ኢትዮጵያ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያሳየች ከምትገኝባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ብስክሌት ነው። ይህ ስፖርት በኢትዮጵያ ጠንካራ ሥራ ከተሠራ ካለው ምቹ ሁኔታ አንጻር ውጤታማ ለመሆን የሚቻልበት መሆኑ ይታመናል። የብስክሌት ስፖርት በኢትዮጵያ እስከ ኦሊምፒክ የደረሰ ተደጋጋሚ የተሳትፎ ታሪክ ቢኖረውም ሃገርን የሚያስጠራ ስኬት ማስመዝገብ ግን አልተቻለም። ይህንን ተከትሎም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት በተያዘው ዓመት በብስክሌት ስፖርት ልማት፣ ውድድርና ተሳትፎ በአገር አቀፍ፣ አህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻሉ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን ገምግሟል።
የውድድር ዓመቱ በሀገር አቀፍ ውድድሮች የተሻለና ውጤታማ ዝግጅት በማድረግ በስኬት ሊጠናቀቅ ችሏል። ዓመታዊው የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና በሰኔ ወር አጋማሽ በመቐለ ከተማ መድረጉን ያስታወሰው ፌዴሬሽኑ ካለፉት ዓመታት ለየት ባለመልኩ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኞች እና ሀገር ውስጥ ያሉ ሁሉንም ክለቦች አሳትፎ በስኬት ተጠናቋል። ውድድሩን ከታዳጊ ወጣቶች እስከ ‹‹ቱርደ ፍራንስ›› ባሉት ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚካፈሉ ብስክሌተኞች የደመቀ ነበር። ሻምፒዮናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስም ከ70 ሺ በላይ ተመልካች ሊታደም ችሏል።
ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃም ውጤታማ እንቅስቃሴን ያደረገች ሲሆን በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ተሳትፎዋ አንድ ወርቅና ሁለት ነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። ይኸውም ከሀገር ውስጥ ተሳትፎ ባለፈ ከሀገር ውጪ በሚካሄዱ መሰል ውድድሮች ላይ ውጤታማነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያመላክት ተጠቅሷል።
በሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ወጣቱ ብስክሌተኛ ኪያ ጀማል(የቀድሞው ታዋቂ ብስክሌተኛ ጀማል ሮጎራ ልጅ) በቀጥታ ለዓለም ሻምፒዮና ማለፍም ችሏል። በሴቶች ደግሞ ቀኖ አለሙ ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገበች ሲሆን፤ ሁለቱ ብስክሌተኞች ባስመዘገቡት ውጤት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሦስተኛ ሆና ውድድሯን እንድታጠናቅቅና በአህጉራዊ ውድድር የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲደረግ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ችግሮች ውስጥም ሆኖ የተሻለ ውጤት ማምጣቱ አበረታች መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በአህጉር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ የቱር ውድድሮች ኢትዮጵያ ተወክላ ነበር። በግብፅ ካይሮ የተደረገውና 12 ሀገሮች የተካፈሉበት ቱር ናይል የወጣቶች ውድድር አንዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በወጣቶች ጥምር ሦስት ብስክሌተኞችን አሳትፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች። ሌላኛው ኢትዮጵያ በተጋባዥነት የተሳተፈችበት እና በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው ቱር ጆበርግ ነው። በዚህም ውድድር ኪያ ጀማል አንደኛ በመውጣት ለውድድሩ የተዘጋጀውን የዋንጫ ሽልማትና የወርቅ ሜዳለያ መውሰድ ችሏል። ይህም በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች ጎልተው እንዲታዩ ያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከተሳትፎ በማለፍ በውጤታማነት እየቀጠለ መሆኑን እንደገመገመም ፌዴሬሽኑ ገልጿል። ባለፉት ዓመታት በዓለም ሻምፒዮናው ጥሩ ተሳትፎን እና እንቅስቃሴን ማድረግ መቻሉም ማሳያ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ወንድሙ ኃይሌ፣ ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሳትፎዎችን የምታደርገው የውድድሩን መመዘኛ አሟልታ እንጂ በኮታ አለመሆኑን ያስረዳሉ።
በዚህም በመስከረም ወር 2015 ዓም በአውስትራሊያ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሦስት ስፖርተኞችን በጥምር ውድድር አሳትፋ ከ57 ሀገሮች 13ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቀን ለአብነት ይጠቅሳሉ። በአውስትራሊያ እና ቤልጅየም በተደረጉ የዓለም ሻምፒዮናዎች ከአፍሪካ ሚኒማ አሟልተው የሚሳተፉት አራት ሀገራት ብቻ ናቸው። እነሱም ኤርትራ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ ሲሆኑ ፌዴሬሽኑ በሠራው ልክ ተሳትፎ እየተደረገና ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም እንደሚያመለክት ይናገራሉ።
በስፖርቱ ካለው አቅም አንጻር በደንብ ቢሠራ ከዚህም የተሻለ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ይታመናል። ብስክሌት ከአትሌቲክስ በመቀጠል በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ ቢሆንም በብዙዎች አእምሮ ውስጥ አለመኖሩን ፕሬዚዳንቱ ያብራራሉ። ይህም ስፖርቱ በሚገባው ልክ ብዙ እንዳይነገርለትና የፋይናንስ ድጋፍ አግኝቶ እንዳያድግ አድርጎታል ባይ ናቸው። የስፖርቱን ውጤታማነት ለማስቀጠልና ተወዳጅነትና ታዋቂነት እንዲያገኝ መረጃን ማድረስ ዋንኛው ሥራ በመሆኑ በስፋት ለመሥራት መወሰኑን ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ ውጤታማነቱን ለማስቀጠልና ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ለስፖርተኞችና ባለሙያዎች የሚያግዙ የአቅም ግንባታ ሥራዎችንም እንደሠራ በቀረበው ሪፖርት ጠቅሷል። ከነዚህም መካከል ውጤታማ የሆኑ ብስክሌተኞች ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ የሚገቡበት ሥርዓት ተዘርግቷል። በተዘረጋው ሥርዓትም በአገር አቀፍ ውድድሮች ባስመዘገቡት ውጤት አራት ብስክሌተኞች የውጭ ክለቦችን መቀላቀላቸውን አስታውሰዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015