ግራንድ አፍሪካን ሩጫ- የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን መገናኛ

ስፖርትን ልዩ ከሚያደርጉት ባህሪያቶች መካከል አንዱ ሰዎችን ለአንድ የጋራ ዓላማ ማሰባሰብና ህብረትን እንዲፈጥሩ ማስቻሉ ነው፡፡ የቦታ ርቀት፣ አኗኗር፣ እምነት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣… የሚለያቸው ሰዎች በተመሳሳይ ጉዳይ ሊያገናኛቸው የሚችለው ሁነኛ መድረክ ስፖርት ነው፡፡ እንደ ኦሊምፒክ፣ የዓለም ዋንጫ እና ሌሎች የስፖርት ቻምፒዮናዎች በዚህ ረገድ ያላቸው ሚና ትልቅ ነው፡፡

ስፖርት የሚሰጠውን ይህን ትልቅ እድል የተረዱና በኑሮ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራቸው ርቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ለመሰባሰብና ለመቀራረብ ስፖርትን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀትና ተሳታፊ በመሆንም፤ በስፖርታዊ ውድድሮች ከሚያገኙት ጥቅምና ከአብሮነታቸው ጎን ለጎንም ሌሎች መርሃ ግብሮችንም እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ባህር ማዶ ሆነው ከሚሰባሰቡባቸው የስፖርት መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ ግራንድ አፍሪካን ሩጫ ሲሆን፤ ለአምስተኛ ጊዜ ሕዝባዊ ሩጫውን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡

በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደውና በኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረገው ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍንም ነው፡፡ በመጪው ዓመት 2016 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጀመሪያ በሚካሄደው ሩጫ ተሳታፊ ለመሆን የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም በድረ ገጽ አማካኝነት መመዝገብ እንደሚችሉ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹አብሮነት መሻል ነው›› በሚል መሪ ቃል በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ዝግጅት፤ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ፣ የመጀመሪያው ትውልድ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብ እና ለተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ የሚከናወን ነው። በዚህ ዝግጅት፥ በሺዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉም ይጠበቃል፡፡

በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ በታወቀችበት የአትሌቲክስ ስፖርት የሩጫ ውድድር ከማድረጉ ባለፈም በኦሊምፒክ እና ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረኮች የሀገራቸውን ስም ማስጠራት የቻሉ ጀግና አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ከኦሊምፒያኖቹ እና የዓለም ቻምፒዮኖቹ ባሻገር ከ20 በላይ የሚሆኑ ታዋቂና ስመ ጥር አትሌቶች የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና ዝነኛ ግለሰቦች በክብር እንግድነት እንደሚገኙም የሩጫው አዘጋጆች የላኩት መግለጫ ይጠቁማል። ከእነዚህም መካከል የቀድሞዋ ድንቅ አትሌትና የአሁኗ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ አንዷ ስትሆን፤ ከመጀመሪያው ውድድር አንስቶ በአካል በመግኘት አዘጋጆቹን ስትደግፍ ቆይታለች፡፡

ሩጫውን በሚመለከትም ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ከሀገር ውጭ ያሉ ወገኖች የሚሰባሰቡበት መድረክ በመሆኑ ልዩ ትርጉም እንዳለው ገልጻለች። ሌላው ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ በክብር ያስጠራውና ባንዲራዋንም በከፍታ ላይ ማውለብለብ የቻለው አትሌት ቀነኒሳ በቀለም በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት ከሚታደሙት መካከል ነው፡፡ ስለ ግራንድ አፍሪካን ራንም ‹‹ኢትዮጵያን በበጎ መልክ ለማሳወቅ ጉልህ ድርሻ ባለው መድረክ ላይ በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ። ቀኑንም በአብሮነት በደማቅ ሁኔታ እንድናሳልፍ ጥሪ አቀርባለሁ›› ሲል ቀነኒሳ ተናግሯል።

የግራንድ አፍሪካን ራን ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ፤ ባለፉት የሩጫ ዝግጅቶች፣ የኢትዮጵያ ብርቅዬ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ የዲባባ ቤተሰብ(ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ እጅጋየሁ ዲባባ)፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ስለሺ ስህን፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና ሌሎችም በክብር እንግድነት ተገኝተው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ስለ ሩጫ ዝግጅቱ ሲያብራሩም ከአንድ ቀን የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫነት የበለጠ ፋይዳ ያለው መርሀ ግብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡ ከሩጫው ጎን ለጎን ለሚኖሩበት የአሜሪካ ማህበረሰብና ለትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ የጎላ አስተዋጽኦ ላደረጉ የዲያስፖራ ወገኖች ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *