የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተሰባስበው የህልውናቸው ዋስትና የሆነውን የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ያፀደቁት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ነበር። ሁሉም የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚወከሉበት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው 3ኛ የምክር ቤት ዘመን ስብሰባ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህገ መንግስቱ በፀደቀበት ቀን እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በዓሉ ለ12 ግዜያት በተለያዩ ክልሎች ተከብሯል፡፡
አዲስ አበባም 13ኛውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦች ቀን ለማክበር በዝግጅት ሽር ጉድ በማለት ላይ ናት፡፡ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ መዲናችን በልዩ ልዩ ትርኢትና በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ጭፈራ ትደምቃለች። በበዓሉ የሃገራችን ህዝቦች የባህል ልውውጥና ትውውቅ ከማድረጋቸው ጎን ለጎንም በጋራ አብሮ የመኖርና የመበልፀግ የጋራ ራዕይ ሰንቀው ይኸንኑ ለማሳካት ቃላቸውን እንደሚያድሱበትም ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስም በዓሉ የአገሪቷን ብሄሮች፥ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባሳተፈ መልኩ በየዓመቱ በየክልሎቹ ዋና መዲና በደማቅ ሁኔታ ቢከበርም አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት አድርገን ስንመለከተው ግን ውጤታማነቱ ላይ ጥያቄ አንድናነሳ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በዓሉ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መልካም መስተጋብር የመፍጠር ዓላማን ሰንቆ መከበር ከጀመረ ከ12 ዓመታት በኋላም እንኳ በሀገሪቱ ብልጭ ድርግም እያሉ የሚታዩት መገፋፋቶችና ግጭቶች በዓሉ የተቀመጠለትን ግብ ከማሳካት አንጻር የሚቀረው ነገር እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለሆነም ቆም ብሎ የበዓሉ አከባበር ሂደት ውጤታማነት ምን ነበር የሚለውን ማጤን የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ይሆናል፡፡
በሃገራችን እየተከሰተ ያለው ብሄር ተኮር ጥቃትና ማፈናቀል፣ በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች የአብሮነትን ገመድ የሚያቀጭጩ፣ ቅራኔን የሚፈጥሩ በመሆናቸው መቆም አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልም እነዚህንና ሌሎች ችግሮች በሚፈታ መልኩ ሊከበር ይገባዋል እንጂ የመርሃ ግብር ማሟያ መሆን የለበትም፡፡
በዓሉ በኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል መቻቻልና መከባበር እንዲጎለብት፣ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፋጠንና አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ምቹ ምህዳር ለመፍጠር የተያዘውን ግብ በሚያሳካ መልኩ መከበር አለበት፡፡
የእስካሁን አከባበሩ ግን በእነዚህ ግቦች ሲለካ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ነበር ማለት አይቻልምና ቅኝቱ መለወጥ አንገብጋቢ ጉዳይ ይሆናል፡፡
አንዳንድ አመራሮችን ጨምሮ የጥፋት ሃይሎች በሚፈጥሩት ግጭት በህዝብ መካከል እርስ በእርስ የመጠራጠር ሁኔታን እየተፈጠረ ነው፡፡ ‹‹በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ብሄር ተኮር ግጭቶች በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል ቅሬታና መጠራጥር ፈጥረዋል።
ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እየተጠቁ ባለበት ሁኔታ ማንነታችሁን ከፍ አድርጋችሁ የምታሳዩበት በዓል ነው ብሎ ለመናገር በራሱ ይከብዳል›› ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የገለጹበት ሁኔታ የእስካሁን የበዓል አከባበር ሂደት የተፈለገው ውጤት ላለማስገኘቱ ማሳያ ነው፡፡ ስለሆነም በዓሉ የሃገራችን ህዝቦች ከዚህ አሉታዊ አስተሳሰብ በሚወጡበትና ጠንካራ መስተጋብር ሊፈጥሩ በሚያስችላቸው መንገድ መከበር አለበት፡፡
በዓሉ ከትርዒትና ባህል ማንጸባረቂያነት በላቀ ለኢትዮጵያ ብሩህ እድል ምቹ ሁኔታ በሚፈጥር መልኩ ህዝቦቿ ተከባብረውና ተፈቃቅደው አንድ ጠንካራ አገር እንዲሁም የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚችሉበትን ሁኔታ በሚያመቻች አግባብ መከበር ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጥርጣሬ ከመተያየት ወጥተው በመቻቻልና መከባበር የሚኖሩበትን ሁኔታ በማጎልበት ረገድ በዓሉ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ማድረግም ይጠበቃል፡፡ በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የታዩ ጉድሎቶችን መለስ ብለን የምንዳስስበትና ግድፈቶችን የምናርምበትም ሊሆን ይገባል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ዓለምን እያስደመመ የሚገኝ ለውጥ ላይ ናት። አገሪቷና ሀዝቦቿ እየሄዱበት ያለው የለውጥ ጎዳናም ተስፋ የተጣለበት ነው። በአገሪቱ ወደ እኩልነት ፣ፍትህና ዴሞክራሲ የሚወስደው ጎዳና እየተጠረገ ነው። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ታይተዋል። የዴሞክራሲ ተቋማት በማጠናከርና የመድብለ ፖለቲካ ስርዓቱ ምቹ ምህዳር በመፍጠር ረገድ የሚታዩ ጅምር ለውጦች እጅግ ተስፋ ሰጪ ናቸው። ስለሆነም ይህ ምቹ ሁኔታ ባለበት በዚህ ጊዜ የሚከበረው 13ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በህዝቦች መካካል የሚፈጠሩ ችግሮች በሚፈታ፣ አብሮነትን በሚያጠናክርና የተጀመረው ለውጥ ስር እንዲሰድ ምቹ ሁኔታ በሚፈጥር መልኩ መከበር አለበት፡፡
በዓሉን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀምም በህዝቦች መካካል መጠራጠር የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በዕርቀ ሰላም ፈትቶ እንዴት አገር የመገንባት ጉዳይ ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በዓሉ የእርስ በእርስ መቀራረባችንንና ለረጅም ዓመታት ጠብቀን የቆየነውን የመቻቻል ባህል በማጎልበት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግላችንን አጠናክረን የምናስቀጥልበትና፤ አገራችንን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ ቃላችንን የምናድስበት መሆን ይኖርበታል!