በመካከለኛ ርቀት በርካታ ክብረወሰኖችን እንዲሁም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የምትታወቀው ኢትዮጵያዊት አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረጅም ርቀት ውድድሮች በተለይም በማራቶን በመወዳደር አዲስ ምዕራፍ ጀምራለች። በመም ውድድሮች ላይ ከተፎካካሪዎቿ ጋር ሰፊ ልዩነትን በመፍጠር በአስደናቂ ብቃት የምትታወቀው ገንዘቤ እአአ ከ2020 ወዲህ በጎዳና ላይ ሩጫዎች መታየት ጀምራለች። ከወራት በኋላም ከታላላቅ ማራቶኖች አንዱ በሆነው የቺካጎ ማራቶን ትሳተፋለች።
በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው 6ቱ ሜጀር ማራቶኖች መካከል አንዱ የሆነው የቺካጎ ማራቶን ከሁለት ወራት በኋላ ይካሄዳል። ለ45ኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር በሺዎች የሚቆጠሩ ሯጮች የሚካፈሉበት ሲሆን፤ የዓለም ከዋክብት አትሌቶች የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የአሸናፊነት ቅድመ ግምት በማግኘት ቀዳሚዎቹ ናቸው። የቺካጎ ማራቶን በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ከሚሰበርባቸው ውድድሮች መካከል አንዱ እንደመሆኑም ፈጣን ሰዓት ይመዘገባል ተብሎም ይጠበቃል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር ገንዘቤ ዲባባ ውጤታማ ትሆናለች ተብሎ ተገምቷል። ፈጣኗ አትሌት ከ1ሺ500 እስከ 5ሺ ሜትር ባላት ተሳትፎ ውጤታማነቷን በተለያዩ ጊዜያት አስመስክራለች። በ1 ማይል፣ በ3ሺ ሜትር እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኖችን መሰባበር የቻለችው ገንዘቤ፤ እአአ በ2015 የዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በዚያው ዓመት በተካሄደው የቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይም በ1ሺ500 የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ለሀገሯ ማስመዝገብ ችላለች። ይኸውም የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት በመሆን ለመሸለም አብቅቷታል።
ገንዘቤ ከመም ውድድሮች ባሻገር በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮናም ስኬታማ አትሌት ስትሆን፤ የጎዳና ውድድሮች ላይ መሳተፍ የጀመረችው ከሶስት ዓመታት ወዲህ ነው። የመጀመሪያ ተሳትፎዋ በሆነው የቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን አሸናፊ ነበረች። በወቅቱ የገባችበት 65:18 የሆነ ሰዓትም ምርጥ ሰዓት በሚል ተመዝግቦላታል። ባለፈው ዓመት ደግሞ በአምስተርዳም ማራቶን ሮጣ የሀገሯን ልጅ አልማዝ አያናን ተከትላ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛም ነበር። በዚያ ውድድር ያስመዘገበችው 2:18:05 የሆነው ሰዓቷም በቀጣዩ ቺካጎ ማራቶን ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ምርጥ አትሌቶች ሶስተኛው ፈጣን ሰዓት ነው። ይህም አትሌቷ በሩጫው አሸናፊ ትሆናለች የሚለውን ግምት እንድታገኝ አድርጓታል።
ገንዘቤ በውድድሩ ከባድ ፈተና ከኬንያዊያን ተፎካካሪዎቿ ልታስተናግድ እንደምትችል ይጠበቃል። ፈጣን ሰዓት ያላት ሩት ቼፕኬቲች በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች በደቂቃዎች የፈጠነ የተሻለ ሰዓት ያላት ሲሆን፤ ጆይሲሊን ቼፕኮስጊ ደግሞ ከገንዘቤ በአንድ ደቂቃ የቀደመ ሰዓት ባለቤት ናት። ይኸውም በአትሌቶቹ መካከል ሊኖር የሚችለው ፉክክር ጠንካራ እንደሚሆን ያመላከተ ነው። ገንዘቤ ዲባባ ጠንካራ ፉክክር በሚጠበቅበት ውድድር በተካነችበት ፈጣን አሯሯጧ ታግዛ ድሉን በእጇ እንደምታስገባ ግምት ተሰጥቷታል። በሌላ በኩል በማራቶን ሰፊ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሱቱሜ ከበደ፣ ትዕግስት ግርማ እና አባበል የሻነህ ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አትሌቶች እንደማይሆኑ ይጠበቃል።
በወንዶች በኩል የአምና አሸናፊው ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ እና ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን የፈጸመው ኢትዮጵያዊው ሰይፉ ቱራ በዚህ ውድድር ተካፋይ ናቸው። ከዓመት በፊት የተቀዳደሙት ሁለቱ አትሌቶች በዚህ ውድድር ዳግም የበላይነት ለመያዝ የሚፋለሙ ይሆናል። ኬንያዊው አትሌት ለሁለተኛ ጊዜ በዚህ ማራቶን ተሳትፎ የበላይነቱን መቆጣጠር ይፈልጋል። በአንጻሩ እአአ በ2021 የቺካጎ ማራቶን አሸናፊ የነበረው ሰይፉ ለሶስተኛ ጊዜ በመድረኩ በሚኖረው ተከታታይ ተሳትፎ አሸናፊ ለመሆን ተዘጋጅቷል። አትሌቱ ያለፈው ዓመት ለአሸናፊነት ብርቱ ጥረት ያደረገ ቢሆንም በ25 ሰከንዶች ብቻ ብልጫ ተወስዶበት ነበር የአሸናፊነት ዕድሉን የተነጠቀው። በመሆኑም ይህንኑ ለማስመለስና በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን የሚያደርገው ጠንካራ ፉክክር በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ነው።
ከሰይፉ ባለፈም ዳዊት ወልዴ፣ ሁሰዲን ሞሃመድ እና ሚልኬሳ መንገሻ በውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸውን ያሳወቁና ለጠንካራ ፉክክርና ውጤታማነት የሚጠበቁ ኢትዮጵያዊ አትሌቶች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015