ለኢንቨስትመንት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥረው የካፒታል ገበያ

በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ሚና ካላቸው ግብዓቶች መካከል አንዱ የፋይናንስ አቅርቦት ነው፡፡ የዚህ ወሳኝ ግብዓት አቅርቦት እጥረት ለብዙ ሀገራት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የካፒታል ገበያ (Capital Market) የፋይናንስ እጥረትን ለማቃለል ከሚተገበሩ የመፍትሄ አማራጮች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

የካፒታል ገበያ የገንዘብ ገበያ ሲሆን፣ የሚሸጥ አክሲዮን ያላቸውን ድርጅቶች እና ገንዘብ ያላቸውን አካላት በማገናኘት ሽያጭ እንዲከናወን ያግዛል። ከባንክ ቤቶች ውጪ ተጨማሪ የገንዘብ ዝውውር የሚካሄድበትም ነው፡፡ ገንዘባቸውን ይዘው በሚገኙ (Saving) እና ገንዘባቸውን ሥራ ላይ ባዋሉ (Investment) አካላት መካከል አገናኝ ሆኖ በሚሰራው በዚህ ዘመናዊ ገበያ ውስጥ ሰዎች፣ ኩባንያዎች እና መንግሥት ይሳተፋሉ፡፡

የካፒታል ገበያ ባደገበት ሀገር አምራች ኩባንያዎች የአክስዮን እና የብድር ሠነዶችን በመሸጥ የረዥም ጊዜ እና የአደጋ ሥጋት ያለባቸውን ነገር ግን የምርታማነት ባህሪ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በቀላሉ ፋይናንስ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለህብረተሰቡ አማራጭ የቁጠባ መንገዶችን በማቅረብ ረገድም ቢሆን የካፒታል ገበያ ጠቃሚ ሲሆን፣ ገበያው የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ቁጠባ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህም ኢንቨስትመንት በሀገር ውስጥ የቁጠባ ፋይናንስ እንዲከናወን በማድረግ በውጭ ፋይናንስ ላይ የሚኖርን ጥገኝነት ይቀንሳል፡፡ በዚህ ረገድ ገበያው የሀገርን የክፍያ ሚዛን በማስተካከል ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ይጠቀሳል፡፡ የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን ተወስኖ ውሳኔውን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ እየተተገበሩ የሚገኙ ማሻሻያዎች አካል የሆነው የካፒታል ገበያ ትግበራ ጥቂት የማይባሉ ርምጃዎችን ተራምዷል፡፡ ለአብነት ያህል የካፒታል ገበያ አዋጅ ፀድቋል፤ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተቋቁሟል፤ የባለሥልጣኑ የቦርድ አመራር አባላት ተሹመው ሥራ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡

በካፒታል ገበያ አዋጅ (1248/2013) ላይ እንደተጠቀሰው፣ የካፒታል ገበያው ካፒታል በማሰባሰብ፣ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ እና የኢንቨስትመንት ስጋቶችን የመጋራት አሰራርን በማስፋፋት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት የመደገፍ ዓላማ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የካፒታል ገበያው የሚመራበት አዋጅ የተዘጋጀው ኢንቨስተሮችን ለመጠበቅ እና ገበያው ፍትሃዊ፣ ተአማኒ እና ቀልጣፋ እንዲሆን የሚያስችል የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት ነው፡፡

ገበያውን በበላይነት ለመከታተል እንዲሁም በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ የሚፈጠሩ መዋቅራዊ ስጋቶችን ለመለየት፣ ለመከላከል፣ እና ለመቀነስ በካፒታል ገበያ ላይ ጠንካራ የቅርብ ክትትል እና የቅኝት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እና ከሕዝብ ካፒታል ለመሰብሰብ

 የሚፈልጉ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጭዎች የሚገዙበት ወጥ የሆነ መስፈርት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ቀልጣፋ የካፒታል ገበያ አለመኖር የፋይናንስ ተደራሽነት ውስንነትን ስለሚያስከትል በግል ኩባንያዎች እድገትና ልማት ላይ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል። የካፒታል ገበያ ሲቋቋም የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ስለሚያገለግል የግል ኩባንያዎችን እድገት በማፋጠንም ሆነ የመንግሥትን ገቢ በመጨመር ረገድ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡ ፡ ከዚህ በተጨማሪም የገበያው መቋቋም በዘርፉ ልምድ ያላቸው አካላት ሕጋዊ ድርጅት በመክፈት ድርጅቶችን በተጨማሪ አክሲዮን እንዲሸጡ፤ አዳዲስ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ፤ ግለሰቦች አክሲዮን እንዲገዙ እና እንዲሸጡ የማማከር እና የማከናወን ሥራዎች እንዲጠናከሩ ማድረጉም አይቀርም፡፡

የካፒታል ገበያ አወንታዊ አስተዋፅኦ ከሚያበረክትባቸው የምጣኔ ሀብት ዘርፎች መካከል አንዱ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚያስረዱት፤ የካፒታል ገበያ ለኢንቨስትመንት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የምጣኔ ሀብት ሳይንስና የፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ እንደሚሉት፣ የካፒታል ገበያ ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ ውስጥ ከሚያስቀምጡ ይልቅ አክሲዮን ገዝተው ሥራ እንዲሰሩበት እድል ስለሚሰጥ ተከማችቶ የነበረ ገንዘብ የኢንቨስትመንት ተግባራትን ለማከናወን እንዲውል ለማድረግ ያስችላል፤ በዚህ ሂደት የኢንቨስትመንት እድገት ይመዘገባል፡፡

የካፒታል ገበያዎች ትልልቅ ድርጅቶች ካፒታል እንዲያሰባስቡ ያግዛሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግለሰቦችና ተቋማት ካሉበት ቦታ ሆነው አክሲዮን መግዛት ይችላሉ፡፡ ይህም ሥራውን ዓለም አቀፍ በማድረግ ገበያዎቹ ለምጣኔ ሀብት መሠረት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የካፒታል ገበያ አስፈላጊነት የሚሸጥ አክሲዮን ያላቸውን ድርጅቶች እና ገንዘብ ያላቸውን አካላት በማገናኘት ሽያጭ እንዲከናወን ማገዝ ነው፡፡

‹‹በካፒታል ገበያ፣ ኩባንያዎች ተጨማሪ ካፒታል የሚሰበስቡበት ይህ የገበያ ሥርዓት (Secondary Market) ለኩባንያዎቹ ተጨማሪ ገንዘብ ይፈጥራል፡፡ የኩባንያዎቹ ትርፋማነትም ይጨምራል፡፡ መንግሥት ደግሞ ተጨማሪ ታክስ እንዲሰበስብ እድል ያገኛል፡፡ የእነዚህ ሂደቶች ድምር ውጤት የሚያሳየው የካፒታል ገበያ በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው›› ሲሉ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያብራራሉ፡፡

የካፒታል ገበያ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የተረዱ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ከብዙ ዓመታት በፊት ገበያውን አቋቁመው እየሠሩ እንደሚገኙና በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ማሰባሰብ መቻላቸውን የሚጠቅሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ብትዘገይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም የጀመረቻቸው ተግባራት ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁም የካፒታል ገበያ ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለው ጠቅሰው፣ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይናገራሉ፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ፣ ኢንቨስትመንት፣ ካፒታልን ወደ ሥራ በማስገባት ሀብት የመፍጠር ተግባር በመሆኑ ካፒታል ለኢንቨስትመንት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለኢንቨስትመንት ሲታሰብ ቀዳሚ ትኩረት ከሚያገኙ ግብዓቶች መካከል አንዱ ካፒታል ነው፡፡ ኢንቨስትመንት የሌለበትን የምጣኔ ሀብት እድገት ማሰብ አይቻልም፤ ስለሆነም የካፒታል ገበያ ለምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ ሚና አለው፡፡

‹‹ፋይናንስ ለምጣኔ ሀብት እድገት አንዱ ግብዓት ነው፤ የካፒታል ገበያ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የካፒታል ገበያው ጠንካራ ሲሆን የተሻለ የካፒታል አቅምና ምንጭ ይኖራል፡፡ ስለሆነም የገበያው ማደግ ለአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው›› ይላሉ፡፡

ዶክተር ሞላ እንደሚናገሩት፣ የካፒታል ፍሰትና እንቅስቃሴ ከሌለ ምጣኔ ሀብቱ ጤናማ ነው ተብሎ ስለማይታሰብ ብዙ ሀገራት ለካፒታል ገበያ እድገት ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ይህን ለማድረግ የካፒታል ገበያቸውን ያዋቅራሉ፤ በአግባቡ እንዲመራና ኢኮኖሚው የተሻለ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ፡፡

የካፒታል ገበያው ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሊሟሉ እንደሚገቡም ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የካፒታል ገበያው ውጤታማ እንዲሆን ሊተገበሩ ስለሚገባቸው የአሰራር ሥርዓቶች ሲያስረዱ ‹‹ካፒታል ገበያው መጀመርና መመራት ያለበት አሁን ባለው ሀገራዊ የፋይናንስ ሥርዓት አይደለም፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ መቀየር ይኖርበታል፡፡ የውጭ ባንኮች ተሳታፊ መሆን አለባቸው፡፡›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የምዕራቡ ዓለም በ300 ዓመት ያሳካውን እድገት ቻይናና ቬትናም በአጭር ጊዜ ማሳካት የቻሉት የውጭ ባንኮችንና የካፒታል ገበያን አጣምረው በማሳተፋቸው ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ካፒታል ይዘው ይገባሉ። ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጡ ከባንኮቹ እየተበደሩ አክሲዮን ይገዛሉ፤ አዳዲስ ኩባንያዎችን ያቋቁማሉ፡፡ የካፒታል ገበያ ሲኖር ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ሀገራት ሰዎችም አክሲዮን እየገዙ የኩባንያዎቹ ካፒታል በከፍተኛ ደረጃ ዳብሮ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ መንግሥት ከዚህ ተግባር የሚያገኘው የታክስ ገቢ ለሀገር ልማት ይጠቀማል፡፡

ገበያውን መምራት ያለባቸው ሥራውን የሚያውቁ ባለሙያዎች (የፋይናንስ፣ የገበያ እውቀት ያላቸው) እንጂ የፖለቲካ ሹመኞች ሊሆኑ አይገባም ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡ የሙያው ባለቤት የሆኑ ኢትዮጵያውያን በበቂ ሁኔታ ከሌሉ የውጭ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ማሠራት እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት፡፡ የፋይናንስ ፖሊሲው ግልፅ ሆኖ መቀመጥ እንዳለበትም አስገንዝበው፣ በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮች መጥተው ተዋናይ ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ፖሊሲው ግልፅና ለሀገር ጥቅም የሚያስገኝ መሆን ይኖርበታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም የምታደርገው ጥረት ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው የሚጠቅሱት ዶክተር ሞላ፣ የሚቋቋመው የካፒታል ገበያ ውጤታማ እንዲሆን አሳሪ የሆነውን የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻል እንደሚገባ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ለኢንቨስትመንት እድገት በቂና ጤናማ የሆነ የካፒታል ፍሰት ሊኖር ይገባል፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ማሻሻያዎች ዘርፉን የተሻለ ውጤታማ ለማድረግ ያስችላሉ፡፡ አሁን ባለው አሳሪ የቁጥጥር ሥርዓት የካፒታል ገበያን ለማቋቋም መሞከር ውጤቱን እንደተጠበቀው ላያደርገው ስለሚችል በጥንቃቄ የታጀበ አሰራር ያስፈልጋል፡፡›› ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህም ለሥራው የሚያስፈልጉ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ያሉትን ማጠናከር እንዲሁም ተቋማዊ አደረጃጃቶችን ማዘጋጀትና ማዘመን ይገባል፡፡ ገበያውን ሀገር ውስጥ ብቻ ባሉ የገንዘብ ምንጮች ማንቀሳቀስ አስቸጋሪ ስለሚሆን የገበያውን ተሳታፊዎች ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ከግምት ውስጥ ያስገቡ አሠራረሮችን መተግበርም ያስፈልጋል። ገበያው የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ፣ መንግሥት ወሳኝ የአስተዳደር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል፡፡

ለኢንቨስትመንት ተግባራት ከሚያስፈልጉ ዋና ዋና ግብዓቶች መካከል አንዱ የሆነውን የፋይናንስ አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የካፒታል ገበያን በአማራጭነት መጠቀም በብዙ ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነና በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም የሚመከር ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የካፒታል ገበያ የማቋቋም ተግባር ውጤታማ ለማድረግ ኢ-መደበኛ ኢኮኖሚውን ወደ መደበኛ ማሸጋገር፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማትን አሠራር ማስተካከል፣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን መቃኘት፣ የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ማድረግ እና ለኢንቨስተሮች በቂ ዋስትና መስጠት ይገባል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *