አቶ ልጅዓለም ጌታቸው እና ወይዘሮ ቆንጅት ሙለታ በ2011 ዓ.ም ሶስት ጉልቻ ቀለሱ። ትዳራቸው በአንድ ጣሪያ ሥር መድመቁ ቀጠለ። ሁለት ልጆችን አፈሩ። አቶ ልጅዓለም የአክስቱ ልጅ የሆነችውን አስቴር ነገሳን ገና እድሜዋ 10 ዓመት ሳይሞላ፤ ከወለጋ ክፍለ ሀገር “እኔ ላሳድጋት” ብሎ አክስቱን ወይዘሮ አድስ ታዬን አስፈቅዶ ወደ አዲስ አበባ ይዟት መጣ። ከእነርሱ ጋር መኖር ጀመረች፤ እንደዋዛ ዓመታት ነጎዱ።
አስቴር አንድ ፍሬ ልጅ ለራሷ ገና ሳታድግና ጉልበቷ ሳይጠና እጣፈንታዋ ልጆች አሳዳጊነት ሆነ። ወደ አዲስ አበባ መጥታ መኖር ከጀመረች ዓመታት ቢያልፉም የተሻለ ኑሮ እና የትምህርት እድል አልገጠማትም። ልጅ አሳዳጊ ሆና የነገ ተስፋዋም ጨልሞ በሰላም እንድትኖር አልተፈቀደላትም። የቤት እመቤቷ ወይዘሮ ቆንጂት ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ በማገዶ ፍልጥ እንጨት እያገላበጠች ትቀጠቅጣታለች፤ ትወግራታለች።
“ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ” እንዲሉ፤ አባወራው አቶ ልጅዓለም ባለቤቱን “ተይ! ልጅ በምክር እንጂ በዱላ አይታረቅም” ብሎ መምከር ሲገባው በተመሳሳይ መልኩ ባለቤቱ ስትቀጠቅጣት የዋለቻትን አንድ ፍሬ ልጅ እርሱ ደግሞ ማታ ሥራ ውሎ ሲገባ ተራውን ተቀብሎ ይቀጠቅጣታል። ይህቺን ለጋ ህፃን እንዲህ ባልና ሚስቱ እየተቀባበሉ ሲቀጠቅጧት ያዩ ጎረቤቶች “ኸረ ተው! ይቺ ልጅ እጃቹህ ላይ ሕይወቷ ያልፍባችኋል” በሚል ይገለግላሉ፤ ይመክራሉ።
“ልጄን ስገርፍ ተው ብሎ የገለገለኝ የልብ ወዳጄ ነው” ከሚለው የሀገሬው ብሂል በተቃራኒው በተለይ ወይዘሮ ቆንጅት ልጅቷን ስትገርፍ “ተይ አትምቻት” ብሎ የገላገላትና የመከራትን ሰው እንደ ጠላት ማየት ጀመረች። ለእርሷ ብለው የመከሯትን ጎረቤቶቿን እላፊ ቃላት ከመናገር አልፎ ተርፎም ወደ ጥል ለማምራት ይቃጣት ጀመር። ይህኔ ጎረቤቱ ልጅቷ ጠዋት እና ማታ እንደ እባብ እየተቀጠቀጠች እያዩ ልባቸው ቢያዝንም “ተው አትምቷት” ብሎ መናገር ሌላ መዘዝ የሚያስከትል በመሆኑ ሁኔታውን በዝምታ መከታተል ጀመሩ።
ባልና ሚስቱ ልጅቷን ሲገርፉ “ተዉ አትምቷት” ብሎ የሚገላግልና የሚመክር ሰው ሲጠፋ ጭራሽ ነጋ ጠባ አንዴ በማገዶ ፍልጥ እንጨት፣ በሶኬት (በኤሌክትሪክ ሽቦ)፣ በጎማና በውሃ ማስተላለፊያ የፕላስቲክ ቱቦ መቀጥቀጡን ተያያዙት። በዚህም የልጅቷ ገላ ላይ ዱላ ያላረፈበት የሰውነት ክፍል አካል ፈልጎ ማግኘት ከባድ ሆነ።
ልጅቷ በደረሰባት ድብደባ በተለይ እጇ ዝሎ እንደፈለገች እጆቿን ለማዘዝ ቢሳናትም በደመነፍስም ቢሆን የሚያዟትን ለመሥራት ተገደደች። ያቅሟን ለመሥራት ደፋ ቀና ትላላች። ባልና ሚስት ግን አስቴር በደረሰባት ድብደባ አካሏ ዝሎ ተዳክማ እያዩዋት ልባቸው አይራራም። ወደ ሀኪም ቤት ወስደው ሊያሳክሟትም አልፈቀዱም።
በተለይ ወይዘሮ ቆንጅት በጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም “ወተት ሰረቅሽኝ” በሚል ሰበብ እንደለመደችው ህጻኗ አስቴርን ኩሽና አስገብታ ትደበድባት ጀመር። ይህኔ በጣም ዱላው የበረታባትን ህጻን ሲቃ ሰምቶ እንዳልሰሙ መሆን ያቃታቸው ጎረቤት ወይዘሮ በቀሉ ሸዋዬ፤ በአጥር ብቅ ብለው ለምን ትመቻታለሽ ይሏታል። “ወተት ሠርቃኝ ነው” ብላ መልስ ትሰጣለች። ወተት ሰረቀችኝ ብለሽ ከምትደበድቢያት ለምን መጀመሪያ አጥግበሽ አታበያትም ይሏታል።
ይህኔ ወይዘሮ ቆንጅት ልጅቷ ውጭ እንደወደቀች ልጅቷን ስትገርፍበት የነበረውን የፍልጥ እንጨት አሽቀንጥራ ጥላ ወደ ቤት ገባች። ህጻኗ አስቴር ግን ከወደቀችበት ለመነሳት አቃታት። ጉልበቷ ቄጠማ ሆነባት። በዚያው አፈር ላይ እንደወደቀች ሰዓታትን ቆየች። ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ገደማ ሲሆን፤ አንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ጎረቤት ወይዘሮ ፀሐይ አገዘ ከሥራ ውለው ወደ ቤታቸው ሲገቡ፤ ከወደቀችበት መነሳት ያቃታት አስቴርን አንስተው ወደ ቤት እንዲያስገቧት ተማጸኑ። ምላሽ ሲያጡ፤ ነገሩ ሌላ እንዳይተረጎምባቸው “ወደ ቤት ላስገባት ወይ” ብለው ወይዘሮ ቆንጅትን ጠየቁ። ወይዘሮ ቆንጅት ግን ህጻኗን “መነሳት ትችያለሽ ለምን አትነሺም” ብላ በፍልጥ እንጨት መሃል ወገቧን ከወደቀችበት ሁለት ጊዜ መታቻት። ይህኔ ወይዘሮ ፀሐይ የልጅቷን ስቃይ ከማይ ብለው ትተው ወደ ቤታቸው ገቡ።
ታዲያ አንድ ቀን እንደልጅ ሳትቦርቅ፣ ከእኩዮቿ ጋር ስቃ ሳትጫዎት እንዲህ ጠዋት ማታ ዱላ የበዛባት አስቴር በዚሁ ዕለት ምሽት 2:00 ሰዓት ሲል በደረሰባት ድብደባ ሕይወቷ አለፈ። ባልና ሚስቱ ግን አስቴር ሕይወቷ ማለፏን ለማንም ትንፍሽ አላሉም። እንደልጅ ሊያሳድጓት ያመጧት አንድ ፍሬ ልጅ ሕይወቷ ሲያልፍ አላለቀሱም፤ ጎረቤትም አልጠሩም። ይልቁንም የሬሳ ሳጥን ገዝተው አስከሬኑን በሳጥን ውስጥ አድርገው በድብቅ ሊቀብሩ ሲሰናዱ በሁኔታው የተጠራጠሩ ጎረቤቶች ለፖሊስ ጥቆማ ያደርሳሉ።
ፖሊስም ጥቆማው እንደደረሰው በእግር በፈረስ ገስግሶ ባልና ሚስቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወረዳ 11 ክልል ልዩ ቦታው ማንጎ ሰፈር አካባቢ ቤት ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት ሰተት ብሎ ሲገባ የሟች አስክሬን በሬሳ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ተቀምጦ አገኘ። ፖሊስም በጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ባልና ሚስቱን በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪዎቹን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን ቃል፣ የሟች አስከሬን የህክምና ውጤትና የአማሟት ሁኔታዋን የሚያሳዩ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰርትባቸው መረጃውን አቀረበ።
ጎረቤቶች ምን አሉ?
ከላይ በተጠቀሰው ቦታ በጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 12:00 ሰዓት ገደማ ወይዘሮ በቀሉ ሸዋዬ የተባሉት ግለሰብ፤ ከጎረቤቷ ወይዘሮ ጠጄ አስፋው ቤት እቃ ለመዋስ ያመራሉ። በወሬ ተነስቶ ወይዘሮ ጠጄ “እዚህ ግቢ ውስጥ ሁሌ የምትደበደብ ልጅ አለች” ብላ ለወይዘሮ በቀሉ ትነግራታለች። ጎረቤታማቾቹ ስለ ልጅቷ እያወሩ እያለ “ድው! ድው”! የሚል ድምጽ ሰምተው ወደ ውጭ ወጥተው በአጥር በኩል ሲያዩ፤ ወይዘሮ ቆንጂት የተባለችው ግለሰብ አስቴር ነገሳ የተባለችውን ሟች ህጻን ልጅ ኩሽና አስገብታ በፍልጥ ደጋግማ ስትደበድባት ያያሉ።
ይሔኔ ሲያዩ በአጥሩ ብቅ ብለው ልጅቷን የምትደበድበውን ግለሰብ ‹‹ለምን ትመቻታለሽ?›› ይሏታል። እሷም “ወተት ሰርቃኝ ነው” ብላ ትመልስላቸዋለች። “ምንሽ ናት?” ይሏታል ጎረቤታማቾቹ፤ “ልጄ ናት” ትላቸዋለች። ጎረቤታማቾቹም “ልጅሽማ አይደለችም፣ ልጅሽ ብትሆን እንደዚህ አትመቻትም” ይሏታል። እሷም መለስ ብላ “አይ የአክስቴ ልጅ ናት” ትላቸዋለች። ወይዘሮ በቀሉ “የአደራ ልጅ እንዲህ አይመታም። ወተት ለምን ሰረቅሽ ብለሽ ከምትመቻት አጥግበሽ ለምን አታበያትም? እንዲህ ካስቸገረችሽስ ለምን ወደ ቤተሰቦቿ አትሰጃትም?›› ይሏታል። እንዳልሰዳት “ጅማ መስመር መንገዱ ዝግ ነው” ብላ መልስ ስትሠጥ “ጅማ መንገዱ ሰላም ነው፤ ብር ከሌለሽ ከሰፈር አሰባስቤ አምጥቼ ልስጥሽ። ለፖሊስ አሳውቀሽ ለቤተሰቦቿ ደውለሽ አሳፍረሽ ላኪያት። ትሞትብሻለች በልጆችሽ ይዥሻለሁ አትምቻት” ብለው ወይዘሮ በቀሉ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።
ወይዘሮ በቀሉ በቤታቸው አገር አማን ብለው በተኙበት በጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጠዋት 1:00 ሰዓት ላይ ጎረቤታቸው ወይዘሮ ጠጄ ከተፍ አሉ። “በጠዋት ምን እግር ጣለሽ ወይዘሮ ጠጄ” ሲሉ፤ የትናንትናይቱን ልጅ ገደሏት ብለው” ይነግሯቸዋል። ወይዘሮ በቀሉ ይህንን አስደንጋጭ ዜና ሲሰሙ እጃቸው ላይ የገባውን ነጠላ ቢጤ አፈፍ አድርገው ወደ ተጠርጣሪዎቹ ቤት ከወይዘሮ ጠጄ ጋር ተያይዘው እየተጣደፉ አመሩ። ወደ ተጠርጣሪዎቹ ቤት ሲገቡ የአስከሬን ሳጥን ቤቱ መሀል ላይ ተጎልቷል።
አቶ ልጅዓለምን “ምን ሆና ሞተች? ትናንት 12:00 ሰዓት ላይ አይተናታል” ሲሉት “ምሽት 2:00 ሰዓት ላይ ወድቃ ሞተች” ብሎ መልስ ይሰጣቸዋል። ከዚያ እነ ወይዘሮ በቀሉና ጠጄም “ምን ጭካኔ ነው! እሬሳ ታቅፋችሁ እንዴት አታለቅሱም? ጎረቤትስ ለምን አልጠራችሁም?” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ አቶ ልጅዓለም የአክስቴ ልጅ ናት አያገባችሁም ከግቢው ለቃችሁ ውጡልኝ ብሎ ያስወጣቸዋል።
“ትናንት ባለቤቱ የአክስቴ ልጅናት አለች። ዛሬ ደግሞ አባወራው የአክስቴ ልጅ ናት አለን” ይሄ ነገር ሁኔታው አላማረንም” ይሉና እነ ወይዘሮ በቀሉና ጠጄ ደውለው ለፖሊስ ጥቆማ በማድረስ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደርጋሉ። ከነዚህ በተጨማሪ ሌሎች ጎረቤቶችም ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ከዛ በፊትም በተለያየ ጊዜ ባልና ሚስት እየተፈራረቁ ሟችን እንደሚደበድቧት ለፖሊስ የምስክርነት ቃላቸውን እንደሰጡ ልብ አድርጉ።
የተጠርጣሪዎች የእምነት ክህደት ቃል
ሟች አስቴር ነገሳ የተባለችውን ህጻን ከክፍለ ሀገር በቤት ሠራተኝነት አምጥታችሁ በተለያየ ቀን በማገዶ ፍልጥ እንጨት ዱላ፣ በሶኬት (በኤሌክትሪክ ሽቦ)፣ በጎማና በውሃ ማስተላለፊያ የፕላስቲክ ቱቦ የተለያየ የሰውነቷን ክፍል ስትደበድቧት ከላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓትና ቦታ ሕይወቷ አልፏል። ሕይወቷ ካለፈ በኋላም በድብቅ ለመቅበር የአስከሬን ሳጥን በማምጣት ከትታችሁ ለመቅበር ሞክራችኋል፤ ተባሉ።
የአካባቢው ማህበረሰብ ለፖሊስ ባቀረበው ጥቆማ መሰረት ፖሊስ 1ኛ ተጠርጣሪ አቶ ልጅዓለም እና 2ኛ ተጠርጣሪ ወይዘሮ ቆንጅት ከላይ በተጠቀሰው ዕለት በቁጥጥር ሥር አውሎ ለቀረበባቸው የሰው መግደል ወንጀል ክስ የሚከተለውን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
አንደኛ ተጠርጣሪ ሟች የአክስቱ ልጅ እንደሆነች ጠቅሶ፤ በ2008 ዓ.ም ከአክስቱ ነጥሎ ከወለጋ ክፍለ ሀገር “ላሳድጋት” ብሎ ወደ አዲስ አበባ ያመጣት መሆኑን ገልፆዋል። እርሱም በ2012 እና 2013 ዓ.ም የመጀመሪያና ሁለተኛ ልጁን ሲወልድ ሟች ልጆቹን ይዛ ተንከባክባ እንዳሳደገችለት ይናገራል። ሟች እቤት ውስጥ ቁጭ ብላ ቴሌቪዥን እየተመለከተች እያለ እንድትጠብቅ አደራ የተሰጣት የተጠርጣሪዎቹ ልጅ ከቤት ወጥታ ጎዳና ላይ አባቷ ሲያገኛት “ለምን ልጄን አትጠብቂም?” ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጀሉ ከመፈጸሙ ከሁለት ወር በፊት በቻርጀር መቀመጫዋ ላይ ደጋግሞ እንደመታት ይናገራል። ከዚህ ውጭ ገርፏት እንደማያውቅ እና እንደ ልጁ እንደሚያያት ተናግሯል።
“በጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ላይ ሥራ ውዬ ወደ ቤት ስገባ ባለቤቴ ተኝታ ልጅ እያጠባች ነበር። ሟች ቆሻሻ ውሃ እደፋለሁ ብላ ይዛ ከቤት ስትወጣ በር ላይ ስትደርስ ማስታጠቢያውን እንደያዘች በፊት ለፊት በኩል ወደቀች። እኔም የሚጥል በሽታ ስላለባት የሚጥለው ነው ብዬ ከወደቀችበት አንስቼ ወደ ቤት አስገባኋት። ፍራሽ ላይ አስተኝቻት ልብስ አለበስኳት። ከዛ እረጅም ሰዓት ሳትነቃ ስትቆይ ምን ሆና ነው? ብዬ ልብሱን ገልጬ ስመለከታት አትተነፍስም፤ ሞታለች። የተፈጠረው ይህ ነው፤ እኔ ደብድቤ አልገደልኳትም” ሲል የእምነት ክደት ቃሉን ይሰጣል። 2ኛ ተጠርጣሪም በተመሳሳይ የሚጥል በሽታ ስላለባት የሞተችው ወድቃ እንጂ እኔ ደብድቤ አልገደልኳትም፤ መትቻትም አላውቅም” ብላ የእምነት ክደት ቃሏን ሰጠች።
ዐቃቢ ሕግ
አጠቃላይ ሟች በሰውነቷ ላይ በደረሰባት በርካታ ጉዳቶች ምክንያት ሕይወቷ እንዲያልፍ ካደረጉ በኋላ በቀን በጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 3:00 ሰዓት የሟችን አስከሬን ሳጥን ውስጥ በማስገባት በድብቅ ለመቅበር ሲሉ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ልጅዓለም እና 2ኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ቆንጅት የተያዙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል።
ዐቃቢ ሕግም አምስት የሰው ማስረጃ፤ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ያካሄደውን የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በደብዳቤ ቁጥር ጳሀ8/3028 በታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም የተሰጠ የሟች አስቴር ነገሳ የሞቷ ምክንያት በሰውነቷ ላይ በተለያየ ቦታዎች ላይ ጉዳቶች በመድረሳቸው ሕይወቷ ያለፈ መሆኑን የሚያስረዳ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከነ ትርጉሙ07 ገፅ የሰነድ ማስረጃ፤ የሟችን የአማሟት ሁኔታ፣ ጉዳት እና ወንጀሉ የተፈጸመበትን ስፍራ የሚያሳይ 24 ገላጭ ፎቶ ግራፎችን እንዲሁም ተከሳሾች በወ/መ/ስ/ህ/ቁ 27(2) መሰረት ለፖሊስ የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃል በማስረጃነት አያይዞ ለፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በፍጥነት እንዲታይ አቅርቧል። ዐቃቢ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።
ውሳኔ
ታህሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሾች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡና ለአምስት ዓመት ህዝባዊ መብቶቻቸው ተሽረው እንዲቆዩ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015