አማኑኤል ክበበው ይባላል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነው። የ2015 ብሩህ ኢትዮጵያ ውድድር አሸናፊ ነው። አማኑኤል የግብርና ኬሚካል መርጫ ድሮን የፈጠራ ሀሳብ ይዞ ቀርቦ ነው ለአሸናፊነት የበቃው።
ከውጭ ገዝተን የምናስገባው ድሮን አንድ አይነት አገልግሎትን ለመስጠት (ኬሚካል ለመርጨት) ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን የሚገልጸው አማኑኤል፤ አዲሱ የድሮን ፈጠራ ግን አራት አይነት ጠቀሜታዎች እንዲሰጥ ተደርጎ መሰራቱን ይናገራል። ድሮኑ ኬሚካል ይረጫል፤ አንበጣ ይከላከላል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንዲሁም የቁጥጥር ሥራዎችን መሥራት ያስችላል።
ከውጭ ሀገር የሚመጡት ድሮኖች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚገዙም ተማሪ አማኑኤል ጠቅሶ፤ በሀገር ውስጥ የተሰራው ግን ኪስ በማይጎዳ ዋጋ በርካታ አገልግሎቶች እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚሰራ ይገልጻል። ድሮኑን ከአልሙኒየም፣ ከእንጨት እና ከመሳሰሉት ነገሮች መስራት እንደሚቻል የሚናገረው አማኑኤል፤ ድሮኑን በሚፈለገው ልክና መጠን መስራት እንደሚቻልም ይጠቁማል። ለምሳሌ 30 ሄክታር መሬት ላይ ኬሚካል ማስረጨት የሚፈልግ ሰው የሚፈልገውን አይነት ድሮን ለመስራት እንደሚችልም ነው ያመለከተው።
እሱ እንዳለው ከውጭ የሚገባው ድሮን ከ8 እስከ 12 ሚሊዮን የሚገመት ብር ይጠይቃል። በሀገር ውስጥ የሚመረተው ድሮን ግን የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እስከ 67 ሺ ብር ብቻ ነው። በድሮኑ አምስት አምፑሎች ማብራት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይልም ማመንጨት ይቻላል።
‹‹ይህን የፈጠራ ሀሳብ ለማመንጨት የረዳኝ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ነው›› የሚለው ተማሪ አማኑኤል፤ በአካባቢው የግብርና እንቅስቃሴ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች በዚህ የፈጠራ ሀሳብ እንድመሰጥ አድርጎኛል ይላል።
ተማሪ አማኑኤል እንደሚለው፤ ፈጠራውን ሲጀምር ትኩረቱ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በፈጠራ ዲዛይኑ ላይ መጠበብ ነበር። ለውድድር ሲመጣ ግን የፈጠራ ሀሳቡን ወደ ቢዝነስ ለመቀየር የሚችልበት እውቀት አግኝቷል፤ ቡራዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማእከል አብረውት ከገቡት የብሩህ ፈጠራ ባለሙያዎች ብዙ ትምህርት ማግኘት ችሏል።
የሰራው ድሮን አራት ጠቀሜታዎች ያሉትና የብዙ ሙያዎች ጥምረትን እንደሚጠይቅ የጠቆመው ተማሪ አማኑኤል፤ የፈጠራ ሀሳቡ ካለው ጠቀሜታ አንጻር በፍጥነት ወደ ቢዝነስ በመቀየር ሥራ ላይ እንደሚያውለው ይናገራል። ‹‹በዚህ አይነት ሁኔታ ታግዘን የፈጠራ ሀሳባችን ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ቢዝነስ በመቀየር የምንችልበት ስልት ማግኘታችን ደስተኛ ነን›› የሚለው አማኑኤል፤ በተለይ ወጣቶች ሀሳባቸውን ይዘው እንደዚህ አይነት ቦታዎች ቢመጡ ሀሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ እገዛ ሊያገኙ ሊበረታቱ እንደሚችሉም ተናግሯል።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ካሳሁን በፍቃዱም ሌላው የ2015 የብሩህ ኢትዮጵያ ውድድር ተሸላሚ ነው። ካሳሁንና ሁለት ጓደኞቹ ያገለገሉ ፕላስቲኮችን በመጠቀም የሰሩትን የፕላስቲክ ቴራዞ ማምረት የሚያስችል የፈጠራ ሀሳብ ለውድድር ይዘው ቀርበው ተሸላሚ ሆነዋል።
ይህንን የፈጠራ ሀሳብ እንድናመነጭ በዋናነት ያነሳሱን በአካባቢያችን የምንመለከታቸው የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ናቸው የሚለው ተማሪ ካሳሁን፤ ቆሻሻውን ከማስወገድ አንጻር ምን መስራት እንችላለን በሚል ሀሳብ ከጓደኞቹ ጋር ይህንን የፈጠራ ሀሳብ ሊያገኙ መቻላቸውን ይናገራል።
ካሳሁን እንደሚለው፤ አሁን በገበያ ላይ ያለው የቴራዞ ምርት ቶሎ ተሰባሪና በዋጋም ቢሆን በጣም ውድ ነው። ቴራዞው ቶሎ እየተሰበረ ለተደጋጋሚ ውጪ እየዳረገ ይገኛል። እነ ካሳሁንም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ወደ አዲሱ የፈጠራ ሀሳብ ሊገቡ ችለዋል።
አዲሱ የፈጠራ ሀሳብ በቀላሉ የማይሰበር የቴራዞ ምርት ማምረት እንደሚያስችል ተማሪ ካሳሁን ይናገራል፤ የቀለጠን ፕላስቲክ ከአሸዋ ጋር በመደባለቅ የሚመረተው ይህ ቴራዞ በጣም ረጅም ጊዜ ሊያገለግል እንደሚችል ገልጿል። እነ ካሳሁን የቴራዞ ምርት ማምረቻ ማሽኑን በራሳቸው ፈጠራ የሰሩት ሲሆን፤ የቴራዞውን ምርት ከመንገድ ላይ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ቀለም ተጨምሮበት እንዲያመርት ከተደረገ ለቤት ውስጥ ወለል ምንጣፍ አገልግሎት ሊውል እንደሚቻልም ይገልጻል።
እነ ካሳሁን አሁን የማምረቻ ዲዛይኑን ሰርተው ጨርሰዋል፤ ከሚቀጥለው አመት አጋማሽ ጀምሮ ወደ ምርት ሂደት ለመግባት እያሰቡ ይገኛሉ። ይህንን የፈጠራ ሀሳብ ለማዳበር እንዲያስችላቸው ቡራዩ በሚገኘው የልዩ ፍላጎት ማበልጸጊያ ማዕከል በገቡበት ሦስት ሳምንታት ውስጥም የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ቢዝነስ መቀየር የሚችሉበት እውቀት አግኝተዋል፤ የማእከሉ ቆይታቸው በፈጠራ ሀሳባቸው ላይ ተጨማሪ ማዳበሪያ ሀሳቦች እንዲያገኙና የፈጠራ ሀሳባቸውን እንዲያዳብሩ እንደረዳቸው ነው ካሳሁን የገለጸው።
የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ቢዝነስ ለመቀየር ከአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ብር በላይ ያስፈልጋል የሚለው ተማሪ ካሳሁን፤ በመንግሥት በኩል የተደረገላቸው እንዲህ አይነት ድጋፍ የፈጠራ ሀሳባቸውን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማስኬድ እንደረዳቸው ይገልጻል። በተለይ እንደኛ ያሉ ወጣቶች ተምረው ሥራ ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸው ሥራ ፈጣሪ በመሆን ያላቸውን ሀሳብ ይዘው ሊበረታቱና ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ምክረ ሀሳቡን ለግሷል።
ከጭሮ አካባቢ የመጣው አዲስ አፈወርቅ ከጓደኛው ጋር በፔዳል የሚሰራ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ለመሥራት የሚያስችላቸውን የፈጠራ ሀሳብ ይዘው ቀርበው በውድድሩም አሸናፊ ሆነዋል። አዲስ እንደሚለው፤ የልብስ ማጠቢያ ማሽኑ ነዳጅም ሆነ ኤሌክትሪክ ሳይስፈልገው በፔዳል ብቻ በመጠቀም ልብስ ማጠብ ያስችላል። ማሽኑ እስከ አሥር ኪሎ ክብደት ያለው ልብስ ማጠብ ይችላል። ማሽኑን እንደሳይክል በመንዳት በቀላሉ ልብስ ማጠብ ይቻላል ይላል።
35 በመቶ ያህሉ ተላላፊ በሽታ በልብስ ንጽህና ጉድለት እንደሚመጣ ካገኘሁት መረጃ ተረድቻለሁ የሚለው አዲስ፤ በተለይ በሚኖርበት አካባቢ ያለውን ማህበረሰብ ከዚህ ችግር ለማዳን ያስችል ዘንድ የፈጠራ ሀሳቡን መጠንሰሱን ይገልጻል። የልብስ ማጠቢያ ማሽኑ በየትኛውም ቦታና አካባቢ ያለው ማህበረሰብ የልብሱን ንጽህና በቀላሉ ሊጠብቅ የሚችልበት ድካምና ጊዜ፣ ወጪንና ጉልበትን የሚቀንስ እንደሆነም ነው ያብራራው።
በፔዳል የሚሰራ ማሽን በገበያ ላይ ካለው በኤሌክትሪክ ከሚሰራው ዘመናዊ የልብስ ማጠቢያ ማሽን የሚለየው በብዙ ነገሮች መሆኑን ጠቅሶ፤ በዘመናዊው ማሽን ከዋጋ አንጻር ከ18ሺ እስከ 65 ሺ ብር እንደሚሸጥ ይናገራል። ባለፔዳሉ ማሽን የሚገጣጠመው በሀገር ውስጥ በመሆኑ በዋጋው በ50 በመቶ ቅናሽ አለው።
ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ለዩኒቨርሲቲ፣ ለሆስፒታሎችና ለመሳሰሉት በርካታ ሕዝብ ለሚስተናገድባቸው ተቋማት አገልግሎት መስጠት ያስችላል። እነዚህ ተቋማት ውስጥ ማሽኑ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ ሁሉም ተማሪዎች በቀላሉ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ነው የሚያስረዳው።
ማሽኑ ሁለት ሲስተሞች አሉት። አንደኛው እንደ ሳይክል በመንዳት ማጠብ የሚቻልበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በእጅ በማሽከርከር ማጠብ የሚያስችል ነው። በሌላ በኩል በሀገራችን በተለምዶ ያለው የአኗኗር ዘይቤ ደካማ መሆኑን ጠቅሶ፣ በተለይ እንደሳይክል በመንዳት ልብስ ማጠብ ቢቻል ጤናንም ከመጠበቅ አንጻር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ይላል።
የብሩህ ኢትዮጵያን ውድድር መቀላቀሉ ማሽኑን በተለያየ መልኩ እንደገና እንዲያሻሸል እድል እንደፈጠረለት የሚናገረው አዲስ፤ የቢዝነስ እቅዶችን በማውጣት ገበያ ላይ ለማዋል አስተማሪ ጊዜና ጥሩ ግብዓት ያገኘበት እንደነበር እና በቀጣይም የልብስ ማጠቢያ ማሽኑን በማምረት ለገበያው ለማዋል የሚያስችላቸውን ስትራቴጂክ እቅድ ነድፈው መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።
ይህ የብሩህ ኢትዮጵያ የሀገር አቀፍ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ከመላ ሀገሪቱ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን እንካችሁ ያሉበት ልዩ ክህሎትና ችሎታ የታየበት ነው። በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ‹‹ማሰልጠን፣ መሸለም፣ ማብቃት›› በሚል መርህ በቅርቡ የተካሄደው ይህ የ2015 ብሩህ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል፤ አንድ ሺ 137 የክልል እና የዩኒቨርሲቲ አመልካቾችን በማሳተፍ የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸው እንዲወዳደር ተደርጓል።
ከየክልሉ ያለፉ 200 ተወዳዳሪዎች ከግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተዘጋጀላቸው ቡራዩ ተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት የማሰልጠኛ ካምፕ (Boot camp) ገብተው ለ15 ቀናት በተዘጋጀ የሥልጠና እና የውድድር ጊዜ እንዲሳተፉ ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል በቅድሚያ 70 ያህል የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ውድድሩን አልፈው ለመጨረሻው ውድድር ቀርበዋል። ከእነዚህም መካከል 50 ተወዳዳሪዎች ለሽልማት በቅተው የአምስት ሺ ዶላር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የእነዚህ የብሩህ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ሀሳቦች በውድድሩ የመጨረሻ እለት ለእይታ ቀርበዋል። ለእይታ የቀረቡት የፈጠራ ሀሳቦች ዛሬ ላይ ሆኖ የነገዋን ኢትዮጵያ ማሳየት የሚችሉና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደፊት ሀገሪቱን ለማሻገር የሚያስችል አቅም እንዳለ ማየት ያመላከተ ነው።
ይህ ውድድር በ2013 የተጀመረ ሲሆን እስካሁን በተካሄዱ ሰባት ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ውድድሮች በአጠቃላይ ሁለት ሺ 412 አመልካቾች የተሳተፉ ሲሆን፣ ለ400 የሃሳብ ባለቤቶች ወይም ለ552 ወጣቶች የገቡት ካምፕ ሥልጠና ተሰጥቷል። በአጠቃላይ ለ167 ምርጥ ሃሳቦች የአንድ ሚሊዮን 518 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2015