ጥቅም ላይ ያልዋለው የማዕድን ሀብት

በዓለማችን ብዙ የኖራ ድንጋይ ክምችቶች እንዳሉ ይነገራል። ከዓለም ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሀብቱ በስፋት ካላቸው ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከ900 ሚሊዮን ቶን በላይ የኖራ ድንጋይ ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል። ይሁንና የኖራ ድንጋይ በጣም ውድ የተፈጥሮ ሀብት እንደመሆኑ ሃብቱን በሚፈለገው ልክ መጠቀም አልተቻለም። የኖራ ድንጋዩ ውድነትም ሃብቱን ከከርሰ ምድር ለማውጣት አጋዥ ከሆኑ ቁሳቁሶች ይጀምራል።

በሀገሪቱ የኖራ ድንጋይ በስፋት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋና ደቡብ ክልል ይጠቀሳሉ። የኖራ ድንጋይ ማዕድን ለተለያዩ ዘርፎች ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ሲሆን፤ በዋናነት አሲዳማ አፈርን ለማከም ነው። አሲዳማ አፈርን ማከም ደግሞ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፤ እንደ ሀገር ቁጥሩ ሰፊ የሆነ የኖራ ድንጋይ ቢኖርም ጥቅም ላይ የዋለው ግን በጣም ጥቂት ነው። ለምሳሌ፡- አሲዳማ አፈርን ከማከም አኳያ ጥቅም ላይ የዋለው 10 ነጥብ ሶስት በመቶ ብቻ ነው።

የግብርና ሚኒስቴር የስትራቴጂክ እና እቅድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዜና ሀብተወልድ ለተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አፈጻጸምን አስመልክተው ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ በአሲድ የተጠቃ መሬትን ለማከም በ2015 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ ነበረ። ይሁንና በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም በተደረገው ጥረት 10 ነጥብ ሶስት በመቶ ብቻ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ማቅረብ የተቻለው ከሚያስፈልገው የኖራ መጠን 110 ሺህ ኩንታል ያህል ሲሆን ይህም እጅግ ዝቅተኛ ነው።

ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወይንም አሁን እየታረሰ ካለው መሬት 43 ከመቶ የሚሆነው መሬት በአሲድ የተጠቃ ሲሆን፤ ይህንን መሬት በኖራ ማከም አልተቻለም። በመሆኑም አሲዳማነቱ ሰፍቷል። የአሲዳማነቱ መስፋት ደግሞ የማዳበሪያን ውጤታማነት ከ71 እስከ 100 በመቶ እየቀነሰ ስለመሆኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሲያስረዱ፤

በብዙ ጥረት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የመጣው ማዳበሪያ 71 በመቶው ሥራ ላይ የማይውል ከሆነ ለሀገር ኢኮኖሚ ምን ያህል ኪሳራ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ለአርሶ አደሩም ቢሆን ፈተና ነው። ስለሆነም ያለንን ሀብት መጠቀም ላይ በስፋት መሥራት ይገባል ባይ ናቸው።

አንድን መሬት ለማከም የሚያስፈልገው የኖራ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ የጠቀሱት የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት እና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ በበኩላቸው፤ አንድ ሄክታር መሬትን ለማከም እስከ 30 ኩንታል ኖራ የሚያስፈልግና ለዚህም 35 ሺህ ብር ይጠይቃል ነው ያሉት። አያይዘውም ይህን ያህል መጠን ኖራ አርሶ አደሩ በቀላሉ ማግኘት የሚችለው አይደለም። ስለሆነም የኖራ ማዕድን በስፋት ለመጠቀም በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ እንደ ሀገር መሥራትና ችግሩን ለመፍታት መሞከር የውዴታ ግዴታ ነው። ከዚህ አንጻር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር ለመሥራት እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ኖራ አሲዳማ አፈርን በማከም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ከአሥር ኩንታል ወደ 40 እና 50 ኩንታል ያሳድጋል። በተለይም እንደ ሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚታረስ መሬታቸው ሙሉ ለሙሉ በአሲዳማነት የተጠቃባቸው ክልሎች ይህንን ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል በኩል በከፍተኛ መጠን መሥራት ይኖርባቸዋል። ለዚህም ደግሞ የግብርና ሚኒስቴርና የማዕድን ሚኒስቴር በጋራ ለመሥራት ስምምነት መድረሳቸው የኖራ ድንጋይን ጥቅም ላይ ለማዋል በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነ ነው ።

ስምምነቱ አሲዳማ አፈርን በአጭር ጊዜ ለማከም የሚያስችለውን የኖራ አይነት በመለየትና ምን ያህል ሀብት እንዳለ በማወቅ እንዲሁም ምርቱ የሚመረትበትን አግባብ በተለያየ መልኩ ለመሥራት ያስችላል። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን አሲዳማ አፈር በኖራ ድንጋይ ለማከም የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል።

እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ፤ አሲዳማ አፈር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመምጣቱ በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በደቡብ ክልሎች ምርትና ምርታማነት ቀንሷል። በአጠቃላይ እንደ ኢትዮጵያ ችግሩ እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው የተመላከተው።

በኢትዮጵያ ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በከፍተኛ ሁኔታ በአሲዳማ አፈር ተጠቅቷል። በመሆኑም ይህንን እየተስፋፋ የመጣውን አሲዳማ አፈርን በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ለማከም የኖራ ድንጋይ ሀብትን መጠቀም ፍላጎት ሳይሆን ግዴታ መሆን ይገባዋልም ሲሉ የሁለቱም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች በስምምነቱ ወቅት አስረድተዋል።

ኖራ ድንጋይ በዋነኝነት በካልሲየም ካርቦኔት (CaCO3) የተዋቀረ ሲሆን፤ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው። እንደ አይነቶቹም ስፋትና ጥልቀት አለው። ይሁን እንጂ እንደ ዓለም ጭምር በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ሶስቱ የኖራ አይነቶች ብቻ ሲሆኑ፤ እነዚህም የግብርና ኖራ፤ ፈጣን ኖራ እና የታሸገ ኖራ ናቸው።

የኖራ አይነትና ጥቅማቸው

የግብርና ኖራ ‹‹ Agricultural limestone››

ይህ የኖራ አይነት በሀገራቱ የተለያየ ስም ይሰጠዋል። ጥቅሙ ግን ተመሳሳይነት ያለው ነው። ለእጽዋት እድገት እጅግ በጣም ጥቅም ላይ የሚውል የኖራ ዓይነት ሲሆን፤ በተለይም አፈር ማሻሻል እና ፒ ኤችውን (የአፈር ጣዕም) ከፍ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው ነው። የእጽዋትን የካልሲየም አቅርቦት በመጨመር እጅግ በጣም የተሻሉ ንጥረ ነገሮች እንዲመረቱ ያደርጋል። ፈንገሶችን በመቆጣጠር የአፈር አሲዳማነትን ይከላከላል። ብዙ ጊዜ ከመጠን በላይ የሆነ ዝናብ ሲጥል እጽዋት በአሲድ ሊጠቁ ይችላሉና ይህንን በማከም በኩል የሚያክለው የለም።

የግብርና ኖራ የማዳበሪያ አይነቶችን በመተካት ጭምር የሚያገለግልም ነው። የሰብል ቅሪቶች እንዲበሰብሱ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች እንዲሆኑ ያስችላልም። ይህ ማለት የአፈር አሲድን በመቀነስ በሰብሎች ውስጥ ምርትን እንደገና እንዲጨምር ያደርጋል። የአሉሚኒየምን መርዛማ ንጥረ ነገር ይቀንሳል። ማዳበሪያዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ይረዳል። አሲዳማነትን በመቀነስ የአፈርን አካላዊ ሁኔታ እንዲስተካከልም ያደርጋል። የውሃም ሆነ የአየር መመጣጠንን ይጨምራል። ፎስፈረስ በአፈር ውስጥ የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውል እድል የሚፈጠር ነው።

በተጨማሪም በሰብሎች ውስጥ በጣም በተለመደ መልኩ የሚፈጠሩ በሽታዎችን በመከላከል በፈንገስ ምክንያት የሚደርሰውን የእጽዋት ጉዳቶችን ይቀንሳል። ይህ የኖራ አይነት እንደሀገር ስጋት የሆነውን የምርትና ምርታማነት መቀነስ ችግርን መቅረፍ የሚችል ነው። ማለትም አሲዳማ መሬትን በማከም ከ50 እስከ 118 በመቶ ምርታማነትን ከፍ የምናደርግበት ዘዴ ነው።

ፈጣን ኖራ ‹‹Quick lime››

ፈጣን ኖራ ‹‹Quick lime›› የሚባለው በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውለው የኬሚካል ውህድ በመሆን ነው። ፈጣን ኖራ ጠጣር ሲሆን፤ ሙቀት ባለበት ክፍል ውስጥ ነጭ መልክ ሊኖራቸው ይችላል። እንደ ግብርና ኖራ ሁሉ ለእጽዋት ጥቅም የሚሰጡ ሲሆኑ፤ እጽዋትን የሚጎዱ ተባዮችን የሚያስወግዱ፣ እንደ አረም ማጥፊያ እና እንደ ማዳበሪያ የሚያገለግሉ ናቸው። ለእጽዋት እድገት እና ሕክምና በጣም አስፈላጊ የሆነውን ካልሲየም የሚሰጡ በመሆናቸውም ብዙውን ጊዜ ለበረሃ ጉድጓዶች እና ለተፈጥሮ ፍርስራሾች እንደ ማከሚያ ጥቅም ላይ ይውላሉ። መጥፎ ሽታንም ለማስወገድም የሚጠቅሙ ሲሆን፤ በተመሳሳይ እንደ ፈንገስ እና ባክቴሪያ ማጥፊያ ሆነውም ያገለግላሉ።

እንዲህ ዓይነት ኖራዎች ፀረ-ተባይ፤ ማለስለሻ፣ ማድረቂያ እንዲሁም እንደ ጥሬ ዕቃ ጭምር በመሆን በሁሉም የኢንዱስትሪ ሂደቶች ውስጥ ያገለግላሉና ሁለገብ በመባልም ይጠራሉ። በብዝኃነታቸውም ተለይተው ይታወቃሉ።

የታሸገ ኖራ ‹‹ Slaked Lime››

የታሸገ ኖራ ከሌሎች የኖራ አይነቶች ለየት የሚለው በዋናነት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው። አንዱ እርጥበትን ለመጠበቅ ያስችላል። ብዙ እጽዋት ከአፈሩም ሆነ ከአካባቢው ከመጠን በላይ እርጥበት ሲያጋጥማቸው የሚከላከል ነው። አሲዳማ ዝናብን ተከላክሎ እጽዋት እንዲያድጉ የሚያስችላቸውም ነው። እናም ኖራ እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ያሉ በመሆኑ ተመራጭ ነው። በበሽታ መከላከል ዙሪያም ከሌሎቹ የተለየ ነው። ማለትም ተባዮች እና በሽታዎች ወደ ሰብሎች ወረራ እንዳያደርጉ የሚከላከል ነው። ፀረ-ፈንገስ መድኃኒትም ነው። ለሕክምና ከሚያገለግሉ የኖራ አይነቶች መካከልም እንደ አንዱ ይጠቀሳል። ለፍሳሽ ማጣሪያ፤ ለወረቀት ምርት፤ ለግንባታ እና ለምግብ ማቀነባበሪያም እንዲሁ የሚያገለግል ነው።

እነዚህ የኖራ አይነቶች ይህንን ያህል ጥቅም ቢኖራቸውም ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ እምብዛም እየተሠራበት አይደለም። በአሁን ወቅትም “ጠንካራ” በሚባል ደረጃ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር የሚደርስ መሬት በአሲድ የተጠቃ መሆኑም በዚሁ ምክንያት ነው። ይህን ያህል መሬትን በአንድ ጊዜ ማከም የማይቻል እንደሆነም መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁንና አሁን ላይ መንግሥት እንደ መንግሥት ይህን ችግር ለመፍታት ዝግጅት በማድረግ በግብርና ሚኒስቴር በኩል በቀጣይ አሥር ዓመት ውስጥ በአሲድ የተጎዳው መሬትን ለማከም ታቅዷል። እቅዱን ለማሳካት ደግሞ በየዓመቱ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ያስፈልጋል። ለዚህም በዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ ማግኘት የግድ ይላል። ይህንን ለማግኘት ደግሞ ኖራ የሚመረትባቸውን ፋብሪካዎች በማስፋት አርሶ አደሩ የኖራ ድንጋዩን በቀላሉ ማግኘት እንዲችል ማድረግ አስፈላጊ ነው። የማዕድንና የግብርና ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችም ጉዳዩን በዋናነት በመያዝ ለመሥራት ተግባብተዋል።

አንዳንድ ክልሎችም በዚህ ረገድ የተወሰነ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለዚህም በአብነት ልናነሳ የወደድነው የአማራ ክልልን ተሞክሮ ሲሆን፤ ክልሉ የኖራ ድንጋይ ሀብት በስፋት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። እናም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬት በግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሰራው ዘገባ እንዳመላከተው፤ በክልሉ ባለፈው ዓመት ሶስት ሺህ 390 ሄክታር በአሲድ የተጠቃን መሬት በኖራ ማከም ተችሏል።

ጥቅሙ ይበልጥ እየታየ በመሆኑ በቀጣይ የምርት ዘመን ደግሞ ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ በመጠቀም 12 ሺህ 500 ሄክታር በአሲድ የተጠቃን መሬት ለማከም ታስቧል። ለአርሶ አደሩ ኖራ የማቅረብ ሥራም ተጀምሯል። ኖራ እንደ ሀገር በስፋት ቢኖርም ተደራሽነቱ ግን አሁንም ፈተና ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ ክልሉ ይህንን ከመፍታት አኳያ እየሠራ ስለመሆኑም አመላክቷል። በዚህም አምራች ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው የሚሰሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል። ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከሰባት ሺህ 800 ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ እየተሰራጨ መሆኑ ተነግሯል። ስለሆነም በሌሎች አካባቢዎች ላይም ይህንን ስራ አጠናክሮ መቀጠል ሀገርን መታደግ እንደሆነ ማሰብ እንደሚገባም ተብራርቷል። እኛም ሀብት ካልተለየና በባለሙያ እየተመራ ጥቅም ላይ ካልዋለ ሀብትነቱ ምንም ነውና ጅማሮው ይጠናከር በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን። ሰላም!!

 ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *