ቢራ ፋብሪካዎችና ሌሎችም ተባባሪ እንዲሆኑ የጋራ መድረክ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። ሁሉም በጋራ ከተረባረበና የድርሻውን ከተወጣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር የተያዘውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
ችግሩን በጋራ ለመፍታት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ ግብርና ሚኒስቴርና ማዕድን ሚኒስቴር ደግሞ ዋንኛ ተዋናይ እንደሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም በቅርቡ በሁለቱ ተቋማት መካከል የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል። ስለስምምነቱም አቶ ፋኖሴ እንዳሉት፤ የግብርና ኖራ ማዕድን በመሆኑ ማዕድኑ የሚገኝባቸውን አካባቢዎችና የክምችት መጠን ማዕድን ሚኒስቴር በጥናት እንዲለይ፣ በዘርፉም የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የሥራ ዕድል በመፍጠር ቀደም ሲል ከሚኒስቴሩ ጋር የሚሰሩት አምራች ድርጅቶችም በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ የግብርና ኖራ አቅርቦትን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ስምምነት ነው የተደረገው። ግብርና ሚኒስቴር ደግሞ የግብርና ኖራውን ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግና ግንዛቤ የመፍጠሩን ሥራ ያጠናክራል።
የግብርና ኖራ አምርተው ከሚያቀርቡት አንዱ የሆነውና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ቶኬ ኩታዩ ወረዳ መልካነጋ ደንቢ ቀበሌ የሚገኘውን ፋብሪካ የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ኃላፊ አቶ ፊጣ ኩምሳ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው የተቋቋመው በ2003ዓ.ም ሲሆን፣ በሁለት ፋብሪካዎች በቀን 240 ኩንታል በማምረት ነው ሥራውን የጀመረው። በአሁኑ ጊዜ የግብርና ኖራ የሚያመርቱ ማሽኖችን ወደ ስድስት በማድረስ፣ በቀን ወደ አንድ ሺ 600 ኩንታል የማምረት አቅም ፈጥሯል። ፋብሪካው ማምረት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2013ዓ.ም ድረስ ባሉት አመታት የግብርና ኖራን ለክልሉ አርሶ አደሮች በነፃ ይቀርብ ነበር።
እንደ አቶ ፊጣ ማብራሪያ፤ ከ2014 ወዲህ ግን በፋብሪካው የመሸጫ ዋጋ አንድ ኩንታል በ230 ብር እየቀረበ ሲሆን፣ ስርጭቱም የሚከናወነው ከገበሬዎች የህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመሆን ነው። ሽያጩ በዚህ መልኩ የሚከናወን ቢሆንም፣ የመጓጓዣ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በተለይም ራቅ ወዳለው አካባቢ ለሚገኘው አርሶ አደር እየደረሰ ያለው አንድ ሺ ብርና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ ነው። ይህን ችግር ለመፍታትም ፋብሪካው የመጓጓዣ ወጪውን ሸፍኖ አርሶ አደሩ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ የሚያገኝበት ሁኔታ በማመቻቸት ለዘጠኝ ዞኖች ወደ 82ሺ ኩንታል የግብርና ኖራ ለማሰራጨት ጥረት ተደርጓል።
ፋብሪካው የሠራተኛ ማደሪያ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ቢመቻችለትና 24 ሰዓት ማምረት ቢችል በተሻለ ተደራሽ ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ፊጣ፣ ለምርቱ የሚሆን ግብዓትም በአካባቢው ላይ መኖሩን አመልክተዋል። የግብዓት ሥርጭቱም ጉጂ፣ ቦረና፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ኢሊባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ነቀምት አካባቢዎች እንደሆነም ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2015