በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አወዛጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከውድድር ጊዜ መጀመር ጋር የተያያዘ ነው። ባለፉት ዓመታት በዚሁ የተነሳ ክለቦች በቂ ዝግጅትን ማድረግ ሳይችሉ ወደ ውድድር እንዲመለሱ ይገደዱ ነበር። ሊጉ የሚጀመርበት ቀን ቀድሞ ቢታወቅም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች እየተገፋ በወቅቱ ውድድር እንዳይጀመር፣ በወቅቱም እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት በመሆን ክለቦችን ላልተገባ እንግልት እና ወጪም ሲዳርግም ነበር። ዘንድሮ ግን ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ የሊጉ አወዳዳሪ አካል ለተወዳዳሪ ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉ የሚጀመርበትን ቀን ቀደም ብሎ ሊያሳውቅ ችሏል። በዚህም መሠረት የቀጣይ ዓመት የውድድር ዘመን የሚጀምረው መስከረም 20/2016 ዓ.ም እንደሆነ ይፋ ሆኗል።
ይህም ካለው ሰፊ ጊዜ አንጻር 16ቱ ክለቦች በቶሎ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው በመመለስ የተሳካ ውድድር ዓመት ለማሳለፍ ጥረት ሊያደርግ ይችላል። የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሐምሌ 1/2015ዓ.ም በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን በካፍ የክለቦች ቻምፒንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚወክሉ ክለቦች ከመታወቃቸው በተጨማሪ ሦስተኛው ወራጅ ክለብንም መለየት ተችሏል። በዚህ ወቅትም ሁሉም ክለቦች በእረፍት ላይ የሚገኙ ሲሆን እረፍታቸውን እንደጨረሱ ለቀጣይ የውድድር ዓመት ተሰባስበው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም ቅድመ ዝግጅት እንዲረዳቸው የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር የ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመን የሚጀመርበትን ትክክለኛ ቀን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ከነዘርፈ ብዙ ችግሮቹ ሲመራ ቆይቶ የተሻለ ውድድር እንዲፈጠርና ሊጉም እንዲያድግ ክለቦች የራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ታስቦ አክሲዮን ማኅበሩ ሊቋቋም ችሏል። በዚህም ሊጉ ቀስ በቀስ የተሻለ ፉክክር የሚታይበት፣ በገቢ ረገድም ለውጥ አሳይቷል። ምንም እንኳን አሁንም በአክሲዮን ማኅበሩ አቅም ደረጃ የማይፈቱ ችግሮች ቢኖሩም እንደ ጅማሮ አበረታች የሚባል ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 30 ሳምንታት 240 ጨዋታዎች ተደርገው 583 ግቦች ሊቆጠሩ ችለዋል። በአማካይ በየጨዋታው 2ነጥብ4 የሚሆኑ ግቦች ተቆጥረዋል ማለት ነው። ከነዚህ ውስጥ 167 ጨዋታዎች በዴኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭትን አግኝተው ለተመልካች መድረስ ችለዋል። ክለቦቹ ከነበራቸው አጭር የዝግጅት ወቅት አኳያም የተሻሉ ፉክክሮች የታዩበት ዓመት በመሆን ተጠናቋል ማለት ይቻላል፡፡
የጉዳዩ ባለቤት ራሳቸው ክለቦች እንደመሆናቸው ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ የተሻለ ሊግን በመፍጠር ራሳቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ። የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበርም ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ መሥራት የሚጠበቅበትን ሥራ እያከናወነ ነው ማለት ይቻላል። ሊጉን ከመሸጥ እና የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር በደንብና ሥነ ሥርዓት እንዲመራ ከማድረግ አንጻር ወሳኝ የሆኑ ሥራዎችን አከናውኗል። ክለቦች በሊጉ ላይ ተፎካካሪና የተሻለ እግር ኳስን በሜዳ ላይ እንዲተገብሩ ጥሩ የሆነ የዝግጅት ወቅትና እራሳቸውን በዝውውር ማጠናከር ዋንኛው መገለጫ ነው። ለዚህም የእረፍት ጊዜን በአግባቡ ተጠቅመው በወቅቱ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ ለመግባት ሊጉ የሚጀምርበትን ትክክለኛ ጊዜን አስቀድሞ ማወቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው። እንደ አውሮፓ ባሉ ታላቅ ሊጎች ያለው ተሞክሮም ይሄንኑ ያሳያል። ሊጎቹ ከመጀመራቸው ከ3 ወራት በፊት የዓመቱ መርሃ ግብር ለክለቦቹ ይፋ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግን የሚመራው አክሲዮን ማኅበርም የዚህ ዓይነቱን አሠራር ለመከተልና የፕሮፌሽናሊዝምን ጽንሰ ሃሳብ ለመተግበር ቀድሞ የቤት ሥራውን ጀምሯል። የ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመን ከሁለት ወር አስቀድሞ መታወቁ ደግሞ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ መለያ መካከል እንዲሁም ክለቦቹን በብዙ መልኩ ከሚጠቅም ጉዳይ ውስጥ ዋንኛው ነው። ክለቦች የሊጉን መጀመር አስቀድሞ ማወቁ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ እንዲኖራቸው ከማድረጉም በላይ በዓመቱ የሚሳተፉባቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ውድድር መርሃ ግብሮች ጋር አጣጥመው ለመሄድ በእጅጉ የሚረዳቸው ይሆናል።
ከእረፍት እንደ መመለሳቸው ወደ ትክክለኛ አቋማቸው ለመመለስ ከፍተኛ ልምምድና የመዘጋጃ ጨዋታዎችን ቀደም ብሎ እንዲያደርጉም የጎላሚናን ይጫወታል። አዳዲስ የሚያስፈርሟቸውን ተጫዋቾችንም ከቡድናቸው ጋር ውህደት እንዲፈጥሩ፤ ነባር ተጫዋቾችም ወደ ሚፈለገው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ብቃታቸው በፍጥነት እንዲመለሱም ለማድረግ በቂ ጊዜ ያስፈልጋል። በመሆኑም የውድድር ቅድመ ዝግጅት ገበሬ ጥሩ ምርት ለማግኘት ማሳውን በዘር ከመሸፈኑ በፊት ደጋግሞ እንደሚያርሰው ሁሉ በእግር ኳስም ለተመልካች ሳቢ ጨዋታን ማየት እንዲቻል እና ውጤታማ ለመሆን በእቅድና በጥሩ ዝግጅት የታጀበ መሆን ይኖርበታል፡፡
ዓለማሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2015