ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በአግባቡ ለመቆጣጠር

ትምህርት የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ የተፈጠረና እስካሁንም ከሰው ልጅ ጋር አብሮ እየኖረ ያለ ማህበራዊ ዘርፍ ነው፡፡ የሰው ልጅ ኑሮውን ለማቅለል በማሰብ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ ምርምሮችን እና ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ ትምህርቶችን በመማር በአድናቆት አፍን ጉንጭ ላይ የሚያስጥሉ የተለያዩ ምርምሮችን አድርጓል ፤ አሁንም እያደረገ ይገኛል፡፡

ለምሳሌ ጥንታዊት ህንዳውያን ሲሚንቶ፣ መስተዋት ፣ ቀዶ ጥገና ፣ከቅጠላ ቅጥል መድኃኒት መቀመምን… ወዘተ ለዓለም ህዝብ አስተምራለች ፡፡ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የሰውን ልጅ ያስደመሙ ኪነ ህንጻዎች ፣ የስነ ፈለክ ምርምሮች ሰርተዋል፡፡ ከጸጥታ አካላት ጋር በተያያዘ ቅራት የተባለውን ህዝባዊ ፖሊስ በማቋቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ህዝብ ማስተዋወቃቸውን የሚጠቁሙ ጥናቶችም ለንባብ በቅተዋል ፡፡ ይህ ሁሉ በትምህርት እና በምርምር የሚፈጠር እንጂ እንዲሁ በታምር የተገኘ አይደለም ፡፡

ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገዳማት እና መስጅዶች የዓለማችን ግንባር ቀደም የእውቀት መገኛ እና ሁነኛ የምርምር ቦታዎች መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በእኛ ሀገርም ገዳማት እና መስጅዶች ጥንታዊ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ሙሁራን በተለያዩ ጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

ገዳማት እና መስጅዶች የሀገራችን ጥንታዊ ዩኒቨርሲቲዎች ስለመሆናቸው የላሊበላ ውቅር ዓብያተ ክርስቲያናት የአሰራር ጥበብ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው ፡፡

በነገራችን ላይ ንጉስ ላሊበላ ከላይ በወደ ታች ካስገነቧቸው አብያተ ክርስቲናት ባለፈ በሀገራችን ዜጎች እምብዛም የማይታወቅ ነግር ግን በተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች ጎልቶ የሚነገር ድንቅ የትምህርት እና የምርምር ውጤጥ በሀገረ ሱዳን መኖሩ ይነገራል፡፡

አሰፋ አሊ ኡመር ቁስለኛዋ ሀገር በተሰኘ መጽሐፋቸው ፤ ንጉስ ላሊበላ ድንጋይን በድንጋይ የማቅለጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ካርቱም ላይ ነጭ አባይን እና ጥቁር አባይን ገድበው ነበር ፡፡ ካርቱም የተሰኘው የሱዳን ዋና ከተማን ሥም ንጉሱ እንዳወጡት እና በአገውኛም ካርቱም ማለት “ማገድ” ወይም “ማቆም” መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እዚህ ላይ ካርቱም የሚለውን ቃል ፍች እዚህ ላይ ያነሳሁት ስለ ተባለው ግድብ ለማንሳት ሳይሆን ፤ የኢትዮጵያን የትምህርት እና ምርምር እድገት በተለይም በኪነ ህንጻ የነበረንን ኃያልነት ለመጠቆም በማሰብ ነው ፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ገዳማት እና መስጅዶች ጥንታዊ ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ገዳማት እና መስጅዶች የተለያዩ ትምህርቶችን ይሰጡ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ በተለይም በአውሮፓዊያን በገዳማት እና በመስጅዶች የሚሰጡ ትምህርቶችን በአዲስ ለመተካት በማሰብ ህዳሴ (RENAISSANCE) ብለው እንደ አዲስ እውቀታቸውን ለትውልድ የሚያስተላልፉበትን አብዮት አካሂደዋል፡፡

የምሁራኑ ንቅናቄ (Enlightenment ) ፣ኢንዱስትሪያል አብዮት (Industrial Revolution) የተሰኙ አብዮቶችን አቀጣጠሉ፡፡ ከእነኝህ አብዮቶች የተገኙ እውቶችን በመቀመር የተዋጣለት ሀገር በቀል ዕውቀት መፍጠር ቻሉ፡፡

በእኛ ሀገር ግን የሀገር በቀል እውቀቶችን እንደመነሻ ከመጠቀም ይልቅ እንዲሁ መሬት ላይ በመወርወር የውጭን ትምህርት ብቻ በማቃረም ውጮች በቀደዱት ቦይ መፍሰስን እንደ ጉብዝና ቆጠሩ፡፡ የተቀረው ህዝብም መጀመሪያ ላይ ሥርዓተ ትምህርቱን ቢቃወምም እየቆየ ግን በውጩ አለም የሥርዓተ ትምህርት ቦይ የፈሰሱ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ሁነኛ የሀገራቸው ችግር ፈቺዎች አድርጎ ቆጥሯቸዋል፡፡

የራሱን ሀገር በቀል እውቀት እርግፍ አድርጎ በመተው፤ የውጩ ዓለም ከየት ተነስቶ ወድየት የሚለውን የኋላ ወቅት ተጠቃሚነት “የሌት ካመር አድቫንቴጅ” መጠቀም ሳይችል ቀርቷል ።

“የሌት ካመር አድቫንቴጅ” አንዱ እና ዋነኛ ጥቅሙ ሌሎች ካለፉበት መንገድ ችግሮችን እና አካሄዶችን ተረድቶ የራሱን አካሄድ በተስተካከለ መንገድ መምራት መቻል ነው ፡፡ ይሁን እንጂ እኛ ይህንን ማድረግ ባለመቻላችን ተጠቃሚ ሳንሆን ቀርተናል ።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው አሁን ላይ ጭራሽ ሁሉንም እርግፍ አድርገን ትተን ባልተማርነው ትምህርት ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመያዝ ሀገርን በከፍተኛ ደረጃ እያጎሳቆልን እንገኛለን ፡፡ መምህሩ ፣ ሐኪሙ ፣ ኢንጅነሩ ወዘተ የትምህርት ማስረጃቸው የሐሰት መሆኑን ስንሰማ ሀገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡

እንደ አውሮፓዊያን የትምህርት አብዮት ቀስቅሰን ሥርዓተ ትምህርታችንን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ማድረግ ባንችል ምነው ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃ እንዲኖረን ማድረግ ተሳነን ጎበዝ!? እውነታው የጤነኝነት አይመስለኝም፡፡ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የምሰማው የአፈጻጸም ችግር ምንጩ ምን እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው ፡፡

የሀገራችንን ትምህርት ለማሳደግ በተደረገ አንድ ሀገራዊ ንቅናቄ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የላቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት የላቁ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ፤ ካልሆነ ግን በመጪው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንደማንችል አመልክተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራት ችግሮች መንስኤ ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም የትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆናቸው ከመሠረታዊ ችግሮች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ 86 በመቶ በላይ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማቶች የተሟላ ደረጃ ስለሌላቸው ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ከባቢ ውስጥ ለመማር ተገደዋል ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆነ በትምህርት ሚኒስትሩ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የምስማማ ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የትምህርት ንቅናቄ ውጤት እንዲመጣ ከተፈለገ ከመሰረተ ልማቶች ግንባታ በላይ ተማሪዎችን የሚቀርጹ መምህራን ፣ መምህራንን የሚመሩ አስተዳዳሪዎች ፣መምህራንን እና ተማሪዎችን እንዲሁም አስተዳዳሪዎችን የሚያክሙ ሐኪሞች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ፡፡

የሐሰት የትምህርት ማስረጃ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያቀጭጭ ብሎም የሚገድል በመሆኑ እንደ ጸረ ሙስና ፣ እንባ ጠባቂ ወይም ሌላ የትምህርት ማስረጃዎችን የሚያጣራ ከችግሩ ቀድሞ እራሱ ነጻ የሆነ ትልቅ የጋራ ተቋም ያስፈልጋል ባይ ነኝ ፡፡ ሰላም !

አሸብር ኃይሉ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 24/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *