የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለመሥራት ፍላጎት እያሳዩ ያሉ የሀገር ውስጥ አምራቾች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ በምርት፣ በግንባታና በሎጂስቲክስ ዘርፎች ከሚሰማሩ ስምንት ኩባንያዎች (ሰባት የሀገር ውስጥ እና አንድ የውጭ) ወደ ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመግባት በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የተፈራረሙት ስምምነት እንዲሁም በቦሌ ለሚ፣ በቂሊንጦ፣ በሰመራና በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚሰማሩ አስር ሀገር በቀል ኩባንያዎች በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ከኮርፖሬሽኑ ጋር የገቡት የሥራ ውል የሀገር ውስጥ አምራቾች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ ስለመሆኑ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በ2015 በጀት ዓመት አስር ወራት (ከሐምሌ 2014 እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ባለሀብቶች ከ37 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል እና ለ300ሺ አርሶ አደሮች ደግሞ ዘላቂ የሆነ የገበያ ትስስር ፈጥረዋል፤ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ምርት ለውጭ ገበያ መላካቸው የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጆነዲ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ወደሚያስተዳድራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት የሚያሳዩ ባለሀብቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ባለፉት አስር ወራት (ከሐምሌ 2014 እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም) ከ30 በላይ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራርመዋል፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ከ583 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲሆኑ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካል እንዲሁም በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ዘርፎች ይሰማራሉ፡፡ ወደ ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የገቡት ባለሀብቶችም ከምርት ሥራዎች በተጨማሪ በንግድና በሎጂስቲክስ ተግባራት ላይ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል፡፡
ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለመሥራት ፍላጎት እያሳዩ ያሉ የሀገር ውስጥ አምራቾች ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል፤ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች መደረጋቸው፣ ለኢንቨስትመንት እድገት መሰናክል የነበሩ ሕጎችና መመሪያዎች መሻሻላቸው፤ የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ ዘርፎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እየተገበረ ያለው ቀልጣፋና ፈጣን አሠራር፤ ከባለ ድርሻ አካላት (ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎችም ተቋማት) ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ ሥራዎች፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ በመንግሥት ልዩ አቅጣጫ መቀመጡና ትኩረት መሰጠቱ እና ኮርፖሬሽኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የሪፎርም ሥራ መተግበር መጀመሩ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹በኮርፖሬሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት የተገበርናቸው የሪፎርም ሥራዎች ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ መጨመር ዋነኛው ምክንያት ናቸው›› ሲሉ የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ያመለክታሉ፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው፡፡ የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሰው ኃይል የሚሸከም የሥራ ዕድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን ተወስኖ ውሳኔውን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው፡፡
የኢንቨስትመንት ሕግጋት መሻሻልን ጨምሮ ሌሎቹ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እርምጃዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚገቡ ባለሀብቶችን ቁጥር በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጁ መሻሻሉ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ብዙ ባለሀብቶችን በመሳብ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈው ውሳኔም ትልቅ የገንዘብ አቅም ያላቸው ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡና ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ማሻሻያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገቡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ደግሞ የሚኖራቸው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
አቶ ዘመን ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ እና በሥራ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎችም ሥራቸውን እንዲያስፋፉ የሚተገበሩ አሠራሮች እንዳሉም ያስረዳሉ፡፡ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ምቹ ማድረግ፤ በኮርፖሬሽኑ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል (Digital) የአሠራር ሥርዓት መቀየር፤ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የሥራ ውል ተፈራርመው ሥራ ለጀመሩ ባለሀብቶች ድጋፍ መስጠት፤ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር (የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) ጋር በመቀናጀት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሠሩ ባለሀብቶች አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን ማፈላለግ እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተኪ ምርት ማምረት ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል የባለሀብቶቹን ተሳትፎ ለማሳደግ በቀጣይ የሚተገበሩ አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው ስለሚታመን መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግም አቶ ዘመን ይገልፃሉ፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ባለሀብቶች በአማካኝ እስከ አስር ዓመት የሚደርስ የገቢ ግብር እፎይታ የሚፈቀድላቸው ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚያለሙ ድርጅቶች ደግሞ ከአስር እስከ 15 ዓመታት የሚደርስ የገቢ ግብር እፎይታ መብት ይሰጣቸዋል፡፡ ከገቢ ግብር ነፃ የመሆን ማበረታቻ በተሰጠበት ዘመን ውስጥ ኪሳራ ያጋጠመው ማንኛውም ባለሀብት ከገቢ ግብር ነፃ የመሆኛ ዘመኑ ከተጠናቀቀ በኋላ የዚሁ ዘመን ግማሽ ለሚሆን ጊዜ ኪሳራው ይተላለፍለታል፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ ከሚከፈል ማንኛውም የወጪ ግብር እና ከሌሎች የግብር ክፍያ ነፃ የመሆን መብት እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማምረት በግብዓትነት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ከውጭ የማስገባት መብት አላቸው።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ከትርፍ፣ ከሀብት ክፍፍል፣ ከወለድ፣ ከድርጅት ሽያጭ እና ከመሰል ተግባራት ያገኟቸውን ገቢዎች በውጭ ምንዛሪ መንዝረው ወደ ሀገራቸው መላክም ይችላሉ። የውጭ ባለሀብቶች የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ የሆኑ የማይንቀሳቀሱ ሀብቶች ባለቤት የመሆን መብትም አላቸው፡፡ በፓርኮቹ ውስጥ ተሰማርተው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሀብቶች በኤክስፖርት ምርት ላይ ምንም ዓይነት የኤክስፖርት የዋጋ ተመን ቁጥጥር አይደረግባቸውም፤ በፍራንኮ ቫሉታ (Franco-Valuta) አማካኝነት ከውጭ ሀገር ጥሬ ዕቃ ማስገባት ይችላሉ፡፡
አምራቾች አዲስ ፕሮጀክት ወይም ነባር ድርጅት ለማስፋፋት ወይም ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑና አግባብነት ያላቸውን የማምረቻና የአገልግሎት መስጫዎችን፣ የካፒታል ዕቃዎችን፣ የግንባታ ዕቃዎች እና ተሽከርካሪዎችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ማስገባት እንዲሁም የካፒታል ዕቃውን ዋጋ ከ15 በመቶ ያልበለጠ መለዋወጫ ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይችላሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ጥበቃና ዋስትና የሚደነግጉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የተፈራረመችና ከዓለም ባንክ ጋር የተቆራኘ የባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ዋስትና ድርጅት (Multilateral Investment Guarantee Agency – MIGA) አባል በመሆኗ ለኢንቨስትመንት የዋለ ሀብት ለሕዝብ ጥቅም ሲባልና በሕግ በተደነገገው መሠረት ካልሆነ በስተቀር ሊወሰድ ወይም ሊወረስ አይችልም። እነዚህ ሁሉ ማበረታቻዎች የተሰጡት ባለሀብቶች፣ በተለይም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው እንዲያለሙ ተሳትፏቸውን ለመጨመር ታልሞ መሆኑን አቶ ዘመን ገልጸዋል፡፡
ባለሀብቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የምጣኔ ሀብት ጥናቶች እንደሚያስረዱት፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉ የልማት አንቀሳቃሾች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ የሠሩት ሥራ የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሏቸዋል፡፡ የበለፀጉት የዓለም ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን ቀደም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሳይሆን አሁንም ከፍተኛ ድጋፍና ጥበቃ ያደርጉላቸዋል፡፡ ሀገራቱ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለባለሀብቶቻቸው የተለየ የድጋፍ መርሃ ግብር አላቸው፡፡ የበለጸጉት ሀገራት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከሚያደርጉት ድጋፍ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡ ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሠረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የውስጥ አምራችነት አቅማቸው ማ ደግ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡
መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት ከሚያግዙት ግብዓቶች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሳደግ ነው፡፡ ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም፡፡ ስለሆነም ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ሀገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል፡፡ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል፡፡ አምራችነቱን ያላሳደገ እና ፍላጎቱንና አቅርቦቱን በራሱ የማምረት አቅም ላይ ያልመሠረተ ምጣኔ ሀብት ደግሞ ዘላቂ እድገትን ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ለማድረግ መንግሥት ለዓመታት ሠርቷል፡፡ ኢንዱስትሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል በማስገኘት፣ ለባለሀብቱም ለሀገርም የሚተርፍ መሆኑን በመጥቀስ የንግዱ ማህበረሰብ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲገባ ጥሪዎች ይደረጉ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ይሁንና የባለሀብቶች ምርጫ በቀላሉ የሚከበርበት የንግዱ ዘርፍና ሕንፃ መገንባት ሆኖ ቆይቷል፤ አሁን ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች መሰማራታቸው እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ የብዙ ሥራዎች ውጤት ነው፡፡
በቀጣይ ደግሞ የባለሀብቶቹን የተወዳዳሪነት መገንባት ላይ መሥራት ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት እንድታስመዘግብ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል፡፡ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም ሀገራትንና ተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2015