እኛ ሰዎች ከአቅማችን በላይ የሆኑ ነገሮችንና ሁኔታዎችን መቀየር አንችልም። መቀየር የምንችለው ራሳችንን ብቻ ነው። የናቋችሁና ፊት የነሷችሁ ወዳጆች እናንተ ካልተለወጣችሁ በስተቀር አያከብሯችሁም። ‹‹ኑሮ መቼ ነው የሚረክሰው?›› አትበሉ። ኑሮ መቼም አይረክስም። ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ኑሮ እየናረ እንጂ እየቀነሰ ሲመጣ አልታየም። ስለዚህ ‹‹እንዴት ገቢያችንን እናሳድግ?›› በሉ። ‹‹እንዴት ራሳችንን እንለውጥ?›› በሉ።
አንተም ብትሆን ‹‹የአሰሪዬ፣ የአለቃዬ፣ የፍቅረኛዬ፣ የጓደኛዬ ፀባይ መቼ ነው የሚቀየረው?›› አትበል። የሰዎች ፀባይ ካለፍላጎታቸው አይቀየርም። አንተ ስለፈለክ ብቻ እነርሱን አትቀይራቸውም። ራስህን መቀየር ግን ትችላለህ። እነርሱ እስኪቀየሩ የምትጠብቅ ከሆነ ግን ታረጃለህ። ስለዚህ አንተ ራስህ መለወጥ አለብህ። ቁርጥህን እወቅ በሁኔታዎች ታማርር ይሆናል። ‹‹ይህችን ሀገር እንዴት ልቀይራት?›› ልትል ትችላለህ።
የዚህች ሀገር ፖለቲካ እጅህ ላይ አይደለም። እጅህ ላይ ያለው የራስህ ህይወት ነው። ራስህን መቀየር አለብህ። ተደጋጋሚውንና አሰልቺውን ኑሮ በቃኝ ማለት አለብህ። እስከመቼ ታማርራለህ። በሰዎች ላይ ጥገኛ መሆኑን ይብቃኝ ማለት አለብህ። እስከመቼ የእነርሱን እርዳታና ገቢ ብሎም ሃሳብ ጠባቂ ሆነህ ትቀራለህ። ገንዘብ ያለምክንያት ማጥፋቱን ግዜህን ማባከኑን በቃኝ ማለት አለብህ። እስከመቼ ብኩን ትሆናለህ?
በፍርሃትህ ምክንያት ቆሞ መቅረቱን በቃኝ ማለት አለብህ። አስከመቼ በሰዎች ለውጥ ትቀናለህ? ለውጥ ለመጀመር ወሳኙ ሰዓት የባነንክበትና የነቃህበት ሰዓት ነው። እሱም አሁን ነው። መለወጥ አለብህ ወዳጄ!
አንዳንድ ሰው ህይወቱን ለመቀየር ከሰው ይጠብቃል። ከሰው መጠበቅ ግን ልብን ይሰብራል። እድል እስኪመጣ ቁጭ ማለት ብኩን ያደርጋል። ስለዚህ በሰዎች ጥገኛ የምትሆንበት ዘመን ማብቃት ይኖርበታል። ነገን የምትፈራበት፣ መለወጥን ስታስብ የምትሳቀቅበት ዘመን ማብቃት አለበት። ስራህ ላይ፣ የፍቅር ግንኙነትህ ላይ፣ ትምህርትህ ላይ በሰዎች ተደግፈሃል? ‹‹አንድ ቀን እነሱ ቢሄዱስ የሆነ ነገር ቢፈጠርስ ብለህ ትረበሻለህ?›› ለማንኛውም ብቻህን መጠንከር አለብህ።
ሰዎች ካንተ ጋር የሚሆኑት በጣም ምስኪን ስለሆንክ ወይም ስለምታሳዝናቸው መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ አንተነትህን ብለው፣ ማንነትህን አክብረውና ጥንካሬህ ማርኳቸው መሆን አለበት። እንደዚህ የሚሆነው ደግሞ ከተለወጥክ ብቻ ነው። ብቻዬንም ቢሆን ከፈጣሪ ጋር የማላልፈው የለም፤ ምን እሆናለው፤ አሁኑኑ መለወጥ እጀምራለሁ ካልክና ወደለውጡ ከገባህ ሰዎች ይከቡሃል። ካንተ ጋር መስራት፣ ካንተ ጋር መሆን የማይፈልግ የለም። የተለወጠን ሰው ደግሞ ሁሉም ይወደዋል፤ ሁሉም ይፈልገዋል።
ህይወት ሲከብድህ ሞትን አትመኝ። ሞትን አንተ ብትመኘውም ባትመኘውም መምጣቱ አይቀርም። ነገር ግን በህይወትህ ባትመኛቸው የማይመጡ ነገሮች አሉ። ለውጥን አንተ ካልፈለከውና ካልተመኘኸው አይመጣም። አትለወጥም። ቁጭ ባልክበት ለውጥ አይመጣም። አንተ ራስህ ተነስተህ ለውጡን መፈለግ አለብህ። ህይወቴንና ስራዬን እንዴት ልቀይር ማለት አለብህ። ህይወት የሚቀየረው ደግሞ በፍላጎት ነው። ለውጥ አንተ ካልፈለከው በስተቀር አይመጣም።
በሰው ቀልድ ከምትስቅ አሰልቺ ቢሆንም የሰዎችን ስኬት ታሪክ አድምጥ። አንተ እንድትለወጥ የሚያደርጉህን ቪዲየዎችን ተመልከት። አዲስ ነገር ሞክር። ተንቀሳቀስ። ወራጅ ውሃ ንፁህ የሚሆነው ከመነሻው ጀምሮ ምንጩ የጠራ ከሆነ ነው። ምንጩ ከደፈረሰ ወራጁም አብሮ ይደፈርሳል። ያንተ የመቀየር ምንጭ የቀን ውሎህ ነው። ህይወትህ እንዲቀየር የቀን ተግባርህ አብሮ መቀየር አለበት። ስፖርት መስራት ጀምር። በግዜ ተኛ። በጥዋት ተነሳ። አምሽቶ ቲቪ ላይ መጣድና ፊልም ማየቱን ተው። ይህን ማድረግህ የሚጠቅምህ ቢሆን ኖሮ አሁን ራስህን ትልቅ ቦታ ላይ ታገኘው ነበር።
ቆራጥ መሆን ስትጀምር፣ ወደራስህ ስታተኩር ምድራዊ ጥያቄህ ሁሉ መመለስ ይጀምራል። እጣፈንታህ በሰዎች እጅ መሆኑ ያቆማል። ህይወትህን የሚቀይረው ከሰዎች የምታገኘው እርዳታ ወይም ትብብር አይደለም። ወይም ሁኔታዎች የሚያመጡት እድል አይደለም። ህይወትህን የሚቀይረው ቆራጥ በመሆንህ ፈጣሪህ በሚያዘጋጅልህ ስጦታ ነው። ለዛም ነው መጠንከርና መለወጥ ስትጀምር ሰዎች የሚያከብሩህ። ለዛ ነው ስራው፣ እድሉ፣ ገንዘቡና የፍቅር ግንኙነቱ ሁሉ የሚስተካከለው።
ወዳጄ! መጠንከር እንደጀመርክ አውቃለሁ። ግን ወደኋላ ማየት የለም። የሚለወጥ ሰው አያፈገፍግም። ውስጥህ የሚናገር አንበሳ የሆነ ድምፅ አለ። አዎ! ምንም ነገር እንደማያቅትህ፣ እንደምትችልና ጀግና እንደሆንክ አጥብቆ የሚነግር በውስጥ የአንበሳ ድምፅ አለ። ይህን ድምፅ በደምብ አድምጠው፤ እመነው። ዛሬ ሰው ጫን አድርጎ የሚነግርህን ድክመት አምነሃል እኮ! ከዚህ በኋላ ግን ጆሮህ የሚከፈተው ለሚለውጥህ ወይ ለሚያሳድግህ ነገር ነው እንጂ ወደኋላ ለሚጎትትህ አይደለም። ስራህ ላይ ጠንክረህ ስትሰራ ደሞዝ ታገኛለህ። ገቢህ ያድጋል። በተጨማሪ ራስህ ላይ የምትሰራ ከሆነ ደግሞ ሀብት ትገነባለህ።
ለሰዎች ብለህ ማስመሰሉ እኮ ነው ደስታህን የነሳህ። ማህተመ ጋንዲ ‹‹ ደስታ ማለት የምታስበው፣ ከምትናገረውና ከምታደርገው ጋር አንድ ላይ ሲዋሃድ ነው›› ይለናል። ብቻህን ደስተኛ ያልሆንክ ይመስልሃል እንጂ በሰዎች ብትከበብም ሙሉ ደስታ አይኖርህም። ሁልግዜም ውስጥህ የሚነግርህን፤ ህሊናህ የሚያዝህን አድርግ። መለወጥህን ሰዎች ላይወዱት ይችላሉ። ላይቀበሉት ይችላሉ። የምትለወጠው ግን እነርሱን ለማስደሰት አይደለም። ካልተለወጥክ ህይወት ባዶ ስለሚሆን ነው።
አንዳንዴ መለወጥ ስትፈልግ ራስህን እንደሌላ ሰው እየው እስኪ? ለምሳሌ ቀራፂ ሃውልቱ ፊት ለፊት ይቆምና ‹‹ምን ላስተካክል? ምን ልጨምር? ምን ልቀንስ?›› ብሎ ያስባል። የሚቀየር ነገር ካለ ምንም አይሳሳም ይቀይራል። ‹‹እንደው ያመው ይሆን? ይሰማው ይሆን?›› አይልም። መጨመር ያለበትን ይጨምራል መቀነስ ያለበትን ደግሞ ይቀንሳል። ለምን? ሃውልቱ ማማር አለበት።
አንተም እንድትቀየርና ህይወትህ እንዲያምር ከፈለክ መጀመሪያ ራስህን ለብቻህ አስቀምጥና ተመልከተው። ለሰው መምከሩንማ እንችልበታለን። ሰው ምን ቢያደርግ እንደሚለወጥ እናውቅበታለን። ለራሳችን ነው የማናውቀው። አሁን ግን ራሳችንን እንደ ሌላ ሰው ቆጥረን እንምከረው እስኪ። አየህ! ያ ሃውልት ሲታደስ፣ ሲኮሮኮም ህመም አለው። አንተም ስትቀየር ደስ የሚል ሰላማዊ ስሜት አይሰማህም። ህመም አለው። በህመም ውስጥ የሚመጣ ለውጥ ግን ጣፋጭ ነው።
አለመለወጥ በራሱ ህመም አለው። ባለመለወጥህ ዋጋ ትከፍላለህ። ቆሞ መቅረትን የሚያክል ምን መስዋዕትነት መክፈል አለ? መለወጥ መስዋዕትነት አለው ፍሬው ግን ጣፋጭ ነው። ስለዚህ ለመለወጥ ስትነሳ ባለበት እንዳይቀጥል የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው? ስራህ ነው?፣ ገቢህ ነው?፣ ሰውነትህ ነው?፣ የፍቅር ግንኙነትህ ነው?፣ ከፈጣሪህ ጋር ያለህ ግንኙነት ነው? ይህን ለይተህ እወቅ። ወረቀት ላይ ፃፈው። የወር ገቢዬ ይህን ያህል እንዲሆን እፈልጋለሁ፣ የሰውነቴ ክብደት ይህን ያህል እንዲሆን እፈልጋለሁ……ወዘተ እያልክ ፃፍ። ስፅፈው አይምሮህ አቅጣጫ ይይዛል። መፈለግ ብቻውን በቂ አይደለም። መፃፍ አለበት።
ህይወት ትርጉም የሚኖራት አንተ እስካለህ ድረስ ነው። ‹‹አንተ ከሌለህ እኮ ያ ለቤተሰቡ የሚያስበው፣ ለሚወዳቸው ዋጋ የሚከፍለው ጠንካራው ሰው የለም›› ትባላለህ። አየህ! መኖር አለብህ። መጥፎ ስሜት ሲሰማህ ተስፋ መቁረጥ ሊፈታተንህ ይችላል። ወዳጄ! ያንተ መበርታት ለሌሎችም ነው። አንተን የሚጠብቁ ብዙ ሰዎች አሉ። ካልተለወጥክ ግን አትደርስላቸውም። ለውጥ ዋጋ ያስከፍላል። ውጤቱ ግን የሚያረካ ነው።
ስለዚህ ማመንታቱን አቁም። ፍርሃቱን በፍላጎትህ ተካው። ሁሉም ሊለወጥ ሲል ይፈራል። ያመነታል። ሚጨክን ግን ህይወቱን ይቀይራል። አንዳንዴ መጨከን አለብህ። ለመዳን ስትል ጨክነህ መርፌ ትወጋለህ። መርፌ ያስፈራል። ከበሽታ የመዳን ፍላጎትህ ግን ጥልቅ ስለሆነ ጨክነህ ትወጋለህ። የመለወጥ ፍላጎትህ ለምትወዳቸው የመድረስ ፍላጎትህ ፍርሃትህን ሁሉ ይበጣጥሰዋል። በመቀየር የምታገኘውን ስታስብ መፍራት ታሪክ ይሆናል ወዳጄ!
አንድ ነገር በህይወትህ ለመለወጥ ስትነሳ ከስሩ ስለመቀየር አስብ። አየህ! ከላይ ከላይ ከሆነ ብዙ አትለወጥም። አንዳንዴ ሰዎች ክብደት ለመቀነስ ስፖርት ይጀምራሉ። ግን ክብደታቸው እንዳይቀንስ ያደረጋቸው አበላላቸው ሊሆን ይችላል። ሀይለኛ ስፖርት ሰርተው እንደጨረሱ ይደውሉና ‹‹አንድ ኪሎ ስጋ ከጃምቦ ድራፍት ጋር አዘጋጅልኝ እየመጣሁ ነው›› ይላሉ። ስለዚህ ችግሩ ስፖርት መስራታቸው ላይ አይደለም። አበላላቸው እንጂ።
አንድን ዛፍ መቁረጥ ፈልገህ ቅጠሉን ብቻ ብትለመልመው ማደጉ አይቀርም። ቅርንጫፉንም ብትቆርጠው ማደጉ አይቀርም። ግንዱንም ብትቆርጠው የሆነ ግዜ ማቆጥቆጡ አይቀርም። ስለዚህ ከስሩ መመንገል አለብህ ማለት ነው። አንዳንዴ ለውጥ የሚያስፈልግህ ከስርህ ነው። የምትለውጠው ጓደኞችህ ስለተለወጡ አይደለም። ‹‹የተሻለ ነገር ላይ ስለደረሱ እኔም ቢያንስ ከነእርሱ ማነስ የለብኝም። እኩል እሆናለሁ›› ብለህ አይደለም የምትለወጠው። የምትለወጠው የተሻለ ነገር ስለሚገባህ ነው። አሁን ያለው ህይወት ላንተ አይመጥንም። መቀየር አለበት።
ግን በራስህ መቀየር ስትሞክር ስለሌሎች የምታስብ ከሆነ አጠነክርም። በህይወት አጋጣሚ እነርሱ ጥለውህ ሄደው ሊሆን ይችላል። ተለውጠው ሊሆን ይችላል። ጨረቃና ፀሃይ እኩል አይወጡምና ያንተ ፀሃይ የሚወጣው ሲነጋ ነው። እስኪነጋ ግን ጥረትህን ማቆም የለብህም። አየህ! አንተ ገንዘብ በደምብ አድርገህ እያስቀመጥክ ሊሆን ይችላል። ግን ለምንድን ነው አልበረክትልህ ያለኝ? ልትል ትችላለህ። እውነተኛ ለውጥ የሚያስፈልግህ ገቢህን ለማሳደግ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጊዚያዊ መፍትሄ ብቻ አይደለም ማሰብ ያለብህ። የረጅም ግዜ ለውጥ ማሰብ አለብህ።
ሰውዬው ሁልግዜ ፀሃይ እየመታው ወደቤቱ ይገባል። በየቀኑ ራሱን ያመዋል። ከዛ መድሃኒት ይውጣል። ቀጥሎ ይድናል። መድሃኒት መዋጥ ግዚያዊ መፍትሄ ነው። ይህ ሰው እከመጨረሻው ራሱን እንዳይታመም ከፈለገ ፀሃይ ላይ መዋል የለበትም። ስለዚህ ‹‹ምንድን ነው ህይወቴን ከስር መሰረቱ የሚቀይረው?›› ማለት አለብህ። እኔና ፈጣሪ በቂ ነን ብለህ ማሰብ አለብህ። ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ በል ቁጭቱን አቁም። ራስህን መውቀስ የለብህም። ምክንያቱም ያኔ በነበረህ እውቀትና አረዳድ መወሰን ያለብህን ወስነሃል። ትናንት ላይመለስ አልፏል። ነገም አስተማማኝ አይደለም። ዛሬ ግን ያንተ ነው። አሁኑኑ መለወጥ አለብህ።
ወዳጄ! ዋጋህ እኮ አይቀንስም። የትኛውም ገንዘብ ቢተጣጠፍ አልያም ቢጨማደድ ዋጋው እንደማይቀንስ ሁሉ እኛም በከባድ ውጣውረድ ብንፈተን ዋጋችን መቼም አይቀንስም። ስትለወጥ እኮ ዋጋህ አብሮ ነው የሚጨምረው። አንዳንዴ ከጓደኞችህ ወይ በዙሪያህ ካሉ ሰዎች ኋላ መቅረትህ ሊያንገበግብህ ይችላል። ግን አትጥላው። ምክንያቱም ረጅም ርቀት ለመወርወር ወደኋላ በደምብ መንደርደር በጣም ወሳኝ ነው።
ለሁሉም ግዜ አለው። ግን በተለይ አሁን ራስህን ለመቀየር በጣም ወሳኝ ሰዓት ነው። እየታሸህ ያለኸው በደምብ እንድትበስል ነው። እድል ጓዟን ጠቅላ እጅህ ውስጥ እስክትገባ ድረስ ጥረትህን እንዳታቆም። የዚህ ዓለም እድለኞች አብዝተው የሚለፉ እንጂ አብዝተው የሚመኙ አይደሉም። የምትለወጠው ራስህን ለመቀየር፤ ወጥረህ የምትሰራው ለማንም ብለህ አይደለም። ነገ በራስህ እንድትኮራና ለልጆህ የምትነግረው ታሪክ እንዲኖርህ ነው። ታሪክ ደግሞ በመሰልቸትና ተስፋ በመቁረጥ አይሰራም። ስለዚህ ታላቅነትህን ቀስቅሰው። ተነስና ዛሬን አሸነፍ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም