የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የመቀሌን ከተማ ጽዱ፣ ውብና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ኢንጂነር አርአያ ግርማይ አስታወቁ፡፡
በመቀሌ ከተማ ከ300 በላይ የሚሆኑ “የጽዱ መቀሌ ፎረም አባላት” ውይይት ትላንት ተካሂዷል፡፡
የከተማው ከንቲባ ኢንጂነር አርአያ ግርማይ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት መቀሌ ከተማ ጽዳቷ የተጠበቀ፣ ውብና አረንጓዴ ከተማ እንደትሆን የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለእዚህም ለከተማው ጽዳትና ውበት ከሴፍቲኔት የተገኘው 86 ሚሊዮን ብር ሥራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በጽዳት፣ በውበትና በአረንጓዴ ልማት የሚሳተፉ ከ10ሺህ በላይ ዜጎች ሥራ መጀመራቸውን ነው ከንቲባው የገለጹት፡፡
“በየዓመቱ ከማዘጋጃ ቤት የሚሰበሰበውን በጀት በማጠናከርና የሰው ኃይል በመመደብ ሥራውን ቀጣይና ከተማዋን ለኑሮና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል” ብለዋል፡፡
“የከተማውን ፅዳት መጠበቅ የህብረተሰቡን ጤና ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል ያስችላል” ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረክርስቶስ ናቸው ፡፡
በሥራው ላይ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግም ነዋሪዎችን በፎረም የማደራጀት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የግልና የመንግት ተቋማት አካባቢቸውን ለማጽዳት የሚያስችል ስርዓትም የተዘረጋ ሲሆን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ ከታህሳስ ወር 2011ዓ.ም ጀምሮ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል፡፡
“በየቤቱ ሄደን በማስተማር የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራዎች እየሰራን እንገኛለን” ያሉት ደግሞ በከተማው አስተዳደር የጽዳትና ውበት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገብረሚካኤል እኑን ናቸው፡፡
በተደጋጋሚ ጥፋት የፈጸሙ ግለሰቦችና ድርጅቶችም በገንዘብ መቅጣትና ተቋማቸውን የማሸግ ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ጤና ቢሮ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ቸርነት በመቀሌ ከተማ ከ460ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል፡፡
የከተማው ነዋሪ ህዝብ እየበዛ ከመምጣት ጋር ተያይዞ በየቀኑ ለሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ከወዲህ ታቅዶ ካልተሰራ ከተማዋን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በየቀኑ ከነዋሪው ህዝብና ከተለያዩ ተቋማት ከ102 ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ እንደሚወጣም አቶ ሙሉጌታ አክለው ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡