የማህበራዊ ትስስር ገጾች ከዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን (ሜይንስትሪም ሚዲያዎች) ጋር ቦታ እየተቀያየሩ ነው። ማህበራዊ ገጾች ሊሰሩት የሚገባውን እንቶ ፈንቶና ዋዛ ፈዛዛ የሆኑ ነገሮችን ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ላይ፤ በተቃራኒው ደግሞ ጠንካራ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ይተነተናሉ።
ይሄ ነገር እየተለመደ ይመስላል። ለዚህም ነው አሁን አሁን ማህበራዊ ገጾች ላይ የሚደረግ ነገር እንደ ቁም ነገር ተቆጥሮ ትችትና ወቀሳ እየተደረገበት ያለው። ማህበራዊ ገጾች ላይ ቀልድና ዋዛ ፈዛዛ የሆነ ነገር ሲጻፍ ብዙ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ‹‹ለምን ቁም ነገር አትጽፍም?›› የሚል ነው። አዎ! ቁም ነገር ቢጻፍ የበለጠ ጥሩ ነበር፤ ዳሩ ግን እንቶ ፈንቶ ነገሮች ደግሞ ከማህበራዊ ገጾች ሊጠፉ አይችሉም።
ማህበራዊ መገናኛ (ሶሻል ሚዲያ) ማለት ልክ እንደ ማህበራዊ ሕይወታችን ማለት ነው። ‹‹ማህበራዊ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውም ለዚህ ነው። በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ደግሞ ብዙ ነገሮች አሉ። ማህበራዊ ሚዲያ ልክ እንደ ማህበራዊ ሕይወታችን ነው ካልን፤ በማህበራዊ ሕይወታችን የሚደረጉ ነገሮች ይደረጉበታል ማለት ነው፤ በማህበራዊ ሕይወታችን ብዙ ነገሮችን የምናደርገው ትዝ እንዳሉን ነው።
በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ከጓደኛችን ጋር፣ ከሥራ ባልደረባ ጋር፣ ከጎረቤትና ከቤተሰብ ጋር ሁልጊዜ ጠንካራ ጉዳዮችን አናወራም። ካፌ ውስጥ ወይም መዝናኛ ቦታ ወይም ቤት ውስጥ ሰብሰብ ስንል ቀልድና ጨዋታዎች ናቸው የሚበዙት፤ ማህበራዊ ሚዲያ ልክ እንደዚያ ማለት ነው። ተራ ገጠመኞች ሲያጋጥመን አጠገባችን ላለ ጓደኛ
እንናገራለን፤ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንታችንም ልክ እንደዚያ ማለት ነው፤ ተራ ገጠመኞችን ሁሉ ልናጋራበት እንችላለን። ይሄ ማለት ግን ለሰዎች ምንም ስሜት የማይሰጥ ወይም ከባህልና ወጋችን ውጪ የሆነ ነገር ሁሉ ይደረግበት ማለት አይደለም፤ እንደዚያ ከሆነ የራሳችንን ክብር ነው የሚያወርደው።
ማህበራዊ ሚዲያ የማህበራዊ ሕይወታችን ነፀብራቅ ነው። ይሄ ማለት ሀሜትና አሉባልታም ይኖርበታል ማለት ነው። ዲያቆን ዳንኤል ክብረት (አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የፓርላማ አባል) በአንድ ወቅት በአርትስ ቴሌቪዥን የደረጀ ኃይሌ ‹‹በነገራችን ላይ›› ፕሮግራም ላይ የተናገረውን ደጋግሜ አስታውሰዋለሁ። ደጋግሜ ያስታውስኩበት ምክንያት የልቤን ስለተናገረልኝ ነበር።
የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሃሳብ ሲጠቃለል፤ ማህበራዊ ሚዲያ አዲስ ነገር ይዞብን አልመጣም፤ በማህበረሰባችን ውስጥ የነበረውን ነገር ተደራሽ እንዲሆን ነው ያደረገው፤ ሜዳውን ነው የፈጠረ። ከማህበራዊ የትስስር ገጾች መፈጠር በፊት በጎረቤት፣ በአካባቢ፣ በገበያ፣ በአጠቃላይ በስሚ ስሚ ይዛመት የነበረን ነገር አሁን በአንድ ጊዜ እንዲጥለቀለቅ አደረገ። ቡና ላይ ይወራ የነበረ ሀሜት አሁን በብዙ ሺህ ሰዎች ዘንድ በአንድ ጊዜ እንዲታይና እንዲሰማ ሆነ። ይህ ሲሆን ግን መተግበሪያው ባህሪዎቻችንን ጭምር ይዞብን የመጣ መሰለን። እንደ ማህበረሰብ ስንለወጥ ነው የማህበራዊ ገጾቻችን ገጽታም የሚለወጠው። ምክንያቱም ገጾች ላይ የሚጽፉትም ሆነ የሚያወሩት በየመንገዱና በየመንደሩ ነውር ነገር ሲያደርጉ የምናያቸው ሰዎች ናቸው።
በቀልድና ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች በኩል ግን በኢትዮጵያ ብቻ ያለ አይደለም። በሌሎች የዓለም ሀገራትም ማህበራዊ ሚዲያ ቀለል ላሉ ነገሮች ነው የሚያገለግለው፤ እንዲያውም ጠንካራ ሃሳቦችን በማሰራጨት በኢትዮጵያ ያለው ድርሻ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም።
እስኪ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የማህበራዊ ገጾቻቸውን ተመልከቱ። የሚሰጣቸው ግብረመልስና ከሀገራችን መገናኛ ብዙኃን በታች የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ይሄ ማለት በሀገራችን ማህበራዊ ገጾች ንቁ ተሳታፊ አላቸው ማለት ነው።
ማህበራዊ ገጾች ለምን የጠንካራ ሃሳቦች ማንሸራሸሪያ ሆኑ ቢባል ምናልባትም የዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ጠንካራ አለመሆን ነው። ፖለቲካዊ ጉዳዮች በስፋትና በድፍረት ስለማይተነተኑ፣ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ክስተቶች በፍጥነት ሽፋን ስለማያገኙ ሰዎች ወደ ማህበራዊ ገጾች አዘወተሩ ማለት ነው። ይህ ነገር ልማድ እየሆነ መጣ፤ አሁን ላይ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ራሱ ‹‹ሰበር ዜና›› የሚያስተዋውቁት በማህበራዊ ገጻቸው ሆነ። ማታ ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ ስንከፍት ምንም አዲስ ነገር አናገኝም። በማህበራዊ ገጾቻቸው ስናየው የቆየነውን ዜና ነው ማታ ሲያነቡት የምንሰማው። በማህበራዊ ገጾቻቸው የሚለቁት ደግሞ ላለመቀደም ሲሉ ነው። ይህ ዘመኑም የሚያስገድደው ሁኔታ ነው።
በሌላ በኩል ማህበራዊ ገጾች ልቅ የሆነ ነፃነት ስላላቸው ሰዎች ያዘወትሯቸዋል። ዋናዎቹ የኤዲቶሪያል ህግ አላቸው፣ ያልሆነ ነገር ቢናገሩ ተጠያቂነት አለባቸው፤ ትልቅ ኃላፊነት አላቸው። ማህበራዊ ገጾች ግን ባለቤታቸው ማን እንደሆነ ራሱ አይታወቅም፤ ተጠያቂነታቸው ጠባብ ነው። የሚለቀቀው መረጃ በኤዲቶሪያል ውሳኔ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ ፍላጎት ሊሆን ይችላል። ችግሩ ግን ማህበረሰባችን ደግሞ ይህን አያገናዝብም። የተባለ ነገር ሁሉ እውነት የሚመስለው ብዙ ነው።
ከምንም በላይ ግን ማህበራዊ ገጾችና ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ቦታ እየተቀያየሩ መሆኑ መጥፎ ልማድ ነው። የውሃ መራጨትና ከዶሮ ጋር መሯሯጥ የመሳሰሉ የሕጻናት ጨዋታ የሚመስሉ ፕሮግራሞችን በቴሌቪዥን መስኮት እያየን፣ ቀጣናዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትንታኔዎችን ከፌስቡክና ዩትዩብ መከታተል የተገላቢጦሽ ነው።
በእርግጥ ዲጂታል ሚዲያው በዓለም አቀፍ ደረጃም አይነቱና ተጠቃሚው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ነው። ‹‹ስማርት ኢንሳይት›› የተባለው ድረ ገጽ የ2023 የማህበራዊ ገጾችን መረጃ አውጥቷል። በዚህ መረጃ 60 በመቶ (4 ነጥብ 80 ቢሊዮን ሕዝብ ማለት ነው) የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ ማህበራዊ ገጾችን ይጠቀማል። በቀን ያለው አጠቃቀም በአማካይ 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ነው። በፊሊፒንስ ተሰራ በተባለ ጥናት ግን አንድ ሰው በቀን 4 ሰዓት ይጠቀማል። ከማህበራዊ ገጽ ፕላትፎርሞች ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው ፌስቡክ ነው (ይህ እንኳን በግምትም ቢሆን ያስታውቃል)። ቀጥሎ ግን ዩትዩብ ነው።
በሀገራችን ያለው አጠቃቀምም ዓለም አቀፉን ሁኔታ የተከተለ ይመስላል። በዋናነት አገልግሎት ላይ የሚውሉት እነዚህ ሁለቱ ናቸው። ልዩነቱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ለጠንካራ ጉዳዮችና ለሀሰተኛ መረጃዎች እየዋለ ነው። ይህን ልማድ ማስቀረት አለብን። ይህን ልማድ ለማስቀረት ደግሞ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን መብለጥ አለባቸው። መብለጥ ሲባል ማህበራዊ ገጾች ላይ ያለውን ግሳንግስ ሁሉ ይዞ መሄድ ሳይሆን ጠንካራ ጉዳዮችን መተንተን ማለት ነው። ምክንያቱም የተሻለ ታማኝነት ያላቸው ዋናዎቹ ናቸው። በማህበራበዊ ገጾች የሆነ ዜና ሲሰራጭ ለማረጋገጥ ወደ ዋናዎቹ ነው የምንሄደው።
በአጠቃላይ የማህበራዊ ገጾችና ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ቦታቸውን አይቀያይሩ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 /2015