የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮች ጠቅለል ተደርገው ሲገለፁ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ዋጋና እንዲሁም በሚፈለገው ጥራት አለማጠናቀቅ በሚለው ክፍተት ላይ የሚያርፉ እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በተለይ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አስተዳደር (ማኔጅመንት) ችግር እንዳለባቸው ይጠቆማል። የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የአቅም ክፍተቶች ይስተዋሉበታል፤ ዓለም አቀፍ የገበያ ተለዋዋጭነት፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መማር አለመቻል፣ ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡
የዘርፉን ችግሮች በጥናትና ምርምር በመታገዝ የመፍታትና የግንባታ አስተዳደርን የማሳደግ ኃላፊነት የተሰጠው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትም (Construction Management Institute) ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ከ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ ያስረዳሉ፡፡
የ’ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት’ ምንነት
‹‹ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት›› ማለት አንድን ግንባታ በጊዜ፣ በዋጋ እና በጥራት መምራት፣ ወይም ግንባታን ጊዜውንና ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት ጊዜና የውል ዋጋ ማጠናቀቅ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ግብ ፕሮጀክቶችን በዋጋ፣ በጊዜና በጥራት ማጠናቀቅ ነው፡፡
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተግባራትና ኃላፊነቶች
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በደንብ ቁጥር 289/2005 የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንትን ማሳደግን ግብ ካደረጉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዋና ኃላፊነቶችና ተግባራት መካከል የፖሊሲ ግብዓቶችን በማመንጨት እንዲተገበሩ ማድረግ፤ ተግባር ተኮር የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ሥልጠናዎችን መስጠት፤ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ዓለም አቀፋዊ ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያደርግ የምዘናና የብቃት ማረጋገጫ (ሰርቲፊኬሽን) እንዲኖር ማመቻቸት፤ ለኮንስትራክሽን ማኔጅመንት እድገት የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች እንዲስፋፉና እንዲሰርፁ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ተቋራጭ፣ አሰሪ እና አማካሪ በተደራጀ መልኩ የሚሠሩበትን የአሠራር ሥርዓት እያጠኑ እንዲተገበር ማድረግ፤ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ዘርፍ የማማከር አገልግሎት መስጠት፤ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ዘርፍ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ ለኮንስትራክሽን እድገት አስተዋፅዖ የሚያደርጉ መረጃዎችን እያሰባሰቡና እየመዘኑ ለዘርፉ ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚስተዋውቁና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያተኮሩ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ተመሳሳይ ተግባር ካላቸው የግልና የመንግሥት ተቋማት በትብብር መሥራት፣ ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲቀመሩ ማድረግ፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ለኮንስትራክሽን ማኔጅመንት እድገት አስፈላጊ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወንና ተቋማቱ የጥናትና ምርምር ማዕከላት እንዲሆኑ ማገዝ የሚሉትም የኢንስቲትዩቱ ሌሎች ኃላፊነቶቹና ተግባሮቹ ናቸው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሰንዳፋ ከተማ የልህቀት ማዕከል እያስገነባ ነው፡፡ ማዕከሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ትልቅ ተቋም ስለሚሆን ማዕከሉን ማስተዳደር በተቋሙ ተግባርና ኃላፊነት ውስጥ ይካተታል፡፡ የልኅቀት ማዕከሉ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የሰው ኃይል ማበልፀጊያ ተቋም ነው፡፡ ማዕከሉ ግንባታዎች ሳይፈርሱ የግንባታ ጥራትን ለመፈተሽና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሠራሮችና መሣሪያዎች (Non-Destructive Testing Methods) እንዲሁም የጥራት ማረጋጋጫ ተግባራት የሚከናወኑባቸው የቤተ-ሙከራ ማዕከላት ይኖሩታል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ በሁለት ምዕራፎች የሚከናወን ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በሦስት ዓመታት፣ ቀሪውን ደግሞ በሁለት ዓመታት በማከናወን ማዕከሉ ከአምስት ዓመታት በኋላ በሙሉ አቅም ሥራ እንዲጀምር ይደረጋል፡፡ የግንባታው 17 በመቶ ሥራ በ2016 ዓ.ም ይጠናቃል ተብሎ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት የቀረበው የተቋሙ የደንብ ማሻሻያ፣ ኢንስቲትዩቱ የምዘናና የብቃት ማረጋገጫ ሥራውን ከማመቻቸት ባለፈ በራሱ የምዘናና የብቃት ማረጋገጫ ሥራ እንዲያከናውን ይጠይቃል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የበጀት ዓመቱ
ዋና ዋና ተግባራት
ኢንስቲትዩቱ በዘንድሮው የበጀት ዓመት በኢንዱስትሪው ውስጥ በሥራ ላይ ለሚገኙ 2442 ተቋራጮች፣ አማካሪ መሐንዲሶች ሌሎች የዘርፉ ተቋማት ባለሙያዎች ተግባር ተኮር ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ይህ ሥልጠና የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የሚያግዝ ነው። የምንመድባቸው አሠልጣኞች በዘርፉ በቂ ልምድና ዝግጅት ያላቸው ናቸው፡፡ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከ20ሺ በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡
ለ180 ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ (Project Management Professionals) እንዲሆኑ የሚያስችላቸውንና ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ዕድል የሚፈጥርላቸውን ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ይህ ሥልጠና ለ120 ባለሙያዎች ተሰጥቶ ነበር፡፡
ኢንስቲትዩቱ በ2015 የበጀት ዓመት ያከናወነው ሌላ ተግባር የ‹ቢም› (Building Information Modeling) ቴክኖሎጂ ስልጠና ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የዲዛይን ሥራዎችን በማስተባበር የጊዜና የገንዘብ ብክነት እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በተለያዩ ባለሙያዎች የሚሠሩ የዲዛይን ዝግጅት ሥራዎች የተናበቡ እንዲሆኑ ለማድረግ ቁልፍ ሚና ያለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ዘንድሮ 243 ባለሙያዎች ሥልጠናውን ወስደዋል፤ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከ400 በላይ ባለሙያዎችን በ‹ቢም› ቴክኖሎጂ አሰልጥኗል፡፡ አማካሪ መሐንዲሶችን ጨምሮ የዘርፉ መንግሥታዊ ተቋማት ባለሙያዎችና የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ሥልጠናውን ወስደዋል፡፡ ቴክኖሎጂው የተበላሸውን የኢንዱስትሪውን ገፅታ ለመገንባት እና ሥራን በእውቀት ለመምራት ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፉ እየተመራ ያለው ባለሙያዎች ተመዝነው ብቃታቸው በምዘና ተረጋግጦ ስላልሆነ የብቃት ምዘና መመሪያ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ መመሪያው ሲጸድቅ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ባለሙያዎች በጥንቃቄ በሚዘጋጅ የፈተና ሥርዓት አማካኝነት ብቃታቸው ይመዘናል፤ ለፈተናው የሚያግዙ ግብዓቶችም እየተዘጋጁ ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማዘመን የሚያግዙ የአሠራር ሥርዓቶችንም ያስተዋውቃል። ለአብነት ያህል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ሃሳቦችን ይዘው የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን የሚያበረታቱ እንዲሁም የሥራ ቅብብሎሽ እንዲኖር የሚያስችሉ አሠራሮች የሚመሩባቸውን መመሪያዎችን አዘጋጅ ቷል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር አንድ ባለሙያ ከረዳቶቹ ጋር ሆኖ በቀን ምን ያህል ሥራ መሥራት እንደሚችል የሚያመለክት የምርታማነት መለኪያ (Productivity Norm) እያዘጋጀ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የምክር አገልግሎቶችንም ይሰጣል፡፡ በቂ ባለሙያ ለሌላቸው ተቋማት የሙያ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ለብዙ ተቋማት ሥራዎች ሙሉ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
የተቋማት ፕሮጀክት የመምራት ደረጃን (Organizational Project Maturity) የማሳደግ ሥራ በዚህ ዓመት የተከናወነ ሌላው ተግባር ነው፡፡ ይህ አሠራር በዓለም አቀፍ መመዘኛ አምስት ደረጃዎች አሉት፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ (በተቋማት ፕሮጀክት የመምራት ደረጃ) የምትገኘው ከአንድ እስከ ሁለት ባለው ወሰን ውስጥ ነው፤ ይህም አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህን ደረጃ በ10 ዓመት ውስጥ ወደ አምስት/አራት ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ ሦስት ለማድረስ እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተዘጋጅተው የአሠልጣኞች ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ከተቋማት ኃላፊዎች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የመሠረተ ልማት ቅንጅት እጦት እያስከተለ ያለውን ችግር በማጥናት በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ከተሠማሩ ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል፤ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆን ቴክኖሎጂንና አማራጭ የግንባታ ግብዓቶችን (ለምሳሌ ከአፈር የሚሠሩ ብሎኬቶችን) አስተዋውቋል፡፡ ተቀባይነት ያገኙት ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮች ደግሞ ብሔራዊ ደረጃ (National Standard) እንዲወጣላቸው እየሠራ ነው፡፡ የ‹‹ቢም›› ቴክኖሎጂ አስገዳጅ ብሔራዊ ደረጃ እንዲኖረው የሚያስችሉ ግብዓቶች ተሟልተው ደረጃው ለሚኒስትሮች ኮሚቴ ቀርቧል፤ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የሀገር በቀል ተቋራጮች አቅምና ችግሮች
የሀገር በቀል ተቋራጮች ከዚህ ቀደም በጥሩ እድገት እየተጓዙ የነበረ ቢሆንም መልሰው ተዳክመዋል፡፡ የእውቀትና፣ የአደረጃጀት ችግሮች አሉባቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ተወዳዳሪ መሆን አልቻሉም፡፡ ለዚህ ችግር ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ተቋማቱ በኮርፖሬት ደረጃ የተደራጁ አለመሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት በአንድ ግለሰብ ስም ተሰይሞ፣ ግለሰቡ ሁሉንም ኃላፊነት ይዞ ሥራ ይጀምራል፡፡ ግለሰቡ በሆነ ምክንያት ሥራውን ሲያቆም ድርጅቱም አብሮ ይከስማል፡፡ ተቋማቱ የአንድ ሰው ተቋማት ሳይሆኑ የኮርፖሬት አሠራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሰውየው ኖረም አልኖረም ተቋማቱ እንዲቀጥሉ የእውቀት ሥራ መሥራት ይገባል፡፡
የኮርፖሬት አሠራር ስልት (Corporate Culture) አንድ ተቋም በአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሥርዓት ባለው አሠራር (System) ሥራውን እንዲያከናውን የሚያስችል ነው፡፡ ይህ ስልት ዝርዝር የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋትና ውሳኔዎች በተገቢው ጊዜ እንዲወሰኑ በማስቻል፣ የፕሮጀክት አፈፃፀም ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆን ያደርጋል።
ክፍያዎች በተገቢው ጊዜ አለመከፈላቸው ተቋራጮቹን አዳክሟቸዋል፡፡ ሥራ ለማግኘት ሲባል ብቻ አዋጭ ያልሆነ (በጣም ዝቅተኛ) ዋጋ ያቀርባሉ። ገበያን በሚገባ አጥንቶ ለፕሮጀክት የሚመጥን ዋጋ ያለማቅረብ ችግር አለ፡፡ ይህ ደግሞ ሥራው እንዳይሠራና ሀገርም ኪሳራ እንዲገጥማት ያደርጋል፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ጎድቶታል፡፡
ስለሆነም ‹‹ተቋራጮቹ ለሥራው የሚመጥን ዋጋ አስገብተዋል ወይ?›› የሚለውን ጉዳይ በጥንቃቄ መመልከት ይገባል፡፡ የግዥ ሥርዓቱ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበ እንዲያሸንፍ ዕድል የሚሰጥ (Least Evaluated Bid) ነው፡፡ ይህ የግዥ ሥርዓት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለብዙ ዓመታት የቆዩና ልምድ ያላቸው ተቋራጮች ከሥራ እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ስለሆነም ‹ተቋራጮቹ ለሥራው የሚመጥን ዋጋ አስገብተዋል ወይ?› የሚለውን ጉዳይ በጥንቃቄ መመልከት እና የግዥ ሥርዓቱን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
የውጭ ሀገራት የሥራ ተቋራጮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሥራ በሚጀምሩበት ጊዜ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ወሳኝ በሆኑ ሥራዎች ላይ እንዲያሳተፉ የሚያስችል አሠራር (Joint Venture System) ተዘጋጅቷል፡፡ በ10 ዓመት ውስጥ በሀገር ውስጥ ከሚወጡ ዓለም አቀፍ ጨረታዎች መካከል 75 በመቶው የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የገበያ ድርሻ እንዲኖራቸው ታቅዷል፡፡
ኢንጂነር ታምራት ‹‹የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የአቅም ክፍተት አለባቸው፡፡ ክፍተቶቻቸውን ለማስተ ካከልም የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለሥራ ተቋራጮች በብዙ ዘርፎች ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። የእኛ ሀገር የሥራ ተቋራጮች የ10 ዓመት ብቻ ታሪክ ባለቤት እየሆኑ ነው፡፡ ለትውልድ የሚተላለፉ ተቋራጮችን ማፍራት አለብን ብለን እየሠራን ነው›› ይላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የሥራ ተቋራጮችን አቅም ለመወሰን ተቋራጮቹ ያላቸውን ማሽኖችና ሌሎች መሣሪያዎችን ከግምት ውስጥ የማስገባት አሠራር ይተገበር ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ተቋራጭ እውቀቱ ካለው ማሽኖችን ተከራይቶ እንዲሠራ በማድረግ ተቋራጩ ያለውን አቅም ለሀገር ልማት መጠቀም ይቻላል፡፡ ብዙ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች፣ ማሽኖች ስለሌሏቸው ብቻ ለብዙ ዓመታት ተቀጣሪ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ተቋራጭ የሁሉም ማሽኖች ባለቤት ሊሆን እንደሚገባ የሚያስገድደው መስፈርት አስገዳጅ መሆን እንደሌለበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ያለውን ሀብት በአግባቡ የሚያስተዳድር የአሠራር ሥርዓት መፍጠርም አስፈላጊ ነው፡፡ ተቋራጮችን አቀናጅቶ ማሠራት በጣም ይጠቅማል፡፡ ትልቅ የአመለካከት ችግር አለ፡፡ የጥቅም ግጭትና ቅሬታ እንዳይፈጠርም የሚገኘውን ትርፍ ተቋራጮቹ በሥራው ላይ ባላቸው አበርክቶ መሠረት በማስላት መከፋፈል ይገባል፡፡
‹‹በባለሙያ እየተመሩ ያሉ ተቋማት አሉ፤ በባለሙያ የማይመሩ ተቋማትም አሉ፡፡ በአመዛኙ ግን የኮንስትራክሽን ዘርፉ በባለሙያ እየተመራ አይደለም›› የሚሉት ኢንጂነር ታምራት፣ ‹‹አሠራራችንን ፕሮፌሽናሊዝምን የሚጋብዝ ከሆነ፣ አሳማኝ ያልሆነና ዘርፉን የሚጎዳ ዋጋ ይዘው የሚቀርቡ ተቋራጮችን ከጨዋታው ውጪ የምናደርግበት አሠራር ከተፈጠረ፣ የሚጠየቁት የምዘና መስፈርቶች የተቋማትን ብቃት መመዘን የሚያስችሉ ከሆኑ፣ ልምድ ያላቸው፣ በኢንዱስትሪው ላይ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ፣ ሀገርን ሊገነቡ የሚችሉ ከገበያ የወጡ ተቋራጮች ወደ ገበያው ሊመለሱ ይችላሉ›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
ቀጣይ እቅዶች
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዘርፉን ለማሳደግ በቀጣዩ በጀት ዓመት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውንና ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ዕድል የሚፈጥርላቸውን ሥልጠና አጠናክሮ መቀጠል አንዱ ነው፡፡ በዚህም 180 ለሚሆኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለሚመሩ ተቋማት ባለሙያዎች ይህ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ 200 ባለሙያዎች የ‹ቢም› እና ለሦስት ሺ 800 የዘርፉ ባለሙያዎች የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥልጠናዎች የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ለአንድ ሺ ባለሙያዎች የብቃት ምዘናና ማረጋገጥ ሥራ ለመሥራት አቅዷል፡፡ የልኅቀት ማዕከሉን 17 በመቶ ግንባታውን ማጠናቀቅም የኢንስቲትዩቱ የቀጣዩ ዓመት እቅድ ነው፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015