ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ለትምህርት ተደራሽነት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካውያን በትብብር የሚሰሩባቸው መንገዶች እየተጠናከሩ የመጡ ይመስላሉ፡፡ ለዚህም ማሳያው ድርጅቶችን ጭምር በማቋቋም በጋራ ጉዳያቸው ላይ አብረው መስራታቸው ነው፡፡ ከዚህም ሻገር ብለው ከዓለም አቀፍ ህብረቶች ወይም ድርጅቶች ጋር ሳይቀር በትብብር ሲሰሩ ይታያል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት ልዩ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ያካሄደው ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (OEC) አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (OEC) የተቋቋመው እ.ኤ.አ ጥር 2020 ሲሆን፤ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ ፓሲፊክ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን እና የአረቡን ዓለም ሀገራት በአባልነት አቅፏል። ድርጅቱ ህልውናውን ያገኘው ደግሞ በጅቡቲ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። የድርጅቱ መተዳደሪያ ቻርተር እንዳሰፈረው፤ የትምህርት ትብብር ድርጅቱ ዓመታዊ በጀቱን የሚያገኘው ከአባል ሀገራት እና ከተባባሪ አባላት ነው። ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች በስጦታ እና በኑዛዜ እንዲሁም በቀጥታ ከመንግሥት፣ ከህዝብ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጥ ርዳታም ሊቀበል እንደሚችል በቻርተሩ ተቀምጧል፡፡

ሆኖም የትምህርት ትብብር ድርጅቱ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እና ከግለሰቦች የሚሰጠው ስጦታ ከአጠቃላይ በጀቱ ከ10 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት በመተዳደሪያው ተደንግጓል። የድርጅቱ ዓላማ ዓለም የትምህርት ዘርፉ በሚዛናዊ ፣ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ሥርዓት ኖሮት እዲሰራ ማድረግ ነው። ትምህርት በእኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና በአጋርነት ላይ ተመስርቶ እንዲሰራም ይፈልጋል። ማንኛውም የትምህርት ልማት በትብብር የሚሰራ መሆን እንዳለበትም ያምናል፡፡ በዚህ የትኩረት አቅጣጫም ድርጅቱ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ የድርጅቱን መተዳደሪያ ቻርተር የፈረመችው በ2013 የካቲት ወር ላይ ሲሆን፤ አሁን ላይ የተቋሙ መስራች አባል እና ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ ሆና እያገለገለች ትገኛለች። በዚህም የዘንድሮውን የመጀመሪያው የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ልዩ ጉባዔ አዘጋጅ ሆናለች፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ የተለያዩ ሀገራት ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮችና የተቋሙ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ወሳኝ የሚባሉ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙት የኮሞሮስ ፕሬዚዳንትና አሁን ላይ የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማሊ እንደ ድርጅት አሁን ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ፍትሃዊነትን መሰረት ያደረገ አካታች የትምህርት ትብብር ማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል። በቀደመው የልማት አካሂድ በተለይም የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት እየገጠማቸው ያለውን አዳዲስ ተግዳሮቶች መፍታት እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከደቡብ ሀገራት የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገ ፍትሃዊና አካታች የልማት መንገድን መከተል እንደሚገባ አስምረዋል። ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በአዲስ ትብብር መፍታት የሚያስችል ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ብዝኃዊነትን ያገናዘበ ፤ ሰው ተኮርና አካታች የልማት መንገድን መከተል ያለብን ጊዜ አሁን ነው›› ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተደምጠዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀገር በቀል እውቀቶችን መጠቀም ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምጣኔ ሀብት የተሻሉ ሥራዎችን እንድናከናውን የሚያግዙን ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አማራጮችን ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ሲሉንም ተናግረዋል፡፡ እነርሱን በመጠቀም ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻልና ይህም የተሻለ የትምህርት ሥርዓት ለመገንባትም እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። ‹‹የጋራ የሆነው ድርጅታችን የምንፈልገውን የትምህርት መንገድ ለመገንባት ያስችለናል፤ እናም ልንጠቀምበት ይገባል›› ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የቀድሞው የድርጅቱ ፕሬዚዳንት፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በጉባዔው ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ድርጅቱ ያስቀመጣቸው ውጥኖች እውን እንዲሆን የባለ ብዙ ወገን ትብብር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ይታመናል፡፡ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድህነትን ጨምሮ እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ትብብር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለሆነም ሁሉም የድርጅቱ አባል ሀገራት ይህንን አምነው በትኩረት ሊሰሩ ይገባል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ ትኩረት ከሚሰጥባቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ በቁርጠኝነትም የምትሰራበት ይሆናል፡፡

የድርጅቱ አባል ሀገራት መንግሥታት፣ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ወጣቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጋምቢያ ያቀረበችውን ጥያቄ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መቀበሉን በጉባዔው ላይ አንስተዋል፡፡ በመቀጠልም የደቡብ ንፍቀ ክበባት ሀገራት ድርጅቱን እዲቀላቀሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥሪ ማቅረቡን ለጉባዔው ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱን መቀላቀል እንደ ታዳጊ ሀገራት ያሉንን ጥቅሞች ለማስከበር ያግዛል፡፡ ሚዛናዊና አካታች ትምህርትን በማስተዋወቅ ተገቢ፣ ትክክለኛ እና የበለጸገ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣትም ያስችላል፡፡ ድርጅቱ ከኃላፊነቱ ጋር የሚጣጣም ስም ከመስጠት አኳያም ‹‹የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት ትብብር ድርጅት›› ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑን በዕለቱ ለታዳሚው ይፋ አድርገዋል፡፡ ድርጅቱ በዚህ ስም መጠራቱ ድርጅቱን ብሎም ዋና ጸሐፊውን ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሀገራትን በስፋት ባሳተፈ መልኩ ስትራቴጂክ እቅዶችንና ፕሮግራሞችን ገቢራዊ እንዲያርግ እንደሚያግዘው ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ያለውን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል የትምህርት ሥርዓቱ ወቅቱን በዋጀ መልኩ መሻሻል እንዳለበት በጉባዔው ላይ የተናገሩት ደግሞ የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (OEC) ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳለም ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ትምህርት ያለውን የመለወጥ አቅም በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻለው የትምህርት ሥርዓቱን ሪፎርም ማሳደግ ሲቻል ነው። የሚፈለገውን የትምህርት ሥርዓት አካታችነት ከሚለው እሳቤ በላይ ማሻገርና ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡

ነገር ግን አካታችነት ውጤታማ የሚሆነው ሰው ተኮር ተራማጅ የማህበራዊ ፖሊሲ ሲኖር ነው። ስለሆነም የትምህርት ሥርዓቱን ይዘትና የትምህርት አሰጣጥ ተሻጋሪ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ዓለምአቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት አካታች፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የትምህርት ሥርዓት እንዲኖር በትኩረት ይሰራል፡፡

ድርጅቱ የተቋቋመበት ዓላማ የሚማረውን ሕዝብ ቁጥር መጨመር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ማንም ሰው ከትምህርት ተገልሎ እንዳይቀር ሥርዓት የሚዘረጋበት ነው፡፡ ስለዚህም ሀገራት ሰው ተኮርና ማህበራዊ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ትምህርት ለውጥ ያመጣል። ትምህርት የልማት መሠረትም ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገራቶቹ በቋንቋ፣ በባህል እንዲሁም በሀገር በቀል ዕውቀት መበልጸግ በብዙ መልኩ ያግዛቸዋል። ዕምቅ ሀብታቸውን እንዲያወጡም ያስችላቸዋል፡፡

የደቡብ ለደቡብ ትብብር ማዕቀፍን ለማጠናከር፣ በትምህርቱ ዘርፍ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት መሠረት ያደረገ አዲስ የባለ ብዙ ወገን ትብብር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የፖሊሲ ውይይቶች እና ክርክሮች የተደረገበት ጉባዔ በሁለተኛው ቀን ውሎው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድንም ዶ/ር አሳትፏል፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ገንቢ ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን፤ በዋናነት ኢትዮጵያና ድርጅቱን በሚያገናኘው ጉዳይ ላይ አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት ትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ዓለምን በበጎ መልኩ ለመቀየር ወሳኝ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ አካታች የሆነ የትምህርት ሥርዓትን በመከተል በዘርፉ ሁሉም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራች ነው፡፡ ሰፊ የሥራ እድል በሚፈጥሩ በፈጠራና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ አበክራ በመስራት ላይ ትገኛለች። በኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ ላይ አካታችነት እንዲረጋገጥ ጥረት እየተደረገም ይገኛል፡፡

በዘርፉ ያለው የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ክፍተት እንዲጠብና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው፡፡ ለአብነት በትምህርት መሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ በአርብቶ አደሩና በከፊል አርብቶ አደሩ በኢመደበኛና በሥልጠና አማራጮች እንዲሁም ጎልማሶች በትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በከፍተኛ ትምህርት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ለትምህርት ተደራሽነት ከተሰጠው ትኩረት አንዱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዓለም እያጋጠማት ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ብዝኃነትን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ የመፍትሄ አማራጮች ያስፈልጋሉ፡፡ የጉባዔው ዓላማ በሀገራቱ መካከል መልከ ብዙ ትብብር ለመፍጠር እንዲሁም ፍትሀዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም መፍጠር በመሆኑ ይህንን እውን ለማድረግ ድንበር ተሻጋሪ ጠንካራ ትብብር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቀደመውን የዓለም የፋይናንስና ልማት አካሄድ ወቅቱን በዋጀ አግባብ መቀየርም ምርጫ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ማመን ይገባል፡፡ በጋራ መቆም ከተቻለ ድንበር ተሻጋሪ የአጋርነትና የትብብር ትስስር መፍጠር ይቻላል። አዳዲስ እድሎችን በመፍጠር በጋራ ለማደግም ያስችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የወቅቱ የዓለም የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት የተቀመጠለትን ዓላማ በሚያሳካና የሃያ አንደኛው ክፍለዘመን እውነቶች በዋጀ መልኩ አዲስ የአስተሳሰብ መንገድ ያስፈልገዋል። የወቅቱን የዓለማችንን ችግሮች የሃያ አንደኛው ክፍለዘመንን መፍትሄ በመከተል በቀላሉ መፍታት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የወቅቱን የዓለም ጸጥታ ፣ ፋይናንስና የኢኮኖሚ መዋቅር በአዲስ አስተሳሰብ መቀየር ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡

የደቡብ ደቡብ ትብብር አማራጭ የልማት መፍትሄዎች ያለው በመሆኑ ሀገራትን አቀራርቦ ይበልጥ እንዲጠናከሩ ያደርጋል፡፡ ትብብሮችን በማጠናከር፣ ልምዶችን በመቀመር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ በደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት መካከል ያለውን ንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር በማጠናከር ያሉ ጠንካራ ጎኖች እንዲሰፉና ችግሮች እንዲፈቱ ያስችላል፡፡ የትብብር ድርጅቱ የዓለምን ትብብር ለማጠናከርም እንዲሁ ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ስለዚህ የደቡብ ደቡብ ትብብርን ለማሳለጥ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንደምትጫወት በጽኑ ታምናለች፡፡ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባልና መቀመጫ ሀገር እንደመሆኗ አዲሱ ድርጅት የተቋቋመበትን ቁልፍ ዓላማ እንዲሳካ በቁርጠኝነት ትሰራለች፡፡

 ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *