በ1943 ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት የቀድሞዋ ‹‹ቢራሮ›› የአሁኗ ኮምቦልቻ ከተማ፣ ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ በማስተር ፕላን የምትመራ ዘመናዊ ከተማ ሆናለች፡፡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሪጂኦፖሊታን ከተማ አስተዳደር መዋቅር እየተዳደረች የምትገኝ ሲሆን፣ በ14 የከተማ እና በስድስት የገጠር ቀበሌዎች ተዋቅራለች፡፡ በውሃ አቅርቦት ስማቸው በበጎ ከሚነሱ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከልም አንዷ ናት፡፡
ኮምቦልቻ ከምትታወቅባቸው መለያዎቿ መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ መናኻሪያነቷ እና የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷ ነው፡፡ ከተማዋ የበርካታ አምራች ድርጅቶች መገኛ ናት፡፡ በከተማዋ የሚገኙት የደረቅ ወደብ (በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ)፣ የአውሮፕላን ማረፊያና የኢንዱስትሪ ዞን እንዲሁም በከፊል የተጠናቀቀው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ሃዲድ ኮምቦልቻን ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተማዋን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያስተሳስራትና የደረቅ ጭነት መተላለፊያ አውራ ጎዳና መኖሩ ለኢንዱስትሪ መናኻሪያነቷ ትልቅ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡
የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊታን ከተማ ዋነኛ የኢንቨስትመንት የትኩረት ማዕከል የአምራች ዘርፍ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከዚህም መካከል የጨርቃ ጨርቅ እና የምግብ ማቀነባበር ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ዘርፎቹ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው ከተማዋ መሰል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለመሳብና ለማስተናገድ ልዩ ትኩረት ትሰጣለች፡፡
በመልካም የኢንቨስትመንት መነቃቃትና ጉዞ ላይ የነበረችው ኮምቦልቻ፣ የሰሜኑ ጦርነት ለከፍተኛ ውድመት እንደዳረጋት ይታወሳል፡፡ ጦርነቱ በኮምቦልቻ ከተማ ላይ ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት ማስከተሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በርካታ የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውድመቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በአብዛኛው ንብረትነታቸው የኢንቨስተሮች የሆኑ ከ270 በላይ ኮንቴይነሮች ከኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ተዘርፈዋል፡፡ ከገንዘብ በተጨማሪ ከተማዋ ለከፍተኛ ማኅበራዊ ችግሮችም ተዳርጋለች፡፡
በ90 ሚሊዮን ዶላር በተገነባውና በ75 ሄክታር መሬት ላይ ባረፈው በባለዘጠኝ ሼዱ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የተፈፀመው ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት የዚህ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን አምርተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አራት የደቡብ ኮሪያ፣ የኢጣሊያ፣ የአሜሪካና የቻይና አምራች ኩባንያዎች ከገቡበት ከዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተዘረፉት መካከል የፓርኩ የቢሮ እቃዎችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ሲስተሞች፣ የአምራች ኩባንያዎች ቢሮዎችና ቁሳቁስ፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶችና ጥሬ እቃዎች ይገኙበታል። ለፓርኩ ተጨማሪ ግንባታ ለማድረግ እንደመጋዘን ሲያገለግሉ የነበሩ ኮንቴይነሮች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያሉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁስ እንዲሁም የፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች፣ የማምረቻ ቦታዎች፣ የኬሚካል ማጣሪያ እና ሌሎች በፓርኩ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ክፍሎች ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ከተፈጸመባቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በባለሀብቶች ተመራጭ የሆነው ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲመለስ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፤ ይህን ተከትሎም ኢንዱስትሪ ፓርኩ በፍጥነት ወደ ሥራ ሊመለስ ችሏል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር ከዚህ የጦርነቱ ውድመት በማገገም የኮምቦልቻን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለማስቀጠል ከአማራ ክልል መንግሥትና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተግባራትም ለከተማዋ የ2015 በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት አፈፃፀም እምርታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ውድመት ደርሶባቸው ሥራ ያቆሙ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግና ለማበረታታት የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት መድረክ በመፍጠር ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
ተቋማቱ የደረሰባቸውን ጉዳትና ችግሮቻቸውን ማጥናት አስፈላጊ በመሆኑ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ከክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመተባበር የተቋማቱን ጉዳት የማጥናትና ችግሮቻቸውን የመለየት ሥራዎች ተሰርተዋል። በተጨማሪም ከባንኮችና እርዳታ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ትስስር ፈጥረው የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚያበረታቱ በርካታ የማነቃቂያ ስልጠናዎችም ተሰጥተዋል፡፡
የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊታን ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ኃይሌ እንደሚናገሩት፣ የከተማዋ የ2015 በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት አፈፃፀም አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ 23 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 110 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል፡፡
ባለሀብቶቹ በማምረቻ (ኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ ምግብና ፋማሲዩቲካል፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት) እንዲሁም በአገልግሎት (ሆቴልና ቱሪዝም) ዘርፎች የሚሰማሩ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቅሰው፣ የባለሀብቶቹ የኢንቨስትመንት ተቋማት ወደ ሥራ ሲገቡም ከአስር ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል፡፡ ፈቃድ የወሰዱት እነዚህ ፕሮጀክቶች እስከዛሬ ድረስ በከተማዋ የተፈጠሩ የሥራ እድሎችን ያህል የመፍጠር አቅም አላቸው ሲሉም ነው ኃላፊው ያብራሩት፡፡
የመምሪያ ኃላፊው እንዳመለከቱት፤ በበጀት ዓመቱ ፈቃድ ከወሰዱት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው፤ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ፈቃድ ከወሰዱ ባለሀብቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከከተማዋ አምራቾች ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 44 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ባለፈው ዓመት የተገኘው ገቢ አስር ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
መንግሥት፣ በግጭቶችና አለመረጋጋቶች ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ጨምሮ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ ርምጃዎች መካከል በሚያዝያ 2014 ዓ.ም፣ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው፡፡ የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑንም ከዋና ዋና አላማዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህም የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዙ ታምኖበታል፤ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ከተጀመረ አንድ ዓመት የሞላው ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት ተገልጿል፡፡ ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ንቅናቄው በተጀመረበት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በንቅናቄዎች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በዚህም ዘርፉ እንዲነቃቃ አግዟል፡፡ ከ352 በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል፡፡ 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል፡፡ አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጦች በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር መሻሻል ጀምሯል፡፡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይዘውት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል፡፡
ክልሎችም በኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላይ ተመስርተው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄን ተግብረዋል፤ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዳስቻላቸውና በንቅናቄው ትግበራም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ ስለመሆናቸው ክልሎች አስታውቀዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ለኮምቦልቻ ከተማ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ሀብታሙ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹የ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ሀገራዊ ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በኮምቦልቻ ከተማ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፤ ብዙ ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ ለመግባት ጥረት አድርገዋል ሲሉ አቶ ሀብታሙ ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ ሀብታሙ እንዳሉት፤ በንቅናቄው አማካኝነት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ቦርድ በተደረጉ የጋራ ምክክሮች እና ድጋፎች አበዳሪዎችና ማሽን አቅራቢ ድርጅቶች ከአምራቾች ጋር የበለጠ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ ተችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለማሽን ሊዝና ለሥራ ማስኬጃ ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ፈሰስ ሆኗል። ማሽን አቅራቢ ተቋማት ለአምስት ፋብሪካዎች ማሽኖችን እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ማምረት አቁመው ከነበሩ ነባር አምራቾች መካከል አራቱ ወደ ሥራ መመለሳቸውንም የመምሪያ ኃላፊው ይጠቅሳሉ፡፡ አምስት አዳዲስ አምራቾች ማምረት መጀመራቸውን፣ በቀጣይ ይመረቃሉ ተብለው የሚጠበቁ አራት ፕሮጀክቶች ደግሞ የማሽን ተከላ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በመሠረተ ልማት አቅርቦት ረገድም የመንገድ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ያልተመለሱት ፋብሪካዎች አራት ናቸው፡፡ በቀጣይ ከአጋር አካላት ጋር በሚደረጉ ትብብሮች የጥሬ እቃና የብድር አቅርቦት ችግሮቻቸውን በማቃለል ወደ ሥራ እንዲመለሱ ጥረት ይደረጋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችለውን የአሰራር ሥርዓት እየተገበረ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ በዘርፉ የተነቃቃ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡
ይህን ሁሉ ማሳካት የተቻለው በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ባንኮች፣ መሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከኢንቨስተሮች ጋር ባደረጉት የጋራ ቅንጅታዊ ሥራ መሆኑን አቶ ሀብታሙ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ኮምቦልቻ ጦርነቱ ካደረሰባት ውድመት ሙሉ በሙሉ አገግማለች ለማለት ባያስደፍርም፣ የከተማዋ ኢንቨስትመንት ከጦርነቱ ተፅዕኖ እንዲላቀቅና እንዲያገግም በተከናወኑ ተግባራት አማካኝነት አሉታዊ የነበረውን ድባብ መቀየር ተችሏል›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄን ትግበራ አጠናክሮ በማስቀጠል የኮምቦልቻን ኢንቨስትመንት የበለጠ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ይገልፃሉ፡፡
በከተማዋ በሥራ ላይ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም አቶ ሀብታሙ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ባለሀብቶቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድሎችን ከመፍጠራቸው በተጨማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የክልሉን የትምህርትና የጤና ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን እንደሚደግፉም ነው ያስታወቁት፡፡
የከተማ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ቀጣይ ተግባራትንም አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል፡፡ በሳይት ፕላን የተከለለውን 180 ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ ከሦስተኛ ወገን ነፃ በማድረግ ካሳ ከፍሎ ወደ ሥራ ማስገባት፤ የሼድ ግንባታ አጠናቀው የማሽን ተከላ ያልጀመሩ አምራቾችን ወደ ማሽን ተከላ ሥራ እንዲገቡና የሙከራ ምርት እንዲጀምሩ ማድረግ እንዲሁም የከተማውን ነባራዊ የሥራ አጥነት ችግር ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሥራ እድሎች እንዲፈጠሩ መሥራት የ2016 በጀት ዓመት የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊታን ከተማ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ዋና ዋና እቅዶች መሆናቸውን አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2015