የትምህርት ደረጃ ሲጨምር ግንዛቤም ይጨምር!

በአንድ ወቅት የተከራየሁበት ግቢ ውስጥ ባልና ሚስት ተጣሉ:: ሲነጋገሩ የነበረው በጣም ተራ በሚባሉ ሀሳቦችና ቃላት ነበር:: እንኳን ሕይወትን ያህል ነገር የተጋራ ባለትዳር ይቅርና መንገድ ላይ በመተላለፍ የተጋጨ እንኳን በእንደዚያ ዓይነት ተራ ነገሮች ላይ አይጣላም:: እንደምንም ገላግለን ጉዳዩ አለቀ!

ከቀናት በኋላ ነው አንድ በአሽከርካሪነት ሥራ ላይ የተሰማራ ሌላኛው ጎረቤት ሲናገር ነገሩን በደንብ ያጤንኩት:: ለካ ባልየው የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ እንዳለው ቤታቸው ውስጥ ከተሰቀለው ፎቶ አይቶ ነበር:: እሱን እያነሳ ‹‹እንዴት የተማረ ሰው እንደዚህ ይናገራል?›› እያለ ሲጠይቀን ቆይቶ፤ በትዝብት ‹‹እኔ መሃይሙ እሻላለሁ!›› አለ::

የፎቶውን ነገር ካነሳሁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ አንድ መምህራችን የጠየቀን ጥያቄ ትዝ አለኝ:: ወቅቱ የመመረቂያ ጊዜ የደረሰበት ነበር:: ነገርን ነገር ሲያነሳው የምርቃት ነገር ተነሳ:: ‹‹ለምንድነው ሰዎች ሲመረቁ በትልቁ አሠርተው ፎቷቸውን ግድግዳ ላይ የሚያደርጉት?›› አለን:: ሁላችንም የመሰለንን ተናገርን:: የሰጠን መልስ ግን ያልጠበቅነውና ያሳቀን ነበር:: በወቅቱ ተራ መልስ ቢመስለኝም እየቆየሁ ሳስበው ግን ልክ ነበር::

‹‹የዋዛ አይደለሁም! ለማለት ነው›› ነበር ያለን መምህሩ:: በብዙ መንገድ ሊተረጎም ቢችልም፤ በዋናነት ግን የተማርኩ ነኝ ለማለት ነው:: እዚህ ድረስ የተማርኩ ነኝ፣ የምናገረውና የማደርገው ነገር ሁሉ የተራ ሰው ድርጊትና ንግግር ሳይሆን የተማረ ሰው ነው ለማለት ነው:: በአጠቃላይ የተማረ ሰው ክብደትና ግርማ ሞገስ ለማግኘት ነው

 ባለፈው ሐሙስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲህ ብለው ነበር:: ‹‹የተማረ ሰው የሀገሩን ችግር እንዴት እንደሚፈታ ይመራመራል እንጂ ራሱ የችግር ምንጭ አይሆንም›› ብለዋል:: ዋናው ነጥብ ይሄው ነው! ችግር ፈቺ ምርምር ማድረግ ቢቀር ቢያንስ ችግር ባይሆኑ!

በዚሁ ዓምድ እንኳን በተደጋጋሚ ብዙ ትዝብት አጋርተናል:: አንዳንድ መገልገያ ቦታዎች ላይ የሚታዩ ነገሮች ‹‹መማር እንዲህ ነው ወይ?›› ያስብላሉ:: የተማረ ሰው ሊፈታው የሚችለውን ችግር የተማረ ሰው አበላሽቶት እናያለን:: ስለትልልቅ ጉዳዮች አይደለም እያወራሁ ያለሁት፤ በጣም ትንንሽ ነገሮችን ነው! የአንደኛ ክፍል ተማሪ የማያደርገውን የማቆሸሽና የማበላሸት ድርጊት የተማረ ሰው አድርጎት ሲታይ ምን ይባላል?

አሁን አሁን በብዙ ተቋማት ውስጥ ዝቅተኛው የትምህርት ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ እየሆነ ነው:: ሁለተኛና ሦስተኛ የትምህርት ደረጃዎችን በደራረቡ አንዳንድ ሰዎች ላይ የሚታየው የተግባቦት (ኮሙኒኬሽን) ችግር ግን ፊደል ያልቆጠረ ሰው እንኳን የማያደርገው ነው:: ቁጣ፣ ማመናጨቅ፣ መሳደብ፣ ማደነባበር፣ ሥርዓት አልባ ድርጊቶች… መደበኛ እየሆኑ ነው:: ታዲያ የመማሩ ለውጥ የት ጋ ይሆን?

አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ጓደኛዬ ሁለተኛ ዲግሪውን ሲማር መምህራቸው የጠየቃቸውን ጥያቄ ከዓመታት በፊት ነግሮኝ ነበር:: ገና ትምህርቱን የጀመሩ ሰሞን ነው:: አንደኛው መምህር ‹‹እስኪ ሳትዋሹ ለእውቀት ብዬ ነው የምማር የምትሉ?›› ብሎ ጠየቃቸው:: አብዛኞቹ ለህሊናቸው ተገዢ ሆነው ፀጥ አሉ (አስመስለው እጃቸውን አላወጡም):: አንድ ተማሪ ብቻ ከልቡ ይሁን ለማስመሰል ባይታወቅም እጁን

 አወጣ፤ ከዚያ በኋላ በጥያቄ አጣደፉት:: ይሄ ማለት አብዛኞቹ የምርምር የደረጃ ዕድገት ለማግኘትና ግዴታ ስለሆነ ነበር የሚማሩ ማለት ነው::

አሁን አሁን ትምህርት እንደዚያ እየሆነ ነው:: የደረጃ ዕድገት ለማግኘት፣ በሌሎች ሥራዎች ለመወዳደር፣ ይሄኛው ዘርፍ ነው የተሻለ ደሞዝ ያለው ከተባለ ያንን የተሻለ ደሞዝ ያለውን ሥራ ለማግኘት… በአጠቃላይ ለግለሰቡ የተሻለ ጥቅም ሊያስገኝ ስለሚችል እንጂ ሀገርና ማህበረሰብን የሚለውጥ የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት እየሆነ አይደለም:: በአመለካከትና ድርጊታቸው ምንም ትምህርት ቤት ካልገባ ሰው ጋር የማይለዩ የትምህርት ደረጃ የደራረቡ ሰዎች ብዙ ናቸው::

ሌላው ግራ የገባው ነገር ደግሞ የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍና የሚማሩት ትምህርት ግንኙነት ነው:: የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት አንድ ሰው የመጀመሪያ ዲግሪውን ከተማረበት ጋር ተቀራራቢ መሆን ነበረበት:: ለምሳሌ፤ አንድ በግብርና ሙያ የተማረ ሰው ሥራው የግብርና ባለሙያ ከሆነ መማር ያለበት ይህን ሙያ ለማዳበርና በዚህ ሙያ የካበተ የትምህርትና የደረጃ ዕድገት እንዲኖረው ነው:: ዳሩ ግን ሁለተኛ ዲግሪ መሆኑ እንጂ ትኩረት የሚሰጠው የትምህርቱ ቀረቤታ አይደለም::

ከምንም በላይ ግን አስቸጋሪው ነገር በተማረና ባልተማረ መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ መሆኑ ነው፤ ይባስ ብሎ ምንም ልዩነት የሌለ እስከሚመስል ድረስ ለውጥ አለመምጣቱ ነው:: የትምህርት ደረጃ ማደግ ተጨማሪ ክህሎት ለማዳበር፣ አዳዲስ ግኝቶችን ለማግኘት፣ የተሻለ ሀሳብና መፍትሔ ለማምጣት መሆን ነበረበት:: ዳሩ ግን ተደራራቢ የትምህርት ደረጃ ይዞ ‹‹ሽንት ቤት ላይ ውሃ ድፋ›› ተብሎ የሚነገረው ነው ያለ:: እጁን የታጠበበትን የውሃ ቧንቧ የማይዘጋ የተማረ ዜጋ  አለ::

ይህንን ስል ‹‹ሁሉንም መጨፍለቅ ልክ አይደለም›› የሚል ይኖራል:: አዎ! ሁሉም አይደለም፤ ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነት ከሥልጣኔ የራቅን በመሆናችን አለመገረም ደግሞ ድርጊቱን ከማድረግ አይተናነስም:: ሊስተካከል የሚችለው መጀመሪያ በድርጊቱ ነውርነት ስንገረምና የሚያደርጉትን ሰዎች ደፍረን ስንናገር ነው::

እስካሁን ከጠቀስናቸው ችግሮች ከተማረ ሰው የሚጠበቀው በጣም ትንሹን ነው:: ከፍ እናድርገው ከተባለ፤ ይህ ሀገራችን ውስጥ የምናየው ውጥንቅጥ ችግር እንደተማረ ሰው የሀሳብ ዜጎች ባለመሆናችን ነው:: ከተራ የግለሰቦች ግጭት እስከ ሀገራዊ ጦርነቶች የችግሮች መነሻ ለሀሳብ ቅድሚያ አለመስጠት ነው::

በትንሹ ታክሲ ውስጥ እና መገልገያ ቦታዎች እንኳን ማየት እንችላለን:: ለትንሽ ስህተት መሰዳደብና ዱላ መማዘዝ ልማዳችን ነው:: ተጠይቃዊ ምክንያቶችን ከማቅረብና ከመቀበል ይልቅ አካላዊና አካባቢያዊ ምንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ በስፋት ይስተዋላል:: ይህን ነውር ድርጊት የተማሩ ሰዎች ሲያደርጉት ትምህርትን ዋጋ ቢስ ያደርገዋል::

መማር ማለት የአሃዝ መረጃዎችን ማወቅ ብቻ አይደለም:: አስተውሎትና ግንዛቤ ነው:: አንድ ሰው የተማረ መምሰል ከፈለገ ወይም የተማረ ሰው ከሆነ አነጋገሩና ድርጊቱ ነው አዋቂነቱን የሚገልጸው:: ነገሮችን የሚያይበት መንገድና ሰዎችን የሚረዳበት መንገድ ነው አዋቂነቱን የሚያሳየው:: ከትንንሾቹም መማር የሚችል ሲሆን ነው::

በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የትምህርት ሥርጭት እየሰፋ ነው:: ተመርቀው ሥራ የያዙትም የትምህርት ደረጃዎቸውን ከፍ እያደረጉ ነው:: በዚሁ ልክ ግን የተማረና የሠለጠነ ዜጋ ባህሪ ይቀረናልና እሱም ይታሰብበት!

 ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *