ትዕግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን ዳግም ለአሸናፊነት ትጠበቃለች

በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የሚደረገው ዓመታዊ የማራቶን ውድድር ለ49ኛ ጊዜ በመጪው 2016 ዓም መስከረም ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል። ከታላላቅ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ከ40ሺ በላይ ሯጮች ይሳተፋሉ፡፡ ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው ማራቶኖች አንዱ የሆነው በርሊን ፈጣን ሰዓትና የዓለም ክብረወሰኖችን በተደጋጋሚ የሚሰበሩበት ነው፡፡ ዘንድሮም በዚህ ውድድር አዲስ ነገር ይታያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሁለት ወር ብቻ በቀረውና በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ማግስት በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይ በዓለም አሉ የተባሉ የማራቶን አትሌት ተሳታፊ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል። አምና የውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በቀጣዩ ውድድር ተሳታፊ መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን ይህም ፉክክሩን በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡

በሴቶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ትእግስት አሰፋ ተሳታፊ መሆኗን ያረጋገጠች ሲሆን፣ በወንዶች የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ ኬንያዊ ኢሉድ ኪፕቾጌ እንደሚወዳደር ተረጋግጧል፡፡

በረጅም ርቀት የመም እና ሌሎች የጎዳና ላይ ውድድሮች ድምቀትና ጥንካሬ የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በበርሊን ማራቶንም ሰፊ የተሳትፎና የአሸናፊነት ታሪክ አላቸው። በውድድሩ ታሪክ ኃይሌ ገብረስላሴ ለአራት ጊዜያት በተከታታይ አሸናፊ በመሆን ቀዳሚው ሲሆን፤ ሌላኛው ጀግና አትሌት ቀነኒሳ በቀለም እአአ በ2016 እና 2019 የበርሊን ማራቶን አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በሴቶች በኩልም እአአ ከ2006 አንስቶ አስር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ በመሆን በውድድሩ ጎልተው ለመታየት ችለዋል፡፡

ከሁለት ወር በኋላ በሚካሄደው በዚህ ውድድርም በተመሳሳይ የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሊሆን ችሏል፡፡ ትዕግስት አሰፋ ደግሞ በተከታታይ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። ከ800 ሜትር ተሳታፊነት ተነስታ በሂደት ወደ ማራቶን ሯጭነት ያደገችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት በተለያዩ ጊዜያት በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ስትሳተፍ ቆይታለች። በማራቶን ያላት ተሳትፎ እጅግ አጭር የሚባል ሲሆን፤ ያላት ፈጣን ሰዓትም 2:34:01 ነበረ፡፡ ይሁንና አትሌቷ ባልተጠበቀ ሁኔታ በርካታ ታዋቂና ልምድ ያላቸው አትሌቶች በተሳተፉበት የበርሊን ማራቶን አስደናቂ ብቃቷን ያስመሰከረ ውጤት ልታስመዘግብ ችላለች፡፡ በዚህም የ26 ዓመቷ አትሌቷ ውድድሩን ከማሸነፍ ባለፈ እጅግ ሰፊ በሚባል ልዩነት ሰዓቷን ወደ 2:15:37 ልታሻሽል ችላለች፡፡ በዚህም አትሌቷ የርቀቱን ሶስተኛ ፈጣን ሰዓት እንዲሁም የኢትዮጵያን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ በቀጣዩ ውድድር ላይ ዳግም ተሳታፊ መሆኗን ያረጋገጠች ሲሆን፤ የግሏን ምርጥ ሰዓት በማሻሻልም አሸናፊ ትሆናለች በሚል ትጠበቃለች፡፡

የትዕግስት ተፎካካሪ ትሆናለች ተብላ የምትጠበቀው ኬንያዊቷ አትሌት ሺላ ቼፕኪሩይ በዋናነት ትጠቀሳለች። በቅርቡ የማራቶን ውድድሮችን የተቀላቀለችው ይህች አትሌት በለንደን ማራቶን 2:18:51 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡ ያለፈው ዓመት የበርሊን ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይም ተሳታፊ መሆኗ ለውድድሩ አዲስ እንዳትሆን ይረዳታል፡፡ አትሌቷ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ተመራጭ በመሆኗ ውድድሩ ላይ አሸናፊ መሆኗ በብዙ የሚረዳት እንደመሆኑ ፈታኝ የአሸናፊነት ጥረት እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡

በወንዶች በኩል በሚካሄደው ፉክክር የርቀቱ የወቅቱ ንጉስ ኪፕቾጌ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ማግኘቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ ትልቅ ትግል ያደረገው ይህ የሁለት ኦሊምፒኮች ሻምፒዮን በበርሊን ማራቶን ሲሳተፍ ቀጣዩ ውድድር አምስተኛው ይሆናል፡፡ አራት ጊዜም ይህን ውድድር የደመደመው በአሸናፊነት ነው፡፡

ከአራቱ ድሎች ባሻገር ኪፕቾጌንና በርሊንን ይበልጥ የሚያቆራኛቸው ሁለት ጊዜ የዓለም ክብረወሰኖችን በጀርመና መዲና መስበሩ ነው፡፡ በርሊን እአአ ከ2003 አንስቶ በወንዶች ስምንት ክብረወሰኖች ሲሰበሩባት ሁለቱን ማሳካት የቻለው ይህ ድንቅ ኬንያዊ አትሌት ነው፡፡ ኪፕቾጌ እአአ በ2018 የመጀመሪያውን የርቀቱ ፈጣን ሰዓት 2:01:39 በመግባት ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ባለፈው ዓመት በድጋሚ 2:01:09 በሆነ ሰዓት የግሉን ፈጣን እንዲሁም የዓለም ክብረወሰንን ሊያሻሽል የቻለበት ነው፡፡

‹‹ለፓሪስ ኦሊምፒክ በልምምድ ላይ እገኛለሁ፤ ይህ ውድድርም የዝግጅቴ አንድ አካል ይሆናል፡፡ የበርሊን ጎዳናዎች ላይ በርካታ ትውስታዎች አሉኝ፡፡ በዚህ ሩጫ ላይም በሺዎች ከሚቆጠሩ ሯጮች ጋር እገኛለሁ›› ሲልም ኪፕቾጌ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 13/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *