ከብዛት ወደ ጥራት፤ ከአገልግሎት ወደ አምራችነት እየተሸጋገረ ያለው የክልሉ ኢንቨስትመንት

የአማራ ክልል ለኢንቨስትመንቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በአዲስ አበባ ጭምር የማስተባበሪያ ቢሮ ከፍቶ እየሰራ መሆኑ የክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ከፍቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ፅህፈት ቤቱ በክልሉ ከሚገኘው ዋናው ቢሮ በተጨማሪ ለሥራው ያመቸው ዘንድ እንዲሁም የባለሀብቶችን ፍላጎትና ጥያቄ በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስተናገድ አዳዲስ አሰራሮችን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት አመቺ ሁኔታ በመፍጠር በርካታ ኢንቨስተሮችን መሳብ ተችሏል፡፡

ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ ወደ ክልሉ የሚሄደውን ኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለመደገፍ እና ስለክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በቂ መረጃ ለማደራጀት፣ በክልሉ ባሉ ፀጋዎችና የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ የጠራ፣ ወቅታዊ እና የተጠቃለለ መረጃ ለአልሚዎች መስጠትና መፈጸም ላይ በሰፊው እየሠራ ነው፡፡ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት ስበት ለማሳደግ ጽህፈት ቤቱ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት፣ በተሰሩ ስራዎች ስለተገኙ ውጤቶች፣ ስለዘርፉ መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች እንዲሁም ስለአሁናዊና ቀጣይ ፈተናዎችና መፍትሄዎቻቸው በአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨትመንት ቢሮ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የፅህፈት ቤቱ መከፈት ያስገኘው ጠቀሜታ

‹‹በዚህ ዓመት ብቻ ሦስት ሺ የሚደርሱ ሰዎች ወደ ቢሯችን መጥተው መረጃ ወስደዋል›› የሚሉት አቶ ያየህ፤ ከእነዚህ መካከልም 600 ያህሉ ያቀረቡትን ፕሮጀክት መሰረት በማድረግ ምክክር ተደርጎ ወደ ሥራ መግባታቸውን አመላክተዋል፡፡ እነዚህም ወደ ክልሉ የተለያዩ ዞኖች መሰማራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ 140 ያህሉ ግንባታ አጠናቀው ወደ ምርት የገቡ ሲሆን፤ ክልሉ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለው የውጭ ኢንቨስትመንትና ከፍተኛ አቅም ያላቸው አልሚዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ላይ እንደሆነም አቶ ያየህ አስረድተዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በትክክለኛ እና በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ከ80 በላይ የሚሆኑትም ወደ ኢንቨስትመንት ገብተዋል፡፡ የተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎችም ትልልቅ ፋብሪካዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ብረታ ብረት፣ ሲሚንቶ እና ሌሎች የተለያዩ መስኮች ናቸው፡፡ በ‹‹ጆይንት ቬንቸር›› በርካታ ቻይናውያንና ኢትዮጵውያን ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል አንዱና ትልቁ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር አልሚዎች በጋራ እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ለዚህም በህጎች ላይ ግንዛቤ እየፈጠርን እና እያደራደርን ወደ ሥራ የገቡት ትልቅ ለውጥ እያስመዘገቡ ነው፡፡

ሀገር ውስጥ የካፒታል እጥረት አለ፡፡ ስለዚህ ከውጭ ለኢንቨስትመንት የሚውል መሳሪያ እና ካፒታል ይዞ የሚመጣ ካለ ለእኛ ሀገር ባለሀብቶች አቅም እንዲሆናቸው አብረው እንዲሰሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አቅምና የቴክኖሎጂ ሽግግርም ይሆናቸዋል፡፡ በዚህ ረገድም ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በክልሉ ምዕራብ ቀጣና ባለሀብቶች እርሻ ላይ በሰፊው ገብተዋል፡፡

 ሌላኛው ማዕድን ሲሆን፤ ክልሉን በአሁኑ ወቅት የተስፋ ምድር እያደረገው ያለው የማዕድን ሀብት ነው፡፡ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት በክልሉ ተገኝቷል። በተለይም ግራናይት፣ ማርብል፣ ሲሚንቶ፣ ሴራሚክስ፣ ሲልካ፣ የብርጭቆና መስታወት ፋብሪካ ማዕድናት የተሻለ ፍላጎት ያለበትና በፍጥነትም ወደ ሥራ የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ደግሞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ ውጭ አልሚዎች እየገቡ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን፣ በምግብና መጠጥ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግም ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው፡፡

በተጨባጭ የሚታዩ ፕሮጀክቶች

በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ስር ካሉት በተጨማሪ በክልሉ ብዙ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። በተለያዩ አማራጮችና በራሳቸው አደረጃጀት ወደ ክልሉ የሚሄዱት አልሚዎችም በርካቶች ናቸው፡፡ ለአብነት በዚህ ዓመት ብቻ ወደ ደብረብርሃን ከተማ 730 ፕሮጀክቶች ገብተዋል፡፡ ከደብረብርሃን ከተማ ውጪ ባሉት ሌሎች የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች 600 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን አቶ ያየህ ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ለሚ፣ ጫጫ፣ ቱሉፋ፣ አረርቲ እና ሸዋሮቢት በርካታ ኢንቨስተሮች ተሰማርተዋል። ይህ የሚያሳያው ከፍተኛ ፍሰት የሚታይበት አካባቢ ስለመሆኑ ነው። በክልሉ ያለው አሁናዊ ሠላም በርካቶች ለልማቱ ወደ አማራ ክልል እንዲያቀኑ በማድረጉም ጭምር ነው፡፡ ለዚህም የማስተባበሪያ ጽህፈቱ ቤት ሚና የጎላ ነው፡፡ ክልሉም ትልቅ ትኩረት አድርጎ እየሰራበት ነው፡፡ ቀደም ሲል ይህ የክልሉ ምስራቅ ቀጣና በኢንቨስትመንት ትኩረት አላገኘም ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ትልቅ ትኩረት አግኝቷል፡፡

ኢንቨስተሮች በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ እንዲሄዱ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በአጠቃላይ የበርካቶችን ቀልብ የሚስቡ፣ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ፣ ብሎም ቀጣናዊ ጠቀሜታ ያላቸው፣ በሚቀጥለው ዓመት ማምረት የሚጀምረውን የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን የሆኑበት ወቅት ነው፡፡

የአርሶ አደሩ መለወጥ

በእነዚህ አካባቢዎች ትልቅ ለውጥ እየመጣ ነው። በርካቶች ወደ ዘመናዊ ሕይወት እየገቡ ናቸው። ለምሳሌ በለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ አካባቢ

 በአሁኑ ወቅት ሦስት ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ሌላው ቀርቶ እዚህ አካባቢ የቀን ሠራተኛ እስከ ማጣት ተደርሷል፡፡

አርሶ አደሩ በተቀበለው ካሳ ዘመናዊ ከተሞች እየተገነቡ ነው፡፡ መሰረተ ልማቶችም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እየተሟሉ ናቸው፡፡ ሌሎች ኢንቨስትመንቶችም በዚህ አካባቢ በስፋት እንዲከናወኑ ዕድል ይዞ መጥቷል፡፡

አገልግሎት ላይ መሰማራት የሚፈልጉም በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ አካባቢ ትልልቅ ሎጅዎችንና ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎችን ለመገንባት ፈቃድ እየተጠየቀ ነው፡፡ ዘመናዊ የእርሻ ሥራም በአካባቢው እየተስፋፋ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ መልክዓ ምድሩ አስደሳች በመሆኑም ወደ ቱሪዝም ቢቀየር ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ በአጠቃላይ የተስፋና የኢንዱስትሪ ዞን እየሆነ ነው፡፡ አርሶ አደሩም ጭምር ከቻይናውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች እውቀት እየቀሰመ ነው፡፡

ወደ አምራች ኢንዱስትሪ

በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ ባለሀብቶች በክልሉ በአገልግሎት ላይ ከመሰማራት አለፍ በማለት ወደ አምራችነት እየገቡ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምቹ አጋጣሚ የሚታዩ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለአብነትም የሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መቀየሩ፣ ጥሩ ማበረታቻዎች መኖራቸው፣ ጠንካራ የሰው ኃይል መኖሩ ብሎም በሀገር ውስጥም ከፍተኛ የሆነ የገበያ አቅም መኖሩም በመልካም አጋጠሚ ይጠቀሳሉ፡፡ ለምስራቅ አፍሪካም ሆነ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የኢትዮጵያ በቅርበት መገኘት ስትራቴጂካዊ ትኩረት ይስባል፡፡

ለዘርፉ ምቹ የሆኑ ማዕድናትም በየቦታው እየተገኙ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በርካታ አልሚዎች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰማሩ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበርካታ በረራው የዓለማችን ክፍሎች ተደራሽ መሆንም ሌላው ኢንቨስተሮች የሚፈልጉት ቀዳሚ አገልግሎት ነው፡፡ የኢንቨስትመንቱ ትልቁ ማነቆ የሆነው ካፒታል ሲሆን የውጭ ባለሃብቶች ትልቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የሚያለሙባቸው ጥሩ ዕድሎች ስለመኖራቸውም ጥሩ አመላካች ነው፡፡

የግዙፍ ፕሮጀክቶች አንድምታ

እንደ አቶ ያየህ ገለፃ፤ በአማራ ክልልም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ እንቅልፍ የሚያሳጣው ጉዳይ ሥራ አጥነት ነው፡፡ የግጭት ምንጭ የሚሆነውም በትንሽ ሀብት ላይ መከፋፈልና ሥራ አለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ኢንቨስትመንቶች መምጣት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። የሥራ ዕድል ከተፈጠረ ደግሞ ሠላም ይፈጠራል።በርካታ አካባቢዎች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ሲመጣ ልማቱን እየጠበቀ ያለው ራሱ ነዋሪው ነው፡፡ ይህ የሚያሳያው ሕዝብ ኢንቨስትመንቱን በጣም እንደሚፈልገው ነው፡፡

ኢንቨስትመንት በራሱ ሠላም ነው፤ ሠላምም ይወዳል፤ ህብረተሰቡ ገቢ ያገኛል፤ ከተሞች ይለማሉ። በታክስና ግብር ገቢያቸው ያድጋል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይመጣሉ፡፡ አዳዲስ ሃሳብና የአዳዲስ የከተሞች ምስረታም አብሮ ይመጣል፡፡ በርካታ መሰረተ ልማቶችም በእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ሳቢያ እየተሟሉ ነው፡፡ አረርቲ አካባቢ ያለውን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከዚህ አኳያ መመልከት ይቻላል፡፡

አርሶ አደሩ ያመረተውን በጥሩ ዋጋ ይሸጣል። በሌሎች ከተሞችና የኢንዱስትሪ መዳረሻዎችም ላይ የሚስተዋለው ሁኔታ ተቀራራቢ ነው፡፡ የእነዚህ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች መምጣት ፀረ ኢትዮጵያ በሆኑ አካላት የሚከፈቱ ዓለም አቀፍ ዘመቻዎችን ለማረጋጋት ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ትልቅ አቅም ያላቸው የውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጉ የሚሄዱ ከሆነ ሌሎችን የመሳብ አቅማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አሉታዊ ምልከታዎችንም የመቀየር እድሉ ሰፋ ያለ ነው፡፡

ከብዛት ወደ ጥራት

ቀደም ሲል በብዛት ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው እንዲያለሙ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ማግባባት ላይ ያተኮረ ሥራ ተሰርቶ ነበር፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ግን ‹‹ከብዛት ወደ ጥራት›› የሚል አካሄድ በመከተል ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል። ባለሀብቶችም በብዛት ወደ ክልሉ የገቡበት ወቅት ነው፡፡ ቦታ አጥረው የሚቀመጡ ሳይሆን በፍጥነት ወደ ማልማት የገቡበትና ትልቅ መሻሻል የታየበት ዓመት ነው፡፡ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በሚል መርሐ ግብር ትልቅ ንቅናቄ የተፈጠረበትና የክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ ወደ ማልማት የተገባበት ብሎም ልምድ የተቀመረበት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ መሬት አጥረው የተቀመጡትም በዚህ ንቅናቄ መርሐ ግብር ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ጥሩ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በርካታ ማዕድናት በክልሉ ስለመኖራቸው በሚገባ የታወቀበትና አዳዲስ ግኝትም የታየበት ነው፡፡ ለአብነትም ጂብሰም፣ ሲልካ፣ ግራናይት፣ ማርብልና የመሳሰሉት በክልሉ ምዕራብ ቀጣና እና ዓባይ ሸለቆ በጉልህ የታየበት ዓመት ነው። በክልሉ አቅም ያላቸው ባለሀብቶችም በስፋት በግብርና ኢንቨስትመንት የገቡበትና የኢንዱስትሪ ግብዓት በብዛት የተመረተበት አመት ነው፡፡ በተለይም አኩሪ አተር በብዛት ተመርቷል። ትልልቅ ፋብሪካዎችም በዚህ በጀት አመት ሥራ ጀምረዋል። በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችም ጥገና ተደርጎላቸው በአብዛኛው ማምረት የጀመሩበት ሲሆን፤ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተገኙበት አመት ነው፡፡

ፈተናዎች

ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አልሚዎችን የሚያንገላቱ አካላት እየታዩ ነው፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ የኢንቨስተሮችን ንብረት መፈተሽ እና ተሽከርካሪዎችን ማስቆም ብሎም እንግልት መፍጠር ተለምዷል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ይህን ተከትሎም ወደ ውጭ ገበያ መላክ ያለባቸው ምርቶች መንገድ ላይ እየተበላሹ ነው፡፡ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ወደ ክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኢንቨስተሮችን እየፈተነ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ የተመለከቱ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትም እያማተሩ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን የሚዳኝ ሥርዓት እንደ መንግሥት መኖር አለበት፡፡ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆነው ኢንቨስተሮች በክልሉ ላይ በዚህ ደረጃ መንቀሳቀሳቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም እንግልት ሊደርስባቸው አይገባም፡፡ ይህ ክስተት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችንም ሰለባ እያደረገ ነው። ስለዚህ የሰላም አለመኖር በእጅጉ ፈታኝ እየሆነ ነው፡፡ እየተፈጠረ ያለው ችግር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ለመፍትሄ ግን በዚህ መጠን አልሰራንም፡፡

የውጭ ምንዛሪ እና የካፒታል እጥረትም ሌላኛው ፈታኝ ጉዳይ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትም እንዲሁ የኢንቨስትመንቱ ማነቆ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ የመሰረተ ልማት አለመሟላት እንዲሁም የተቀላጠፈ አገልግሎት አለመስጠትም ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ ነው ብለዋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *