ለ80 ዓመታት ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ

 አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት የተቀጣው የጣሊያን ጦር ዳግም ከ40 ዓመት በኋላ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረ። ሁሌም ለነጻነቱ ክንዱ የማይዝለው ጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሁለተኛ ጊዜ ፋሽስት ኢጣሊያን አንገቱን አስደፍቶ ወደ መጣበት መልሷል። ኢትዮጵያም. በጀግኖች አርበኞች ልጆቿ ተጋድሎ ከአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወራራ በኋላ በ1933 ዓ.ም ነጻነቷን አውጃለች።

ሀገሪቱ ነጻነቷን እንዳገኘች በስደት ላይ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዙፋናቸውን እንደተረከቡ ካከናወኗቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራት አንዱ የመገናኛ ብዙኀን ማቋቋምና ማደራጀት ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ መሠረት ንጉሱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ካቋቋሙ ከሁለት ዓመት በኋላ፤ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመውን “ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ” ጋዜጣን አቋቁመዋል። ከአዲስ ዘመን ቀጥሎ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እየታተመ ያለ ብሔራዊ ጋዜጣ ነው።

ከ1950 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮም ከሰኞ በስተቀር በየቀኑ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተም ብቸኛው የሀገሪቱ ጋዜጣ ነው። የጋዜጣው የመጀመሪያ ዋና አዘጋጅ እንግሊዛዊው ጃን ሆይ ሲምፕሰን፤ ሁለተኛው ዊሊያም ኤም. ስቲን እና ሦስተኛው ደግሞ ዴቪድ ኤ- ታልቦት የተባሉ ነጭና ጥቁር አሜሪካዊ ነበሩ። ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ ግን በኢትዮጵያውያን ዋና አዘጋጆች እየተሰናዳ ይገኛል። የሔራልድ አራተኛውና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አዘጋጅ አቶ ያዕቆብ ወልደ ማርያም ናቸው። አሁን ላይ በዋና አዘጋጅነት እያገለገሉ የሚገኙት ደግሞ አቶ ወርቁ በላቸው ናቸው፡፡

ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም 80ኛ ዓመቱን ደፍኗል። ላለፉት ስምንት አስርት ዓመታት ዜና ከመዘገብና የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለውጪው ዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ታሪክን ሰንዷል። በዚህም ተማሪዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደ ምንጭ እየተጠቀሙበት ይገኛል።

ኢትዮጵያን ለቀሪው የዓለም ክፍል ከማስተዋወቅ ባለፈ በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ የውጭ ዜጎችና የኢምባሲ ሠራተኞች ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ነው። በ80 ዓመት ጉዞው በሀገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲያድግ ከማድረጉ ባለፈ፤ የዜጎች የእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲዳብርና በሀገሪቱ የእንግሊዘኛ ቋንቋ አጠቃቀም እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል። በሀገሪቱ አንቱታን ያተረፉ እንደነ በዓሉ ግርማ፣ ተመስገን ገብሬ፣ …ወዘተ የመሳሰሉ ደራሲያንና ጋዜጠኞች ብዕራቸውን አሳርፈውበታል።

ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ በሀገሪቱ በተለያዩ ሥርዓተ መንግሥታት የታዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለዓለም ህዝብ በማብሰር ግንባር ቀደም ነው። በተለይ ከንጉሡ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በሀገሪቱ የታዩ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችንና እንቅስቃሴዎችን ለውጪው ዓለም ዜጎች በማስተዋወቅ የውጪ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲያድግ ከየትኛውም የመገናኛ ብዙሃን በላይ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።

በተመሳሳይ በ2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ፤ መንግሥት እያከናወነ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጡ ለውጦችን ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ ሰፊ ሽፋን ሠጥቶ እየዘገበ ይገኛል። ይህም በቀጣይ ላይ ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ የውጭ አልሚዎች ቁጥር እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው።

በሌላ በኩል ደግሞ ሀገሪቱ በዩኒስኮ ያስመዘገበቻቸውን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን እንዲሁም የህብረተሰሁን ባህል፣ ወግ፣ ትውፊት….ወዘተ ለውጪው ዓለም በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰቱ እዲያድግ ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል። በጥቅሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ ፈርጀ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ማማ የምታደርገውን ጉዞ በዕለቱ እየሰነደ ለቀሪው ዓለም የመረጃ ምንጭ ሆኗል።

የ80 ዓመት ልምድ ያለው አንጋፋው ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ፤ በቀጠናው ውስጥ ካሉ በጣም ታማኝ እና ታዋቂ ከሆኑ ጋዜጦች አንዱ ነው። በዚህም ጋዜጣው ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጠናው የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሽፋን ለተነፈጉ ወገኖች ድምጽ ነው። ማህበራዊ ፍትህ እና እኩልነት እንዲሰፍንም ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል። በሀገሪቱ ብሎም በሰፊው የአፍሪካ አህጉር ያሉ በርካታ ፈተናዎችን እና እድሎችን ለቀሪው ዓለም በማሳየት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት የጭቆና ቀንበር ተላቀው ነጻነታቸውን ከማግኘታቸው በፊት በምስራቅ አፍሪካይቱ የጀግኖቹ ምድር የተወለደው የአፍሪካ ብሎም የመላው ጥቁር ህዝብ ድምጽ የሆነው ዘ ኢትዮጵያ ሄራልድ፤ ቅኝ ግዛትን በመታገል ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል።

ብዙዎቹ በአህጉሪቷ ያሉ ጋዜጦች ደግሞ በቅኝ ገዥዎች የተቋቋሙ ስለሆኑ በቅኝ ግዛት፣ በአፓርታይድ እና ኢምፔሪያሊዝም መንፈስ የተቃኙ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ የቀኝ ገዥዎች ጋዜጦች የአፍሪካዊያን ልብ ይበልጥ የሚያደሙና የሚሰብሩ ነበሩ። ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ ድምጻቸው ለታፈኑ አፍሪካውያን ወንድሞች ድምጽ በመሆን ቅኝ ግዛትን አጥብቆ በመታገል እረገድ ፊታውራሪ ነበር።

በቅኝ ግዛት ሥር ሆነው ድምጻቸው ለታፈኑ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ድምጽ ከመሆን በተጨማሪ ለነጻነት፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት ለሚታገሉ አፍሪካውያን የሚያበረታቱ ጠቃሚና አስተማሪ መረጃዎችን በማድረስ የተስፋ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ጋዜጣው አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ የሚያስችላቸውን አወንታዊ ለውጥ እያመጡ ስለመሆናቸው በዜና ዘገባው፣ በሪፖርቱ እና ትንታኔው በበርካታ መንገዶች በማሳየት ጭቆናን እና ኢፍትሃዊነትን ለማሸነፍ ለሚጥሩ ሕዝቦች በጨለማ ውስጥ የተስፋ ብርሃን እንዲፈነጥቅላቸው አድርጓል። በዚህ ምክንያት ጋዜጣው ሁል ጊዜ ለአፍሪካ ጉዳይ ተሟጋች ነው ይባላል።

በአፍሪካ ምድር ከበቀሉ ጋዜጦች የአፍሪካን የነፃነት እንቅስቃሴዎች በመደገፍ እረገድ የሔራልድን ያህል የሚያኮራ ታሪክ ያለው ሌላ ጋዜጣ የለም። ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ መለስ ብሎ አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች ጥላ  ስር በነበረችበት ወቅት የታተሙ ጋዜጦችን ገልበጥ አድርጎ ማንበብ በቂ ነው።

በአፍሪካ ሀገራት መካከል የአንድነትንና የትብብር መንፈስ እንዲጎለብት ላለፉት ድፍን 80 ዓመታት ሳይታክት ሠርቷል። በዚህም የፓን አፍሪካኒዝም ጽንስ ሀሳቦችንና ንቅናቄዎችን በማራመድ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወይም ለተተኪው የአፍሪካ ህብረት ምስረታ አይተኬ ሚና ተጫውቷል። የፓን አፍሪካኒዝም ጽንስ ሃሳቦችን የሚያጎለብቱ ጠቃሚ ክንውኖችና ጅምር ሥራዎችን፣ ጽሑፎችን፣ ዋና ዋና የፓን አፍሪካ ኮንፈረንሶችን እና ስብሰባዎችንና የመጡትን ውጤቶች በዘገባው በመዳሰስ ለሰፊው የአፍሪካ ህዝብ አድርሷል።

የአፍሪካ ሀገራት ግስጋሴ እና የስኬት ታሪክ እና ውጥኖችን ለማጉላት ሞክሯል። በእነዚህ ታሪኮች ላይ ጠለቅ ያለ ዘገባ በማቅረብ፣ ጋዜጣው የአፍሪካን እድገት፣ ልማት እና የፈጠራ አቅም ለማሳየት ረድቷል። ጋዜጣው ባለው የረጅም ጊዜ ታሪኩ የአፍሪካን አብሮነት አስፈላጊነት እና በአህጉሪቱ የሚገኙ ሀገራት የጋራ ግቦቸውን ለማሳካት መሰባሰብ እንደሚያስፈልጋቸው ያለማቋረጥ በዘገባው አመልክቷል።

በዚህም አህጉሪቱን በሚመለከቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ባቀረበው ዘገባ፣ የአፍሪካን ድምጽ እና አመለካከቶች በማስተዋወቅ በአፍሪካ ህዝቦች እና ሀገራት መካከል የበለጠ መግባባት እና ትብብር እንዲኖር አግዟል። ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ በአፍሪካ ሀገራት መካከል የፖለቲካ አንድነት እንዲኖር ከማበረታታቱ በተጨማሪ ለአፍሪካ ህዳሴ ከፍተኛ ተሟጋች ሆኖ ቆይቷል።

አንጋፋው ጋዜጣ በአንድ በኩል ቅኝ ግዛትን እየታገለ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ ሀገሮች ወደ አንድ ህብረት እንዲመጡና የአፍሪካ ህብረትን እንዲመሠርቱ ታግሏል። ከ80 ዓመታት በፊት ከነበረው አሁን ላይ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ተላቃ አንጻራዊ ነፃነቷን አግኝታለች። ነገር ግን በእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ሥር ወድቃ ትገኛለች። ይህንን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ከመታገል ባለፈ የአፍሪካ አንድነት እንዲጎለብት ዛሬም እየታገለ ይኛል።

የዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ 80ኛ ዓመት በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ከሰሞኑ በተከበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ. በበዓሉ  ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጋዜጣው በ80 ዓመት ዕድሜው ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን አስገኝቷል። የሀገሪቱን እውነት ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ከማድረስ. አንፃር እንዲሁ የጎላ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

ጋዜጣው አንቱ የተባሉ ጸሀፊዎች ያለፉበት ስለሆነ ጋዜጣው ላይ መሥራት ትልቅ እድል እንደሆነ አስታውሰው፤ ያንን የሚመጥን ሥራ መሥራት ይገባል። ስለዚህ ጋዜጠኞች ዛሬ አቅማቸውን አሟጠው በመሥራት ለነገ ማትረፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የድርጅቱ የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ከተማ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ለፍትሕ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነት… በመሥራት ለአፍሪካዊያን በሙሉ ድምጽ መሆን የቻለ ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባትና ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮዎች በአግባቡ እየተወጣ ቆይቷል። በቀጣይም ጋዜጣው የተሸከመውን የኢትዮጵያን ስም የሚመጥን ለማድረግ ዛሬም በሥራ ላይ ነው።፡

ለ12 ዓመታት ያህል በድርጅቱ በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገሉትና አሁን ላይ የዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ ዋና አዘጋጅ አቶ ወርቁ በላቸው በበኩላቸው፤ ጋዜጣው አንባቢዎቹ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት በሚያስችላቸው መጠን ይዘቱን እያሻሻለ መጥቷል። “ለስምንት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ሔራልድ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ሊያውቋቸው የሚችሉ ታሪኮችን ሲዘግብ ቆይቷል። በተለይ ብሔራዊ ሪፎርም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የይዘትና የመረጃ ጥራት ላይ ወደር የለሽ መሻሻሎች ታይቶበታል።

ዋና አዘጋጁ እየታየ ያለውን አስደናቂ ለውጥ በመገንዘብ ታዋቂ ጸሃፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የድርጅት መሪዎች እና መሰል አካላት በዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ እንግዳ ለመሆንና ፅሁፎቻቸውን ለማሳተም ፍላጎታቸው ይበልጥ አድጓል። ከቀደመው በተለየ በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃ የሚፈልግ እና የሚያቀርብ ሚዲያ ሆኗል። ይህ የሚያስመሰግን ውጤት የተመዘገበው አንድ ዓላማ አንግበው በአንድነት ተስማምተው በሚሠሩ በተቋሙ ጠንካራ አመራሮች የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ።

የዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ የአፍሪካ ቀንድ እና የኢትዮጵያን ጉዳይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማሳወቅ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችንና ቱሪስቶችን በማበረታታት ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ውጤት የሚያስገኝ ትክክለኛ መረጃ መስጠቱን እንደቀጠለም አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የስድስት አገራት አምባሳደሮች የዘ ኢትዮጵያ ሔራልድን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2023 እ.ኤ.አ በተዘጋጀው ልዩ ዕትም ላይ ስለጋዜጣው ያላቸውን አስተያየት ጽፈዋል። ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጃው ጂዋን የእንኳን አደረሳችህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አምባሳደሩም፤ የኢትዮጵያ ሔራልድ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አንጋፋ ጋዜጦች አንዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን የተሐድሶና የእድገት ታሪክ ላለፉት 80 ዓመታት. መዝግቧል። ጋዜጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የውጪ አገር ዜጎች ታላቋን አገር እንዲረዱ በር ከመክፈት ባለፈ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓለምን እንዲገነዘብ ወሳኝ መስኮት ሆኖ እያገለገለ ያለ ግንባር ቀደም ጋዜጣ ነው።

በጋዜጣው ስለቻይና የሚነገሩ ታሪኮች ምን ያህል የቻይና መንግሥት ለሀገሪቱ ልማትና እድገት አጋር መሆኑን ለወዳጅ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስገነዝብ ነው። በጥቅሉ ከሰማንያ ዓመታት ጉዞ በኋላ የዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ ልክ እንደንስር አሞራ እራሱን እያደሰ አሁን ላይ አዲስ ምዕራፍ ላይ ቆሟል። በአዲስ ዘመን ብሩህ ተስፋ አዲስ ምዕራፍ እንደሚሰንድ እምነታቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

ሌላው በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃዲር ፌሬራ ዶሳንቶስ በበኩላቸው፤ ላለፉት 80 ዓመታት በተለይ የውጪው ማህበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ የሚያገኝበት ታማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መቀመጫቸውን. ያደረጉ ዲፕሎማቶች ዘ ኢትዮጵያ ሄራልድን ማንበብ የየእለት አስፈላጊ ልምዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

 ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *