የትግራይ ክለቦችን ለመደገፍ 5 መቶ ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታስቧል

ከጥቂት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩትን የትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ለመደገፍ የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጀ። በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ክለቦቹን ለማነቃቃት የሚያስችል 500 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱም ታውቋል።

መቀሌ ሰባ እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ስሁል ሽሪ የእግር ኳስ ክለቦች ከሶስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊና የዋንጫ ተፎካካሪ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከውድድር ርቀው ቆይተዋል። ተሰጥኦ ያላቸውና ጠንካራ ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በማፍራት አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የቆዩት እነዚህ ክለቦች በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት በደረሰባቸው ውድመት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። በመሆኑም ሶስቱን ክለቦች ከመፍረስ ለመታደግና መልሶ ለማቋቋም ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።

መነሻውን በአዲስ አበባ ከተማ የሚያደርገው ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ትናንት በሸራተን አዲስ በተሰጠ መግለጫ ይፋ የተደረገ ሲሆን በመቀሌ ከተማ የሚጠናቀቅ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

‹‹ክለቦቻችንን እንታደግ›› በሚል ሃሳብ የሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በሁለት ወር ውስጥ የሚከናወን ሲሆን፤ 500 ሚሊየን ብር የመሰብሰብ ግብ እንዳለው ተጠቁሟል። ይህንን ገቢ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ኤምባሲዎችና አጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡ ለመሰብሰብ ታስቧል። በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በድረ ገጽ ገንዘብ የሚለግሱበት አማራጭ የተዘረጋ ሲሆን፤ በቅርቡም ለሀገር ውስጥ የስፖርት ቤተሰቡ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካይነት ገቢ የሚገኝበት መንገድ እንደሚመቻችም በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል። በዚህም ከሚገኘው ገቢ እያንዳንዳቸው ክለቦች 30 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚከፋፈሉ ይሆናል።

በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን የነበረው መቀሌ 70 እንደርታ ስፖርት ክለብ በጦርነቱ ምክንያት እጅግ ከተጎዱ ክለቦች መካከል አንዱ ነው። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ሽፈራው ተክለሃይማኖት፤ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርት ክለቦች ተደጓሚ እንደመሆናቸው መሰል ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ከባድ ችግር እንደሚጋፈጡ ጠቅሰዋል። በመሆኑም ሃብት በማሰባሰብ ክለቦችን ከመፍረስ መታደግ የሚቻለው መሰል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት እንደሆነ አስረድተዋል። በትግራይ ያሉ ክለቦች አሁን ላይ ከዜሮ የሚጀምሩ እንደመሆኑ ከመፍረሳቸው በፊት የስፖርት ቤተሰቡ እገዛ እንዲያደርግላቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል በበኩላቸው፤ ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት ክለባቸው በዝግጅት ላይ እንደነበረ አስታውሰው፣ በጦርነቱ ምክንያት ሰለባ ግን ክለቡ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሃብቶቹ እንደወደሙበት ተናግረዋል። በግንባታ ላይ የነበረው የክለቡ ስታዲየም ከመዘረፉም ባለፈ ሁለት አውቶቡሶቹ እንደተቃጠሉም አክለዋል። በመሆኑም ክለቡን መልሶ ለማቋቋም ከክልሉ የስፖርት ቢሮ ጋር መነጋገር ተጀምሯል። የስፖርት ቤተሰቡም ድጎማ በማድረግ የቀድሞውን የእግር ኳስ ስሜት መመለስ እንዲቻል ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላኛው የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊና በጥሩ ፉክክር ላይ የነበረው ስሁል ሽረም በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ካጋጠማቸው ክለቦች መካከል አንዱ ነው። በትግራይ እጅግ ከተጎዱ ከተሞች መካከል አንዱ ሽሬ መሆኑን የክለቡ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተመስገን ገብረሕይወት ጠቁመዋል። ክለቡ ካምፑ እንደተዘረፈበት ገልጸውም ከኢኮኖሚያዊ ችግር ባለፈ በተጫዋቾች እንዲሁም በከተማዋ በሚገኙ ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ የሥነልቦና ድቀት መድረሱን አስታውሰዋል። በመሆኑም ወጣቱን ለማነቃቃትና ከዚህ ሁኔታ ለመመለስ እንዲቻል የስፖርት ቤተሰቡን ጠይቀዋል።

በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት በርካታ መሠረተ ልማት ወድሞ ሕዝቡም በከፍተኛ ችግር ላይ ያለ ቢሆንም ስፖርት ለሰላም፣ ለአንድነትና ለፍቅር ያለውን ማህበራዊ ሚና በመጠቀም ማነቃቃት ከገቢ ማሰባሰቢያው ዓላማዎች መካከል አንዱ ነው። ክለቦቹም ይህንን በመረዳት በበርካታ ጉድለቶች ውስጥ ወደ ስልጠና መግባታቸውን ተጠቁማል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 12/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *