በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፤ ሌሎች እየተገነቡም ይገኛሉ። ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን ገጽታ እንደሚገነቡ፣ የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ችግሮች እንደሚፈቱ፣ ተጨማሪ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ እየተገለጸ ነው። ከፕሮጀክቶቹ መካከልም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 16 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለምረቃ በቅተዋል።
በፕሮጀክቶቹ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሀዋሳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊና የማስፈጽም አቅም ግንባታ እንዲሁም የአካባቢ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ እንዳሉት፤ በከተማዋ የተሠሩ ፕሮጀክቶች በርካታና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ፕሮጀክቶቹ ለከተማዋ ገጽታ ግንባታ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦም የላቀ ነው። የከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 16 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ማስመረቅ ችሏል። ሌሎች በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ።
ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል የታቦር ተራራ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ እንደ ከተማ፣ እንደ ሀገርና እንደ ክልል ትልቅ ትርጉም ያለውና የቱሪስትን ፍሰት ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ታምኖበታል። ፕሮጀክቱ በ57 ሚሊዮን ብር የዛሬ ዓመት በአንድ ዓመት እንዲጠናቀቅ ውል ተገብቶ እየተሠራ ያለ ሲሆን፤ ሥራው የተጀመረውም የዛሬ ዓመት ሰኔ ወር ነበር። በአሁኑ ወቅትም ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል። ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል።
አቶ ታሪኩ የፕሮጀክቱን ዲዛይን በሚመለከትም በፕሮጀክቱ ላይ ሁለት እርግቦች አገጭ ለአገጭ ተገጫጭተው የሚታዩበትና የመግቢያ በር ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል። ውስጡ እስከ 50 ሜትር የሚደርስ ሽቅብ የሚወር ፋውንቴን ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ የዓባይ ግድብንም ማስታወስ እንዲችል ተደርጎ ዲዛይን መደረጉ ልዩ ያደርገዋል።
ሁለት እርግቦች አገጭ ለአገጭ ተገጫጭተው የሚሳየው ዲዛይን በሲዳማ ብሄረሰብ ዘንድ ሴትና ወንድ አገጭ ለአገጭ ተገጫችተው የሚጨፍሩበትን ሁኔታ ያመለክታል፤ የሲዳምኛ ባህላዊ ጭፈራንም ያሳያል ይላሉ።
ዲዛይኑ እርግብ የሰላም ምልክት እንደመሆኗ ሀዋሳ ከተማም የሰላም ከተማ መሆኗን ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል። ከመግቢያ በሩ ጀምሮ እስከ ፋውንቴኑ ጫፍ ድረስ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ በሁለቱም አቅጣጫ 130 የሚጠጉ ደረጃዎች እንደተገነቡለትም ተናግረዋል። ይህም የሲዳማ ብሔረሰብ የ130 ዓመት የመብት ጥያቄና የትግል ጉዞን እንደሚያመለክት ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ወደ ተራራው ከፍ ሲባል እስከ ተራራው ጫፍ ድረስ የሚጠጉ ዳይመንዶች እንደተደረጉለት ያነሱት አቶ ታሪኩ፤ የዳይመንዶቹ ዲዛይን ሀዋሳ ከተማ በሀገሪቱ ካሉ ከተሞች መካከል በጣም የምትወደድ ከተማ መሆኗን ለማሳየት የተቀመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። በየዳይመንዶቹ የተለያዩ ቦታዎች አሉ። በቦታዎቹም ሼዶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፣ ሰዎች በዚያ አረፍ ብለው ሊዝናኑና አረፍ ሊሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ሼዶቹ ሌሎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉባቸውና ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል የተፈጠረባቸው የገበያ ቦታዎች እንደሆኑ አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ በምዕራፍ ተከፋፍሎ እንደሚሰራ ኃላፊው ጠቅሰው፣ አሁን ላይ የተጠናቀቀው ምዕራፍ አንድ መሆኑን ይገልጻሉ፤ በምዕራፍ ሁለትም እንዲሁ የተለያዩ አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ መስጠት የሚያስችሉ እንደ አምፊ ቲያትር፣ የስብሰባ አዳራሾችና ሎጆች የመሳሰሉት ተቋማት ዲዛይን እየተሰራ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ሀዋሳ ከተማ በፕላን መመራቷ ከሌሎች ከተሞች ለየት ያደርጋታል የሚሉት አቶ ታሪኩ፤ ከጥቁር ውሃ ጫፍ ጀምሮ ሚሊኒየም ፓርክ፣ ከሚሊኒየም ፓርክ ፍቅር ሐይቅ፣ ከፍቅር ሐይቅ አሞራ ገድል ከአሞራ ገደል ታቦር ተራራ እንደሚገኝም ይጠቁማሉ። በፕላን ደረጃ እነዚህ ኢኮቱሪዝም በመባል የተለዩ አካባቢዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል። በከተማዋ እየተሠሩ ያሉት ፕሮጀክቶች እርስ በእርስ የተሳሰሩና የኢኮ ቱሪዝም ግቦችን በእጅጉ የሚሳልጡ ናቸው ብለዋል።
ሌላኛው ፕሮጀክት የሚሊኒየም ፓርክ አካባቢ ፕሮጀክት ነው፤ የአንድ ዓመት ጊዜ የተመደበለትና 90 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት የተሠራ ፕሮጀክት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታሪኩ፣ ፕሮጀክቱ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን የያዘ ስለመሆኑም አስረድተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አንደኛው የሲዳማ ባህላዊ እሴቶችን በዲዛይኑ በማሳየት ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ የሚቀበልበትን ባህል የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው። ሁለተኛው ዘመኑ የደረሰባቸው ዘመናዊ ካሜራዎችና ኤልዲስክሪኖች የተገጠመለት ዲጂታል የማስታወቂያ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ ነው። ይህም ዘመናዊ በሆነ መልኩ ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍ አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ በስፍራው የተገጠሙት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የከተማዋን ገጽታ በመገንባት አይነተኛ ድርሻ አላቸው፤ ለከተማዋም ሆነ ለነዋሪዎች ገቢ በማመንጨትም የጎላ አበርክቶ ይኖራቸዋል ያሉት አቶ ታሪኩ፤ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምርታቸውንና ተቋማቸውን የሚያስተዋውቁባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል። በዚሁ ልክ ከተማዋ ገቢ ማመንጨት የምትችልበት ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ነው ያስረዱት።
አቶ ታሪኩ እንዳሉት፤ የፕሮጀክቱን ዲዛይን በሚመለከት በመግቢያው በሩ አካባቢ የሲዳማ ባህላዊ ቤት ተካቷል። አንዱ ጎጆ ቤት ለሁለት ተከፍሎ እንዲታይ ነው የተደረገው፤ ይህም የሲዳማ ሕዝብ ቤቱን ከፍቶ፣ በሩን ከፍቶና እጁን ዘርግቶ ሁሉንም ‹‹ዳኤ ቡሹ›› በማለት የሚቀበል ሕዝብ መሆኑን ያመለክታል። እነዚህን ለሁለት የተከፈሉ የሲዳማ ባህላዊ ጎጆ ክፋዮች ቤቶችን የሚያገናኝ ድልድይም ተገንብቶላቸዋል። ከአዲስ አበባ ሀዋሳ የሚወሰደው መንገድ በድልድዩ ስር እንዲያልፍ ተደርጓል። በአስፓልቱ መሀል ድልድዩ ላይ በሲዳማ ባህላዊ አመጋገብ ወቅት ለመመገቢያ የሚውለውን ‹‹ሻፌታ›› በመባል የሚታወቀው ቁስ ይታያል። ማህበረሰቡ በድልድዩ ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማከናወን እንዲሁም የሀዋሳ ሀይቅን ከፍ ብሎ ለመመልከት እንዲያስችል ተደርጎም ነው ድልድዩ የተገነባው።
በዚህ መግቢያ በር ላይ 12 የሚጠጉ ካሜራዎች ተገጥመውለታል፤ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የሰሌዳ ቁጥር ጭምር ለይቶ የሚሳይና መረጃ መስጠት የሚችል እጅግ ዘመናዊ እንደሆነም አቶ ታሪኩ ያብራሩት። ካሜራዎቹ አንዳንድ የተጠረጠሩና የሰሌዳ ቁጥራቸው የተያዘ ተሽከርካሪዎች በድልድዩ ስር ሲያልፉ መረጃ መስጠት የሚችሉና እጅግ ዘመናዊ ናቸው።
በድልድዩ አካባቢ ዙሪያውን ሼዶች መገንባታቸውንም ጠቅሰው፣ ይህም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፤ ከዚህ ባሻገር ለከተማው ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ ማገልገል እንደሚችልም ይገልጻሉ።
የመግቢያ በሩ አሁን ባለበት ደረጃ በርካቶች እየተዝናኑበት እንደሆነ ያነሱት አቶ ታሪኩ፤ ለከተማዋና ለክልሉ እንዲሁም በአካባቢው ለተገኙ ኅብረተሰቦች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በሀዋሳ ከተማ የተሠራው ይህ የመግቢያ በር ከሀገራችን አንጻር ሲታይ እጅግ በተሻለ መንገድ የተገነባና ለሌሎች ከተሞች ትልቅ ተሞክሮ መሆን እንደሚችልም እምነታቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ሁለቱም ፕሮጀክቶች በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ታሪኩ፤ የታቦር ተራራ ሰዎች መኪናቸውን አቁመው ወደ ተራራው ጫፍ መጓዝ የሚችሉበት ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሮጀክቱን ዲዛይን ያደረጉት ብዙ ልምድ ያላቸውና በሀገሪቱ አለ የተባለ አማካሪ ድርጅት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ በየጊዜው የጥራት ደረጃው እየተገመገመ ከመሥሪያ ግብዓት ጀምሮ እየተፈተሸ መሆኑንም አብራርተዋል፤ እስካሁን የጥራት ችግር እንዳልተነሳበትም ጠቅሰው፣ በተቻለ አቅም በከፍተኛ ጥራት እየተሠራ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
አቶ ታሪኩ እንዳሉት፤ የጥቁር ውሃ ሚሊኒየም ፕሮጀክት 90 ሚሊዮን ብር ውል የተያዘለት ነው። እስካሁን 80 ሚሊዮን ብር ለፕሮጀክቱ ወጪ ተደርጓል። አጠቃላይ ፕሮጀክቱ አንዳንድ የታጠፉ ሥራዎች ያሉት በመሆኑ ከተያዘለት በጀት ባነሰ ሊጠናቀቅ ይችላል። በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በወቅቱ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል።
የታቦር ተራራ ልማት ፕሮጀክት በበኩሉ 57 ሚሊዮን ብር ወጪ ውል የተገባለት ነው፤ አሁን ከተማዋ ከደረሰችበት ደረጃ አንጻር ተጨማሪ ሥራዎች ተጨምረውለታል፤ ከተያዘለት በጀት በተጨማሪ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ሊያስጨምርም ይችላል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ባለመሆኑ በቀጣይ ርክክብ ለማድረግ ከመደበኛው ጊዜ በተጨማሪ እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ እየተሠራ ይገኛል። የሁለቱ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ የተገኘው ከተሞችን ከሚደግፈው የከተማ መሰረተ ልማትና ተቋማት ልማት ተቋም /ከዩ አይ አይ ዲ ፒ/ መሆኑም ተጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪ በሀዋሳ ከተማ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ እየተሰሩ ያሉ በርካታ የልማት ሥራዎች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ታሪኩ፤ ከእነዚህም መካከል የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንደሚገኙበት ይጠቅሳሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ48 ሺ ካሬ ሜትር በላይ የሆኑ የተለያዩ አካባቢዎችን ማልማት ተችሏል። በዚህም በከተማ አስተዳደሩ በተለይ አሮጌ መናኸሪያ እና አቶቴ ተብለው የሚጠሩ አካባቢዎችን እንዲለሙ ተደርገዋል፤ ከዚህ ቀደም ሕገወጥ በሆነ መልኩ የተለያዩ ሼዶች ዘርግተው እንዲሁም የእግረኛ መንገዶችን ዘግተው ሲጠቀሙ የነበሩን በማንሳት ነው ይህ የልማት ሥራ የተሰራው። በዚህም እስከ ሰባት ሄክታር የሚደርስ ወይም 71 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ማጽዳት መቻሉን አስታውቀዋል።
አካባቢውን የማጽዳት ሥራ ከተሠራ በኋላ የማልማት ሥራው በትኩረት የተሠራ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ታሪኩ፤ ሁለቱም ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ነው የተናገሩት። አሮጌ መናኸሪያ አካባቢ ያለው ከሳውዝ ስታር እስከ ዋንዛ አደባባይ ድረስ ያለው የልማት ሥራ ከአራት ወራት በፊት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። ከዚህ ልማት የተሻለ ልምድ በመውሰድ አቶቴ አካባቢ የተጀመረው ሥራም እንዲሁ 97 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል። የዚህ ልማት የቀረው ሥራ የቀለምና የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ ታሪኩ ከዚሁ ጎን ለጎን ፒያሳ አካባቢ በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከባንኮችና ከግለሰቦች ጋር በመተባበር በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። አጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአረንጓዴ ልማት ብቻ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚወጡ ተግባራት በኅብረተሰብ ተሳትፎ መሠራታቸውን ተናግረዋል።
በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎችና መንደሮቹ የአካባቢ ፖሊስ ጣቢያዎች በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሠሩ ስለመሆናቸውም አቶ ታሪኩ ገልጸዋል። ይህም የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ያለው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ የፍሳሽ ማስወገጃና ሌሎችም ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ ይህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ አጠቃላይ አምስት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ካፒታል በጀት ተመድቦ ሲሰራ የቆየ ነው። ከተሠሩት ሥራዎች መካከልም የመንገድ መብራት፣ የትራፊክ መብራቶች፣ የታክሲ ተርሚናልና በተለያዩ አካባቢዎች ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሼዶች ግንባታ ይገኙበታል።
አጠቃላይ በሀዋሳ ከተማ እየተሰሩ ያሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ ፕሮጀክቶች ለማህበረሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታሪኩ፤ ለአብነትም የኮብልስቶን መንገድን ግንባታን ጠቅሰዋል። የተገነባው 15 ሎት ያለው የኮብልስቶን መንገድ ለየአካባቢው ማኅበረሰብ ምቹ መሠረተ ልማት ያስገኘ መሆኑን ተናግረው፣ ማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቱን ማቀላጠፍ እንዲችል ማድረጉን ገልጸዋል። ሌሎች በርካታ የልማት ሥራዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በዚህ ሁሉ ሥራ ከዚህ ቀደም የንግድ ሥራ ምቹ ያልነበሩ አካባቢዎች ለንግድ ሥራ አመቺ የሆኑበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። የእግረኛ መንገድ ያልነበራቸው የእግረኛ መንገድ እንዲኖራቸው የተደረጉ በርካታ ቦታዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ ለማኅበረሰቡ እያበረከቱ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት በተጨማሪ፣ የዜጎችን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻርም ሰፊ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል። ትላልቆቹ ፕሮጀክቶች ለከተማውና እንደ ሀገርም ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን እንደሚችሉና የቱሪዝምን ፍሰቱን በመጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አመላክተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015