ተወልደው ያደጉት በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ ነው። በዚያው በደብረታቦር ከተማ በሚገኘው በዳግማዊ ቴዎድርስ ትምህርት ቤት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በ1970ዎቹ አጋማሽ ወደ ባህርዳር መምህራን ኮሌጅ ተቀላቀሉ። በ1979 ዓ.ም ከባህርዳር መምህራን ኮሌጅ በጂኦግራፊ ትምህርት ዲፕሎማቸውን አገኙ። የሥራ ዓለምንም በድሮው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር አሁን ሱማሌ ክልል ጭናግሰን ወረዳ በመምህርነት አንድ ብለው ጀመሩ። ሥራ በጀመሩ በስድስተኛው ወር የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሆኑ። በጭናግሰን ከመምህርነት ባሻገር የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበር በመሆን ለሕዝብ አገልግለዋል። በጭናግሰን ለሦስት ዓመታት ከሠሩ በኋላ ወደ ጅግጅጋ ተዘዋወሩ።
በጅግጅጋ ከተማ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት እና ምክትል ርዕሰ መምህርነት ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል። ከመምህርነቱ ጎን ለጎን በጅግጅጋ ከተማም የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበር በመሆን የሱማልኛ እና የአማርኛ ተናጋሪ በሚበዛበት አካባቢ ለ13 ዓመት ሠርተዋል።
የሱማሌ ሕዝብ በጣም ተባባሪ ሕዝብ ነው የሚሉት የዛሬው የዘመን እንግዳችን አሁንም ቢሆን ልባቸው ያለው ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ መሆኑን ይናገራሉ። እስከዛሬ ድረስ ቤተሰቦቻቸውም የሚኖሩት በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ነው።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጂኦግራፊ እና በኢንቫይሮሜንታል ሳይንስ ከሀሮሚያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪቸውን በውሃ ሀብት አስተዳደር (Water Resource Management) እንዲሁም ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንቫይሮመንት ኤንድ ዴቨሎፕመንት በ(Enviroment and Development) በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል።
በሠሯቸው የተለያዩ ሥራዎች በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት ችለዋል። የሥራ ዓለሙን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሥራት ሕዝባቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።
የዛሬው እንግዳችን የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንዴ ገበየሁ ናቸው። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን ፡- ወደ ጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል እንዴት ገቡ? ጂኦግራፊ የማጥናት ፍላጎት ነበረዎት?
ዶክተር ክንዴ፡- የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። አጋጣሚ ሆኖ በዚያ ወቅት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችም የጂኦግራፊ ትምህርት መፈተን ይችላሉ። የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ እያለሁ የደረጃ ተማሪ ነበርኩ።
ይሁን እንጂ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ቤተሰቦች ስለተገኘሁ ራሴን እና ታናናሾቼን እየረዳሁ መማር ግዴታዬ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቤን በማገዝ፣ ታናናሽ እህትና ወንድሞቼን በመርዳት አሳለፍ ነበር። 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ቤተሰቦቼ ተቸግረው ደብተር እንኳን መግዛት ባለመቻላቸው ሁለቱን የክፍል ደረጃዎች ያለደብተር መማር ግድ ነበር። ምንም ደብተር ሳይኖረኝ ልፈተን ተገድጃለሁ። አባታችን በምን ሁኔታ እንደሆነ ባናውቅም ወደ ሱዳን ሀገር በመሄዱ እናታችን ያሳደገችን ብቻዋን ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ወስጄ ነጥብ መጣልኝ። በመሆኑም ወደ ባህርዳር መምህራን ኮሌጅ መግባት ቻልኩ። በባህርዳር መምህራን ኮሌጅ የተመደብንበትን የትምህርት ክፍል የሚገልጽ ማስታወቂያ ተለጠፈ። 11ኛ እና 12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ስለነበርኩ ስሜን የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ዝርዝር ውስጥ መፈለግ ያዝኩ፤ ነገር ግን ላገኘው አልቻልኩም። ተስፋ ቆርጬ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ እያለ ጓደኛዬ ስሜን ከማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ጋር መለጠፉን ነገረኝ። ከጂኦግራፊ ተማሪዎች ዝርዝር ጋር መደልደሌን አስተዋልኩ። የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ እያለሁ ለምን በጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል ተመደብኩ? ብዬ የኮሌጁን ዲን ጠየኩ። ዲኑም «የተፈጥሮ ሳይንስ ሞልቷል» የሚል ምላሽ ሰጠኝ። ስለዚህም ጂኦግራፊ መማር ግድ ሆነ። ከገባሁበት በኋላ ግን ትምህርቱን በጣም ወደድኩት። ከፍተኛ ውጤት አምጥቼም ሁሉንም ተማሪዎች በልጬ ለምረቃ በቃሁ።
አዲስ ዘመን ፡- በብዙ የበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚሳተፉ ይነገራል፤ ጊዜዎትን በእንደዚህ ዓይነት ተግባራት ላይ እንዲያውሉ ያደረግዎ ምንድን ነው?
ዶክተር ክንዴ፡- እንደዚህ ዓይነት ዝንባሌ እንዲኖረኝ ያደረጉኝ ምክንያቶች በርካታ ናቸው። አንደኛው ምክንያት ተፈጥሮዬ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ በዙሪያዬ ወይም በአጠገቤ ያሉ ሰዎች በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳተፊ ሆነው አይደለም። በአካባቢዬ የነበሩ ሰዎች በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተሳታፊ ቢሆኑ ኖሮ የእነሱ ተጽዕኖ ነው እል ነበር። ነገር ግን ከልጅነቴ ጀምሮ በአካባቢዬ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተሳታፊ የነበረ ሰው አላውቅም።
በነገራችን ላይ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተሰቦቼ ይህን ሳታደርግ ቀረህ ብለው ተቆጥተውኝ ወይም ገስጸውኝ አያውቁም። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ጨዋታ አላውቅም። ሁሉንም ጊዜዬን ያሳለፈኩት በሥራ ነው። ከሥራዬ ጎን ለጎን ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል።
በበጎ አድራጎት ሥራ ውስጥ እንድሳተፍ ከሚያደርጉኝ ገፊ ምክንያቶች ሌላኛው ደግሞ ሀገሬን ስለምወድ ነው። ሀገሬን ከስሟ ጀምሮ እወዳታላሁ። ኢትዮጵያ ከልጅነቴ ጀምሮ ታሳዝነኛለች። በዚህም በቻልኩት መጠን ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል።
ለሥራ ያለኝ ፍቅር ትልቅ ስለነበር ከኮሌጅ ተመርቄ ከስድስት ወር በኋላ በጭናግሰን መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ሆኜ ተመረጥኩ። ዳይሬክተር ሆኜ ስመረጥ ለበርካታ ዘመናት ያገለገሉ ልምድ ያላቸው መምህራን በትምህርት ቤቱ ነበሩ።
በትምህርት ቤቱ ያለኝን ታታሪነት የተመለከቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመማር ማስተማሩ ሥራዬ ጎን ለጎን በጭናግሰን በሚገኝ አንድ ቀበሌ በሊቀመንበርነት እንድምራ ተመረጥኩ። ለመንግሥት ሥራ አዲስ ስለነበርኩ እንዴት መምራት እንዳለብኝ ግራ ተጋብቼ ነበር። በመሆኑም የተሰጠኝን ሊቀመንበርነት አልፈልግም አልኩ። ግን ባለሥልጣናቱ አስገድደውኝ ቦታውን ተረከብኩ። ቦታውን ከተረከብኩ በኋላ ግን ትምህርት ቤት እና ቀበሌውን በጋራ እየመራሁ ውጤታማ ማድረግ ችያለሁ። በወቅቱ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር የጭናግሰን ትምህርት ቤት አንደኛ ወጣ። ከመንግሥትም እውቅና ተሰጠን።
ለእኔ አንድ ነገር ያንተ ነው ተብሎ ከተሰጠኝ በቃ የኔ ነው። ስለዚህ የኔ ነው ብዬ እሠራለሁ። ኃላፊ ሆነህ ሥራ ተብለህ ሲሰጥህ ሥራህን በአግባቡ አጠናቅቀህ መሥራት እንጂ በምንም መንገድ ምክንያት መፍጠር ተገቢ አይደለም።
ጭናግሰን እያለሁ በአካባቢው ከነበረው የመከላከያ ሠራዊት ትራክተር በመዋስ በትምህርት ቤቱ በሚገኝ ክፍት ቦታ ስንዴ ዘራሁ። ስንዴውን ከማረም እና ከመንከባከብ ባለፈ በአካባቢው ብዙ ወፍ ስላለ ወንጭፍ ሠርቼ የስንዴ ማሳውን ከወፎች እጠብቅ ነበር። በሱማሌ ክልል ወንጭፍ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ሰዎች ቢገረሙም እኔ ግን ስንዴውን ወፍ እንዳይበላብኝ ራሴ እጠብቅ ነበር። ሥራ ሲበዛብኝ ሰዎችን ተክቼ እንዲጠብቁልኝ አደርግ ነበር። በመጨረሻም ለትምህርት ቤቱ 30 ኩንታል ስንዴ አምርቼ አስገባሁ። የሥራ ቁርጠኝነት የሚጀምረው ከዚህ ነው።
ኢህአዴግ ሲገባ በዝውውር ወደ ጅግጅጋ አመራሁ። በዚያም ኅብረተሰቡን ማሰባሰብ እና ማደራጀት ያዝኩ። ያደራጀሁት ግን እርስ በርሱ እንዲረዳ እና እንዲተባበር እንጂ ለፖለቲካዊ ጉዳይ አልነበረም።
አንድ ቀን እያስተማርኩ እያለ የኢህአዴግ አመራሮች ትምህርት ቤት መጥተው ‹‹ትፈለጋለህ›› ብለው ወደ ቀበሌ ወሰዱኝ። እኔም ምን አጠፋሁ ብዬ ራሴን ደጋግሜ ጠየቅሁ። በራሴ ላይ ጥፋት አጣሁ። ግን ደግሞ ፈራሁ። በመጨረሻም በተፈለኩበት ቀበሌ ደረስኩ። ምን አድርጌ ነው? ስል ጠየቀኩ። አንድ ቀበሌ እንድትመራ መርጠንሀል ተባልኩ። እኔም አልችልም ብዬ ተከራከርኩ። ነገር ግን በግድ እንድይዝ ተደረገ። የቀበሌ አመራር እያለሁ የማገለግለው በነፃ ነበር። ከማስተማሩ ጎን ለጎን አንድን ቀበሌ ለ13 አመታት ያህል በአመራርነት አገልግያለሁ።
በ2006 ዓ.ም የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ጥናት ያደርግ ነበር። በዚያው ዓመት ‹‹ተቋሙ ይፈልግሃል›› ተባለኩ። የሕይወት ታሪኬን ጠየቁኝ፤ በፈለገ መጽሔት እና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወጣ። ከዚያም የምስክር ወረቀት ተሰጠኝ። ሌባ በሚታደበንት ሀገር አመለ ሸጋ፤ ንጹህ ሰው ነህ ተብዬ ተሸለምኩ። እንደዚህ ተብሎ እንደመሸለም የሚያስደስት ነገር የለም።
በጅግጅጋ ባደረኩት የአማራ ልማት ማህበር (አልማ)ን መደገፍ እንቅስቃሴ ከእነ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር የማኅበሩ አምባሳደር ተብዬ ተመረጥኩ። በሀገሪቱ ካሉ ትልልቅ ሰዎች ጋር አምባሳደር ሆኜ መሾሜ አስደስቶኛል።
በ2012 ዓ.ም በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ በርካታ ሥራዎች ከሠሩ ሰዎች መካከል በጎ ሰው ተብዬ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ዶክተር ፀሐይ ጋር ተሸልሜአለሁ። ሽልማቱን ማግኘቴ አይገባኝም ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ከእኔ የበለጡ በጎ እና ታታሪ ሰዎች አሉ የሚል እምነት አለኝ።
እኔ በአለኝ አቅም ኢትዮጵያን መሥራት አለብኝ ብዬ ብዙ ደክሜአለሁ። አንድ ሰው ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆነ ሀገር ይሠራል። በእኛ ሀገር የሚገኙ ምሁራንም ፈቃደኛ ከሆኑ ኢትዮጵያን መሥራት ይችላሉ። ምሁራኑ የእውቀት ችግር የለባቸውም። ችግራቸው የፈቃደኝነት ነው።
አሁን የምትታየው ኢትዮጵያ ትንሽ ፈተና በዝቶባታል። እንዲህ እንዲሆን ያደረግነው እኛው ራሳችን ነን። የበጠበጥናት እኛ ስለሆን የፍቅር እና የመተባበር ሀገር ሆና እንደትቀጥል እኛው ራሳችን ልንሠራት ይገባል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ምሁራኑ ፈቃደኛ ከሆነ የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር፣ የሰላም እና የብልጽግና እንዲሁም የመተባበርን መገንባት ይችላል። ፈቃደኝነት ጥበብን ያመጣል። ፈቃደኝነት መደማመጥን ያመጣል። አሁን በሀገራችን የጠፋው ፈቃደኝነት ነው። አሁን ላይ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በብሔር የመከፋፈሉ ነገር አይታሰብም። ምክንያቱም በዚያ ላይ በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል።
ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ራስን የማዳን ዘመቻ ወቅት እንኳ በወቅቱ በዩኒቨርሲቲያችን ይማሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በሆነ አጋጣሚም ቢሆን ጉዳት እንዳይደርስባቸው በማሰብ ግማሾችን ወደ አዲስ አበባ ሌሎቹን ወደ ትግራይ እንዲሸኙ አድርገናል። የትግራይ ተወላጅ ሆነው ቤተሰቦቻቸው መሀል ሀገር የሚኖሩትን እና ወደ ትግራይ መሄድ የማይፈልጉ ተማሪዎችን ደግሞ በዚያው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን እስከሚጨርሱ ድረስ ተንከባክበን አስመርቀናቸዋል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ መሠራት የምትችለው በዚህ
መልኩ ነው። አንድ ሰው ሰው ሊባል የሚችለውም ሰው መሥራት ሲችል ነው። ሰው ከሠራን ሀገር እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- በዩኒቨርሲቲ ማስተማር እና ዩኒቨርሲቲን ማስተዳደር ልዩነቱን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ክንዴ፡- አንድ አስተማሪ ከማስተማሩ በፊት ለምንድን ነው የማስተምረው? ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይገባል። ሁሌም ሳስተምር ይህን ኃላፊነት ወስጄ ነው። ማስተማር ጤናማነት ነው። ማስተማር መስጠትን መልመድ ነው።
ወደመሪነት ስንመጣ፤ መሪነት መሰጠት ነው። ቢሮዬ ውስጥ በግድግዳ ላይ የተጻፉ የሥነምግባር መርሆች ሁሌም አነባቸዋለሁ። እኔ የት ላይ ነኝ እያልኩም ራሴን እገመግማለሁ።
መሪ ሕዝብ እንዲከተለው መሥራት አለበት። አንድ መሪ የሚመራው ማኅበረሰብ እንዲከተለው ከፈለገ አንደኛ ከሚመራው ማኅበረሰብ በባህሪ ተሽሎ መገኘት አለበት። ሁለተኛ የሚመራውን ማኅበረሰብ በመቅረብ የችግሩ ተካፋይ መሆን አለበት። መሪ ከሚመራው ማኅበረሰብ ጋር ከተራራቀ ልብ ለልብ መገናኘት አይችልም። እነሱ አንተ የምትለውን አይሰሙም፤ አንተም እነሱ የሚሉትን መስማት አትችልም። ስለዚህ የተሻለ መሪ ለመሆን በባህሪ ተሽሎ መገኘት እና ከምትመራው ማኅበረሰብ ጋር በመቀራረብ ችግራቸውን አዳማጭ መሆን ያስፈልጋል።
መሪ ሆኖ ማሳየት እና ሆኖ መገኘት አለበት። መሪ ማለት ሆኖ የሚያሳይ ነው ሳይሆን የሚመራቸውን እንዲሆኑ ቢፈልግ ፍላጎቱ ከፍላጎት የዘለለ ሊሆን አይችልም። ሆኖ የሚያሳይ መሪ ሊከተሉት ያልቻሉትን ተማሪዎች እያበረታታ እንዲከተሉት ማድረግ ይችላል። መሪ በርቀት ሆኖ ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ አባርረው የሚል ከሆነ ሥራ ይበላሻል።
ሆኖ የተገኘ እና አድርጎ የሚያሳይ መሪ ተመሪውን በቀላሉ መምራት ይቻለዋል። ተመሪዎችንም ኑ ተከተሉኝ ሳይል ይከተሉታል። ምክንያቱም የሰው ልጅ ረቂቅ የማሰብ ችሎታ የተሰጠውን ፍጡር ስለሆነ መሪውንም መመዘን ስለሚችል ነው።
እኔ የማስተዳድራቸውን ሠራተኞች በጣም ስለምቀርባቸው የሚያዩኝ እንደ ወንድም እና እንደ አባታቸው ነው። አንድ ቀን አንድ ጥበቃ በር አካባቢ አግኝቶኝ «ዶክተር አንድ ጊዜ ምሳ በልቼ እስከምመጣ እያየህ አለኝ።» እኔም እሺ ሂድ፤ እስከምትመጣ እየጠበቅሁ እቆይሃለሁ አልኩት። እኔ እንደዚህ ዓይነት የአስተሳሰብ ደረጃ የደረስኩት በአንድ ጊዜ አይደለም። ይሄን ዕውቀት ለማዳበር በርካታ አመታትን ወስዶብኛል። ሌላ መሪ ቢሆን ምን አልባትም ሲገባ እና ሲወጣ ስላልተነሳለት የጎሪጥ ሊያየው ይችላል። ያ አለማወቅ ነው። አንዳንዴ መሪ ስትሆን ለሠራተኛህ ትህትናንም ማስተማር ይጠበቅብሃል። ያን ካደረግህ ሠራተኛው ተከተለኝ ሳትለው ይከተልሃል። መምራት በአፍ ሳይሆን በተግባር በማሳየት ጭምር የሚተገበር ነው። ብዙ ከመናገር በምትሠራቸው ሥራዎች ሰዎችን ማስከተል ትችላለህ።
ጥበቃው እኔን ሲያዝዝ ተማሪዎች ሰምተው ነበርና «ለምን ዶክተር ክንዴን ታዝዛለህ?» ሲሉ ሰማኋቸው። እኔም ምን ችግር አለው? አልኳቸው። እነኝህ ተማሪዎች ከእኔ ትህትናን ይማራሉ። በወቅቱ ጥበቃውን ብገስጸው ኖሮ ተማሪዎችም ትህትናን ሳይሆን ትዕቢትን ይማሩ ነበር።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያን ሁሉ መከራ በምሳሌ ሲቀበል ሁሉን የማድረግ አቅም ስላልነበረው አይደለም። ሁሉን የማድረግ አቅም ነበረው። ያን ያህል የተደበደበ እና የተንገላታ እኛን ሊያስተምር ነው። መሪነት እንደዚያ ነው። መሪነት ማለት መኮፈስ ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን ፡- በዩኒቨርሲቲው የተሰጠዎትን ኃላፊነት ለመወጣት ብዙ ጊዜ በቢሮ በሚገኘው ወንበር ላይ ተኝተው እንደሚያድሩ ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው? እንዴትስ ሊሆን ቻለ?
ዶክተር ክንዴ፡- አዎ! እውነት ነው። ብዙ ጊዜ የማድረው ቢሮ ውስጥ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞችም ደብረታቦር በመጡ ጊዜ ጃኬቶቼን፣ ከላይ የሚለበስ ፎጣ፣ አንሶላ እና ብርድ ልብሴን ቢሮ ውስጥ ተመልክተዋል። እኔ ቢሮ ውስጥ የማድረው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። አንደኛ ሌሊት ላይ በዩኒቨርሲቲው ችግር ሊፈጥር ይችላል በሚል ስጋት ነው። የሚፈጠርን ችግር በቀላሉ ለመፍታት በቅርብ መገኘት ደግሞ አስፈላጊ ነው። ሁለተኛ ሌሊት ላይ ተማሪዎች ቤተ መጽሐፍት አጠቃቀማቸው ምን ይመስላል? ምንስ ጎደለባቸው? ምን ያስፈልጋቸዋል? የሚለውን ለማየት ቢሮ ውስጥ ብዙ ጊዜ አድራለሁ።
የእውነት ለመናገር፤ ከቢሮ ውጪ ሳድር ዩኒቨርሲቲውን በሰላም የማገኘው አይመስለኝም። አንዳንድ ጊዜ የምፈልገው ቅያሪ ልብስ እንኳን ካለ ጥበቃውን ቤቴ ልኬ እንዲያመጣልኝ አደርጋለሁ።
በነገራችን ላይ ሰዎች የሚደሰቱበት ነገር ይለያያል። ግማሹ ሲዝናና፣ ግማሹ ከቤተሰቡ ጋር ሲሆን ወዘተ ነው። እኔ ግን የምዝናናው የተሰጠኝን ሥራ በትጋት ሠርቼ በስኬት ሳጠናቅቅ ብቻ ነው። እናም ቢሮ ውስጥ እያደርኩ በመሥራቴ በጣም እርካታ እና ደስታን ያስገኝልኛል።
አንድ ቀን ሌሊት በዩኒቨርሲቲው እያለሁ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በተማሪዎች ሽንት ቤት እሳት ተነሳ። በግቢው ውስጥ እየዞርኩ ስለነበር ቃጠሎውን መጀመሪያ ያየሁት እኔ ነበርኩ። ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ ፖሊሶች ሁኔታውን እንዲቆጣጠሩ አደረኩ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌላ ብሎክ ያሉ ተማሪዎች የብሎካቸውን መብራት አጥፍተው መጮህ ያዙ። እኔም ወደሚጮህበት ብሎኩ ሄድኩ። ብሎኩ በር ላይ ያገኘኋቸውን ተማሪዎች አንበርክኬ ቀጣኋቸው። በዚህ ጊዜ ተማሪዎች ‹‹ማርያምን፤ ማርያምን እኛ አላጠፋንም›› እያሉ ለመኑኝ። እኔም ተናድጄ ስለነበር ልመናቸውን አልሰማኋቸውም። የተማሪዎችን የማደሪያ ክፍል ቁጥር ይዤ ወደ ቢሮዬ ተመለስኩ። በቢሮዬ ተኝቼ እያለ ‹‹ማርያምን፤ ማርያምን እኛ አላጠፋንም›› እያሉ የጮሁትን ጩኸት በአእምሮዬ እየተመላለሰ አላስቀምጥ አለኝ። ተማሪዎችን ያለ ጥፋታቸው እንደቀጣኋቸው ተሰማኝ። ወፍ ጭ..ጭ..ጭ ሲል ከቢሮዬ ተነስቼ ወደ ተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ሄድኩና አንኳኳሁ። ተማሪችም በር ሲከፍቱ እኔን ተመለከቱኝ። አሁንም ‹‹እውነታችንን ነው እኛ አላጠፋንም›› ሲሉ ለመኑኝ። እኔም ይቅር በሉኝ ልጆቼ ብዬ እግራቸው ስር ተደፋሁ። ተማሪዎችም የእኔን አድራጎት ሲመለከቱ ይብሱኑ አለቀሱ። ይህን ገጠመኝ ከዩኒቨርሲቲው የወጡ ተማሪዎች ባሳተሙት መጽሐፋቸው ጽፈውታል።
እኔ እንደ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ይቅርታ ሳልጠይቅ ዝም ማለት እችል ነበር። ነገር ግን ተማሪዎችን ዝቅ ብሎ ይቅር ማለትን ማስተማር አልችልም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ሮኬት ማምጠቅን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ተግባራት እንደተከናወኑ ይነገራል። ይህን እንዴት ይገመግሙታል? ማምጠቁ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ ምን አጋጠማችሁ?
ዶክተር ክንዴ፡- የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ሮኬት ማምጠቁ በተለያዩ ሚዲዎች ተዘግቧል። ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በርካታ ዕድሎች ስለሚኖሩ መምህራን እና ተማሪዎች ከዕለት ከዕለት ከሚማሩት ትምህርት ወጣ ብሎ እንዲያስቡ ዕድል ያገኛሉ። ዩኒቨርሲቲያችን ገና በማደግ ላይ ያለ አዲስ ዩኒቨርሲቲ ነው። ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በሚችለው መልኩ ግብዓቶችን በማሟላት ከፍተኛ የምርምር ሥራዎች እንዲሠሩ እያደረገ ነው።
በዩኒቨርሲቲው ቴዎድሮስ፣ ጣይቱ እና አለማየሁ የተባሉ ሦስት ሮኬቶች ተሠርተዋል። ይሁን እንጂ ሮኬቶች ተሠርተው ለሙከራ ከተወነጨፉ በኋላ ወደ ምድር ሲያርፉ የሚወርዱበት ፓራሹት ጋር ተያይዞ የሚቀሩ ሥራዎች ስለነበሩ የተወሰኑ ችግሮች ተፈጥረዋል።
መጀመሪያ የማምጠቅ ሙከራ የተደረገው በመጠኑ ትንሽ በሆነው አለማየሁ በተባለው ሮኬት ነበር። የመጀመሪያችን እንደመሆኑ መጠን ከተወነጨፈ በኋላ ወደ ምድር ከሚወርድበት ፓራሹት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ክፍተት ስለነበር ሮኬቱ ያረፈው አንድ አርሶ አደር ግቢ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ሕይወት አላጠፋም እንጂ ሁኔታው አደገኛ ነበር። ይህን ተከትሎ የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎ በመካከለኛ ቁመና ያለችውን ጣይቱ የተባለችው ሮኬት ተተኮሰች። እሷም ላይም ከፓራሹት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ክፍተት ባለመቀረፉ ችግር ልትፈጥር ነበር። ቴዎድሮስ የተባለው ሦስተኛው ሮኬት ግን ረጅም እርቀት ተወንጫፊ በመሆኑ እና ሊያደርስ የሚችለው አደጋ ከፍተኛ ስለሆነ ሳይተኮስ ቀርቷል። እንዲመክንም ተደርጓል። በዩኒቨርሲቲው ከሮኬት ባለፈ መድፍም ተሠርቷል። ተተኩሶ ተሞክሯልም።
አዲስ ዘመን፡ – የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከምርምሮች ባለፈ በተለያዩ ማኅበረሰብ አቀፍ ተግባራት ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ክንዴ፡- መጀመሪያም ቢሆን የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰቡ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከተማው ከመቋቋሙ በፊት የደብረታቦር ከተማ እድገት ዘገምተኛ ነበር። ዩኒቨርሲቲው ከተከፈተ በኋላ ግን የደብረታቦር ከተማ እድገት በእጅጉ በመፋጠኑ በከተማዋ እና ዙሪያዋ የሚኖረው ሕዝብ ኑሮው በከፍተኛ ደረጃ መቀየር ችሏል። ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰቡ ነው ያልኩትም ለዚህ ነው ።
በዩኒቨርሲቲው በሚገኘው የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ ማኅበረሰቡ ደረጃውን የጠበቀ እና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት እያገኘ ነው። ከዚህ ባሻገር አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ ስመ ጥር ሪፈራል ሆስፒታሎች አቻ መሆን የሚችል ሪፈራል ሆስፒታል እየሠራን ነው። ሆስፒታሉ ሲጠናቅ ኦክስጅን ማምረት የሚችል ነው። ያ ሲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ ከህክምና አገልግሎት ባለፈ በርካታ የሥራ ዕድሎችንም የሚያገኝ ይሆናል።
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከመማር ማስተማር ተግባሩ በተጨማሪ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዞኑ ለሚገኙ 18 ለሚደርሱ ጤና ጣቢያዎች እና አንደኛ ደረጃ ሆስፒታሎች የተሟላ የህክምና መስጫ መሣሪያዎች እና መድኃኒቶች እንዲኖራቸው አድርጓል። መንግሥት እነኝህን መሣሪዎች ይግዛ ቢባል ከ30 ሚሊዮን ብር ባላይ ወጪ ይጠይቀዋል። በእነዚህ ጤና ጣቢያዎች የሚገኙ አንዳንድ ዕቃዎች ምናልባትም በከፍተኛ ሀኪም ቤቶች የማይገኙ እና ውድም ናቸው።
በገጠሩ አካባቢም ሰባት የዘመናዊ እርሻ የምርምር ጣቢያዎችን በመክፈት አርሶ አደሩን በሰፊው እያገዘ ይገኛል።
ከዚህ ባሻገር የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከ900 በላይ ለሆኑ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የተሟላ የህክምና ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል። የሥልጠናው ሙሉ በጀት የተመደበው ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ነው። ይህን እና መሰል ተግባራትን በማከናወን ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፡- የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱን እና የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መጀመሩን እንዴት ይገመግሙታል።
ዶክተር ክንዴ፡- ትምህርት ሚኒስቴር ከወሰዳቸው እርምጃዎች በግንባር ቀደምትነት የደገፍኩት ተግባር ቢኖር የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱን እና የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መጀመሩ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር እየሄደበት ያለው አካሄድ ሀገርን ከጥፋት የሚያድን በመሆኑም አጥብቄ እደግፈዋለሁ።
እርምጃው እስከዛሬ ከመዘግየቱ ውጪ ሀገርን የሚያድን ተግባር በመሆኑ እኔ እንደ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አጥብቄ እደግፈዋለሁ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትምህርት ሚኒስቴርን በመደገፍ እና በማበረታታት ሚኒስቴሩ እርምጃውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል።
በዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናው የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ስምንት ክፍል ትምህርቶች (ዲፓርትመንቶች) መቶ ከመቶ ሲያመጡ 18 ዲፓርትመንቶች ከ80 በመቶ በላይ አምጥተዋል። መቶ ከመቶ ካመጡ ተማሪዎች መካከል የህክምና ተማሪዎች ይገኙበታል።
አዲስ ዘመን፡- ለትብብርዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ክንዴ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም