እድሜያቸው ስልሳዎቹን ቢጠጋም ፈጣን እርምጃዎቻቸው የ20 እና የሰላሳ ዓመት ወጣትን እንኳን ሊወዳደር የሚችል በመሆኑ ግርምትን ይፈጥራሉ። በተለያዩ ጋዜጣዎች ላይ ሃሳባቸውን በማካፈል የመጻፍ ልምድ አላቸው። ከውትድርና ጀምሮ እስከ ጤና ባለሙያነት አገልግለዋል። የተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ቢሰማሩም በመጨረሻ ግን የቆዳ ውጤቶች ምርት በማዘጋጀት አነስተኛ ገቢ እየፈጠሩ ይገኛል።
እኛም የስራ እንቅስቃሴያቸውን ልንቃኝ ሽሮሜዳ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ጎራ አልን። በመኖሪያ ቤታቸው በረንዳ ላይ ሆነው የስራ ልብሳቸውን እንደለበሱ አገኘናቸው። በጥቁሯ የልብስ ስፌት ማሽናቸው(ሲንጀር) አጠገብ ተቀምጠው በዘመናዊ መልክ የለሰለሱ ቆዳዎችን እያሰማመሩ ሲያበጃጁ በዘርፉ የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው ይመስላሉ።
በፋብሪካ የተዘጋጁ የሚመስሉ የኮፍያ፣ የቦርሳ ምርቶች ደግሞ የመኖሪያ ቤታቸው የውጭው ግድግዳ ላይ ተንጠልጥለዋል። የዛሬው ባለታሪካችን ሙሉ ስማቸው አቶ አሰበ ገብረማርያም ይባላሉ። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በ1954 ዓ.ም ነው ወደዚህ አለም የመጡት። ትውልድ እና እድገታቸው በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ልዩ ስሙ ዘብር ገብርኤል ከሚባለው አካባቢ ነው።
በልጅነታቸው ደግሞ በቀዝቃዛማው የመንዝ ምድር በእረኝነት ተሰማርተው የቤተሰባቸውን ከብቶች በማገድ ያገለግሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በጎን ደግሞ የቤተክርስቲያን ትምህርት በመከታተል ፊደል መቁጠር ጀመሩ። እድሜያቸው አስራ ሁለት እንደደረሰ ግን ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ የሚያስችል እድል ተፈጠረላቸው። በወቅቱ ታላቅ ወንደማቸው አዲስ አበባ ላይ ከትመው ነበርና እርሳቸውን ለመጠየቅ ከእናታቸው ጋር ሆነው ለመሄድ እንዲዘጋጁ ተነገራቸው።
ከእናታቸው ጋር ሆነው ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ተደረገና በወቅቱ ሸገር ላይ የክቡር ዘበኛ የነበሩት ወንድማቸው ቤት አረፉ። ወንድማቸው ደግሞ ‹‹እዚህ መቆየት ከፈለግክ አንድ ሰው አገናኝሃለው›› ብለው ሽሮሜዳ አካባቢ የሚገኘው መንበረ ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ጋር ያገናኟቸዋል።
የወቅቱ ለጋ ወጣት የአሁኑ የእድሜ ባለጸጋ አቶ አሰበም እናታቸውን አስፈቅደው ቤተክርስቲያን እያገለገሉ ዘመናዊ ትምህርት ለመማርም እንደሚመቻቸው አሳምነው አዲስ አበባ ይቀራሉ። የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ እንደአባት ስለሆኑላቸው እርሳቸው ጋር እየኖሩ በመታዘዝ እና በመላላክ እዚያው ለአንድ ዓመት መንፈሳዊ ትምህርታቸውን መቅሰም ቀጠሉ።
አስተዳዳሪው በአሰሩት ዘመናዊ ትምህርት ቤትም ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። በወቅቱ ታዲያ አቶ አሰበ ለአስተዳዳሪው አንድ ጥያቄ ያቀርባሉ። ጥያቄውም አንድ የልብስ መስፊያ ማሽን ቢገዛላቸው ለቤተክርስቲያን አባቶች ቀሚስ እየሰፉ መጥቀም እንደሚችሉ እና ለእራሳቸውም ገቢ መፍጠር እንደሚችል የሚያሳስብ ነበር። ይህ ወቅት አቶ አሰበ በአነስተኛ ወጪ ልብስ እየጠገኑ ገቢ እንዲፈጥሩ የመጀመሪያውን በር የከፈተላቸው አጋጣሚ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ጥያቄያቸው በጎ ምላሽ አግኝቶ ዘመናዊ የልብስ መስፊያ ተገዛላቸውና የቤተሰክርስቲያኑን ሰራተኞች ልብስ እያዘጋጁ ማቅረባቸው ተያያዙት። በጎን ደግሞ ለአካባቢው ነዋሪ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ልብሶች በመስፋት ገቢ መፍጠር ቻሉ። በወቅቱ የመጀመሪያው የልብስ ጥገና ስራቸው 50 ሳንቲም ወይም በእርሳቸው አጠራር ሽልንግ እንዳስገኘላቸው አቶ አሰበ ያስታውሳሉ።
እስከ ስድተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ግን የሽሮሜዳውን ትምህርት ቤት ለቀው ወደ ተፈሪ መኮንን ተዛውረው እስከ ስምንተኛ ክፍል ቀጠሉ። ከዚያ በኋላ ያቀኑት ግን ጃንሜዳ አካባቢ ወደሚገኘው የፖሊስ ሰራዊት ትምህርት ተቋም ነው። በተቋሙ የሚሰጠውን የውትድርና ስልጠናውን ሲጨርሱ ደግሞ በ112 ብር ደመወዝ ተቀጥረው ሻኪሶ እንዲሰማሩ ተደረገ።
አልፎ ተርፎም ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት መሳተፋቸው አልቀረም። በስልጠናቸው ጊዜ መጠነኛ የህክምና ዕውቀት እንዲጨብጡ ተደርጎ ስለነበረ በወቅቱ ከውጊያው በተጨማሪ የመጀመሪያ እርዳታ ህክምና ይሰጡ ነበር። እናም ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ለጤና ረዳትነት ስልጠና በሚል ታጠቅ ማሰልጠኛ ገቡ።
የህክምናውም ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ በጤና ረዳትነቱ በጦሩ ውስጥ መስራት ጀመሩ። ከዓመታት በኋላ ከአለቆቻቸው ጋር በተፈጠረ ግጭት ስራውን ጣጥለው ወደ አዲስ አበባ መመለስ ግድ ሆነባቸው።
ከዚያም ተፈሪ መኮንን ያቋረጡትን ትምህርት ለመቀጠል ከዘጠነኛ ክፍል ጀመሩ። በተፈሪ መኮንን እስከ አስራ ሁለተኛ ድረስ ቢያጠናቅቁም የጤና ረዳትነቱ ስራ አልለቀቃቸውም።
ይልቁንም በወቅቱ አጠራር ወደ ኢሊባቡር ተጉዘው በቡና ሻይ ተቋም በጤና ረዳትነት መስራት ጀመሩ። በሙያው ኤክስፐርትነት ደረጃ ደርሰው በማዕድን ሚኒስቴር፣ ሱዳን ሪፊዩጅ፣ በወተት ሃብት እና የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንሲቲትዩት በጤና ረዳትነት ለ20 ዓመታት ሰርተዋል። እስከአሁን ድረስ ግን ወደ ንግዱ እና በራስ ስራ ገቢ ወደሚያስገኝ ስራ አልተሸጋገሩም።
በመጨረሻ የገቡበት የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የክሊኒክ ስራቸው ግን በተጓዳኝ ሌላ ሙያን ይዞላቸው መጣ። በኢንስቲትዩቱ ሲሰሩ በትርፍ ጊዜያቸው የቆዳ ምርቶች እንዴት ዲዛይን እንደሚደረጉ እና እንዴት እንደሚሰፉ በማምረቻ ውስጥ እየገቡ ትምህርት ይወሰዱ ነበር። በተለይም አጫጭር የቆዳ ሙያ ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት ሳይመዘገቡ እና እውቅና ሳይሰጣቸው የጤና ስራቸውን እያከናወኑ ከሰልጣኞች ጋር አብረው ይማሩ ነበር።
በኬሚካል እና በማሽን ጉዳት የደረሰባቸው ሰራተኞች እያከሙ በጎን ደግሞ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ አሰልጣኞችን አጫጭር ስልጠናዎች በትርፍ ጊዜያቸው በመስሪያ ቤታቸው መከታተሉን አላቆሙም። በግቢው ከሚገኙ ሙያተኞች ጋር ባላቸው ቅርበት የተነሳ የተለያዩ የቆዳ ምርት ዘዴዎችን በትርፍ ጊዜያቸው ያስተምሯቸው ነበር።
አንድ ቀን ታዲያ አሰልጣኞች ለባለሙያዎች ካስተማሩ በኋላ አነስተኛ የቆዳ ኳስ ሰፍተው እንዲያዘጋጁ ፈተና ያቀርባሉ። ከሰልጣኞች መካከል ግን አብዛኛው ክብ ኳስ ለመስፋት ቢቸገሩም የጤና ረዳቱ ግን የልጅነት የልብስ ስፌት ሙያቸውን እና የስልጠና ትምህርቱን አጣምረው አነስተኛ የቆዳ ኳሱን በሚገባ አዘጋጅተው ማሳየት ቻሉ። በመሆኑም የአቶ አሰበ የልጅነት የልብስ ስፌት ሙያ ከቆዳ ዘርፍ ጋር ማዛመድ እንዳለባቸው ልባቸው ይነግራቸው ጀምሯል።
አምስት ዓመታትን በቆዳ ኢንስቲትዩቱ እንዳገለገሉ ግን እድሜያቸው ለጡረታ በመድረሱ መሰናበታቸው አልቀረም። ይሁንና በቀጥታ ወደአምራችነት እና ገቢ ፈጣሪነት አልተሸጋገሩም፡ ፡ ይልቁንም በወንድማቸው የኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ።
በዚያም የኮንስትራክሽን ሳይቶች ተቆጣጣሪ በመሆን መስራታቸውን ቀጥለዋል። ስራው ግን ከግንባታ ሰራተኞች ጋር በየጊዜው የሚያጨቃጭቅ እና በጡረታ እድሜያቸው ሁሉንም ተቆጣጥሮ የማይዘለቅ መሆኑን በመረዳታቸው ለእርሳቸው የሚሆን ዘርፍ አለመሆኑን ተገንዝበዋል።
ፍላጎታቸው የቆዳ ምርቶቹን እያዘጋጁ በቤታቸው ሆነው ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ነውና ስራውን ለመጀመር አላመነቱም። በመኖሪያ ቤታቸው አንድ ክፍል ውስጥ በእጅ ብቻ የሚዘጋጁ የሴቶች እጅ ቦርሳዎችን ማበጃጀቱን ተያያዙት። የመጀመሪያው አነስተኛ ገንዘብ እና ሳንቲም መያዣ የእጅ ቦርሳ ሰርተው ሲያጠናቅቁም የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ አይረሱትም። የያኔዋን የእጅ ቦርሳ የሸጧት በ25 ብር ነበር። ይህች 25 ብር ነገ እና ከነገወዲያ አድጋ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡ ምርቶችን እንደምታስገኝላቸው ደግሞ እምነታቸው ነበር።
በእጅ ብቻ ከሚዘጋጁ ምርቶች በተጨማሪ በቆዳ መስፊያ ማሽን የሚታገዙ ምርቶችን ለማቅረብ አላማቸው ቢሆንም የማሽን መግዣ ገንዘብ ግን በወቅቱ አልነበራቸውም። ይህን ችግራቸውን የተረዱ እህታቸው ደግሞ አንደ መስፊያ ሲንጀር ማሽን ገዝተው በስጦታ አቀረቡላቸው።
ይህ አጋጣሚ ለአቶ አሰበ እጥፍ ድርብ ደስታን የፈጠረ ነበር። ምክንያቱም በእጅ ብቻ አዘጋጅተው ከሚያቀርቡት በተሻለ በማሽን የተዘጋጁ ምርቶችን በብዛት እንዲያመርቱ እና ገቢያቸውንም እንዲያሳድጉ እድል የሚፈጥርላቸው በረከት ነበርና ነው።
ከዚህ በኋላ የእራሳቸው ፈጠራ የታከለባቸው የሚነገቱ የቆዳ ቦርሳዎችን እና የተለያዩ ቀበቶዎችን እንዲሁም የእጅ ቦርሳዎችን ማዘጋጀታቸውን ተያያዙት። ለዚህ እንዲረዳቸውም የቴክኒክና ሙያ የመጀመሪያ ደረጃ የቆዳ ሙያ ስልጠናን ወስደዋል። ከዚያም የቤታቸው ጠባብ በረንዳ ላይ ባስቀመጧት የመስፊያ ማሽን በጥራታቸውም ሆነ በዋጋቸው እንዲሁም በጥንካሬያቸው ተወዳጅ የሆኑ ምርቶችን ማዘጋጀቱን ተያያዙት።
ከመርካቶ የገዙትን የለሰለሰ ቆዳ በመቆራረጥ የቻይና እና የተለያዩ ውጭ አገራት ምርቶችን በሚወዳደር ደረጃ ሰፍተው ለገበያ ያቀርባሉ። ከተዋበ ስፌት ጋር ዲዛይኑን አዘጋጅተው የሰሩት ትልቁ የቆዳ ቦርሳ እስከ አንድ ሺ ሁለት መቶ ብር እየተሸጠ ይገኛል። በተለያዩ ባዛሮች ላይ ምርቶቻቸውን አቅርበው ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል። ዋናው ትኩረታቸው የቆዳ ምርት ፈጠራው እና ጥራቱ ላይ ነው እንጂ ገበያው ላይ አለመሆኑን ቢናገሩም በአንድ ሳምንት ሽያጭ እስከ ስምንት ሺ ብር ያገኙበት አጋጣሚም እንዳለ ይናገራሉ።
በመሆን የእራሳቸው የቆዳ መስፊያ ማሽን ስሌላቸው በብዛት እንዳያመረቱ እየያዛቸው መሆኑን የሚናገሩት የቆዳ ስፌት ባለሙያው፣በቀን እስከ ሶስት የኪስ ቦርሳዎችን ማምረት እንደሚችሉ አሳይተዋል። በእራሳቸው የእጅ ጥበብ የተዋበውን የቆዳ ኮፍያ ለማምረት ደግሞ አንድ ቀን ሙሉ እንደሚፈጅባቸው ያስረዳሉ።
በተጨማሪም በዲዛይን አቀራረባቸው ያማሩ የቆዳ ምርቶችን ስለሚያቀርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ እና ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት በግላቸው ገዝተው የሚልኩ ሰዎች በመኖራቸው አቶ አሰበ ደስተኛ ናቸው። ነገር ግን እራሳቸው አምርተው እራሳቸው ወደ ውጪ አገራት መላክ ቢፈልጉም የመስሪያ ቦታ እና የማሽን እጥረት እጃቸውን ይዟቸዋል።
በተለይ የዘመናዊ ቆዳ መስፊያ ማሽን ስለሌላቸው በብዛት አምርተው ወደገበያ ለማቅረብ ፈትኗቸዋል። ይህ ችግራቸውን ደግሞ ከተቋማት ብድር ወስደው ለመስራት አይፈልጉም። ምክንያቱም ብድር ከማይፈልጉት ነገር አንደኛው ነው።
ለልመና እጄን አልዘረጋም፣ ማንም ሰው ልመናን ማበረታታት የለበትም የሚሉት ጠንካራው አዛውንት፤ በጡረታ ገንዘብ ብቻ ከመኖር ይልቅ ስራ ፈጥረው ገቢ መፍጠር መቻላቸው ለሌሎች አምራቾችም ምሳሌ እንደሚሆን ይገልጻሉ። አንድን ስራ እችለዋለሁ ብሎ በጥንካሬ መንቀሳቀስ ከተቻለ ማደግ ይቻላል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በጌትነት ተስፋማርያም