በታላቁ ሩጫ 45 ሺ ተሳታፊዎች ይወዳደራሉ

ለ23ኛ ጊዜ የፊታችን ህዳር ለሚካሄደው ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ውድድር ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው እውቁ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ሲካሄድ 45 ሺ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉም የውድድሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ትናንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በአፍሪካ ከሚካሄዱ የጎዳና ላይ ውድድሮች ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ማስጠራት የቻሉ ኮከብ አትሌቶችን በማፍራትም ተጠቃሽ ነው። በዓለም ላይ ከሚካሄዱ አስር የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ ተብሎ በተመረጠው በዚህ ውድድር ላይ በመጪው ዓመት መሳተፍ ለሚፈልጉ ምዝገባው ከዛሬ ጀምሮ ይፋ ተደርጓል፡፡

እንደ ስሙ ታላቅ መሆን የቻለው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ባደረጋቸው ውድድሮች ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን ማግኘት የአገር ኩራት መሆን እንደቻለ በመግለጫው የተጠቆመ ሲሆን በቀጣይም ዓመት በርካታ ተሳታፊዎችን እንደሚያወዳድር አሳውቋል፡፡

ይህ ታላቅ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከ45 ሺ ቀንሶ የነበረ ቢሆንም በ2016 ዓ.ም ወደነበረበት የተሳታፊዎች ቁጥር እንደሚመለስ ተጠቁሟል፡፡

የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ቀድሞው መመለሱን ተከትሎ የውድድር ደረጃውን አሳድጓል፡፡ ከዚህም ቀደም በሶስት ማዕበሎች (የተሳታፊ ካኒቴራ ቀለም) ሲካሄድ የቆየው ውድድር ዘንድሮ ወደ ቀድሞ በመመለስ በሁለት ማዕበሎች ብቻ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም የውድድሩን ድባብ ወደ ቀድሞ ድምቀቱ ይመልሰዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ የመሮጫ ካኒቴራዎቹ ቀለምም አረንጓዴና ቢጫ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በውድድሩ ለመሳተፍ መመዝገብ የሚፈልጉ ተሳታፊዎች እንደየፍላጎታቸው በተለያዩ አማራጮች ምዝገባቸውን ማድረግ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡ የተሳተፊዎችን ምቾትና ፍላጎትን ባገናዘበ መልኩ በሁለት ደረጃዎች ምዝገባቸው የሚከናወን ሲሆን፣ ውድድራቸውን ከ1 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የሚፈልጉ ፈጣን ሯጮች በአረንጓዴ ማዕበል ስር ይካተታሉ፡፡ በዚህም ከ45ሺ ተሳተፊዎች 9 ሺዎቹ በአረንጓዴ ማእበል ውድድራቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቢጫ ማዕበል ስር ተካተው ውድድራቸውን ከ1 ሰዓት በላይ ማጠናቀቅ የሚፈልጉት ደግሞ 36 ሺ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በቢጫ ማዕበል ስር የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች የተለያዩ ትዕይንቶችን እያሳዩ ማዝናናት ለሚፈልጉ ተሳታፊዎች እንደሚዘጋጅ ይታወቃል፡፡

በአረንጓዴ ማዕበል ተካቶ ውድድራቸውን የሚያደርጉ ተሳታፊዎች 700 ብር የመመዝገቢያ ክፍያቸውን በመፈጸም መመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ በቢጫ ማዕበል ስር የሚሳተፉት ደግሞ 640 ብር በመክፍል ተመዝግበው ውድድሩ ሲቀርብ የመሮጫ ካኒቴራቸውን መረከብ እንደሚችሉም አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ በአረንጓዴ ማዕበል ለሚሳተፉ የድርጅት ተወዳዳሪዎች በሚያሳትፉት የሰው ብዛት መሰረት ለአምስት ሰው የአንድ ወር የውድድር ስልጠና በታላቁ ሩጫ የሚሰጥም ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ሁሉም ተሳታፊዎች ውድድራቸውን በተሻለ ፍጥነት እንዲጨርሱ ለ6 ሳምንታት ያክል በአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት የልምምድ ስልጠና የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡

የግል ተወዳዳሪዎች ምዝገባው ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በሁለት መንገዶች የሚደረግ ሲሆን፣ በቴሌ ብር መተግበሪያ አማካኝነት በስልክ ክፍያ በመፈፀም የውድድር መመዝገቢያ ፎርሙን መሙላት እንደሚቻል ተጠቅሷል፡፡ ክፍያቸውን በቴሌ ብር መፈጸም የማይችሉ ሰዎች ደግሞ በ6 የተመረጡ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፎች አማካኝነት ክፍያ ካከናወኑ በኋላ ውድድሩ የሚደረግበት ቀን ሲቃረብ በነዚሁ ቅርንጫፎች የመወዳደሪያ ካኒቴራ እንዲረከቡ ይደረጋል፡፡ የድርጅት ተመዝጋቢዎች ደግሞ በሚሰሩበት ድርጅት አማካይነት በመታገዝ በታላቁ ሩጫ ቢሮ ምዝገባቸውን ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

‹‹ታላቁ ሩጫን እንደ ኢትዮጵያ እንኮራበታለን›› በማለት በመግለጫው የተናገረው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ውድደሩ በዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ መሆኑን አስታውሶ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ ሊሆንበት ይገባል ብሏል፡፡

ጀግናው አትሌት አክሎም ‹‹ሩጫን የህይወታችን አካል እናድርግ ስንል ለታላቁ ሩጫ ብለን ሳይሆን ለራሳችን ጤና ሊሆን ይገባል፣ ውድድሩ ባለቤት የለውም ባለቤቱ ኢትዮጵያ ነች›› በማለት የተናገረ ሲሆን፣ ውድድሩ ዓለም አቀፍ መመዘኛ ማሟላቱን ተከትሎ በውድድሩ የሚሳተፉ ትልልቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሊመሰገኑ ይገባል ብሏል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *