መተማመን እስከምን ?

ከጥቂት የዕረፍት ቆይታ በኋላ ወደሥራ ገበታዬ ተመልሻለሁ። ብዙ ጊዜ ይህ መሰሉ እረፍት ንቁ መንፈስ ያላብሳል፣ ለአዲስ ሥራ ያዘጋጃል። በእኔ ውስጠት የነበረው እውነታም ይኸው ነበር። ለሚዘጋጀው ሳምንታዊ የጋዜጣ ዓምድ ‹‹ይበጃል›› ባልኩት ዕቅድ ከራሴ ስመክር ሰንብቻለሁ።

ሥራ በገባሁ ማግስት ዕቅዴን አፀድቄ ከሚመለከታቸው ጋር ቀጠሮ ይዣለሁ። ‹‹እንዲህም ይኖራል›› የተሰኘውን ሳምንታዊ ዓምድ ለማዘጋጀት። በነገራችን ላይ ይህ ዓምድ በዝቅተኛና በአስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ሕይወት ይዳስሳል። በሕመም የሚሰቃዩ፣ በችግር የሚፈተኑ፣ አግኝተው ያጡ፣ ወጥተው የወረዱ ሰዎችን ጓዳ ይፈትሻል ።

እነዚህ ነፍሶች ያለፉባቸው ውጣ ውረዶች፣ ሻካራማ መንገዶች፣ክፉና በጎ አጋጣሚዎች ተሞክሮው አይናቅም። ልምዳቸው ለሌሎች ይተርፋል። ተምሳሌታቸው ለብዙዎች ያስተምራል። የዓምዱ ዋና ዓላማ ለእነዚህ ወገኖች የሚበጅ ዘላቂ መፍትሔ ማዘጋጀት ነው።

በታሪካቸው ልባቸው የተነካ አንባቢያን ዝም እንዳይሉ፣ ስለነሱ ግድ የሚላቸው፣ ዕንባቸውን የሚያብሱ ሸክማቸውን የሚካፈሉ፣ ልበ መልካሞች እጃቸውን እንዲዘረጉ ዕድል ይፈጥራል።

በበኩሌ በዚህ ዓምድ አጋጣሚ ባገኘኋቸው በርካታ ወገኖች ታሪክ ልቤ ሲያዝን፣ ዓይኔ ሲያነባ ከርሟል። ባወጋኋቸው ጊዜ አብሬያቸው ተንሰቅስቄያለሁ፣ ታሪካቸውን ስጽፍ፣ መልሼም ሳነበው ደጋግሜ አልቅሻለሁ። ይህ እውነታ ደግሞ በእኔ ብቻ አይቀርም። ስሜቱ ለበርካታ አንባቢያን ይጋባል።

የዛሬውን ትዝብት የመጻፌ ዋንኛ ዓላማ ስለዚህ ድንቅ ዓምድ በስፋት ለማስተዋወቅ፣ አይደለም። ዓምዱን ለማዘጋጀት በተንቀሳቀስኩበት አጋጣሚ የደረሰብኝን አሳዛኝ አጋጣሚ ለመጠቆም እንጂ።

ጉዳዩ የተፈጸመው ባሳለፍነው ሳምነት መጀመሪያ ላይ ነበር። የዓምዱ እንግዶች ለመሆን ከኔ ጋር ቀጠሮ ከያዙ እናቶች ጋር አስቀድሜ በስልክ አውርቻለሁ። ቀጠሯችን ከቀትር በኋላ እንዲሆን በመሻታቸውም ፍላጎታቸውን አክብሬያለሁ።

ለዛሬ የማገኛቸው እንግዶች ጉልት ተቀምጠው የሚነግዱ ምስኪን እናቶች ናቸው። እያንዳንዳቸው ስላሉበት ፈታኝ ሕይወት ሊተነፍሱልኝ አስበዋል። ከእንዲህ አይነቶቹ ወገኖች ተሞክሮ ተመሳሳይ ታሪኮች እንደሚመዘዙ አውቃለሁ ።

ስለሴቶቹ እያሰብኩ፣ ስለሚነግሩኝ እውነታዎች እያብሰለሰልኩ፣ በስፍራው ከሚያደርሰኝ መኪና ገብቼ ጉዞ ጀምሬያለሁ። ከታሪካቸው ባሻገር ስለ መፍትሔው ማሰብ ልማዴ ነውና ገና ሳላገኛቸው ከራሴ ውዝግብ ይዣለሁ። መንገዴ ከቢሮዬ ሳብ ቢልም ርቀቱ አልተሰማኝም። በሀሳብ ተጠምጃለሁ። ከቦታው መድረሴን ያሳወቀኝ ሾፌሩ ነበር። ከመኪናው ወረድኩና ወደስፍራው አመራሁ።

አካባቢው አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በተለምዶ ‹‹አስኮ አዲስ ሰፈር››ይባላል። እግሬ ስፍራውን እንደረገጠ ከምፈልጋቸው እናቶች ጋር ተገናኘሁ። አብዛኞቹ ጥቂት ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቃሪያና ጎመን ይዘው ከመንገድ ዳር ተቀምጠዋል። በሁሉም ገጽታ መረጋጋት አይታይም። ‹‹አዩኝ፣አላዩኝ››በሚል ስጋት እየተሸማቀቁ ነው። በእጃቸው ያለውን የጉልት ግብዓት ለመቃኘት ሞከርኩ። እምብዛም ከዓይን አይገባም ።

ሴቶቹ ማንነቴን ባወቁ ጊዜ በተለየ አክብሮት ተቀበሉኝ። አብዛኞቹ የኑሮ ሸክም አድክሟቸዋል፣ ተጎሳቁለዋል። በትህትና ለሰላምታ የተዘረጉ እጆቻቸውን መጨበጥ ጀመርኩ። የሁሉም መዳፍ ሻካራ ነው። ከእያንዳንዳቸው ገጽታ ላይ ጥንካሬን ከተስፋ መቁረጥ ያነበብኩ መሰለኝ። ውስጤ ይበልጥ ለጥያቄ ተነሳሳ።

ለቃለመጠይቅ ያመቻል ባሉኝ ቦታ አረፍ ብለን ከአንዲት እናት ጋር የመጀመሪያውን ውይይት ጀምሬያለሁ። ጆሮዎቼ በንቃት ያዳምጣሉ፣ መቅረፀ ድምፁ በአግባቡ ድምፅ ይቀዳል። በአሳዛኝ የሕይወት ውጣውረድ ያለፈችው ሴት ታሪክ ውስጤን ይነካኝ ይዟል።

በየአጋጣሚው ከምሰማቸው እውነታዎች ከማዘን ባለፈ አብሬ ማልቀስ ልማዴ ነው። ዛሬ ግን ራሴን እየተቆጣጠርኩ ነው። እያዳመጥኳት ብዙ አሰብኩ፣ ብዙ አዘንኩ። ከእሷ ጋር የነበረኝን ቆይታ አጠናቅቄ ከሁለተኛዋ እናት ጋር ውይይቴን ቀጠልኩ።

የእሷም ሕይወት ተመሳሳይ ነው። ከማንነቷ እየመመዘዘች የምታጋራኝ ታሪክ መንፈሴን ሰቀዞታል። ውስጤ እንደልማዱ እያነባ ነው። ቀጣይዋን ሴት መጠየቅ ጀምሬያለሁ። ተመሳሳይ ሕይወት፣ አሳዛኝ ታሪክ፣ የሚያስለቅስ እውነታ ለጆሮዬ አደረሰችኝ ።

ከአንዲት ልጅ እግር ጋር ውይይቴን ቀጥያለሁ። ውስጤ በግርምታ እያዳመጠ መቅረፀ ድምፁ የምሰማውን ታሪክ በአግባቡ መያዙን ቀጥሏል። በዚህ መሐል ቀና ብዬ አካባቢውን ቃኘሁ። ብዙ ሰዎች በዙሪያችን ቆመዋል። ወደነበርኩበት መለስ ብዬ አስገራሚውን ታሪክ ማዳመጤን ቀጠልኩ። አፍታ አልቆየሁም። በርከት ያሉ ፖሊሶች ሰዎችን እየጣሱ አጠገቤ መድረሳቸውን አስተዋልኩ። አልደነገጥኩም።

ከፖሊሶቹ መሐል ፊቱ ላይ የተለየ ምልክት ያለበት በቁጣ እየተንደረደረ ሥራዬን እንዳቆም አስጠነቀቀኝ። ምክንያቱ ባይገባኝም ትዕዛዙን ፈጸምኩ። በዚህ ብቻ አልቆመም። የፈቃድ ደብዳቤ ይዤ እንደሆን ጠየቀኝ። ጥያቄው ለእኔ ያልተለመደና አዲስ ነው። በኩራት የምሠራበት የሚዲያ ዓርማና ስያሜ ያለበትን መታወቂያዬን አውጥቼ ሰጠሁት። ከምንም አልቆጠረውም። እየደጋገመ ደብዳቤውን እንድሰጠው ወተወተኝ።

ከዚህ በኋላ ያለው ጉዳይ በሁለታችን ምልልስ ብቻ አልተቋጨም። አብረውት የነበሩ ሌሎች ፖሊሶች መታወቂያዬን ጨምሮ ሞባይሌንና የድምጽ መቅረጫ ቴፔን ነጠቁኝ። መዋከቡ ቀጠለ። በስፍራው ምን ላደርግ እንደመጣሁ ተጠየኩ። በተቻለኝ አቅም ተረጋግቼ ለማስረዳት ሞከርኩ።

ጉዳዩ ጥያቄ ብቻ አልሆነም። እኔና መሰሎቼ ሀገር ለማወክ፣ለማሸበር ይህን መሰሉን ተግባር እየፈጸምን ስለመሆናችን እየወቀሱ ያሰረዱኝ ጀመር። በእርጋታ ለማስረዳት ሞከርኩ። ሰሚ አላገኘሁም። ዞር ስል በበርካታ ፖሊሶችና ሰዎች ታጅቤ እየተነዳሁ ነው። እነዛ ምሰኪን ሴቶችም ተይዘው ተከትለውኛል። በመንገዳችን ላይ ከእያንዳንዱ ፖሊስ የሚቀርብልኝ ጥያቄ አስገራሚ ነው። ‹‹ሰፈርሽ የት ነው?›› ‹‹ጀሞ››ስል ፈጠን ብዬ መለስኩ።

ጠያቂዬ በንዴት አይኑን አፍጥጦ ከጀሞ አስኮ ምን ላደርግ እንደመጣሁ ጠየቀኝ። ‹‹እንዴ አስኮ ኢትዮጵያ አይደለም እንዴ? ጀሞስ? በውስጤ አልጎመጎምኩ። ይግረምሽ ብለው ከምሠራበት አራት ኪሎ እነሱ አጥቢያ ድረስ ለምን እንደመጣሁ ጭምር እንድመልስላቸው ያዋክቡኝ ጀመር።

ከማን ጋር እያወራሁ እንደሆነ ግራ ገባኝ። አንዳቸው እንኳን ሊረዱኝ አለመቻላቸው ደግሞ አስገረመኝ፣ አናደደኝ። እውነት ለመናገር ለፖሊስ የተለየ ፍቅርና አክብሮት አለኝ። ከዚህ ቀደም በሚዲያው ጭምር እሠራ ስለነበር ራሴን እንደ አንድ የፖሊስ አባል እቆጥራለሁ። ይህ ትውስ ቢለኝ በአግባቡ ለማስረዳት ሞከርኩ። ሰሚ አላገኘሁም።

አሁን መታወቂያዬን ጨምሮ ሞባይሌና ድምፅ መቅረጫዬ ከእጄ የሉም። በፖሊሶች እንደታጀብኩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከሴቶቹ ጋር እየተጋዝኩ ነው። በፊት በኋላዬ ያሉት ፖሊሶች በድንገት አንድ መንገደኛን ባለመኪና አስገድደው አስቆሙት። ወጣቱ ሾፌር ተደናግጦ መኪናውን ከማቆሙ ሁላችንንም አጭቀው ወደጣቢያ ወሰዱን።

ጣቢያ ግቢ ስደርስ ውስጤ መረጋጋት ጀመረ። ከዚህ በኋላ ለምጠየቀው ሁሉ በተገቢው መልኩ ምላሽ እሰጣለሁ፣ አልዋከብም፣ አልሰደብም። ፖሊሶቹ አንድ አሸባሪን አሳደው እንደያዙ ሁሉ ሪፖርት አድርገው ግዳያቸውን አስረክበው ከአካባቢው ርቀዋል። ‹‹እሰይ!›› እፎይታ ተሰማኝ።

በእኔና በመርማሪው መካከል ጥያቄና መልሱ ቀጠለ። ሁኔታውን በአግባቡ አስረዳሁ። ቃሌን የሚቀበለው ፖሊስ በወጉ አደመጠኝ። ውስጤን ቀለል አለው። ደግነቱ እነዛ ምስኪን እናቶች ላይ ነገር አልከረረም። በወቅቱ እየተመናጨቁ ቢዋከቡም ስማቸውን አስመዝግበው ሲፈለጉ እንደሚመጡ ተነግሯቸው ሄደዋል።

መርማሪው እውነታውን ከተረዳ በኋላ በበለጠ ማስረጃ ማረጋገጥ ፈልጓል። ታዛዥ ሆኛለሁ። በምሠራበት የሚዲያ ተቋም ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር እንዳገናኘው ጠይቆኝ ስልካቸውን ሰጥቼ ሐቁን አረጋግጧል። የያዙኝ ፖሊሶች እንዳሰቡት ያለፈቃድ ደብዳቤ የምንቀሳቀስ አሸባሪ ሳልሆን አንዲት የመንግሥት ሚዲያ ጋዜጠኛ ነኝ።

ይህ እውነታ ቢታወቅም በስንብት ብቻ አልተለቀቅኩም። ከድርጅቴ ማንነቴን የሚያስረዳ ሕጋዊ ደብዳቤ እስኪመጣ በስፍራው እንድቆይ ተደረገ። ሰዓቱ እየቆጠረ፣ ጊዜው እየመሸ ነው። ጉድ ፈላ! አመሻሹ ላይ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ስምና ፊርማ ያረፈበትን ደብዳቤ የያዙ ኃላፊዎች በስፍራው ደረሱ። ደስ አለኝ።

ከመርማሪው ጋር ውይይቱ በሰላማዊ መግባባት ቀጠለ። አሁን አስቀድሞ በልቦናዬ የነበረው እውነተኛ የፖሊስ ማንነት በውስጤ አንሰራራ። ጭውውታችን በፍጹም እህታዊና ወንድማማችነት ሆነ። ከጣቢያው ተለቅቄ ለመውጣት የአንድ ሰው ማረጋገጫን ማግኘት የግድ ነበር። ኃላፊው በስፍራው አልነበሩምና እስኪመጡ ጠበቅን። ስናገኛቸው በፍጹም ትህትናና አክብሮት አስተናገዱን።

ጥያቄው አልቀረልንም። አሁን ሦስት ሆነናል። ኃይላችን ጠንክሯል። ሦስታችንም የሚዲያ ባለሙያና ጋዜጠኞች ነን። ለምላሹ እጅ አልሰጠንም። ተገቢውን ማስረዳት በብቃት ፈጽመን በምስጋናና መግባባት ለስንብት ተጨባበጥን።

በመጨረሻ የፖሊሰ ኃላፊው እንዲህ አሉን ‹‹የቀደሙት አባላት ቃልሽን አምነው፣ በመታወቂያሽ ቢያሰናብቱሽ መልካም ነበር›› ሁላችንም ሀሳባቸውን ተረዳን። እኔ ግን በውስጤ እነዛን የፖሊስ አባላት እያሰብኩ መልሼ ተገረምኩ። መተማመን ማለት እስከምን ይሆን? ስልም ራሴን ጠየቅሁ።

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *