ጅማ ከተማንለነዋሪዎች ተስማሚ፣ ለጎብኚዎች አማላይ ለማድረግ

ከኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ጅማ ናት። ጅማ ስትነሳም ንጉስ አባጅፋር ቀድመው ይታወሳሉ። ንጉሡ በመልካም ግንኙነትና አስተዳደር እሴታቸውም ለጅማ ከተማ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ትልቅ ዕሴት ጥለው ያለፉ መሆናቸው በርካቶች ይመሰክሩላቸዋል።

ጅማ በቡና ምርቷ ይበልጥ የምትታወቅ ሲሆን፤ በጅማ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አብዛኞቹ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች ቡና በስፋት የሚመረትባቸው ናቸው። የሕዝቡም ሕይወት ቡና ላይ የተመሰረተ ነው። ሌላኛው መገለጫዋ ፍቅር ነው። ጅማ የፍቅር ሀገር ናት። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው በፍቅርና በመተሳሰብ ይኖሩባታል። በኪነ-ጥበቡም ብዙ የተሰራበት፣ በርካቶችን ያፈለቀች ከተማ ናት። ከየትኛውም የሀገሪቷ አካባቢ የመጣ ማንኛውም ሰው በሰላም የሚኖርባት በመሆኑም ‹‹ጅማ የፍቅር ከተማ›› በመባልም ትታወቃለች።

ጅማ ከተቆረቆረች ወደ 200 ዓመት ገደማ እንደሚጠጋት ይነገራል። እኔ በተደጋጋሚ በወፍ በረር ቅኝት ከተማዋን የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር። በዚህ ወቅት ከተማዋ የእድሜዋን ያህል ማደግና መመንደግ አለመቻሏን መታዘብ ችያለሁ። ይህን ያህል አመታትን ያስቆጠረችው ከተማ ‹‹ምን አገኛት?›› ብዬ አዝኛለሁ። በእድሜ ሆነ በታሪክ የታናሾች ታናሽ የሆኑ ከተሞች እድገታቸው አስገራሚ በሆነበት በዚያ ወቅት፣ ጅማ ለምን አንቀላፋች ስልም ጠይቄአለሁ።

ምንም እንኳን የተለያዩ ሕንፃዎች እዚህም እዚያም ቢስተዋሉም ጅማን ለምታክል ሰፊና ታሪካዊ ከተማ ግን የሚመጥኑ ሆነው አላስተዋልኩኝም። በንግድና በዘመናዊ ከተማነት ከቀዳሚዎቹ አንዷ ብትሆንም ዛሬም ድረስ መንገድ በጅማ ብርቅ ነው።

ከዋናው የአስፋልት መንገድ ውጭ ያሉት የውስጥ ለውስጥ መንገዶች አንድም በመንገድ ሥራ አልያም በሌላ ምክንያት ተቆፋፍረዋል። በእድሜ እርጅና ምክንያት ተበለሻሽተዋል። ጠንካራ ዝናብ በሚኖርባቸው ወቅቶች ላይ የከተማዋ መንገዶች በጎርፍ መጥለቅለቃቸው፤ እንዲሁም ጎርፍ በፍሳሽ ቱቦዎች ከመውረድ ይልቅ በንግድ ተቋማትና በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሲንሸራሸር ማየት የተለመደ ነው።

ከተሞችን ተወዳዳሪና ለነዋሪዎች ተስማሚ፣ ለጎብኚዎች አማላይ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል የመሰረተ ልማት መሟላት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ሲሆን፤ ውበትና መናፈሻዎችም በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁንና ጅማ ስሟን፣ ዝናዋንና የዕድሜዋን ርዝማኔ ያህል በመሰረተ ልማት ቀዳሚ ካለመሆኗ ባለፈ ከተማዋን የሚመጥኑ ውብ መናፈሻዎችና አረንጓዴ ስፍራዎችን ሳትታደል ቆይታለች።

የከተማዋ ነዋሪዎችም ሆኑ እግር የጣላቸው እንግዶች ውስጣዊ ስሜታቸውን የሚያዳምጡባቸውና አዕምሯዊ ዕረፍት የሚያገኙባቸው ብሎም የሚዝናኑባቸው ውብና ንፁሕ መናፈሻዎችና አረንጓዴ ስፍራዎች ማግኘት የሰማይ ያህል ርቋቸው አመታት ስለማስቆጠራቸው ያስታውሳሉ።

ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ ግን ጅማ ከተማ በርካታ መሻሻሎች እያሳየች በልማት እጦት የጠቆረ መልኳን ለመቀየር እየፈገገች መጥታለች። ለዚህ ምስክርነት የሚበቁ የተለያዩ የልማት ሥራዎችም በከተማዋ መስተዋል ጀምረዋል። ጅማን ለነዋሪዎች ተስማሚ፣ ለጎብኚዎች አማላይ ከተማ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ዕውን በማድረግ ጅማሬውን ማሳመር ተችሏል።

የጅማ ከተማን ለሁለት አቋርጦ የሚያልፈው የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ ልማት የጅማን መልክ ለመቀየር በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀስ ነው። ይህ ወንዝ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይለማና የሚፈለገው እንክብካቤ ሳይደረግለት በመቆየቱ ተገቢውን የመስህብነት ጥቅም መስጠት ሳይችል ከመቅረቱም ባለፈ ለነዋሪዎች ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

ወንዙ፤ ለተለያዩ ሆቴሎች፣ ከትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከነዋሪዎች የሚለቀቅ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ በመሆን ያገለገለው አዌቱ ወንዝ፣ በተለይ ክረምት ወቅት ስለሚሞላ በዙሪያው ላሉ ነዋሪዎች የጭንቀትና የስጋት ምክንያት ሆኖም አመታት አልፈዋል።

ከተማዋን 12 ኪሎ ሜትር ያህል አቋርጦ የሚያልፈው አዌቱ ወንዝ በርካቶችን ከመኖሪያ ቀያቸው ያፈናቀለና አለፍ ሲልም ሕይወት የቀጠፈ ነው። በበጋም ቢሆን የተለያዩ ቆሻሻዎች የሚጣሉበትና የሽንት ቤት መስመሮች የሚለቀቅበት በመሆኑ የጤና ጠንቅ እንደነበር ነዋሪዎቹም ሆኑ ከተማዋን የሚጎበኙ እንግዶቿ ትውስታ ነው።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዋሴ ግርማም፣ ‹‹የአዌቱ ወንዝ ከዚህ ቀደም በኅብረተሰቡ ችግር ፈጣሪ ተደርጎ የሚወሰድ የነበረና በክረምት ቆሻሻን ይዞ በመምጣት ሰዎችን ከማፈናቀል አልፎ ለተለያዩ በሽታዎች ሲዳርጋቸው የቆየ ወንዝ ነበር›› ይላሉ።

ምክትል ከንቲባው እንደሚገልፁት፣ አሁን ላይ ግን ይህ የጅማ ታሪክ ተቀይሯል። በአሁን ወቅትም በከተማዋ በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሚገመት በጀት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ናቸው። የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ፣ የቁጠባ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የስራ እድል ለመፍጠር የሚያግዙና የከተማዋን ውበት የሚያጎሉ ፕሮጀክቶች ጨምሮ ከ29 በላይ ትናንሽ እና ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋን ለማደስ በግንባታ ምእራፍ ላይ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል ሁለት ትልልቅ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። አንደኛው ፕሮጀክት የሚገነቡት ከተማዋን አቋርጦ በሚያልፈው አዌቱ ወንዝ ላይ ነው። አዌቱ ፔይስትሪ ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲሰጥ ታስቦ የተጀመረ ነው።

አዌቱ ፓርክ ለከተማዋ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች የመዝናኛና የእፎይታ ስፍራ ሆኖ እንዲያገለግል እንዲሁም ጅማ ከተማ የቱሪዝምና የንግድ ማዕከል ለመሆን የሰነቀችውን ራዕይ እውን ለማድረግ ታስቦ የተሰራና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነባ ያለውን የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ሌጋሲን ለማስቀጠል ታስቦ እየለማ ያለ ፕሮጀክት ነው።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ የአዌቱ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ግንባታ በሶስት ምእራፎች የሚገነባ ነው። ሁለት ዙር ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው 400 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ይሆናል። ግንባታው በከተማ አስተዳደሩና በተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እየተካሄደ ይገኛል። አስተዳደሩ በ84 ሚሊዮን ብር ሦስተኛ ዙር የፓርኩን ግንባታ ሥራ ለማስጀመርም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

መናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች በከተሞች መኖራቸው ነዋሪዎች ንጽህ አየር እየተነፈሱ እንዲሁም በለምለም ዛፎች መካከል በፍፁም ምቾት እየተንሸራሸሩ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ያደርጋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ግላዊነት የጎላበትን የማህበራዊ ግንኙነት ፈር በማስያዝ የጋራ ማህበራዊ እሴትን ያጠናክራል።

በከተማ መሃል የሚገኙ መናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች መስተጋብርን ከማጠናከር ባሻገር የተለያዩ ጥበባዊ የሆኑ አውደ ርእዮችን ዝግጅቶች ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። ከሕፃን እስከ አዛውንት ለሁሉም ክፍት እንደመሆናቸውም በአጠቃላይ ጤናማና ደስተኛ ሕዝብ ለመፍጠር ሁነኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በኢኮኖሚ ረገድ በአግባቡ ከተሰራባቸው የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላሉ፤ በሥራ ፈጠራው ወቅታዊውን የሀገሪቱ ራስ ምታት የሆነውን የሥራ አጥነት ችግር የማቃለል አቅማቸው ግዙፍ ይሆናል።

የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ ልማት መጠናቀቅም ለከተማው ነዋሪም ሆነ ለእንግዶች የመስህብ ስፍራ ከመሆን ባለፈ የገቢ ምንጭ የመሆን አቅሙም ግዙፍ ነው። ዜጎች በክረምት ወራት ይደርስባቸው ከነበረው ለጎርፍ የመጋለጥ ስጋት እንዲላቀቁ ምክንያት ይሆናል።

ፕሮጀክቶቹ ከመስህብነት ባለፈ በሥራ እድል ፈጠራ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው የሚጠቁሙት አቶ ዋሴም፣ በተለይ በወንዝ ዳር አካባቢዎች የሚገኙ መናፈሻዎችና ሱቆችም ለበርካቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ታሳቢ በማድረግ ከተማ አስተዳደሩም ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው በአዌቱ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የወንዝ ዳር ፕሮጀክት አካል ሲቲ ፓርክ ነው። ምክትል ከንቲባው አቶ ዋሴ እንደሚገልፁትም፣ ሲቲ ፓርኩ የሚያርፈው 12 ሄክታር ስፋት እና አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝማኔ ባለው ቦታ ላይ ነው። ‹‹የፓርኩ ግንባታ ሦስት ዙሮች አሉት›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ በዚህ አመት እየተከናወነ መሆኑንና በመጀመሪያው ዙር ግንባታም 150 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተሠራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ፓርኩ ወደፊት የጅማ ከተማን የቱሪዝም፣ የኮንፈረንስና የንግድ ማዕከልነት የሚያሳድግ፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ እንግዶች ማረፊያ እና ለከተማዋ ነዋሪዎችም የመዝናኛ ስፍራ የመሆን ጉልበቱ ጠንካራ ነው። ፓርኩ ሲጠናቀቅ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የልጆች መጫወቻ ሜዳ፣ የውሃ ፏፏቴ፣ የመዋኛ (የኩሬ ውሃ) ካፌና ሱቆች ይኖሩታል።

አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ግንባታም በሚቀጥለው አመት ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅትም በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ አመት ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከመንግስት በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ገንዘቡንና ጉልበቱን ከማስተባበር ባለፈ በሃሳብ ጭምር ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በበጀት ዓመቱ የኑሮ ውድነትና የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መናርን የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ ሁኔታ የተፈታተነ ቢሆንም ኅብረተሰቡ ባለው አቅም የልማት ሥራዎችን በማስተባበርና በፕሮጀክት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የልማት አጋርነቱን አሳይቷል።

ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ ባሻገር በአግባቡ ከማስተዳደርና ለእይታ ማራኪና ሳቢ በሆነ መልኩ እንዲታዩ በማድረግ ረገድ በተለይም የአገልግሎት ዘመናቸውን ከማስረዘም አንፃር የህብረተሰብ ግንዛቤን የማጎልበትና በኃላፊነትና በጥንቃቄ እንዲመለከታቸው ብሎም እንዲጠብቃቸው በማስገንዘብ ረገድ በትኩረት መሥራት ይገባል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *