ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? መቼም ልጆች በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር አራት ወቅቶች እንዳሉ ታውቃላችሁ አይደል? እነርሱም መከር፣ በጋ፣ ፀደይ (በልግ) እና ክረምት ናቸው አላችሁ? ጎበዞች። በመሆኑም አሁን ያለንበት የክረምት ወቅት ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ትምህርት ቤቶች ለጥቂት ወራት ብቻ ዝግ ሆነው ይቆያሉ። እናንተም የክረምት ጊዜያችሁን በአግባቡ እንደምትጠቀሙ የተለያዩ አማራጮችን እንጠቁማችኋለን።
እንደምታስታውሱት የበጋውን ወቅት በሚገባ ትምህርታችሁን ተከታታላችሁ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ስትሞክሩ የነበረበት ጊዜ እንደነበር፤ በዚህም ጥሩ ውጤት እንዳመጣችሁ ጥርጥር የለኝም። በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት ያላመጣችሁ ወይም ደከም ያላችሁ ተማሪዎች ካላችሁ ደግሞ የክረምት ትምህርት በመማር አልያም ታላላቆቻችሁን እየጠየቃችሁ ለቀጣዩ የትምህርት ዓመት ዝግጅት ለማድረግ የሚረዳችሁ በመሆኑ ወቅቱን በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባል።
ልጆች ለመጪው የትምህርት ዘመን ከመዘጋጀት በተጨማሪ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ የክረምት ጊዜያችሁን በሚገባ ማሳለፍ ትችላላችሁ። ለምሳሌ ቋንቋ፣ ኮምፒውተር ወይም ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዲሁም የዕደ ጥበብ (በእጅ የሚሠሩ) የእጅ ሥራዎችን በመማር ወቅቱን በሚገባ ማሳለፍ ትችላላችሁ። ታዲያ ልጆች ማወቅ ያለባችሁ ነገር፤ አንዳንዶቹ ሥልጠናዎች የግድ ትምህርት ቤት ገብቶ መማርን የማይጠይቁ በመሆናቸው ወላጆቻችሁን፣ ታላላቆቻችሁን እና ለእናንተ የቅርብ ቤተሰብ የሆኑትን በመጠየቅ ብትማሩ ብዙ ነገሮችን እንድታውቁ ከማድረግ ባለፈ ነገሮችን በራሳችሁ ማከናወን እንድትለማመዱ ይረዳችኋል።
ልጆች እንደምታውቁት የደን መመናመን በሀገራችን የዝናብ እጥረት፣ የአፈር መሸርሸር እና ሌሎች ችግሮች እንዲፈጠር ያደርጋል። ችግሩን ለማቅለልም በአሁን ወቅት በሀገራችን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄደ እንደሆነ እንደሚገኝ ማስተዋላችሁን አልጠራጠርም። ታዲያ የደን መመናመን በምድራችን ላይ የሚያደርሰውን ችግር በመገንዘብ ችግሩን ለመፍታትም ከወላጆቻችሁ ጋር በመሆን የተለያዩ ችግኞችን በመትከል እና እንዲጸፀድቁ በመንከባከብ የክረምት ወቅቱን በሚገባ ብታሳልፉ ራሳችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁን እና ሀገራችሁን ጭምር መጥቀም ትችላላችሁ።
ከነዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ጨዋታዎችን ከወንድሞቻችሁ፣ እህቶቻችሁና ከጓደኞቻችሁ ጋር በመጫወት ማሳለፍ ትችላላችሁ። ጨዋታዎቻችሁ በሞባይል ስልክ ወይም በታብሌት የታገዙ ጨዋታዎች ባይሆኑ ይመከራል። ለምን? ካላችሁ ለአዕምሯችሁም ይሁን ለአካላዊ እንቅስቃሴያችሁ እንዲሁም እድገታችሁ ስለማይጠቅማችሁ ነው። በምትጫወቱበት ወቅትም አካላችሁ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄ መሆን አለበት። ለጨዋታ የሚሆን ሰዓት እና ቦታ መምረጥም ይኖርባችኋል። ከጨዋታ በተጨማሪም ለልጆች የተሠሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ቃለ መጠይቆችን፣ ፊልሞችን እና ቴአትሮችን በመመልከት ማሳለፍ የምትችሉ ሲሆን፤ እነዚህ ሁሉ ስታደርጉ ግን ከወላጆቻችሁ ፈቃድ ብሎም ትዕዛዝ ውጭ መሆን የለባችሁም ።
ልጆች ያለፈውን ወቅት የተለያዩ የትምህርት መጽሐፍትን እና አጋዥ መጽሐፍት ስታነቡ እንደነበር
አምናለሁ። ከነዚህ መጽሐፍት በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እውቀት እንዲኖራችሁ የተለያዩ መጽሐፍትን ማንበብ ይኖርባችኋል። በዚህ የክረምት ወቅት እንደ ፍላጎታችሁ፣ እንደ ዕድሜያችሁ እና እንደዝንባሌያችሁ ዓይነት ወላጆቻችሁን አልያም የቅርብ ቤተሰባችሁን በማማከር የተረት፣ የታሪክ፣ የልብ ወለድ፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች መጽሐፍትን ብታነቡ ብዙ እውቀት እንድታገኙ ከማድረግ አልፎ የማንበብ ልምዳችሁ እንዲዳብር ያደርጋል።
ልጆች የተለያየ ተሰጥዖ ሊኖራችሁ ይችላል። ለምሳሌም በሥነ ጽሑፍ፣ በሥዕል፣ በፈጠራ፣ በትወና፣
በምግብ ማብሰል፣ በጋዜጠኝነት፣ በቴክኖሎጂ፣ በእጅ ሥራ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ፍላጎት እና ልዩ ተሰጥዖ ያላችሁ ልጆች ካላችሁም በእረፍት ሰዓታችሁ በሚገባ በመለማመድ፣ በማንበብ እና ወላጆቻችሁ ድጋፍ እንዲያደርጉላችሁ በመጠየቅ የተሰጣችሁን በሚገባ ለማውጣት ይረዳችኋል።
ወላጆቻችሁ እናንተን ለማስደስት ብዙ ነገር እንደሚያደርጉ ታውቃላችሁ አይደል ልጆች? እናተስ ወላጆቻችሁ ደስተኛ እንዲሆኑላችሁ ትፈልጋላችሁ? እንግዲያውስ በርትታችሁ ካጠናችሁ፣ ወላጆቻችሁን በመጠኑም ቢሆን የቤት ሥራ የምታግዟቸው ከሆነ፣ ጥሩ እና ጎበዝ ልጅ ስትሆኑላቸው ደስተኛ ይሆናሉ። ወላጆቻችሁን በሚገባ ለማገዝም እና ከወላጆቻችሁ ጋር በሚገባ ለማሳለፍ የክረምት ወቅት በሚገባ የሚረዳችሁ መሆኑን በመገንዘብ፣ በመመካከር እና በመወያየት ደስተኛ ሆናችሁ ማሳለፍ አለባችሁ።
ልጆች ሀገራችን የብዙ ባሕል፣ ቅርስ፣ እና ታሪክ ባለቤት እንደሆነች ታውቃላችሁ። እናንተ በምትኖሩበት አካባቢም በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ይኖራሉ። ስለሆነም በከተማችሁ (በምትኖሩበት አካባቢ) መጎብኘት ያለባቸውን ታሪካዊ እና የመዝናኛ ቦታዎች በመሄድ ማሳለፍ ትችላላችሁ። ወላጆቻችሁ ከቻሉ ደግሞ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሄዳችሁ ከዘመዶቻችሁ ጋር ጥሩ ጊዜን ከማሳለፍ ባሻገር የዛን አካባቢ ባሕል እና ታሪክ እንድታውቁ ይረዳችኋል።
ታዲያ ልጆች የክረምት ወቅት ዝናብ የሚበዛበት ወቅት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በዝናብ ወቅት አለመጫወት፣ በቱቦም ይሁን ወንዝ አካባቢ አለመገኘት፣ ከመኖሪያ አካባቢያችሁ ርቃችሁ አለመሄድ ይኖርባችኋል። በአጠቃላይ ሁሉንም ነገር በምታደርጉበት ወቅት ራሳችሁን ከሚጎዱ ነገሮች በማራቅ እና በመጠንቀቅ እንዲሆን የዛሬው መልዕክታችን ነው።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2015