የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለልማት ፖሊሲ ፋይናንስ ማስፈፀሚያ በኢትዮጵያ መንግስትና በአለምአቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፀደቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በአንድ ተቃውሞና አንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቀው የብድር ስምምነት 340 ሚሊዮን 100 ሺህ ኤስ.ዲ.አር ነው።
“ኤስ.ዲ.አር” ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የገንዘብ መጠንን ከአሜሪካው ዶላር፣ ዩሮ፣ ከጃፓኑ የን፣ ከቻይናው ይዋንና ከእንግሊዙ ፓውንድ ስተርሊንግ አንፃር የሚለካበት መጠሪያ ነው።
ብድሩ ከወለድ ነፃ ከመሆኑም በላይ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑም ተብራርቷል።
ብድሩ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ የፖሊሲ እርምጃዎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ አንዲቻል በቀጥታ ወደመንግስት ካዝና ገብቶ የፌዴራል በጀትን ለማጠናከር የሚውል ጭምር ነው።
ለግል ዘርፍ ተሳትፎ አመቺ ሁኔታ በመፍጠር የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ የሚሰሩ የለውጥ ተግባራትን ለመደገፍም ብድሩ እንደሚያግዝ በምክር ቤቱ የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጎ አብራርተዋል።
ብድሩ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ ምርታማነት ለማሳደግ፣ ቅልጥፍና እና ተወዳዳሪነትን ከፍ ለማድረግ ፤በግልፅነትና ተጠያቂነትን እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝም ገልፀዋል።
ምክርቤቱ ከብድር ስምምነት አዋጁ በተጨማሪ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
ከእነዚህም መካከል አንዱ የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል።
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ከእስራኤል፣ ከፈረንሳይና ከሞሮኮ መንግስታት ጋር ያደረገቻቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ለማፅደቅ የቀረቡ ሶስት ረቂቅ አዋጆች ላይም ተነጋግሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በኢትዮጵያ መንግስትና በሞሮኮ ንጉሳዊ መንግስት መካከል የተደረገውን በኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ጥበቃ ዘርፍ የትብብር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን የግብርና ዘርፍ ትብብር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ምክርቤቱ በዛሬ ውሎው የ4ኛ አመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለጉባኤም መርምሮ አፅድቋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት ዳኛ የነበሩት አቶ ተከስተ ሙሉጌታ ስራ ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸውን የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ለምክርቤቱ በዛሬው እለት ማሳወቁም ተገልጿል።