‹‹የሀርመኒ ሂልስ አካዳሚ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ብቻ ሳትሆኑ ሁላችንም ልጆች እንኳን ደስ ያለን። ወላጆች፤ መምህራን፤ የትምህርቱ ማኅበረሰብ በሙሉም እንኳን ደስ ያላችሁ! ኢትዮጵያ እንኳን ደስ ያለሽ፤ አህጉራችን አፍሪካም የደስታችን ተጋሪ በመሆንሽ እኛ ልጆችሽ እጅግ ደስ ብሎናል። ሰላም ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ! ወላጆችና የትምህርት ማኅበረሰቡስ እንዴት ናችሁ?›› ምን ተገኘና ነው፤ ማነውስ ይሄን የሚለን አላችሁ አይደል? የሀርመኒ ሂልስ አካዳሚ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ዳግም ማህደር ነው።
ዳግም ሀገሩንና ትምህርት ቤቱን ወክሎ በአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ በመመዝገቡ እጅግ ደስ ብሎታል። ዳግም የደረጃ ተማሪ በመሆኑ ብዙ መጽሐፍት ተሸልሟል። ከተሸለማቸው መጽሐፍት መካከል የእንግሊዝኛና ስለስፔስ ሳይንስን የሚያጠና መጽሐፍት ይገኝበታል።
ልጆች ዳግም መጽሐፉን አንብቦ ሲጨርስ ወደፊት ጠፈርተኛ መሆን እንዲፈልግ አድርጎታል። በዚህም አሁን ድረስ ትምህርት ቤቱ ይሄን ፍላጎቱን የሚያሳካበት መጽሐፍት ያቀርብለታል። ለዚሁ የሚረዳው ፊልም እንዲያይም ያደርገዋል።
ሌላው ትምህርት ቤቱን በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ያደረገው ነገር የየራሳቸው የወደፊት ራዕይ ያላቸው ልጆችን ማፍራቱ ነው። ሀገራቸውን በጣም ይወዳሉ፤ ስለእሷም ይዘምራሉ። ደግምን ያገኘነውም ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ ድንቃድንቅ መመዝገቡን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የመዝሙር ሥነሥርዓት ላይ ነው። መዝሙሩ ሁላችሁም የምትወዱትና ሁልጊዜ የምትዘምሩት “ፀሐዬ ደመቀች“ የተሰኘው ነው።
ይሄ መዝሙር የኢትዮጵያ ልጆች ብሔራዊ መዝሙር ነበር ይባላል። ይህንን የነገረችን ማን መሰለቻችሁ ተማሪ ሀኒ ደሳለኝ ነች። የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፤ የአርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ድርሰት ነው ብላናለች። እሷን ጨምሮ መዝሙሩ በዕለቱ በብዙ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በመዘመሩ እጅግ ደስተኛ ሆናለች። በአፍሪካ ድንቃድንቅ ሊመዘገብ በመብቃቱም ተገርማለች። መዝሙሩን ከዚህ ቀደምም በጋራ ይዘምሩታል፤ ከዚህ በኋላም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ነግራናለች።
ትምህርት ቤቱ እርግቢቱ ሂጂ፤ እማማ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በርካታ የሕፃናት መዝሙሮችን ተማሪዎች እንዲያውቁና እንዲዘምሯቸው ያደርጋል። ሀኒ ሁሉንም መዝሙሮች ትችላቸዋለች። በዚህ ደግሞ ሁለቱንም ዓመት አንደኛ በመውጣቷ ብቻ ሳይሆን መዝሙሩን ሙሉውን መዘመር በመቻሏም ተሸልማለች። ያለማመዷት መምህራኖቿ ናቸው። ሀርመኒ ሂልስ ትምህርት ቤት የተሟላ ቤተ ሙከራ፤ ቤተ መጽሐፍትና ለእነሱ ተስማሚ የሆነ ቦታ ላይ መገንባቱም በድንቃድንቅ እንዲመዘገብ አስችሎታል ብላናለች።
ሀኒ የዛሬ 40 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መዝሙሩን ከዘመሩት ጋር አብራ መዘመር በመቻሏ ደስ ብሏታል፤ የዚህ ታሪክ አካል በመሆኗ ኩራት ይሰማታል። አድጋ እነሱ ዕድሜ ላይ መድረስና እንደነሱ ከቀጣይ ትውልድ ህፃናት ጋር መዘመርም ተመኛለች።
የሀርመኒ ሂልስ አካዳሚ ዳይሬክተር ወገኔ ይርጋ በበኩሉ ‹‹ፀሐዬ ደመቀች›› መዝሙርን በልጅነቱ በአባቱ ሬዲዮ የዘመረው መሆኑን አስታውሶ ነግሮናል። እንደ እሱ ሁሉ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መዝሙሩን እንዲችሉ የትምህርት ቤቱ መምህራን እንዲያለማምዷቸው አድር ጓል። በጋራ ዘምረው መዝሙሩን በአፍሪካ ድንቃድንቅ ላይ በልጆች ብሔራዊ መዝሙርነት እንዲመዘገብ ያደረጉትም ለዚህ ነው። መዝሙሩ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ጭምር በመሆኑም እጅግ ደስ ብሎታል።
መምህርት ሩት መንበረና መምህር አዱኛ አንበሉ የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ናቸው። እነርሱ እንዳሉን፤ እንዲህ ዓይነት ጎበዝ ተማሪዎች ያለው ትምህርት ቤት በመክፈታችን ደስተኛ ነን። ከሁሉም በላይ ግን ያስደሰተን ሀገራዊ እሴት ያላቸው መዝሙሮችን እንዲያውቁና እንዲዘምሩ በማድረጋችን ባለታሪኮች መሆናችን ነው። ተማሪዎቹን ከትምህርት ቤቱ አልፈው ሀገራቸውንና አፍሪካን ማስጠራት እንዲችሉ አድርገናልና።
የዳግም ማህደር ወላጅ ወይዘሮ የምስራች ሙሉጌታን በበኩላቸው እንዲህ ይላሉ። ‹‹ሀርመኒ ሂልስ አብሮነትን፤ ሕብረትን፤ ሥራን የሚያበረታታና ለሥራ የሚያነሳሳ ስያሜን በልጆች ላይ የሚፈጥር ነው። ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ይህንን ዓይነት ሥራ ቢሠሩ መልካም ነው።››
አሸናፊ ዓለም የአፍሪካ ድንቃድንቅ መዝገብ ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ልጆች ያሉበትን ዘመንና ሀገራቸውን እንዲወዱ ከታች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ መሠራት አለበት። ማንነታቸውን በደንብ አድርገው ማወቅ ይገባቸዋል። ስለሀገራቸው እንዲናገሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሉም የወደፊት ራዕይ ኖሯቸው እንዲማሩ ማበርታትም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ቀጥሎ ትልቁን ስፍራ የሚይዙት ትምህርት ቤቶች ናቸው። ሀርመኒ ሂልስ ትምህርት ቤት ደግሞ በዚህ የተሳካለት ሆኗል። በአፍሪካ ድንቃ ድንቅ ኢትዮጵያን ወክሎ እንዲመዘገብ አድርጎታል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም