ገና በለጋ እድሜዋ ዘወትር እሁድ ማለዳ ባደገችበት ካሊፎርኒያ ሳንሆዜ ወደሚገኘው ፓርክ ከቤተሰቧ ጋር በመሄድ ሰንበትን የማሳለፍ ልምድ ነበራት። ቤተሰቧ በፓርኩ ከሚሰባሰበው የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር ሲጨዋወት ታዳጊዋ ናኦሚ ግርማ እዚህም እዚያም ኳስ እያንከባለሉ ከሚጫወቱ ታዳጊዎች ጋር ተቀላቅላ መጫወት ልማዷ ነው።
ናኦሚ እንደየእድሜያቸው በሦስት ተከፍለው በፓርኩ ኳስ እያንከባለሉ የልጅነት ጣፋጭ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ታዳጊዎችን ስትቀላቀል ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። ያስተዋላት አልነበረም እንጂ ትልቅ የእግር ኳስ ተሰጥዖ መገለጥ የጀመረውም ያኔ ነበር። እንደ ቀልድ በእረፍት ቀን ከእኩዮቿ ጋር ፓርኩ ውስጥ ስታንከባልል የነበረው የኳስ ክህሎት ወደ መደበኛ የታዳጊዎች እግር ኳስ ሲሸጋገር ብዙ ጊዜ አልፈጀም። እዚያ ለመድረስ ግን የነበረውን ውስብስብ ሂደት ከቤተሰቧ ጋር መጋፈጧ አልቀረም።
“ወደ እግር ኳስ ዘው ብዬ ለመግባት ስወስን አስቤበት አልነበረም፣ ባደረኩት ነገር ግን በጣም ደስተኛ ነኝ” ትላለች የትናንቷ ታዳጊ የዛሬዋ የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ቁልፍ ተጫዋች ለዘ ጋርዲያን አስተያየቷን ስትሰጥ።
ናኦሚ 23 ዓመት የሞላት ከወር በፊት ነው። በዚህ አጭር እድሜዋ ጊዜ ግን የዓለም ዋንጫ የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ለ3ኛ ተከታታይ ጊዜ ለሻምፒዮንነት ሲታጭ ትልቅ ተስፋ የተጣለባት የመሐል ተከላካይ ለመሆን በቅታለች። ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ጋር በአንድ ለአንድ ግንኙነት(man to man marking) ድንቅ ብቃት አላት፣ ከኳስ ጋር ያላት ምቾትና የሚታይባት እርጋት ብዙዎች እንዲደነቁባት አድርጓል።
በሴቶች እግር ኳስ የመጪው ዘመን ድንቅ የመሐል ተከላካይ እንደምትሆን የተመሰከረላት ወጣት በኳስ ተሰጥዖዋ ብቻ አይደለም የምትደነቀው። ድንቅ ስብዕናና ሥነምግባሯም ተፈላጊነቷን አሳድጎታል። ለዚህም የተረጋጋ ማንነቷ አስተዳደጓ ትልቅ ሚና አለው። ናኦሚ በ1980ዎቹ ከኢትዮጵያ በስደት ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ያቀናው አባቷ በጥሩ ሥነምግባር አሳድጓታል። ዘወትር እሁድ ማለዳ በለጋ እድሜዋ አስከትሏት በሺዎች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር “ማለዳ እግር ኳስ ቡድንን” እንድትቀላቀል ማድረጉ ለዛሬው የእግር ኳስ ስኬቷ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖራት አድርጓታል።
“ለጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነትና ለቤተሰብ ዋጋ እንድሰጥ አድርጎኛል፣ ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነት መፍጠር አሜሪካ ውስጥ ትልቅ ቦታ አይሰጠውም፣ በኢትዮጵያ ግን ትልቅ ዋጋ ያለው ይመስለኛል” የምትለው ናኦሚ ቤተሰቦቿም በዚህ ባሕል እንድታድግ ማድረጋቸውን ትናገራለች።
ናኦሚ አሁን ላይ ዘወትር እሁድ ማለዳ ወደ ፓርኩ የምታቀናው እንደ ልጅነቷ ለጨዋታ ብቻ አይደለም። የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሕይወቷን ለማሳደግ ጭምር ነው። አሁን ግን እንደ ልጅነቷ ከአባቷ ጋር ሳይሆን ትውልደ ኢትዮጵያዊ እናቷ ነች ወደ ፓርኩ በመኪና የም ታደርሳት።
ናኦሚ ከኳስ ሕይወቷ ጎን ለጎን በትምህርቱም አትታማም። እንዲያውም ለኳስ ሕይወቷ መንገድ የጠረገላት ወደ ሳንፎርድ ዩኒቨርስቲ ማቅናቷ ነው። በዚህ ዩኒቨርስቲ ቆይታዋም በቴክኖሎጂና በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ የትምህርት መስኮች ከፍተኛ ውጤት ከማስመዝገቧ በተጨማሪ በማኔጅመንትም ሳይንስና ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪዋን ጨብጣለች።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሳንፎርድ ቡድንን 2019 ላይ በአምበልነት እየመራች በአሜሪካ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና ተሳትፋለች። ይህም አጋጣሚ ነው ወደ ፕሮፌሽናል ተጫዋችነት እንድታመራ በር የከፈተላት።
“እንደ ናኦሚ በሁሉም ነገር የተዋጣለት ሰው ገጥሞኝ አያውቅም፣ እጅግ ትሑት ነች፣ ሁሌም በራስ መተማመንና እያንዳንዱን ጨዋታ ለማሸነፍ ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች፣ እኔም በሁሉም ነገር ድንቅ መሆኗን ሳልነግራት አልፌ አላውቅም” ትላለች በሳንዲዬጎ ዌቭ ክለብ ናኦሚን ያሰለጠነቻት ካሴይ ስቶኔይ ምስክርነቷን ስትሰጥ።
በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በሦስት የዓለም ዋንጫዎች በተከላካይ መስመር ተሰልፋ የተጫወተችው የአሁኗ አሠልጣኝ ስቶኔይ የናኦሚን ድንቅ የኳስ ብቃት ስታስረዳ “ብዙ ተጫዋቾች በተከላካይነት ወይም እንደ አማካኝ ኳስ በማከፋፈል ጥሩ ናቸው፣ ናኦሚ ግን በሁለቱም ድንቅ ነች፣ እኔ የእሷን ግማሽ ያህል ጥሩ አይደለሁም” በማለት ትገልፃታለች። ይህም ብቃቷ ሳንዲዬጎ ክለብ እስከ 2026 የሚቆይ ረጅም ኮንትራት ሊያስፈርማት ችሏል።
ናኦሚ በአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ተጫዋች መሆኗን ማሳየት የጀመረችው ባለፈው ዓመት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጃማይካ ጋር በነበረው ጨዋታ ነው። በዚያ ጨዋታ ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ቡድኗ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር በግሩም ሁኔታ አመቻችታ በማቀበል ነበር።
ባለፈው የውድድር ዓመት በአሜሪካ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተከላካይ የተባለችው ናኦሚ ሳንዲዬጎ በሊጉ ትንሽ ግብ የተቆጠረበት ክለብ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥታለች። በዚህም ሳንዲዬጎ የውድድሩን ግማሽ መምራት ችሎ ነበር።
የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቭላትኮ አንዶኖቭስኪም ናኦሚ ትልቅ ተሰጥዖ ያላት የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋች መሆኗን መስክረውላታል።
ናኦሚ እዚህ ደረጃ ለመድረሷ ታላቅ ወንድሟና ከኢትዮጵያ የተገኙት ወላጆቿ ብዙ ዋጋ እንደከፈሉ ትናገራለች። “ወላጆቼ እኔ ላይ የሠሩት ነገር፣ ያደረጉልኝ ድጋፍና የሚሰጡኝ ፍቅር ለዚህ አብቅቶኛል” በማለት የስኬቷን ሚስጥር ለዘ ጋርዲያን አካፍላለች። ዛሬም ግን ዘወትር እሁድ ማለዳ ከልጅነቷ አንስቶ ወደ ምታዘወትረው ፓርክ መሄዷን አላቋረጠችም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2015