የማዕድን ሀብት ጥናትና ፍለጋ  የክልሎች የትኩረት አቅጣጫ

ለግንባታው ዘርፍ አስፈላጊ ከሆኑ ግብዓቶች አንዱ የሆነውን የብረት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት መንግሥት ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ ለማቅረብ የሚያስችል አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወቃል። በዚህም ከተለያዩ አካባቢዎች አገልግሎታቸውን የጨረሱ ቁርጥራጭ ብረቶችን በመሰብሰብ ለኢንዱስትሪዎቹ ማቅረብ መጀመሩም ይታወሳል። በዚህ መልኩ ግብዓቱን ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች የማቅረቡ ተግባር ለሁለት ዓመታት እንደሚቀጥል ተጠቁሟል። ይህ እርምጃ ችግሩን ለመፍታት በጊዜያዊነት የተወሰደ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ ለግብርናው ዘርፍ የሚውል የአፈር ግብዓት ከውጭ ለማስገባት መንግሥት ድጎማ እያደረገ ይገኛል። ለአብነትም ለተያዘው 2015/16 የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ 21 ቢሊዮን ብር መድቦ ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል፤ ማዳበሪያ ለዓለም በስፋት በሚያቀርቡት ሩሲያና ዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ግን የግዥው ሂደት ተግዳሮቶች ገጥመውት ቆይቷል። ይህም ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ በወቅቱ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ መጓተት እንዲከሰት አድርጓል።

ይህ ብቻም ሳይሆን የማዳበሪያ ፋብሪካ ጉዳይ አነጋጋሪ እንዲሆን እስከማድረግ ደርሷል። ሀገሪቱ ለማዳበሪያ ማምረቻ የሚሆን የግብዓት ክምችት እያላት ነው ማዳበሪያውን በውጭ ምንዛሬ ከውጭ እያመጣች የምትገኘው፡፡

የማዳበሪያ ጉዳይ ያሳሰባቸው አካላት ለማዳበሪያ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግ እየጠየቁ ይገኛሉ። በሀገሪቱ ለማዳበሪያ ፋብሪካ ሊውል የሚችል በቂ ግብዓት እንዳለ በመጥቀስ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገሪቱ ለመገንባት ለምን ትኩረት አልተሰጠም የሚሉ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ናቸው፤ በቅርቡም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ለእነዚህ ግዙፍ ዘርፎች እና ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ የማዕድን ሀብቶች በሀገር ውስጥ የሚገኙ ስለመሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። እንደ ሀገር ማዕድኖቹ ከጥራትና ከክምችት አኳያ ያላቸው አቅምም እየተጠና ይገኛል። የማዕድኑ ዘርፍ በተለያዩ ምክንያቶች በፈተና ውስጥ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ ሀገር በምትፈልገው ልክ ተሠርቷል ማለት ግን አይቻልም።

መንግሥት ለማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚው የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በዘርፉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁንም ከዘርፉ ከሚጠበቀው ከፍተኛ ፍላጎት አኳያም በ2016 በጀት ዓመት የተጠናከረ ሥራዎች ማከናወን ያስፈልጋል፡፡

ክልሎችም እንደ ማዳበሪያ፣ ብረት ያሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በሚያስችሉ የማዕድን ግብዓቶች ጥናትና ፍለጋ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል። አሁንም በግብዓቶቹ ላይ የሚያደርጓቸው ጥናቶችና ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህንን በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ትኩረቱን በክልሎች ላይ በማድረግ ተከታዩን ዳሰሳ አድርጓል።

በአማራ ክልል ስላለው የማዕድን ልማት የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ እንደሚሉት፤ በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት በወርቅና በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ ትኩረት ያደረገ የጥናት ሥራ መከናወኑን ይገልጸሉ። በክልሉ የሦስት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተጨማሪም ወሎ ውስጥ ወደ አምስት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ባለሀብቶች የምርመራ ፈቃድ ወስደው በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በቀጣዩ 2016 በጀት ዓመት ለፋበሪካዎቹ የሚያስፈልጉ የማዕድን ግብዓቶችን በየአካባቢያቸው በጥናት ለይቶ ምቹ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በጥናት ላይ የሚገኙ ሥራዎችንም አጽድቆ ወደ ሥራ ለመግባት የጥናት እቅድ ሥራው በግምገማ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፤ በአጠቃላይ በ2016 በጀት ዓመት የከበሩ የጌጣጌጥና የወርቅ ማዕድናትን ጨምሮ የማዕድን ጥሬ ዕቃ ግብዓት ለሚያስፈልጋቸው ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ ለሁሉም ዓይነት የሚሆኑ ማዕድናትን በክልሉ 13 ዞኖች፣ 22 ወረዳዎች፣ በሦስት ሜትሮ ፖሊታን ከተሞችና በአንድ መካከለኛ ከተማ 26 የማዕድን ምርምር ጥናቶችን ለማካሄድ እየተሠራ ነው። ለጥናት ሥራው የሚያስፈልገው ወደ 73 ሚሊዮን ብር ጥያቄም ለክልሉ መስተዳድር ቀርቧል፡፡

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፤ በማዕድን ምርመራ ጥናት ሥራ በተለይ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ በግንባታው ዘርፍ በክልሉ የተሻለ ክምችትና ጥራት ያለው የብረት ማዕድን ፍለጋ እንዲከናወን ትኩረት ተደርጓል። ቀደም ሲል በብረት ማዕድን ፍለጋና ልማት ላይ በሚፈለገው ልክ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አልነበረም። ፍላጎት ያለው አልሚ ባለሀብት ላለመኖሩ ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ዘርፉ የሚፈልገው መሠረተ ልማትና የሚጠይቀው ኢንቨስትመንትም ከፍተኛ መሆን ይጠቀሳል፤ ይህም ባለሀብቱ እንዳይበረታታ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው። አሁን ላይ ግን ክፍተቶቹን ማዕከል ያደረገ፣ በጥራትና በቂ ክምችት የሚገኝበትን አካባቢ በመለየት ላይ ትኩረት በማድረግ በተያዘው 2016 በጀት ዓመት በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሮው አቅዶ እየሠራ ይገኛል፡፡

ሌሎች በጥናት እቅድ ዝግጅት ውስጥ የተካተቱት እንደ ላይምስቶንና ፖታሽ የመሳሰሉ የግብርና የማዕድን ጥሬ ዕቃ ግብአቶች ናቸው። ፖታሽ የሚባለው ማዕድን እስካሁን በክልሉ ስለመኖሩ ገና አልተረጋገጠም። ሆኖም ግን የአፈር አሲዳማነትን ማከሚያ የሚውል ማዕድን ግን ይገኛል።

የግብርና ኖራ አዘጋጅቶ ለተጠቃሚው ለማቅረብ አንድ የልማት ድርጅት ደጀን አካባቢ ወደ ሥራ ገብቷል። የግብርና ኖራ ለማዘጋጀት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ካሉም ቢሮው ያበረታታል። ቢሮው ለግብርና ኖራ የሚውለውን ማዕድን የጥራትና የክምችት መጠንም በጥናት ለይቶ ለአልሚው ለማቅረብም ጎን ለጎን ይሠራል፡፡

የሥነምድር አጠቃላይ ጥናትን በተመለከተም አቶ ታምራት እንዳስረዱት፤ በሥነ ምድር ሳይንስ (ጂኦሎጂካል ሰርቬይ) የጥናት ሥራዎች በሦስት መንገድ ነው የሚከናወኑት። አንዱ የሥነ ምድር ጥናት የሚባለው ሲሆን፤ ይህም የአካባቢውን ሥነ ምድር አፈጣጠር ሁኔታና በአካባቢው ምን ሊገኝ ይችላል የሚለውን በማጥናት ካርታ (ማፕ) ማዘጋጀት ነው። በዚህ መልኩ ከተዘጋጀ በኋላ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የጂኦ ኬሚስትሪ ወይንም የማዕድኑ ውስጣዊ ክፍል ማለትም የኬሚካል መጠን ያጠናል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የጂኦ ፊዚክስ ወይንም የክምችት መጠኑን ለማወቅም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም የሚቻልበትን ጥናት ማካተት ይቻላል። በዚህ ሁኔታ ከተጠና በኋላ ደግሞ ወደ ቤተሙከራ (ላቦራቶሪ) ይላካል። አንድ ማዕድን ማዕድን መሆኑ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚረጋገጠው በቤተ ሙከራ ውስጥ በሚደረግ ፍተሻ ነው፡፡

የተደራጀ ቤተ ሙከራ ክልሉ ስለሌለው ወደ ማዕድን ሚኒስቴር በመላክ የፍተሻ ሥራው እንዲከናወን ያደርጋል ሲሉ አቶ ታምራት ይገልጸሉ። እንደ ሀገርም ቢሆን ያለው ቤተ ሙከራ በቂ ነው የሚባል እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ አንድ ቤተ ሙከራ ብቻ በመሆኑ በሚፈጠር የሥራ ጫና ቶሎ ውጤት አውቆ ወደሚቀጥለው እርምጃ ለመሄድም ሆነ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ለማድረግ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ ነው። ያም ሆኖ የጥናት ሥራዎችን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲል በተከናወኑ የማዕድን ፍለጋ መጠን ክምችት ግመታ የጥናት ሥራዎች መለየት የተቻለው ከአንድ በመቶ በታች እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታምራት፣ አሁን ላይ እየተደረገ ባለው የጥናት ሥራ ላይ ዜሮ ሦስት በመቶ (03 ነጥብ) በመጨመር ወደ አንድ ነጥብ ዜሮ ሦስት (1 ነጥብ 03 በመቶ) ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው።

ሁለተኛው የሥነ ምድር ጥናት መሠረታዊ ጂኦ ሳይንስ ካርታ ዝግጅት የሚካሄድበት ነው። በዚህ ስፋቱን ወይንም አካባቢያዊ ሁኔታን ለመለየት በተሠራው ሥራ ከነበረበት 14 በመቶ ወደ 34 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን አቶ ታምራት ጠቁመዋል። ይሄን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለውም የካርታ ዝግጅት ሥራውን በአንድ ዓመት ብቻ 19 ነጥብ 9 በመቶ በመፈጸም መሆኑን አመልክተዋል። እሳቸው እንዳሉት አሁንም መረጃዎች የሚያሳዩት ወደ 65 በመቶ የሚሆን ሥራ እንዳልተሠራና በእያንዳንዱ አካባቢ ምን እንዳለና ምን ሊገኝ እንደሚችል ሰፊ የጥናት ሥራ እንደሚጠይቅ ነው።

የማዕድን ሀብት ክምችት መጠንና የሚገኝባቸውንም አካባቢዎች በስፋት አጥንቶ መረጃ ለመሰብሰብ ቢሮው በአማራ ክልል ከሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ታምራት፤ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲ ፎረም ጽሕፈት ቤትም በዚህ ረገድ ተባባሪ በመሆን የማዕድን ሀብቶች እንዲያጠኑና እንዲለዩ በማድረግ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በዚህ የጥናት ሥራም መልካም ጎን ብሎ ከሚያነሳቸው አንዱ አጋር አካላትን በጥናት ሥራ ማሳተፉ እንደሆነ አቶ ታምራት ይጠቅሳሉ። በክልሉ የተለያዩ ማዕድናት መኖራቸው እንደሚታወቅ ተናግረው፤ በክምችት መጠንና በጥራት ደረጃ ግን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በጥናት መለየት እንደሚያስፈልግና ሥራዎችም ከዚህ አኳያ እየታዩ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡

የማዕድን ክምችት መጠንና የጥራት ሁኔታን ለማረጋገጥ በእጅጉ የሚያስፈልገው የቤተ ሙከራ ጉዳይም ትኩረት እንዲሰጠው፣ ለፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲደረግና የግብዓት አቅርቦቶችም ምቹ እንዲሆኑ መስተዳድሩን በመጠየቅም በቢሮው በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ጎን ለጎንም የአጋሮችን ተባባሪነት ለመጨመር፣ በአጠቃላይ የማዕድንን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ በመንቀሳቀስ በኩል ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነም አቶ ታምራት አመልክተዋል። በተጨማሪም ጥናቱን መነሻ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችንም በመተንበይ እርምጃዎች የሚወሰዱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የክልሉን መንግሥት ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እንዲያውቁት የማድረግ ተግባርም በቢሮው በኩል እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ታምራት ማብራሪያ፤ አጋር አካላትን በጥናት ሥራዎች በማሳተፍ ቢሮው ያከናወነው ተግባርም በጠንካራ ጎን ካያቸው ሥራዎቹ ውስጥ ይጠቀሳል። ማዕድን ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ሀብቱ የሚገኝበትን በጥናት ለመለየት ሲሠሩ የቆዩትን ተግባራት በማጠናከር ቢሮው በ2016 በጀት አመት ለተሻለ ውጤት ሁለተናዊ ዝግጅት አድርጓል፡፡

የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲም ልክ እንደ አማራ ክልል ሁሉ በተመሳሳይ ከዩኒቨርሲቲዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጥናት ሥራን ማከናወን የትኩረት አቅጣጫው ማድረጉን ይገልጻል። ለእዚህም ለ2016 በጀት አመት በዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኑንም በኤጀንሲው የማዕድን ዘርፍ ኃላፊ አቶ እያሱ ማሞ ገልጸውልናል።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በክልሉ ወደ ሰባት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው፤ የጥናት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። የጥናቱ ውጤቱ ሲጠቃለልም እርሱን መሠረት በማድረግ በተያዘው 2016 በጀት አመት ቀደም ሲል ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ በተጨማሪ የማዕድን ሥራ የማከናወን ሁኔታን ምቹ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል ግብዓትን በሀገር ውስጥ በመተካት ለግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት እንደ መንግሥት የተያዘውን አቅጣጫ በማሳካት ከግብ ለማድረስ ክልሉ በድንጋይ ከሰል ላይ ሲሠራ መቆየቱን አቶ እያሱ ይጠቅሳሉ፡፡

በዚህ የክረምት ወቅት ከሚከናወኑት መካከልም የድንጋይ ከሰል ክምችት የሚገኝባቸውን አካባቢዎች በመለየት ለአልሚዎች ምቹ የማድረግ ሥራ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል። አልሚዎችም በበጋው ወቅት በሙሉ አቅማቸው መሥራት እንዲችሉ እንዲሁም ጥናቶች ላይ ተመሥርተው የሚሠሯቸውን ሥራዎች በጊዜ አጠቃለው ለሥራ ዝግጁ እንዲያደርጉ፣ ጎን ለጎንም ሕጋዊ ለሆኑ አልሚዎችም ፍቃድ በመስጠትና የተለያዩ ተግባራትንም በመወጣት ርብርብ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ እያሱ ገለጸ፤ ሌላው የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ የብረት ማዕድን ነው። በክልሉ የብረት ክምችት ስለመኖሩ ጥናቶች ያሳያሉ። በመሆኑም ይህ ወቅት አልሚው በጥናት የተለዩትን ማዕድናት በስፋት እንዲያለማ ዕድል የሚፈጠርበት ነው።

በክልሉ ሁሉም ዓይነት ማዕድኖች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በጥናት በሂደት እየተለዩ የመጡት የማዕድን ዓይነቶች በመጠንም ይሁን በይዘት ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ በተለይም እንደ ሴራሚክ ያሉ የግንባታ ማጠናቀቂያ ግብአቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ እያሱ በአዲስ መልክ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ደግሞ የብረት ማዕድን ክምችት ላይ ክልሉም ትኩረት በመስጠት በጥናት ለመለየት ጥረት አድርጓል ይላሉ። ልማቱን ለማከናወንም ፍቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች መኖራቸውንና በጥናት ሥራ ላይ እንደሆኑም ገልጸዋል። ለቀለም ፋብሪካ የሚውል «ዶሎማይት» በማልማት ለኢንዱስትሪው የሚያቀርቡ ወደ 16 የሚሆኑ ኩባንያዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ዋና በተባሉ የማዕድን ልማቶች ላይ እንዲገቡ በጥናት የመለየቱ ሥራ ይጠናከራል ያሉት አቶ እያሱ፣ በዚህ ወቅት በጥናት በተለዩት የማዕድን ዓይነቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም በማኅበር የተደራጁ ወጣቶች ከከበሩ ድንጋዮች ለሚያዘጋጁዋቸው የጌጣጌጥ ማዕድናት ልማት መጠናከር ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ በጥናት ልማቱን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

 ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *