አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ አይደለችም፤ የአፍሪካ ዋና መዲና፣ የበርካታ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ኤምባሲዎችና የዲፕሎማቶች መናኸሪያም ናት። ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች በስፋት ይካሄዱባታል።በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች እና የተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ሕዝብ የሚጎርፍባት እንግዳ ተቀባይም ናት።
ወደ ከተማዋ ከሚመጡት መካከል ለጉብኝት የሚመጡት በርካታ ናቸው።ለተለያዩ ጉዳዮች መጥተው በከተማዋ ቆይታ የሚያደርጉትም እንዲሁ በርካታ ናቸው። በእዚህና በመሳሰሉት በከተማዋ ከፍተኛ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይደረጋል። የከተማዋ የቱሪዝም መስህቦችና መዳረሻዎች ይጎበኛሉ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም የተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶች ይሰጣሉ።ይህን ተከትሎም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ ይደረጋል፡፡
በከተማዋ ያሉት በርካታ ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችና መስህቦች እንዳሉ ሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግስት የቱሪስት መዳረሻዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እያለማ ይገኛል።ከዚህ አኳያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡት በርካታ የመስህብ ሥፍራዎች የተካተቱበት አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ እና እንጦጦ ፓርክ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው።በዚህ ላይ ሳይንስ ሙዚየምና አብርሆት ቤተመጻሕፍት ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች መሆን ችለዋል። እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች ከቱሪስት መዳረሻነታቸው ባሻገር የከተማዋን ገጽታ የሚገነቡ እና የቱሪስት ፋሰቱ እንዲጨምር አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው።
ከዚህ ባሻገር ከተማዋ 20 የሚሆኑ ሙዚየሞች፣ 20 የሚሆኑ ፓርኮች፣ የአደባባይ ሐውልቶች፣ ባህላዊ ቦታዎች፣ ትላልቅ ገበያ ቦታዎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች እና የመሳሰሉት በርካታ የቱሪዝም መስህቦችና መድረሻዎች ባለቤትም ናት።ከእነዚህ በተጨማሪ መዲናዋን የኮንፍረንስ ማዕከል (የማይስ ቱሪዝም ሴንተር) ለማድረግም እየተሰራ ነው። ይህን ሁሉ የሚሸከሙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስፋፋትና ለማልማት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የባህል የአዲስ አበባ ከተማ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
የቢሮው የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ዓይናቸው አዲስ አበባን አፍሪካ ውስጥ ካሉ አምስት ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ ከተሞች አንዷ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ አንድነት ፓርክ አይነቶቹ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆኗ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ተናግረዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከተማዋ በየጊዜው በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች የምታስተናግድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ ይጎርፋሉ። የከተማዋ የቱሪዝም መስዕቦች ለመጎብኘትም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተማ የሚመጡት የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።በ2015 በጀት ዓመት በርካታ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ በመምጣት የቱሪስት መስህቦችንና መዳረሻ ቦታዎች ምን ጎብኝተዋል ይላሉ።
በአንጻራዊነት የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ የተረጋጋ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሳምሶን፣ በከተማዋ ውስጥ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችና የኮንፈረንስ ቱሪዝም እየተስፋፉ መምጣታቸውን ይገልጻሉ። ወደ ከተማ የሚመጡት የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያትም ይሄው እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የከተማዋን የቱሪስት መድረሻዎች ይጎበኛሉ ተብለው በእቅድ የተያዙት የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ብዛት በ580ሺ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ነበር፤ የከተማዋ የቱሪስት መዳረሻዎች ግን በ622 ሺ 702 የውጭ ቱሪስቶች ተጎብኝተዋል።ይህም ለኮንፍረንሶች፣ ለኢግዚቢሽኖች፣ ለአውደ ርዕዮች እና በሌሎች ሁነቶችና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ከተማ የመጡትን የውጭ ቱሪስቶች ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከውጭ ሀገር ቱሪስቶች 30 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ለማግኘት
ታቅዶ፤ 39 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ እንዲሆን ተደርጓል። ገንዘቡ ወደ ተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ፈሰስ የሆነ ነው፤ ይህም ጫማ የሚያጸዳውን ጨምሮ የቱሪስት ታክሲ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የሆቴል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ሙዚየም፣ ፓርክና የመሳሰሉት አገልግሎት ሰጪዎች የተሰራጨ ነው።
የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ፋሰትን ስንመለከት ወደ ከተማዋ መጥተው የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ታቅዶ የነበረው አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንደነበሩ አስታወሰው፤ ሰባት ሚሊዮን 353ሺ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በከተማ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችንና .መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል ብለዋል። እነዚህ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡበት ምክንያት የቱሪስት መድረሻዎችን ብቻ ለመጎብኘት አቅደው እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ ለዘመድ ጥየቃ፣ ለመዝናናት፣ ለስብሰባ፣ ለህክምና እና ለመሳሰሉት ጉዳዮች የመጡትንም እንደሚጨምር ያስረዳሉ።
እስካሁን ባለው ሂደት ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚገኘውን ገቢ ማስላት አልተጀመረም የሚሉት አቶ ሳምሶን፤ ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ በከተማው ውስጥ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቆይታ ምን ያህል ቀን ሊሆን ይችላል፤ አንድ የሀገር ውስጥ ቱሪስት በቆይታው ምን ያህል ወጪ ሊያወጣ ይችላል የሚለውን ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ለማስላት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በቀጣይ ግን በፌዴራል ደረጃ ‹‹ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት›› የሚባል ሶፍት ዌር እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሶፍትዌሩ በመታገዝ ከተማዋን ለመጎብኘት የመጣውን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስት ቁጥር እንዲሁም የተገኘውን ገቢ፣ በቱሪዝሙ የተፈጠረውን የሥራ እድልና ተያያዥ ጉዳዮች ትክክለኛ መረጃ የሚወሰድበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸዋል። የነጠረ ዳታ ማግኘት የሚያስችል አሠራር እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
የቱሪስት ፋሰቱን ከባለፈው አመት ጋር ስናነጻጽረው ከቱሪስቱ ቁጥርም ሆነ ፈሰስ ከሚደረገው ገንዘብ አንጻር ጭማሪ አሳይቷል የሚሉት አቶ ሳምሶን፤ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ከተማዋ የሚገቡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥርና ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት 500ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ ይገባሉ ተብሎ ታቅዶ 570 ሺህ 556 ያህሉ ወደ ከተማዋ መግባታቸውንም አስታውሰዋል። ከዚህም 34 ነጥብ 03 ቢሊዮን ብር ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ መደረጉን አመላክተዋል።
አቶ ሳምሶን እንዳሉት፤ ከእቅድ አንጻር ከውጭ ቱሪስቶች የተገኘው ገቢ በአፈጻጸም ከእቅድ በላይ ነው፤ ገቢው የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ፣ የቀን ወጪውን፣ ዕለታዊ የውጭ ምንዛሪውንና የቱሪስቱን ቁጥር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማስላት የተገኘ ነው። ለምሳሌ አንድ ቱሪስት ከተማዋ ላይ ሊኖረው የሚችለው የቆይታ ጊዜያት 5 ቀናት ቢሆን፤ በአምስት ቀናት ውስጥ በቀን የሚያወጣው ወጪ ምን ያህል ነው ተብሎ ሲሰላ በሳይንሳዊ ስሌት 234 ዶላር ያወጣል ተብሎ ይታሰባል።ይህ ዶላር ወደ ወቅቱ ምንዛሪ ይለወጣል፤ ከዚያ በቱሪስቱ ቁጥር በማብዛትና በማስላት የሚገኝ የገቢ መጠን ገቢ ተብሎ ይወሰዳል።
አቶ ሳምሶን፤ በከተማዋ ያሉትን የቱሪዝም መስህቦችና መዳረሻዎችን ለማልማት ለቱሪስቶች ምቹ እንዲሆኑ የተወሰኑ እሴቶች ከማሟላት አንጻርና አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን በመገንባት ረገድ በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በከተማዋ የቱሪስቱን ቆይታ ሊያራዝሙ የሚችሉ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ለይቶ የማልማት ሥራ መጀመሩን ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ከማልማት አንጻር የተከናወነው ተግባር የኒልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም (የኒልሰን ማንዴላ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክት) አንዱ እንደሆነ ነው።የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ታጋይ እንደሆኑ የሚታወቁት ኒልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱበት የቀድሞ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊሲ ማሰልጠኛን (የአሁኑ የፌዴራል ፖሊሲ ማስልጠኛን) አሞልቶ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅትና የዲዛይን ሥራዎች ተጠናቀዋል።የሙዚየሙ ሥራ ተጠናቅቆ በተያዘው 2016 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ለቱሪስቶች ክፍት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 18 ማዞሪያ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ (የፌዴራል ፖሊሲ ማስልጠኛ) ግቢ ውስጥ የሚገነባው ይህ የቱሪስት መዳረሻ፤ በወቅቱ ኒልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ በቆዩበት ወቅት ሲያከናወኗቸው የነበሩትን ተግባራት ሊገልጽና ሊያስረዳ በሚችል መልኩ የሚሰራ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም መታሰቢያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ የነጻነት ትግል ወቅት የነበራትን ሚና አጉልቶ የሚያሳይና በብዙ ቱሪስቶች ሊጎበኝ የሚችል ሙዚየም ሊሆን እንደሚችል ነው የሚያመላክቱት።
እንደዚህ አይነት መዳረሻዎችን ማስፋት የቱሪስቱን ቆይታ በመጨመረ ረገድ አዎንታዊ ሚና አለው ያሉት አቶ ሳምሶን፤ የቱሪስቱ ቆይታ በጨመረ ቁጥር ከቱሪዝም ዘርፍ የምናገኘው ጥቅም በዚያው ልክ ይጨምራል ይላሉ።እንደዚህ አይነት ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎች ብዝሀነት ማስፋት የሚያስችሉ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ የቱሪስቱ የቆይታ ጊዜንና የገቢ መጠንንም በመጨመር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና በቱሪዝም ለመጠቀም ሰፊ እድልን ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
አቶ ሳምሶን እንዳብራሩት፤ በተመሳሳይ በፌዴራል መንግሥት ተነሳሽነት የተገነቡት እንደ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እና የመሳሰሉት አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችና መዳረሻ ቦታዎች ወደ ከተማዋ የሚመጡትን ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ ከመጨመር አንጻር የጎላ ሚና አላቸው።የቱሪስቱ የቆይታ ጊዜ በጨመረ ቁጥር የሚገኘው ገቢም በዚያው ልክ ይጨምራል፤ እነዚህ የመስህብ ስፍራዎች ገቢንና የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜን ከማራዘም ፣ የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።
ለአብነት እንጦጦ ፓርክ ለአትሌቶች ልምምድ ምቹ የሆነ ቦታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓ ያሉ አትሌቶች ልምምድ ማድረግ የሚችሉበት እድል መከፈቱን ያመላክታሉ፡፡
አቶ ሳምሶን፤ ነባር የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪስቱ ምቹ ከማድረግ አንጻር እሴቶች በመጨመር የጎደሉትን፣ የቱሪስት መረጃ መስጫ ማዕከላት፣ የጌጣጌጥ መሸጫ፣ የአቅጣጫ መጠቆሚያና ሌሎች ነገሮች በማሟላት ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ከቱሪስቱ የሚገኘውን ገቢ እንዲጨምር ከማድረግ አንጻር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በዓመቱ የከተማዋን ገጽታ ከማስተዋወቅ አንጻር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። የከተማዋን የቱሪዝም መለያ (ብራንድ) “አዲስ አበባ አፍሪካዊቷ መልኅቅ”/ “Addis Ababa the vibrant Hab of Africa”/ የሚለውን የከተማዋ የቱሪዝም ገበያ መለያ መቅረጽ ተችሏል። ይህንንም በተለያዩ ሁነቶች በከተማዋና ከከተማዋ ውጭ በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል። ቱሪስቶች በከተማዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በቀላሉ መጎብኘት የሚያስችላቸው “የቱሪስት ጋይድ ቡክ” ታትሞ ለተጠቃሚዎች ተሰራጭቷል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስፋት ረገድም የንቅናቄ ሥራዎችን በመሥራት ተማሪዎች እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ ግንዛቤ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል።በከተማዋ ያሉ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማሳየት “የአዲስ አበባ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ፕሮፋይል” ተዘጋጅቷል።
በሚቀጥለው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ቱሪስት ቁጥርን ለመጨመርና ለማስፋት የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን ጠቅሰው፤ በተመሳሳይም የውጭ ቱሪስቶችን ለመሳብ የውጭ ሚዲያዎችን ሳይቀር በመጠቀም የተለያዩ አማራጭ ተጠቅሞ የፕሮሞሽን ሥራዎች ማካሄድ የሚያስችሉ ተግባሮችን ለማከናወን መታቀዱ ነው አቶ ሳምሶን የጠቆሙት።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም